* 20ሺ እስረኞችን ነጻ አውጥቷል
«አብዛኞቹ እዚያ የታሰሩት ወንጀል ሠርተው አይደለም» የሚለው የዱባዩ ነጋዴ ፊሮዝ መርቻንት፤ «የታሰሩት ሊከፍሉት ያልቻሉት ዕዳ ስላለባቸው ብቻ ነው» ሲል ያስረዳል፡፡
ፊሮዝ መርቻንት እነዚህን ዕዳዎች እየከፈለ ሰዎችን ከእስር ነጻ ያወጣል፡፡ ነጋዴው ይህንን በጎ ተግባር ላለፉት 18 ዓመታት በኤምሬቶች ውስጥ እያከናወነ የቆየ ሲሆን፣ እስከ ባለፈው የካቲት ወር ድረስ ከ20,000 በላይ ሰዎችን ከእስር ታድጓል።
በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ50 በላይ አገራት የመጡ 2,972 ሰዎችን ዕዳ ከፍሎ ከእስር ያስፈታ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት የካቲት መጨረሻ ደግሞ ተጨማሪ 497 ሰዎች በነፃነት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አድርጓል።
ፊሮዝ መርቻንት ስለነዚህ ሰዎች ሲናገር፡ «እነዚህ ሰዎች ጨካኝ ወንጀለኞች አይደሉም፤ አብዛኞቹ የሁኔታዎች ሰለባ የሆኑ ምስኪኖች ናቸው» ይላል።
በዚያ አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የከፈለው ዕዳ 2.4 ሚሊዮን ዲርሃም (653,506 ዶላር ገደማ) ይደርሳል። በተጨማሪም ለ11 ታካሚዎች የኩላሊት እጥበትና የሕክምና ወጪ የሚሆን 1 ሚሊዮን ዲርሃም አውጥቷል።
የእርሱ መልካምነት ከእስር ቤት በማስወጣት ብቻ ግን አያበቃም፡፡ ከእስር የተፈቱት ሰዎች ወደ አገራቸው የሚመለሱበት የቪዛና የአየር መንገድ ትኬት ወጪም ይሸፈንላቸዋል።
ነጋዴው ይህን በጎ ተግባሩን የሚከውነው በጁሜራ ሌክስ ታወርስ ሕንፃ 39ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሮው ውስጥ ሆኖ ነው።
«አንድ ሰው ዕዳው ተከፍሎለት ወደ ቤተሰቡና ወደ አገሩ ከተመለሰ፣ ለእኔ ያ ትልቅ ነገር ነው» ይላል ፊሮዝ።
ለካስ ደግነትም መሰጠትን ይጠይቃል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas
Published in
ህብረተሰብ

