Tuesday, 20 October 2026 10:25

ጠ/ሚኒስትሩ ለትግራይ ወጣቶች ያስተላለፉት ጥብቅ መልዕክት

Written by 
Rate this item
(0 votes)
"የጠመንጃ ቃታ መሳቡን አቁማችሁ ወደ ልማትና ሥራ ተመለሱ!"
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢቢሲ ጋር በትግሪኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የትግራይ ወጣቶች የመሣሪያ ቃታ ከመሳብ ይልቅ ወደ ልማት፣ ትምህርትና ሥራ ሊመለሱ እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ። እርስ በእርስ የሚደረግ ውጊያ አሸናፊ እንደሌለውና በተለይም ለባዕዳን ኃይሎች ጥቅም የሚደረግ ግጭት በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅርብ ጊዜያት በነበሩ ውጊያዎች ቀላል የማይባል ወጣት ሕይወቱን ማጣቱንና አካሉ መጉደሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጦርነት ሲንከራተት የነበረው ወጣት ወደ መደበኛ ሕይወቱ በመመለስ በክልሉ መልሶ ግንባታ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ተገደው ወደ ጦርነት ለገቡ ወጣቶች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሕወሓት አመራሮች ላለፉት 50 ዓመታት ሲዋጉ ቢቆዩም ራሳቸው እንደማይሞቱና እንደማይቆስሉ ገልጸዋል። አመራሮቹ ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ እንዲሁም በወርቅ ንግድና በሕንፃ ግንባታ ተሰማርተው የተመቸ ሕይወት እየኖሩ እንደሚገኙ በመጠቆም፣ "እነሱ ተንደላቀው ሲኖሩ አንተ ለምን ትሞታለህ፣ ትቆስላለህ?" ሲሉ ወጣቱ እራሱን እንዲጠይቅ አሳስበዋል።
ሕይወት የራስ እንጂ የድርጅት ወይም የመሪዎች እንዳልሆነች ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ወጣቱ ለራሱና ለቤተሰቡ ሲል አካሉንና ሕይወቱን ጠብቆ ለልማት ማዋል እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቱ ትክክለኛ ቦታ በዩኒቨርሲቲ፣ በንግድ፣ በእርሻና በፋብሪካዎች ውስጥ መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል። የወጣቱ እጅ የጠመንጃ ቃታ ከመሳብ ይልቅ በኮምፒውተርና በቴክኖሎጂ ላይ ማረፍ እንዳለበት በመጠቆም፣ መላው የትግራይ ወጣት ከጥፋትና ከጦርነት መንገድ በመውጣት የወደፊት ሕይወቱንና የአካባቢውን ኢኮኖሚ የሚገነባበት የልማት መስመር ላይ እንዲሰለፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 9199 times