Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 March 2012 09:31

ውበት ሲለካ…

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሴቶቻችን አንድ ሆነዋል:: ከአንድ ፋብሪካ ተሠርቶ የተገጠመላቸው እስኪመስል ድረስ ባለረጃጅም ፀጉር ሴቶች ከተማውን አጨናንቀውታል፡፡ በቀለሙ፣በቁመቱ እና በዓይነቱ ተመሳሳይ የሆነ ፀጉር በበርካታ ሴቶች አናት ላይ ተንዠርጎ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ሴቶቻችን ተፈጥሮ ከለገሰቻቸው እህቶቻቸው በገዙት ተቀጣይ የሰው ፀጉር ባለረጃጅም ፀጉር ሆነዋል፡፡ ከዓመታት በፊት ገንዘብ ያላቸው ጥቂት ባለሀብት ሴቶች ብቻ የሚደፍሩት ተቀጣይ የሰው ፀጉር (Human hair extensions) አሁን የበርካታ ሴቶች መለያ ሆኗል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ በፀጉር ላይ ሌላ ፀጉር መቀጠል መቼ እንደተጀመረ የሚጠቁም ጥናት ባይኖርም ረከስ ያሉ የፕላስቲክ ዊጎችን የሚጠቀሙ ሴቶች ነበሩ፡፡የፕላስቲክ ዊግ  ተቀጣዮች በቀላሉ ስለሚለዩ ተጠቃሚዎቹን ያን ያህል የሚያዝናኑ አይደሉም፡፡ ስለዚህም  ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር በርካቶች የዚህ ተጠቃሚ አልነበሩም፡

ተቀጣይ የሰው ፀጉር (Human hair extensions) ፋሽን ሆኖ ሲመጣ ግን በርካቶች መረባረብ ጀመሩ፡፡ተቀጣይ የሰው ፀጉር ከሰው ላይ የተላጨ ፀጉር ፋብሪካ ውስጥ ወይም በተደራጁ ግለሰቦች ቤት ተዘጋጅቶ ለገበያ የሚቀርብ ነው፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ገበያ ይሄ ፀጉር ከ5000 እስከ  7000 ሺሕ ብር የሚሸጥ ሲሆን እስከ 17 ሺሕ ብር የሚደርሱ የፀጉር ዓይነቶች እንዳሉም ይታወቃል፡፡

ኦሎምፒያ አካባቢ የሚገኘው የ‹‹ዐይንዬ የውበት ሣሎን›› ባለቤት የዐይኔ አበባ መኩሪያ፤  ለስምንት ዓመታት ያህል ለሰው ፀጉር ስትቀጥል ኖራለች፡፡

በወቅቱ የምሽት ክለብ ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች እና ሴተኛ አዳሪዎች የፕላስቲኩን ፀጉር ይጠቀሙ እደነበር ትናገራለች፡፡ “ከዓመታት በፊት የተፈጥሮ ፀጉር  የሚቀጥሉ ሴቶች ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር፡፡

ቀስ በቀስ ግን ተጠቃሚዎቹ ከፕላስቲኩ ፀጉር ይልቅ እውነተኛውን የሰው ፀጉር እየወደዱት እና እየለመዱት መጡ፤ አሁን የእኔ ደንበኞች በሙሉ የዚህ ፀጉር ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡››ትላለች፡፡የዚህ የሰው ፀጉር መለመድ ለዐይኔ አበባ የሥራ ዕድል ፈጥሮላታል፡፡ ቀደም ሲል በነጻነት የውበት ሳሎን ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር፤ አሁን ደግሞ የግሏን ፀጉር ቤት ከፍታለች፡፡

በየሁለት ሰዓቱ ልዩነት አንድ ሰው ትሰፋለች፡፤ቀኑን ሙሉ በሰው አናት ላይ አጎንብሳ ትውላለች፡፡ በፀጉር ቤቱ መደበኛውን የፀጉር ሥራ አገልግሎት ፈልገው ከሚመጡት ይልቅ የሰው ፀጉር ለመቀጠል የሚመጡ ደንበኞች ቁጥር ያመዝናል፡፡ ወደዚህ ፀጉር ቤት የሚሄዱ ደንበኞች መጀመሪያ በስልክ ቀጠሮ ማስያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በቀጠሮአቸው መሰረት ከደረሱ፣ ይህን ፀጉር ተቀጥለው ለመጨረስ ሁለት ሰዓት ይፈጅባቸዋል፡፡

የዐይኔ አበባ እንደምትለው አንድ ጊዜ የተገዛው ፀጉር በጥንቃቄ ከተያዘ አንድ ዓመት ያገለግላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዝቅተኛ የሚባለው የሰው ፀጉር 5ሺ ብር ይሸጣል፡፡ አብዛኛው ተጠቃሚ ይህን ፀጉር ቀጥሎ ለሦስት ሳምንት ያቆየዋል፤ ከዛም ፈቶ እና እንደገና ይቀጥለዋል  ለአንድ ጊዜ መቀጠያ ከ80 እስከ 100 ብር ወጪ ይደረግበታል፡፡በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስታይል ይሠራል፤ ቀለም ይቀባል፡፡ይህንን የሰው ፀጉር የምትጠቀም አንዲት ሴት በየዓመቱ እስከ 15 ሺ ብር ወጪ ታደርጋለች ማለት ነው፡፡

የዚህ ፀጉር ተጠቃሚዎች የኢኮኖሚ አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ ሴቶች ብቻ እንዳልሆኑ የምትናገረው የዐይኔ አበባ፤ ‹‹አብዛኛው ሴት ለራሱ አይሰንፍም፤ የኢኮኖሚ አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ በተለያየ መንገድ የተለያዩ ዓይነት ተቀጣይ የሰው ፀጉሮችን የሚጠቀሙ ሴቶች እንዳሉ ሁሉ ዕቁብ ገብተው፣ተበድረው፣ ውጭ ሀገር ያሉ ዘመዶቻቸውን ተማጽነው እና ያላቸውን ገንዘብ አብቃቅተው የሚሠሩ ሴቶችም አሉ፤ ምክንያቱም ይህ ፀጉር ውበት ይሰጣል›› ብላናላች፡፡

ተቀጣይ የሰው ፀጉር የለመዱ ሴቶች ወደ ፀጉራቸው መመለስን አይለምዱትም፡፡ ፀጉሩ ብዛት እና ቁመት ስለሚኖረው እሱን ፈተው በፀጉራቸው ለመሆን ይቸገራሉ፤ ስለዚህ አንዴ ከጀመሩት ሳይወዱ በግድ በዛው ይቀጥላሉ፡፡

ወ/ት ብሩክታይት ዋሲሁን ትባላለች፡፡ የ28 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ብሩክታይት የመጠጥ ማከፋፈያ ሱቅ አላት፡፡ ሥራው ፋታ የሚሰጥ ባይሆንም የውበት ሣሎኖች ሄዳ ለመሠራት ጊዜ አታጣም፡፡ ይህን ፀጉር ላለፉት አራት ዓመታት ተጠቅማለች፡፡ ተገናኝተን ባወራንበት ወቅትም ባለ ሰባት ሺሕ ብሩን ተቀጣይ ፀጉር ቀጥላለች፡፡ ወጣቷ የተቀጠለው ፀጉር የሰጣትን ውበት ወዳዋለች፤ ነገር ግን ፀጉሩ የሚቀጠልበት መንገድ የፊት ፀጉሯን ስለጨረሰው ሁልጊዜ ያሳስባታል፡፡ ይህን ፀጉር ለመቀጠል ከፊት ያለው የፀጉር ክፍል ትንሽ ይቀር እና ዙሪያውን ያለው የፀጉር ክፍል ሹርባ ተሰፍቶ እሱ ላይ በክር ይሰፋበታል፡፡

ሹርባ የሚሠራው የፀጉር ክፍል ቁመት እየጨመረ ሲሄድ ከፊት የሚቀረው ግን እየተሰባበረ እና እያለቀ ይሄዳል፤ ስለዚህ ተቀጣይ ፀጉሩ በሚወልቅበት ጊዜ ባለ ሁለት ዓይነት ፀጉር መሆኗ ለብሩክታይት እንደሚያሳስባት ትናገራለች፡፡ ቢያሳስባትም ግን ፀጉር መቀጠሉን የማቆም ፍላጎት የላትም፡፡ “ሂዩማን ሄር ሱስ አይደለም፤ ገንዘብ ካለኝ ሁልጊዜ መጠቀም እችላለሁ፤ ዋናው ነገር ገንዘብ እንዳላጣ መሟሟት ብቻ ነው›› ያለችው ወ/ት ብሩክታይት፤ ፀጉሯን በ “ዐይንዬ የውበት ሣሎን›› እንደምትሠራ ነግራናለች፡፡

“ጥፍር” ለሌለው “ጥፍር” ይቀጠልለታል

የተፈጥሮ የእጅ እና የእግር ጣት ጥፍሮች የተለያዩ ናቸው፡፡ጠንካራ፣ሰስ፣ቶሎ የሚያድግ ወይም የሚሠባበር ወዘተ… ብቻ ከተፈጥሮም ባሻገር እንደተንከባካቢያቸው የተለያዩ የጥፍር ዓይነቶች አሉ፡፡አብዛኞቹ የውበት ሣሎኖች የሴት ልጆችን የእጅ እና እግር ጣት ጥፍሮች ለመንከባከብ የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በተለያየ የዋጋ ደረጃ አገልግሎት ይሠጣሉ፡፡

ለጣቶቹ እንክብካቤ ካደረጉ በኋላም የጥፍር ቀለሞችን በመቀባት ጥፍሮቹ ውበት እንዲያገኙ ያደርጓቸዋል፡፡ ጥፍራቸው በተለያየ ምክንያት የተጎዳ ወይም ጥፍር የሌላቸውን ሴቶች የፕላስቲክ ጥፍር በመቀጠል ለጥፍሮቻቸው እና ለጣቶቻቸው ውበት ለማጎናጸፍ ይጣጣራሉ፡፡

እነዚህ የፕላስቲክ ጥፍሮች አሚር በተባለ ማጣበቂያ ከተፈጥሮው ጥፍር ጋር እንዲጣበቁ ተደርገው የጥፍር ቀለም ይቀባሉ፡፤ነገር ግን እነዚህን ጥፍሮች በመደበኛነት ለመጠቀም ከባድ ነው፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገላቸው የታሰበውን ጊዜ ያህል ሳያገለግሉ የመነቀል ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት  እንደ ሠርግ እና ለመሳሰሉ ዝግጅቶች ካልሆነ በስተቀር ሴቶች እነዚህን ጥፍሮች አይጠቀሟቸውም፡፡

ሰሞኑን ግን ሴቱን ሁሉ ጥፍራማ በማድረግ ለጣቶቻቸው ውበት የሰጠ ቴክኖሎጂ እዚሁ አገራችን ጥቅም ላይ መዋሉን ሰማሁ እና ተጠቃሚዎቹን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ግን እሩቅ መሄድ አላስፈለገኝም፤ ባለ ተቀጣይ ፀጉሯ ብሩክታይት ይህንን ጥፍርም ቀጥላዋላች፡፡ ብሩክታይት ጥፍሯን የምትሠራው ሌላ ቦታ ነው ‹‹የቲጂ ኔል›› ደንበኛ ናት፡፡በዚህ ቦታ የሚሠራው ጥፍር ብቻ ነው፡፡ከኡራኤል ቤተክርስቲያን ወደ አትላስ ሆቴል በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኝ የጥፍር መሠሪያ ቤት ነው፡፡

ብሩክታይን እንደነገረችን ጥፍሯን በዚህ ቤት መሞላት ከጀመረች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡‹‹አክሌሪክ›› የተባለውና ወጣቷ የምትቀጠለው የጥፍር ዐይነት የሚመጣው ከአሜሪካን አገር ነው፡፡መጀመሪያ ጥፍር ይቆረጣል፡፡ ከዛም ይሞረድ እና በጣም ስስ ጥፍር መሰል ነገር የተፈጥሮው ጥፍር ጫፍ ላይ ይለጠፍበታል፡፡

በተፈለገው ቁመት እና ዓይነት ከተቆረጠ በኋላ ፈሳሽ እና ጠጣር አክሌሪክ እየተቀላቀለ በጥንቃቄ በጥፍር ላይ ይሞላል፡፡ሙሌቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በሻካራ እና ለስላሳ ሞረድ ይሞረዳል፡፡ በመጨረሻ በውሃ እና በቡርሽ ሙልጭ ተደርጎ ከታጠበ በኋላ በተፈለገው ዓይነት ቀለም ይቀባል፡፡ ሲጠናቀቅ አንድም አውቃለሁ የሚል ሰው ይህንን ጥፍር ሰው ሰራሽ ሊለው አይችልም፡፡ይህን ጥፈር ለመቀጠል 200 ብር የሚያስከፍል ሲሆን ቀለሙን ማስለቀቅ እና መቀየር ከተፈለገ አንዳችም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ ይህ ጥፍር ከ20 እስከ 25 ቀናት ምንም ሳይሆን መቆየት የሚችል ሲሆን የተፈጥሮው ጥፍር እያደገ ሲመጣ በድጋሚ ማደስ ያስፈልጋል፡፡ በሚታደስበት ጊዜም 100 ብር ይከፈላል፡፡

ወ/ት ብሩክታይት ፀጉሯን እና ጥፍሯን በተለያየ መንገድ ለመስራት፣ ከግዢው ውጪ  በወር እስከ 600 ብር ልታወጣ እንደምትችል ትናገራለች፡፡ “ተፈጥሮ በሰጠኝ ውበት ላይ ተጨማሪ ውበት ስለሚሰጠኝ የማወጣው ገንዘብ አይቆጨኝም” ትላለች፡፡

‹‹የቲጂ ኔል›› ባለቤት ወ/ሮ ትዕግስት የቀጠሮ መዝገብ አላት፡፡ ደስ ባለ ሰዓት ተነስቶ ጥፍር ለመሠራት መሄድ ደርሶ ከመመለስ ውጪ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ እያንዳንዱን ሰው በየአንድ ሰዓት ልዩነት ታስተናግዳለች፡፡አንገቷን ደፍታ ጥፍር ስትቀጥል ትውላለች፡፡ ጥፍራቸውን ለማሳመር ወደ እርሷ የሚመጡ ሴቶች ሁሌም ተደስተው ጥፍራቸውን ወደውት እንደሚመለሱ ትናገራለች፤‹‹ምቹ እና ውበት የሚሰጥ ከሆነ ሁሉም ሴት ቢያደርገው ምን ችግር አለው?” በማለት ትዕግስት ትጠይቃለች፡፡ብሩክታይት የሚቀጠለውን ጥፍር ከመልመዷ የተነሳ የራሷን ጥፍር በስህተት እንኳን ማየት እንደማትፈልግ ትናገራለች ‹‹ጥፍርሽ ሲያምር” የሚለውን የሁሉም ሰው አስተያየት ትወደዋለች፡፡ “ይህን ጥፍር አውልቄ ጥፍርሽ ሲያምር የሚለውን አስተያየት ማጣት አልፈልግም” ብላናለች፡፡ እናም ለፀጉሯ እና ለጥፍሯ የሚሆን ጊዜና ገንዘብ መቼም ቢሆን አታጣም፡፡

“ቅንድብ” ለሌለው “ቅንድብ” ይጨመርለታል

ወ/ት ብሩክታይት የተፈጥሮ ቅንድቧ በጣም ስስ በመሆኑ ሁልጊዜ በኩል ማድመቅ ይጠበቅባታል፡፡ “አንድ ጊዜ ከእንቅልፌ ስነቃ የአምስት ዓመቷ የእህቴ ልጅ አይታኝ ብሩክዬ ቅንድብሽ አለቀብሽ አለችኝ፤ በወቅቱ በጣም ነበር የሳቅሁት፤ ይህንን እንደቀልድ ለአንድ ጓደኛዬ ስነግራት በሁኔታው ብትስቅም አንድ መፍትሄ አማከረችኝ›› ትላለች፤ ብሩክታይት፡

ይህቺ ጓደኛዋ ሁልጊዜ በኩል ከምታደምቅ አንድ ጊዜ መነቀስ እንደምትችል በመንገር ንቅሳት ቤት ወሰደቻት እናም በንቅሳት በፈለገችው ቅርጽ ቅንድብ ሠሩላት፡፡

‹‹ምንም የህመም ስሜት አልተሰማኝም፤ መጀመሪያ እንደተነቀስኩት በጣም ብዙ መስሎኝ አስጠልቶኝ ነበር፤ ሁለት እና ሦስት ቀን ሲቆይ የፈለኩትን ዓይነት ቅርጽ ያዘልኝ፤ በጣም ተደሰትኩ፤  ከ20 ቀን በኋላ ማስተካካያ ተደረገለት፤ ይኸው አሁን አንድ ዓመት ሆኖታል፤ ሰው በጣም ተጠግቶ ካላየኝ በስተቀር ማንም ሰው አይለየውም››ብላናለች፡

ብሩክታይት ለዚህ ለተሰራላት ቅንድቧ፤ 500 ብር መክፈሏን ትናገራለች፤ ቅንድቧ ግን የጥፍሯን እና የፀጉሯን ያህል እንደማያስደስታት አልደበቀችም፡፡

ሁለት ነገሮች ወደ አዕምሮዬ መጡብኝ፡፡ የመጀመሪያው የውበት ኢንዱስትሪው በአሁኑ አያያዙ ከቀጠለ ወደፊት የተፈጥሮ ውበት የማናይበት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን የሚለው ስጋት ነው፡፡

ሌላው ሁሉም ሴት በቴክኖሎጂ የታገዘ ውበት ተጠቃሚ እየሆነ ሲመጣ ልዩ ልዩ ውበቶች ይጠፉና ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ውበቶች ብቻ ለማየት እንገደድ ይሆን የሚለው ነው፡፡ የእኔን ስጋት ጊዜ ምላሽ ይሰጠዋል፡ እስከዛው ግን ቴክኖሎጂ የሚያመጣውን ውበት እያየን…ህይወት ይቀጥላል!!

 

 

Read 6696 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:35