Wednesday, 20 May 2026 11:08

ቻይና ልዩ የጦር ሐኪሞች ቡድንን ወደ ኢትዮጵያ ላከች

Written by 
Rate this item
(0 votes)
የቻይና ብሔራዊ መከላከያ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕክምና አገልግሎት ድጋፍ ለመስጠት ለአንድ ዓመት የሚቆይ ተልዕኮ ያለው 12ኛውን የወታደራዊ ሕክምና ስፔሻሊስቶች ቡድን ወደ አዲስ አበባ መላኩን አስታወቀ። ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከቻይና የተነሳውና 13 አባላት ያሉት ይህ የባለሙያዎች ቡድን፤ በአጥንት ሕክምና፣ በተላላፊ በሽታዎች፣ በዓይን ሕክምና፣ በነፍስ ወከፍና የመተንፈሻ አካላት ሕክምና፣ በሽንት ቧንቧ ሕክምና፣ በአጠቃላይ ቀዶ ጥገና እንዲሁም በባህላዊ የቻይና ሕክምና ላይ የተሰማሩ ታዋቂ ስፔሻሊስቶችን ያካተተ ነው። ቡድኑ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሆስፒታሎች ውስጥ በመገኘት ክሊኒካዊ ምርመራዎችን፣ የሰው ኃይል ሥልጠናዎችንና የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት የሕክምና አቅምን ለማጠናከርና አዳዲስ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ዝግጁ ሆኗል።
ይህ ስምሪት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ሜይ 2025 ላይ ተሰማርቶ የነበረውንና 14 ወታደራዊ ሐኪሞችን ይዞ የመጣውን 11ኛውን ቡድን የሚተካ ሲሆን፣ በወቅቱ ቻይና ወደ ኢትዮጵያ የላከችው “ከፍተኛው የጦር ሕክምና ቡድን” ተብሎ ተገልጾ ነበር። ከ2015 ጀምሮ የቻይና ሕዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር የሕክምና ዩኒቨርሲቲ ከ100 በላይ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ የላከ ሲሆን፣ እነዚህ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትና ለሲቪሎች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ አጠናክረዋል። ይህ ሰፊ ፕሮግራም ቻይና በዓለም አቀፍ ሰብአዊ ትብብር ላይ ያላትን ንቁ ተሳትፎ የሚያሳይና “ለሁሉም የሚተርፍ ዓለም አቀፍ የጤና ማኅበረሰብ የመገንባት” ራዕይ አካል መሆኑ ተገልጿል።
Read 13425 times