Friday, 18 September 2026 09:47

"በአዲስ ዓመት የምንመኘው አዲስ ሕይወት እንጂ አዲስ የሞት ዜና አይደለም"

Written by 
Rate this item
(0 votes)


አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ይዞ ይመጣል ብንልም፣ ሳምንታት ሳይቆጠሩ የተስፋ መቁረጥ መርዶዎችን እየሰማን ነው። አንድ ሕዝብ በገዛ ሀገሩ፣ በቤቱ አቅራቢያ እና በመንገዱ ላይ በታጣቂዎች ሲገደል፣ ሲታገት እና ሲፈናቀል ከመመልከት በላይ የጸጥታ ቀውስ ከየት ይመጣል?

ይህ መንግሥትን መክሰስ አይደለም፤ ተቋማዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልስ የመጠየቅ ሂደት ነው። የሚቀጠፈው የዜጎች ሕይወት የፖለቲካ መለያ የለውም፤ እነርሱ ወላጆች፣ ልጆች፣ ባሎች እና ሚስቶች ናቸው።

በጉራጌና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች በተለይም በአበሽጌ እና ሶዶ ወረዳዎች ያለፉት አመታትን ክስተቶች ትተን እንኳን ለመጨረሻ ጊዜ ዘግናኝ የጥቃት መርዶዎችን ከሰማን አንድ ወር እንኳን አልሆነም፡፡ የዛኔውም የአሁኑ ከ13 በላይ ሰዎች የሞቱበት የከፋ ጥቃትም ከዲጂታል ሚዲያ ዜና ማዕበል ያለፈ ትኩረት አላገኘም፡፡

ስለዚህ ሕዝቡ የመጠየቅ መብት አለው።

መሰል ጥቃቶች ለምን በተደጋጋሚ በአንድ አካባቢ ይከሰታሉ?

መንግሥት ወቅታዊ የሀገር ውስጥ የጸጥታ ስትራቴጂው ምንድነው?

ጥቃቶችን ከመከላከል ይልቅ፣ ከክስተቶች በኋላ ለምን በቂ ትኩረትና እርምጃ አይወስድም?

እነዚህ የጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው። በአዲስ ዓመት የምንመኘው አዲስ ሕይወት እንጂ አዲስ የሞት ዜና አይደለም። እነዚህ ጥያቄዎች አስቸኳይ መልስ ያስፈልጋቸዋል።

ሰላም የሚጀምረው የጥይት ድምጽ ሲቆም ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብ መልስ ማግኘት ሲጀምርም ነው!

Sodo Lema-

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 5989 times