Wednesday, 14 October 2026 06:47

ኃይሌ ገብረሥላሴ በአፍሪካ ዘላቂ ተጽዕኖ ከፈጠሩ ታላላቅ ሰዎች አንዱ በመሆን ተመረጠ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ታዋቂው አትሌት እና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በአፍሪካ አህጉር ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ከፈጠሩ 15 ራዕይ ያላቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ በመሆን በ'ፎርብስ አፍሪካ' 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የክብር ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። መጽሔቱ ኃይሌን በስፖርቱም ሆነ በቢዝነሱ ዓለም የማይፋቅ አሻራ ያኖረ “የትውልድ ታሪክ” ሲል አወድሶታድ።

የ25 ዓመታት የሩጫ ዘመኑን በድል ያጠናቀቀው ኃይሌ፣ ሁለት የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎችን፣ ስምንት የዓለም ሻምፒዮናዎችን እና 27 የዓለም ክብረ ወሰኖችን በማስመዝገብ ከልጅነት ትግሉ እስከ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ አክሊል ድረስ ታላቅ ጀግና መሆኑን አስመስክሯል።

በስፖርቱ ዓለም ያገኘውን ስኬት እና ልምድ ወደ ሀገሩ በማምጣት በ2000 ዓ.ም 'ኃይሌ እና ዓለም ኢንተርናሽናል'ን የመሰረተው ኃይሌ፣ በአሁኑ ወቅት 11 ሆቴሎችን፣ የመኪና መገጣጠሚያ፣ ሪል ስቴት፣ ግብርና እና ሌሎች ኩባንያዎችን በማስተዳደር ከ5,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል። “በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ከሚገኙ ቀዳሚ ኩባንያዎች አንዱ እንሆናለን” የሚል ጽኑ እምነት ያለው ሲሆን፣ አፍሪካውያን አትሌቶች በሀገራቸው ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉም አበክሮ ይመክራል።

ኃይሌ ለፎርብስ በሰጠው አስተያየት፣ “አፍሪካ ያልተነካች እና ሰፊ ዕድል ያላት አህጉር ናት፤ ባለን እምቅ የሰው ኃይል ምክንያት ወደፊት በአፍሪካ በርካታ ታላላቅ የቢዝነስ ሰዎች ይፈጠራሉ ብዬ አምናለሁ” ብሏል። የኃይሌ ገብረሥላሴ የማይበገር ስኬታማነት ከሩጫ ትራክ ወደ ቢዝነስ ዓለም በተሳካ ሁኔታ መሸጋገሩን ዘገባው አጉልቶ ያሳያል፡፡

የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/Ad

Read 7680 times