ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ ክቡር ገና በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ገጽታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ አነጋጋሪ ጽሑፍ ይፋ አደረጉ። አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች 60 ዓመታት በላይ ቢቆጠሩም፣ አህጉሪቱ አሁንም ጥሬ ዕቃ ብቻ ወደ ውጭ በመላክ የቴክኖሎጂና የማምረት አቅም ጥገኛ ሆና እንደቀጠለች ባለሙያው አስገንዝበዋል። የበለጸጉ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለራሳቸውስትራቴጂካዊ ጥቅም እንጂ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግር ተቆርቁረው እንደማይሠሩ የጠቀሱት ክቡር ገና፣ የውጭ ኃይሎችን ብቻ መወንጀል ፋይዳ እንደሌለው አብራርተዋል።
በሀገር ውስጥ ደረጃም የፖለቲካ ሥልጣን ከኢኮኖሚ ቁጥጥርና ከሀብት ማከፋፈል ጋር የተቆራኘ መሆኑ ለዘብተኛ ዕድገት ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ጽሑፉ ያሳያል። ባለሥልጣናት የንግድ ፈቃድ፣ መሬት እና የውጭ ምንዛሪ በመቆጣጠር ሀብት የሚያከማቹበት ሥርዓት በመዘርጋቱ፣ ፖለቲካዊ ሥልጣን የሞትና ሽረት ውጊያ ሆኗል። ይህ ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር እንዳይመጣ አድርጓል ያሉት ተንታኙ፣ የማንነት ፖለቲካና የሥልጣን ውዝግብ ተቋማዊ ልምሻን እያስከተለ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ሲዳስሱም፣ አገሪቱ ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብትና ወጣት ሕዝብ ባለቤት ስትሆን፣ አብዛኛው የፖለቲካ አቅም በማንነት፣ በታሪክ እና በድንበር ውዝግቦች መባከኑን ጠቁመዋል። ሌሎች ሀገራት በቴክኖሎጂ ልህቀትና በስራ ፈጠራ ሲመሩ፣ እኛ በአስተዳደራዊ ድንበር እና በ ትርክት ላይ መመሰጣችን የትውልዱን ወርቃማ ጊዜ እንዳባከነው ተገልጿል። የፖለቲካ ግጭት ጠማቂዎች ታሪክን እያጣቀሱ ማህበረሰቦችን ሲያቀሳቅሱ፣ የነገው የጋራ ዕጣ ፈንታ ሊታሰብ እንደሚገባ አፅንኦት ተሰጥቷል።
Published in
ነፃ አስተያየት

