Tuesday, 22 September 2026 07:05

የሚዲያን ኃይል ለግል ጥቅም አንጠቀምበት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እኔ ጋዜጠኛ ነኝ። የሚዲያ ሰው ነኝ። ለዓመታት በሙያዬ የሰራሁ፣ የሙያውን ኃላፊነትና ጫና የምረዳ ሰው ነኝ። ዛሬ ግን “ጋዜጠኛ ነኝ”፣ “የሚዲያ ሰው ነኝ”፣ “ቲክታከር ነኝ” በሚል ስም የሌሎችን ባለሙያዎችና አገልጋዮች ሙያዊ ክብር የሚያዋርዱ፣ የሚያስፈራሩ፣ የሚያሸማቅቁ እና “ስሜን ተጠቅሜ ምን ላደርግ እችላለሁ?” የሚል አካሄድ የሚከተሉ ሰዎች መኖራቸው ያሳስበኛል።

ሚዲያ ማለት ሥልጣን አይደለም፤ ኃላፊነት ነው።ጋዜጠኝነት ማለት ሰውን ማስፈራራት አይደለም፤ ለሕዝብ የሚጠቅምእውነታን በሙያዊ መርህ መፈለግና ማቅረብ ነው።
የሚዲያ መድረክም ማንንም ሰው ለማዋረድ፣ ለማስፈራራት ወይም የራስን ጥቅም ለማስፈጸም የተሰጠ የግል መሣሪያ አይደለም።

በተለይ የጤና ባለሙያዎችን እንመልከት። ሐኪም፣ ነርስ፣ ፋርማሲስት ወይም ሌላ የጤና ባለሙያ በየቀኑ የሰው ሕይወትና ጤና ላይ ኃላፊነት ይሸከማሉ። እነሱ ላይ የሚነሳ ችግር ካለ ጥያቄ መጠየቅ፣ ቅሬታ ማቅረብ እና በሕጋዊ መንገድ መከታተል ይቻላል። ነገር ግን ሙያቸውን ማዋረድ፣ ማስፈራራት ወይም በማይገባ መንገድ ማጋለጥ የጋዜጠኝነት ሥራ አይደለም።
ሙያዊ ትችት እና ማስፈራራት ፤ መጠየቅ እና ሰውን ማሸማቀቅ ወይም የሕዝብ ድምፅ መሆን እና የግል ጥቅምን በሚዲያ መድረክ ማስፈጸም አንድ ነገር አይደሉም።

ታዋቂ መሆን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን አይተካም።ብዙ ተከታዮች መኖር ሙያዊ ብቃትን አያረጋግጥም።ማይክሮፎን መያዝም የማንንም ሰው ክብር ለመንካት ፈቃድ አይሰጥም።
ስለዚህ እንደ ጋዜጠኛ እላለሁ፦ ሙያ ክብር አለው። የሌላውን ሙያ ማክበር የራስን ሙያ ማክበር ነው።እንጠይቅ፤ እውነትን እንፈልግ፤ ስህተትን እንተች። ነገር ግን ሰውን አናስፈራራ፣ ሙያን አናዋርድ፣ የሚዲያንም ኃይል ለግል ጥቅም አንጠቀምበት።

ምክንያቱም የሚዲያ ኃይል የሚመዘነው ስንት ሰውን ማስፈራራት በቻልን ሳይሆን፣ ስንት ሰው እውነትን እንዲያይ፣ መብቱን እንዲያውቅ እና በክብር እንዲኖር ማገዝ በቻልን ነው። ሙያ ክብር አለው። እና ያንን ክብር መጠበቅ የእኛ ኃላፊነት ነው!


ግርማ ፍስሃ

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 5702 times