21ኛው የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በአሜሪካ ኦሪገን መካሄድ ይጀምራል፡፡
በሻምፒዮናው በ46 የውድድር ዘርፎች ከ147 ሀገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 800 አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ5 ሺህ ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር፣ 1 ሺህ 500 ሜትር እና በ800 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ትሳተፋለች፡፡
በተጨማሪም በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና በ400 ሜትር በሴቶች እንዲሁም በርምጃ ውድድር ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች የምትሳተፍ ይሆናል፡፡
ዛሬ በመክፈቻው ዕለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የፍጻሜ እና የማጣሪያ ውድድራቸውን ያደርጋሉ።
ምሽት 4 ከ 43 ላይ በ800 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ነጋሄ እያሱ እና የሮሳን ግርማ ሲካፈሉ፤ በሴቶች ደግሞ በዚሁ ርቀት ምሽት 5 ከ 35 ሐብታም ገበየሁ እና ደራርቱ ሽብሩ ማጣሪያቸውን ያከናውናሉ።
ሌሊት 11 ከ 53 በሴቶች 5 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር እመቤት ጥላሁን እና አልማዝ ዮሃንስ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ለማሸነፍ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ማለዳ 12 ከ 20 በወንዶች 5 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ደግሞ ማማሩ ጎዴ እና ዳምጠው ከበደ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
ሻምፒዮናው በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት ዩጂን ከተማ ሄይዋርድ ፊልድ ከሐምሌ 29 ቀን እስከ ነሀሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
Wednesday, 05 August 2026 09:36
21ኛው የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀምራል
Written by Administrator
Published in
ስፖርት አድማስ

