Saturday, 10 March 2012 09:53

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

አንዳንድ ወዳጆቼ ላሊበላን ሳታዩ እንዴት ከቅጽሩ ውጪ ያለውን ቤተ - ጊዮርጊስን አያችሁ ብለው ጠይቀውኛል፡፡ እኔ ጉዞ ማስታወሻ ስጽፍ በየቦታው እንደደረስኩ፣ ራሴ ያየሁበትን ቅደም ተከተል ተከትዬ እንጂ በታሪክ የታነፀበትን ዘመን ቅደም ተከተል ይዤ አይደለም፡፡ ስለሆነም፤ ባለፈው እንደፃፍኩት ሰው ወደ አሸተን ማርያም ሲጓዝ እኔና ባለቤቴ ወደ ቤተ ጊዮርጊስ ነበር የሄድነው፡፡ ይሄ ማለት ዋናው የላሊበላ ክብረ- በዓል የቤዛ ኩሉ ወረብ ቀን እሁድ ሲሆን በዋዜማው የገና ዕለት በ28-04-04 መሆኑ ነው፡፡ ቤተ -ጊዮርጊስ እኛ ካረፍንበት ት/ቤት ቅርብ ነውና ያንን መጐብኘታችንን ጽፌያለሁ፡፡ በ29/04/04 ዓ.ም የገና ማግስት የቅዱስ ላሊበላ የልደት ቀንና የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በአንድ ላይ እንደሚከበር ገልጬያለሁ፡፡ እንግዲህ ዛሬ ዋናው ክብረ በዓል ነው፡፡ ካህናቱ በተስማሙት መሠረት ፆሙ የሚፈሰከውም ዛሬ ነው፡፡

ወደ ዋናው ወረብ ክብረ - በዓል ለመሄድ ከንጋቱ 10 ሰዓት ከ5 ላይ ተነሳን፡፡

ምግብ ሠሪዎቹ ከእኛ ቀደም ብለው መጥተው ይከትፋሉ፡፡ “ታታሪ የቢዝነስ ሰዎች ናቸው” አልኩኝ በሆዴ፤ ሁለቱን ሴቶች ከታፊዎች እያየሁ፡፡ ተጣጥበን ተዘገጃጀንና ወደ ላሊበላ ቤተ - ክርስቲያን አመራን፡፡ ከእኛ ቀድሞየሄደው ህዝበ - ክርስቲያን ይበዛል፡፡ ግቢ - ውጪው ሰው ነው፡፡ መቆሚያ መቀመጫ ያለ አይመስልም፡፡ አገሬው ደብዘዝ ያለ የሀገር ልብስ ለብሷል፡፡ መጤው ወተት የመሰለ ድር በድር ለብሷል፡፡ ተደበላልቋል፡፡ የቆመው፣ የተቀመጠው፣ የተጋደመው ቦታውን አጨናንቆት የመርፌ መጣያ ቦታ የተረፈ አይመስልም፡፡

ጢም - ግጥም ብሏል ዙሪያ ገባው፡፡ ዳገቱ ሁሉ ሰው ሆኗል፡፡ ቤተ - ክርስቲያኑ ውቅሩ፣ ጥርቡ ያምራል፡፡ እንዲህ ብዬ በእንግሊዝኛ ጽፌለታለሁ:-

Lalibela, is a wonder déjà vu of eternal times, a tatoo, not a taboo

A tattoo of the mountains, in a jungle of rocks

We bow for its majestic grace…”

መንፈሱ ሲተረጐም፤

“ሁሌ አዲስ፣ ሁሌ ብርቅ

ግን ጥንት ያየነው ነው፤

ነውር የሌለበት ክልክል የሌለበት

የአለታት ተዓምር ነው!

የዘላለም ግማጅ የቀን ንቅሣት ነው

የቋጥኞች ጫካ፣ አንድዬ ቅርጽ ነው

ለዚህ ነው ጧት - ማታ፣ የምንሳለመው!”

ዣንጥላ የመሰለ የሲሚንቶ ከለላ፣ በመብራት የተንቆጠቆጠ ጣራ ተደርጐለታል፡፡ ዕልልታው አድምቆታል፡፡ ቅዳሴው አሙቆታል፡፡ ሌሊቱን ሲቀደስ ታድሯል፡፡

እንግዲህ ወረቡ እስኪጀመር መጠበቅ አለብን፡፡ በቴሌቪዥን ወይ በስዕል በቀር በዐይኔ አይቼው ስለማላውቅ ጓጉቻለሁ፡፡ ቅዳሴው አለቀና ቁርባን የሚቀበለው ሰው ተጠራ!

ከዚያ ዋናው ሰዓት ደረሰ!

ወረቡ ተጀመረ፡፡

የህዝቡ ብዛት፤ ትርዒቱን ለማየት አስቸገረን፡፡

በቤተ - ክርስቲያናቱ አናት ቀሳውስቱ ከርቀት ይታያሉ፡ ባለቀለም ቀሳውስት (በቴሌቪዥን እንደምናያቸው) ተሰድረዋል፡፡ ዝማሚያቸው እንደ ባህል ማዕበል ሁሉ ይወዛወዛል፡፡ ጐንበስ ብለው ለቤተክርስቲያኑ፤ ወደ ግርጌ፤ እጅ ሲነሱ ዕልልታው ይቀልጣል፡፡ “ወረባውያኑ ቀስ በቀስ፤ በዑደት ክቡን የዓብያተ ክርስቲያናቱን ዙር ጠብቀው “ይጠመጠሙበታል” “ይጠመጠሙበታል” የቤተ - ክህነቱ ቃል መሆን አለበት፡፡ ምነው ቢባል ይህን ቃል የነገረኝ አንድ የቤተ - ክህነት ሰው ነው፡፡ አጠገቤ ቆሞ የሚያስረዳኝ እሱ ነው፡፡ ከታች ጥቁር ካባ ለባሾች አሉ፡፡ ቀስ በቀስ ዑደተኞቹ ይተካካሉ፡፡ ይተምማሉ፡፡

አጠገቤ ሁለት የአገሬው አለባበስ ያላቸው ባላገሮች ያወጋሉ፡፡ ትርዒቱን ለማየት አዳግቷቸዋል፡፡

አንደኛው - “በዋድላ ደላንታ፣ በተንታ አድርጌ ጅሩ ገባሁ፡፡ ለፈጣንና ጠንካራ ሰው አፍታ አትፈጅም፡፡ ላሊበላ በአምስት ቀኔ ገባሁ፡፡”

ወይ አምስት ቀን? ወይ አፍታ? አልኩኝ፡፡ ሁሉ ነገር ተዛማጅ ነው መቼስ “Even Absolute is relative” ይላል አይንስታይን፡፡ ፍፁምም ከሌላ ጉዳይ ጋር ተወዳድሮ ነው ፍፁም የሚሆነው፤ እንደማለት ነው፡፡

ሰው ሌሊቱን አድሯል፡፡ ግራና ቀኙ፤ ዙሪያውን በሰው ተሞልቷል፡፡ አገሬው ከነቡላ ሸማው፣ መጤው ከተሜ ከነነጫጭ የሀገር ልብሱና ድር በድሩ፤ ተኝቷል ተቀምጧል፤ ቆሟል ይዘዋወራል፡፡ መቋሚያቸውን ተደግፈው፣ ራሳቸውን ጭምር በነጠላ ሸፍነው፣ የቆሙ አያሌ ናቸው፡፡ የእናቶቹ ተመስጦ ይመስጣል፣ ያስገርማል፡፡ ጧፍ ይዞ ዳዊት የሚደግም፣ ሌሊቱን ሙሉ አነጥፎ መሬት የተኛው፤ እንደማተቡ ለጉድ ተመስጧል! ወረቡ ጠጋ ላላለ ሰው አይታይም! ዛፉ አናት ላይ የወጡ አሉ፡፡ እዚያ ላሉም አይታይም፡፡ ዛፍ ላይ ያሉት ወጣቶች ናቸው፡፡ ዘበኛው ውረዱ እያለ ይታገላቸዋል፡፡ አዲሳባ ኮንትሮባንድ፣ የቻይና ዕቃ የሚነግዱትን የመንገድ ዳር ነጋዴዎች አስታወሱኝ፡፡ ዓላማቸው ለየቅል ነው ቢባልም ለነገሩ በዚያን ሰዓት ዛፉ ላይ የወጡም አያዩትም! ትሩማን ትሪ ነው - ዛፉ! የናዝሬትን ትሩማን - ትሪ አስታወሰኝ፡፡

የወረቡን ትርዒት ለማየት ያልቻለች እናት ልጅ አዝላ ቆማለች አጠገቤ፡፡

“አይ ልጄ ባይኖር አይ ነበር’ኮ” አለች፡፡

አንድ አዛውንት፤

“ይልቅ ልጁን ይዘሽ ሂጂ! ዝም ብለሽ ቁሚ!

በአንቺ መሰለሽ በረከቱ የሚመጣው? በልጁ ነው!

አንቺ ማ?...” “ይሄን ሁሉ አገር ቆርጠን መጥተን፣ ይሄው ቤዛ ኩሉ እንኳን ማየት አቃተን፡፡” ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንድ ሰባት ፈረንጆች መጡ! መንገድ መሪው እኛን እየገፋፋ መንገድ ከፈተላቸው!

እኛ አዛውንትም፤

“የው ለፈረንጆቹ ሲሆንማ፤ ድንጋይ ይፈነቅላሉ! እኛን እኛን ሲሆን ግን ጥርቅም አድርገው ይዘጋሉ! ዕውነት ይቺ አገር የማናት?” አሉ፡፡

ማዶ ያለው ተራራ ከላሊበላ ጋር ይተያያል፡፡

አንዱ መነኩሲት መጡ፡፡

ነባሩ አዛውንት፤

“ጠበል ይዘው መጡ?” አሏቸው፡፡

“አዎና! ታዲያ ምን ይዘን እንግባ አገራችን?” አሉ መነኩሲት፡፡

“ፈረንጆቹን ለማስገባት እኛን ይገፈትራሉ፡፡ አሁን ዕውነት ፈረንጅ ጠበል ይፈልጋል? ጠበልስ ያድነዋል? ትርዒቱንማ እኛስ ስንት ዓመት እናየው የለ? ደሞስ በቴሌቪዥን መች አጣነው? ቃሉን እንሰማለን ብለን ነው እንጂ!” አዛውንቱ በምሬት መለሱ፡፡

በኋላ ግን መነኩሲቷ፤

“አዪ! ሰው ቢቀመጥ’ኮ ይታየን ነበር” አሉ ወረቡ እየጐላ ሲያዩ፡፡ ቆይቶ ፍንትው ብሎ ለሁሉም ይታይ ጀመር! አንድ የግጥም ማስታወሻ ፃፍኩኝ

“ይህን መሳይ ትርኢት”

“ይህን መሳይ ምትሃት

በምድር ነው እንጂ፣ መች አለ በገነት!

ባላየነው ቦታ፣ ከተቱ ከመኝት

የመዳረሻውን ምን አል ባወቅንበት!

የሄዱት አልመጡ አልነገሩን ዕውነት

ሂያጆቹ አይመጥኑ ከሞት ወዲያ ህይወት

መለኪያ ሰው ማነው ለምድር ላይ ደግነት?

አገሬው ይናገር ከናዳፋ ልብሱ

ወይ ጽዱው ከተሜ ከነአዳፋ አንጐሉ

የቱ ነው በሉና ላሊበላ ዋሉ!

ጽድቅ ከተማ ናት፣ ከተማ ገብታለች?

ለንፁህ ህሊና ያው ትታየዋለች!

ከዚህ ህንፃ አናት ላይ ከቋጥኙ ራስጌ

ይታያችኋል ወይ ማተቤ ማዕረጌ?!”

(ይቀጥላል)

 

 

Read 2507 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 10:10