Saturday, 10 March 2012 10:10

‘ዴስክቶፕ’ እና ‘ሲ ድራይቭ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እሰየው ነው… አሁን አሁን ጋዜጠኝነት አሪፍ እንትናዬዎች ስለገቡበት… ለኢንተርቪው የቀጠረ እንግዳን ጸሀፊ “ለክፉም ለደጉም ሞባይልሽን ብይዘው…” ምናምን መባባል ሊቀርልን ነው፡፡ አሀ… ጋዜጠኞች እስከዛሬ አሯሯጭ (ፔስሜከር) ነበርና! የሪቮሉሽኑ ፍሬ ለእኛም ይዳረሳ! ቂ…ቂ…ቂ…

ስሙኝማ…የምር ግን ይሄ የ‘አሯሯጭነት’ ነገር አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እናንተ እኮ “ይቺን አሥር ሺህ ሜትር ሬከርድ ሰብሬ ባልጨርሳት…” ብላችሁ ገብታችሁ ልክ ሪባኗ አጠገብ ስትደርሱ “አንተ እኮ አሯሯጭ ነህ…” አይነት ነገር መባል አልበዛባችሁም!

እናላችሁ… ‘ፎልድር’ የለ፣ ምን የለ ዴስክቶፕ ላይ ፍጥጥ ብሎ የሚታይ መአት እያለ ‘ሲ ድራይቭ’፣ ‘ፎልደር’፣ ‘ሰብ ፎልደር’ ቅብጥርስዮ እየተባለ በአቋራጭ የወርቅ ሜዳሊያውን የምንነጥቅ በዝተናል፡፡ እናላችሁ… “ሯጭ ነን” ብላችሁ ወደ አሯሯጭነት ወርዳችሁ የላብ ማድረቂያው እንኳን በመከራ ተሰጥቷችሁ “በተመቻችሁ ገደል ሂዱ…” ስትባሉ በቃ… አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ ልክ ነዋ… አንዳንዱ ስንት የኮሌጅ አይነት በጥሶ፣ የጋዋን አይነት ሲቀያይር ኖሮ… ሌላው፣ አይደለም ‘መበጠስ’ የገመዱን ቦታ የማያውቀው በአቋራጭ ወንበሩን ሲይዝ አንድ ቀሽም ነው፣ ሁለት ያስተዛዝባልም! (ነገርዬው… “ብትታዘቡስ ምን ታመጣላችሁ?” ከሆነ መልሱ…ምንም!

ስሙኝማ… ለምንድነው አሁን አሁን ሰዎች ትኩር ብለው ‘ሲያፈጡብን’ ዝቋሏ ተራራን በሩጫ ሽቅብ ብንወጣ እንኳን የማይፈሰን ላብ የሚወጣን!)

እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የማፍጠጥ ነገር ከተነሳ፣ ዘንድሮ መፋጠጥ አልበዛባችሁም! ድሮ እኮ የሆነ ሰው ሲያፈጥባችሁ … አለ አይደል… “ምናልባት ኤለመንተሪ አንድ ክላስ ነበርን…”  “ዓለም ገና ያለችው አክስታችን ዘመድ ይሆን እንዴ!…” ምናምን አይነት ይባል ነበር፡፡ ልጄ… ዘንድሮ እንደሱ አይነት መላ ምት ከሦስት መቶ ብር ማኛ ጤፍ ጋር ታሪክ ሆኗል፡፡ ዘንድሮ ‘የማፍጠጫው’ ምክንያት ከህዝብ ቁጥር እኩል እየበዛ ስለሄደ “የምንፋጠጥበትን ሰበብ ቀንስልን…” ምናምን እያሉ ሱባኤ ነገር መግባት እንጂ እንደ ሆሊዉድ ፊልም “ኋት’ዩ ሉኪን’ አት!” አይነት ‘ወንድነት’ ቅሽምና ነገር ሆኗል፡፡ “እጅህ በሶ ጨብጧል እንዴ!” ”“ወንድ አይደለህም እንዴ!” ምናምን መባባል ፊልምና ቲያትር ላይ እንኳን ቀርቷል፡፡

ስሙኝማ…ካነሳነው አይቀር…… የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ወዳጃችን በአንድ ወቅት በሆነ ጉዳይ ሌላ ሰው ምን ይለዋል መሰላችሁ…“አንተ ወንድ አይደለህም እንዴ! ነገርዬው አለህ አይደል እንዴ!” ምናምን አይነት “ርስቴን፣ ሚስቴን ለማን ትቼ!” ሳያሰኝ “ጎራዴዬ የት ነው የተሰቀለው!” የሚያስብል አይነት ነገር ይናገረዋል፡፡ ወዳጃችን ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “እሱ ታዲያ ለእንትን ነው እንጂ ለመደባደቢያ ነው እንዴ!” አሪፍ አይደል… ልክ ነዋ… ነገሮች ለተፈጠሩባቸው ምክንያቶች አላገለግል እያሉ ነው የተቸገርነው፡፡ (ስሙኝማ… ድሮ በባዮሎጂ ትምህርት “ዓይን መመልከቻ…”፣ “ጆሮ ማዳመጫ…”፣ “አፍንጫ ማሽተቻ…” ምናምን እየተባልን የተማርነው ‘የሥራ ክፍልፍል’ ተለውጧል እንዴ! አሀ… የሰውነት ክፍሎቹን ‘ተግባር’ በተመለከተ ያልገቡን፣ የማይገቡንና ምናልባትም ሊገቡን የማይችሉ ነገሮች በዙብና!)

የምር ግን ለጨዋታው ያህል… ‘ኪሲንግ’ና በ‘ስሞኳ መሳፈር’ እንዳልታየ እየታለፈ…  “አማርኛ መናገር…” አለ አይደል… በኦፊሴል በሚከለከልበት ዘመን… ግራ ቢገባን ታዲያ ምን ይገርማል፡፡  በነገራችን ላይ… እነኚህ አቅራቢያቸው ከጀርባ … አለ አይደል… ጫካ፣ ወንዝ፣ ቁጥቋጦ ነገር ያላቸው ትምህርት ቤቶች… እንኳንስ ዊኪሊክሶች ጥቆማ አልደረሳቸው! ልክ ነዋ… በህጻናቱ ይደረጋሉ የሚባሉ ነገሮች እኮ… ተስፋ ሊያስቆርጡ ምንም አይቀራቸው፡፡

“የእኔ ልጅ በአማርኛ ብዙ አይናገርም…” የሚሉ ስልጣኔ በአይስክሪም ተጀምሮ፣ በቪዲዮ ጌም የሚያልቅ የሚመስላቸው ‘ፓረንቶች’… አይገርሟችሁም!

የ‘ፈረንጅ አፍ’ ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ (ቃል በቃል ለመኮረጅም እኮ ያግዛል! ቂ…ቂ…ቂ…) የምር… በ‘ፈረንጅ አፍ’ መናገር ማለት እኮ አይንስታይንነት ማለት አይደለም! ለነገሩ ጨዋታም አይደል… “ማይ ኔም ኢዝ ምናምን…” የምትለው ድሮ ታች ክፍል ነበር የምታስቸግረው፡፡ ዛሬ ነገርዬዋ ወደ ላይም  እያስቸገረች ነው፡፡ ኮሌጅ በጥሶ ‘ጦጣ መሆን’ አሪፍ አይደለማ! አሀ… የዚህ በፊቱን ‘ፌሚን’ ምናምን የሚለውን ‘ማስፋቅ’ አቅቶናል… ደግሞ ሌላ ለኦክስፎርድ ዲክሺነሪ የሚሆን ነገር እንዳንሰጣቸው ሰጋና!  አሀ … “የተማረ ይግደለኝ…” የሚባልበት ደረጃ ተደርሶ… “ማይ ኔም ኢዝ…” ከተባለ በኋላ ነገርዬዋ ጠፍታ በሆዳችን “ገብሬልዬ እንዲህማ አታዋርደኝም…” የምንል ስንበዛ አጉል ነገር ነው፡፡ እናማ… አንዳንድ ቦሶቻችን…ምናልባት ስብሰባ ላይ ናቸው ከሚባለው ሰዓት እየተቆጠረ ትንንሿን የ‘ፈረንጅ አፍ’ እንኳን ይልመዱልንማ! አሀ… ሲታዘቡን ጠቅልለው ነዋ የሚታዘቡን!

ስሙኝማ… የቦሶች ነገር ከተነሳ… ከሰዓት በኋላ በአንዳንድ ቢሮዎች ላይ የሚለጠፈው “ስብሰባ ላይ ናቸው…” የሚለው ማስታወቂያ በአረንጓዴ ወረቀትና በአረንጓዴ ፊደላት ይጻፍልንማ! ልክ ነዋ… “”አንድ ስዕል የአንድ ሺህ ቃላት ያህል ዋጋ አለው…” ምናምን የሚል አባባል አለ አይደል! እናማ… አረንጓዴ ቀለም የስብሰባውን ‘አጄንዳ’ ስለሚጠቁም “በሪስትራክቸሪንግ ደግሞ ስንት ሰው ሊገነድሱ ይሆን?” ምናምን እያልን ሀሳብ አይገባንማ! ሀሳብ አለን… ለምንድነው ‘ጎ ግሪን’ በሚለው ርዕስ የሆነ ኦስካር ምናምን ሽልማት የማይዘጋጅልን! አንዲት ሳትቀር ‘ምርጥ ቀንጣሽ’፣ ‘ምርጥ በጣሽ’፣ ‘ምርጥ ፈራሽ’… ሁሏንም ሽልማት ባንሰበስብ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… እዚህ አገር ‘ግሪን’ ያልሆነው ተራራውና መስኩ እንጂ ጓዳችን በሙሉ ‘ግሪን በግሪን’ አይደል እንዴ!

እናላችሁ… ዴስክቶፕ ላይ በአንድ ‘ክሊክ’ የምናገኘው እያለ… እንትን ድራይቭ፣ እንትን ፎልደር፣ እንትን ሰብ ፎልድር ምናምን እየተባለ በሰባት ‘ክሊክ’ የሚገኘው … ‘ማስተር ኦፍ ሴርሞኒ’ ሲሆንና… አለ አይደል…ይህ ቀረሽ የማይባለው ደግሞ በር ላይ ትኬት ተቆጣጣሪ ምናምን ሆኖ ሲቀር የሆነ የተበላሸ ነገር አለ ያሰኛል፡፡

ምን መሰላችሁ…የምር ግራ እየገባን ነው፡፡ አሀ… አደባባይ የማይውሉትን ‘የመመረጫ መስፈርቶች’ ወይ በኤስ.ኤም.ኤስ. ምናምን በምስጢር ይላኩልና! ኧረ እባካችሁ… ‘ዴስክቶፕ’ ላይ መአት አሪፍ፣ አሪፍ የሙያና የሥራ ሰዎች አሉበት!

እኔ የምለው… ይሄ የጤፍ ምናምን ነገር… ሰሞኑን የጤፍና የሌላው ነገር ዋጋ እንደ ጃፓን ባቡር ሲወነጨፍ አንድ የሚል ጠፋ ማለት ነው! አሀ… “ቀጥነናል፣ ከስተናል… ብታምኑም ባታምኑም ከሰውነት ውጪ ሆነናል…” ለማለት ምንም አልቀረንማ! (የምር ግን… ለምሳሌ የአንዳንዶቻችን ወገብ እኮ የቱ ቦታ ጀምሮ የቱ ቦታ እንደሚያልቅ የናሳ ቴሌስኮፕ ባያስፈልገው ነው! አጋነንክ አትበሉኛና…  (እንዲህ ከተባለ ነገርዬው መጋነኑን እወቁ፡፡ በነገራችን ላይ… አሁን፣ አሁን ያልተጋነኑ ነገሮች አልናፈቋችሁም!) እናማ… አጋነንክ አትበሉኛና፣ የአንዳንዶቻችን አካል ‘ወጥነት’ ይሄ በየቦታው ለሚሠራው ህንጻ እንደ ውሀ ልክ ማስተካከያ ልናገለግል እንችላለን! እና ሆዳችንን መራብ ብቻ ሳይሆን በጣም ‘እየባሰን’ ነው፡፡ አሀ…በኋላ “እንዲህ ለያዥ፣ ለገናዥ ያስቸገሩት ይሄን ያህል ሆድ ብሷቸው ነበር እንዴ!” ምናምን እንዳንባል ነዋ!

ሆድ ሲብስ አሪፍ አይደለም፡፡ ድሮ ሆድ ሲብሰን እኰ አንድ ሻንጣ ተሸክሞ የቤቷ ግድግዳ ተሸንቁሮ ብርድ ያስቸገራት ጓዳ መግባት ይቻል ነበር፡፡ ግፋ ቢል የተሸነቆረውን ማስደፈን ነው፡፡  (እንትና…የፈለገ ሰምና ወርቅ ቢኖር… ይቺኛዋን አትተርጉምብኝማ!)

እግረ መንገዴን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሻንጣ ይዞ ቤት መለዋወጥ ከተነሳ ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም… ሰባት አግብቶ፣ ሰባት ፈትቶ ስምንተኛው ‘ሠርግ’ ላይ እንደ አብርሀም የሚያስጨፍር! የምር ግን… በ’ብታምኑም ባታምኑም‘ ዘንድሮ እኛን የሚስተካከል ያለ አይመስለኝም፡፡ አሀ… በየቲቪው “ኢንዶኔዥያ ውስጥ ያለች አንዲት ውሻ…” “ሦስት ዓመት የሞላው አንድ የታይላንድ ድመት…” አይነት ‘ትንግርት’ ከሚነገረን እዚህ እኛ የኢንዶኔዥያ ውሻም፣ የታይላንድ ድመትም ሳንሆን… የ‘ሀበሻ ሰዎች’ የሆንነው ላይ የሚደርስ ስንት ‘ብታምኑም ባታምኑም’ አለ አይደል እንዴ! እናማ… ዴስክቶፕ ላይ ሁሉን ነገር አሟልቶ ፍጥጥ ያለው እያለ “እንትን ድራይቭ ላይ ፈልገው…” እየተባለ የፎልደርና የንዑስ ፎልደር መአት ቆፍሮ ማውጣት… አሪፍ አይደለም… ደግሞስ፣ በሰማይ ባያስጠይቅ ነው! (በምድር ‘ማስጠየቁ’ እንኳን በህልማችንም ማየት ትተናል፡፡)  አንተ ወዳጄ… “ይልቅ ጠጋ፣ ጠጋ ብትል ይሻልሀል…” ምናምን ነገር ያልከኝ ‘ወደየትኛው ግድግዳ’ ነው የምጠጋው? ቂ…ቂ…ቂ… አሀ… ሳይገባኝስ! መቼም “አልገባውም” ተብሎ የሄግ ፍርድ ቤት ዋራንት አይቆረጥብኝ!እናላችሁ… የፈለገ ዴስክቶፕ ላይ ቢፈጠጥ… የዘንድሮ ነገር… አለ አይደል… “የአገሬ ሰው”፣ “የመንደሬ ሰው”፣ “የሰፈሬ ሰው”፣ “ዕድርተኛችን…” ምናምን ስለሆነ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ወይ አንደኛውን በየ‘ፋይል ኔሙ’  ዋናው ስማችን ብቻ ሳይሆን ‘እትብታችን የት እንደተቀበረ’ አብሮ ቢጻፍበት “እኛ ተረስተን፣ እነእከሌ ኒሻን የተሸለሙት በምን መለኪያ ነው” የሚለውን ይመልስልናል፡፡

ከሆነ ‘ድራይቭ’ አምስት ደቂቃ ፈጅቶ የወጣው “እሱ እንዴት አሪፍ መሰለህ፤ የዘመኑ ጨዋታ ገብቶታል” እየተባለ ‘ሬድ ካርፔት’ ሲነጠፍለት… ከዴስክቶፕ ላይ በሁለት ሴከንድ የሚገኘውን  “ጓሮ፣ ጓሮውን ሂድ…” ሲባል አሪፍ አይደለም፡፡ የዘመኑን ጨዋታ አላወቀበትማ! የምር ግን… ‘ለእኛ ለእኛ’ ሲሆን አጉሊ መነጽሩ የተራ መነጽርን ያህል የማያሳየው ለምን እንደሆነ አይገርማችሁም!እንደ ‘ሞኝ’ ስንቆጠር አሪፍ አይደለማ! ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የሞኝነት ነገር ከተነሳ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ… ሰውየው ከአምስተኛ ፎቅ አፓርትማው ወርዶ መሬት ሲደርስ ዕቃ መርሳቱ ትዝ ይለዋል፡፡ እናላችሁ… ከታች ሆኖ ሚስቱን ይጣራና “ሞባይሌን አቀብዪኝ” ይላታል፡፡ ሚስትም ከላይ ሆና ስትወረውርለት ሞባይል ሆዬ መሬት ወርዶ ሀምሳ ትናንሽ ይሆንላችኋል፡፡ መቼስ ምን ይደረግ ብሎ “እሺ መነጽሬን አቀብዪኝ” ይላታል፡፡ አሁንም ስትወረውርለት መነጽር እንክሽክሽ ይላል፡፡ ዕድሉን እየረገመ ሳለ ሚስት “መሀረብህን ላቀብልህ እንዴ!!” ስትለው ምን አለ መሰላችሁ… “ቆይ፣ ረጋ ብዬ፡፡ መጥቼ እወስደዋለሁ፡፡” መሀረቡም ‘እንዳይሰበርበት’ ነዋ! (የምር በዚህ ዘመን እንዲህ የለየለት ሞኝነት ሳይሻል አይቀርም፡፡ ልክ ነዋ… ቢያንስ በትንሽ ትልቁ ‘ክሬዚ’ ከመሆን ያድናላ!)

‘ሞኝነታችን መሀረባችን እንዳይሰበር’ ፎቅ እንድንወጣ እስኪያደርገን ድረስ ዴስክቶፕ ላይ ሆነን ‘ኢግኖር’ አታድርጉብንማ! ለዴስክቶፖችም፣ ለሲ ድራይቮችም ይመቻችሁማ!

 

 

Read 2768 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 15:13