በአፋር ክልል አዋሽ አርባ ተወልዳ በአዲስ አበባ ጨርቆስ ያደገችው ኤልሳቤት እቁባይ፤ እናቷ ዜና ማዳመጥ የሚወዱ በመሆናቸው ከልጅነቷ ጀምሮ የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር እንዳደረባት ትናገራለች፡፡ በፖለቲካ ሳይንስ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በሶስዮሎጂ ከፍተኛ ትምህርቷን የተከታተለችው ኤልሳቤት፤ በአማርኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች መግባባት በመቻሏ ታሪካዊ መረጃዎችን ለአንባቢያን በወቅቱ ለማድረስ ችላለች።
በ1990 ዓ.ም በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የጋዜጠኝነት ጉዞዋን የጀመረችው ኤልሳቤት፤ በወቅቱ እንደ ነጋሽ መሀመድና ብርቱካን ሀረገወይን ያሉ አንጋፋዎችን ድምፅ እየሰማች በማደጓ የዜና አንግል አመራረጥ አላስቸገራትም ነበር። የዋልታ ቆይታዋን ተከትሎ በሀገሪቱ የመጀመሪያው እለታዊ የግል ጋዜጣ በሆነው "እለታዊ አዲስ" ላይ አጭር ግን አሻራ ያለው ጊዜ ያሳለፈች ሲሆን፤ የህወሃትን መከፈልና የጋዜጣውን መዘጋት ያበሰረውን ታሪካዊ ዜና ጨምሮ በርካታ ተነባቢ ዘገባዎችን ሰርታለች።
ከ1994 እስከ 2007 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት ባሉት ኃላፊነቶች አገልግላለች፤ በወቅቱም በአባይ ወንዝ ዙሪያ ሰፊ ጥናታዊ ዘገባዎችን ከመሥራት ባለፈ፣ የሶማሊያ ሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩትን አብዱላሂ ዩሱፍን አስገራሚ ቃለ-መጠይቅ በማድረግ በደፋርነቷ ትጠቀሳለች፡፡ አወዛጋቢውን የ97 አገራዊ ምርጫን በንቃትና በድፍረት የዘገበች ሲሆን፣ በምርጫ ዕለትም እስከ ሃዲያ ሾኔ በመጓዝ ከፕሮፈሰር በየነ ጴጥሮስ የምርጫ ጣቢያ ዘገባዎችን አቅርባለች።
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ደፋርና አስተማሪ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ትታወቃለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለ15 ዓመታት ያለማቋረጥ በመከታተል የፓርላማ ውሎዎችን በብቃት የዘገበች ድንቅ የፖለቲካ ሪፖርተርም ነች።
የሙያ ባልደረቦቿ ሚዛናዊነቷንና ጠንካራ ሰራተኛነቷን ሁልጊዜ ይመሰክሩላታል። ዛሬ ላይ ኑሮዋን በውጭ ሀገር ያደረገችና ባለትዳር እንዲሁም የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኤልሳቤት፤ ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያኖረች የሙያ ሰው ናት።
ምንጭ - ተወዳጅ ሚዲያ
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

