ትውልዱ በቀድሞ የኤርትራ ክ/ሀገር መንደፈራ አውራጃ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍናን አጥንቷል። በመምህርነትም አገልግሏል። በሀገረ አሜሪካ በፍልስፍና ትምህርት ገፍቷል። በ Azmerino.com ላይ ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ፁሁፎችን ያጋራል።
"የገድሊ" ( የትግል) ትውልድ የሚባለውን አካል እና የሻእቢያን ባሕሪ በጥልቅ በማጥናት እና ገላልጦ በማሳየት ብዙ በሻእቢያ አስተሳሰብ ተጠምቀው የተወናበዱ ኤርትራዊያንን ያነቃ ሰው ነው። በተለያዩ የዩቱብ ቻናሎች በትግርኛ ፣ እንግሊዘኛ እና አማርኛ ቋንቋ ሀሳቦችን ያጋራል ።
አሳቢ ፣ የማህበረሰብ አንቂ እና ፀኃፊ የሆነው ዮሴፍ ገ/ሂወት ፈልጌ የማዳምጠው ፤ ሀሳቦችንም የማደንቅለት ሰው ነው።
2018 የካቲት ላይ መቀመጫው መቐለ ካደረገ ብራኸ ሾው ከሚባል ቻናል ጋር ባደረገው ቆይታ ያነሳውን ሀሳብ ላጋራችሁ። ይህ ሃሳብም ጠያቂ ጋዜጠኛዋ እንኳን ለየካቲት 11 አደረሰህ ስትለው ዮሴፍ ገ/ሂወት ፈገግ ብሎ የመለሰው ቀልቤን የሳበው ነጥብ አጠር አድርጌ ላቅርበው።
ዮሴፍ ይመልሳል ...
ይሄ ህወኋት የትጥቅ ትግል ጀመረበት ተብሎ የሚከበረው የካቲት 11 በጥልቀት መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው። የትግራይ ፖለቲካዊ ሊሂቅ አፄ ምኒልክን የሚከሰው የዓድዋ ጦርነትን ተከትሎ ትግርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ከመረብ ወዲህና ወዲያ ብሎ ለሁለት ከፈለው። የቀይ ባሕር አካል የነበረቺውን ትግራይ ከባሕር ገፍቶ ከበባ ውስጥ ከተታት ብሎ ነው። እናም ይህን የትግራይን ችግር ቀኃሥ ኤርትራን በፌዴሬሽን የኢትዮጲያ አካል ካደረጓት በኋላ ያለፈው ችግር ቀርፎ ትግራይም ከከበባ በማውጣት የቀይ ባሕር አካል በማድረግ የቀደመው ታሪካዊ ስህተት አርሞት ነበር።
ሆኖም የካቲት 11/1967 ዓ.ም ደደቢት ላይ የተመሠረተው ህወኋት ቀኃሥ ኤርትራን በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀላቸው ስህተት ነው ፤ ኤርትራም ነፃ ሀገር መሆን አለባት የሚሉ ሀሳቦችን በመደገፍ ባደረገው የትጥቅ ትግል ትግራይን ሆነ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር አካልነት ነጥለው ወደ ቀደመ ታሪካዊ ክስተት 1983 ዓ.ም ላይ መለሷት። ትግራይም ሆኑ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር አካል መሆናቸውን አቆሙ።
እናም ለምንድነው የካቲት 11 የምታከብሩበትን ምስጢር የማትመረምሩት በማለት ነበር ሃሳቡን በጥያቄ መልክ የዘጋው።
እኔም እላለሁ የትግራይ ሊሂቅ ሆይ ትግራይን ከቀይ ባሕር አካልነት ያራቀ የትጥቅ ትግል የተጀመረበት ቀንን ምን ጥቅም አገኘንበት ብላችሁ ነው የምታከብሩት ?
ኢትዮጵያ የጀመረቺውን የቀይ ባሕር አካል የመሆን ጉዞ በመደገፍም ህወኋት የሰራውን ታሪካዊ ስህተት ለማረም የሚደረግ እንቅስቃሴን የምትቀላቀሉትስ መቼ ነው ?
Dechasa Angecha Tadesse-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

