Tuesday, 01 September 2026 13:20

የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ትውፊት እና የዘመናዊ አስተዳደር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
የኦርቶዶክስ እምነት ሥነ-መለኮታዊ፣ ምስጢራዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች ለዘመናዊው ዓለማዊ እና ውስብስብ የአመራር ንድፈ-ሐሳብ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ጥልቅ፣ መንፈሳዊ እና ስልታዊ መሠረት ያለው ነው። ምንም እንኳን ዘመናዊው የአመራር ሳይንስ በምዕራባውያን ወይም በዓለማዊ ዩኒቨርሲቲዎች በብዛት ቢተነተንም፣የኦርቶዶክስ እምነት የሰው ልጅን ውስጣዊ ተፈጥሮ፣ የማኅበረሰብ አብሮነትን እና ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ አገልጋይነትን ከመረዳት አንፃር ትልቅ እሴት አለው። በኦርቶዶክስ ሥነ-መለኮት መሠረት እያንዳንዱ ሰው በፈጣሪ መልክና አርአያ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ መሪው ከበታቹ ያሉትን ሠራተኞች በጥልቅ ክብር፣ በሰብአዊነት እና በፍትህ እንዲያስተዳድር ግዴታ ይጥልበታል። በተጨማሪም የሰው ልጅ ከፍ ወዳለ የሞራልና የመንፈሳዊ ልዕልና ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል የሚያስረዳው የቴዎሲስ አስተስህሮ ከዘመናዊው ቀጣይነት ያለው የቪዲዮና የግል ስብዕና ዕድገት ፍልስፍና ጋር በቀጥታ ይገናኛል።
በሌላ በኩል፣ በኦርቶዶክስ ትውፊት መሰረት ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በአንድ ሰው አምባገነናዊ ትዕዛዝ ሳይሆን በጋራ መንፈሳዊ ኅብረትና ስምምነት ወይም ሶቦርኖስት በመሆኑ መሪው ከቡድኑ ተነጥሎ የሚኖር ከፍተኛ አለቃ ሳይሆን የአካል ክፍል እንደሆነ እና እያንዳንዱ አባል እኩል ዋጋ እንዳለው ያሳያል። ይህም ከዘመናዊው አሳታፊ እና አካታች የአመራር ስልቶች ጋር ይጣጣማል። በአሁኑ ዘመን መሪዎች ከሚገጥማቸው ከባድ የውድድር ዓለም ውጥረት እና የስልጣን ጭንቀት አንጻር የኦርቶዶክስ ምስጢራዊ ትውፊት በውስጣዊ ዝምታ እና ከፈጣሪ ጋር በሚደረግ ጥልቅ ጸሎት አማካኝነት ውስጣዊ ሚዛንን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ በሄሲካዝም አስተስህሮ ያስተምራል። ይህም መሪው በውጫዊ ውጥረትና ጫና ውስጥ ሆኖ እንኳ አእምሮውን ሰብስቦ በሰከነና በጥልቀት የማሰብ ችሎታ እንዲኖረው የሚያስችል ሲሆን ከዘመናዊው የንቃተ-ህሊና እና የአእምሮ ሰላም አስተዳደር ጋር አንድ አይነት ነው።
ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የቆየውን እምነት፣ እሴት እና ሥርዓት ትውልድ ከትውልድ ሳታዛባ በማስተላለፍ የምትታወቅ በመሆኗ ዘመናዊው አስተዳደር ድርጅቶች ያለፉትን ስኬቶችና ውድቀቶች በማጥናት የወደፊት እቅዳቸውን እንዲያቀኑ ከሚሰጠው ምክር ጋር ይስማማል። በአጠቃላይ የኦርቶዶክስ እምነት ለዘመናዊው ዓለማዊ የአመራር ሳይንስ ያበረከተችው ትልቁ አስተዋጽኦ አመራር ማለት በቁሳቁስና በውጤት መለኪያ ብቻ የሚለካ ሳይሆን የሰውን ልጅ ሰብአዊ ክብር ከፍ የሚያደርግ፣ በኅብረትና በውይይት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም በከባድ ውጥረት ውስጥ እንኳ ውስጣዊ ሰላምንና ጽናትን ይዞ የመገኘት ጥበብ መሆኑን ማሳየቱ ነው።
ዛዲግ አብርሀ
የአፍሌክስ ፕሬዝደንት
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 895 times