Monday, 26 October 2026 16:42

ፍርሃትና ናፍቆት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)
አንዳንድ ግጥሞች አሉ - አንዴ እንደተነበቡ ወዲያው ለምንጊዜም በውስጣችን ታትመው የሚቀሩ። ለእኔ 'ፍርሃትና ናፍቆት' እንደዚህ ያለ ነው። በረዶውም ፍሙም በቶሎ ተጋብቶብኛል። ገጣሚው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነጽሑፍና የፎክሎር መምህር የነበረው ፈቃደ አዘዘ (PhD.) ነው። መምህሬ ነበረ። ወዳጄም ነው። አሁን ያለው አሜሪካ ነው። ርዕሱ ብቻ ብዙ የሚያናግር "እየሄድኩ አልሄድኩም" የሚል መጽሐፍም አለው። እየሄዱ አለመሄድ፣ እየኖሩ አለመኖር!
በፍርሃት ገደልና በናፍቆት ሜዳ፣ ስጋትና ተስፋ በተሞላበት ትርኢት እንደመሳተፍም ጭምር።
ጋሽ ፈቃደ ይህንን "ፍርሃትና ናፍቆት" ግጥም የጻፈልን በአርባኛ አመቱ ነበረ። ለአርባኛ አመቱ መታሰቢያ ይሆንለት ዘንድ ይሆናል ፍርሃትና ናፍቆቱን ያጋራን ብዬም አምናለሁ። ግጥሙ ከተጻፈም አርባ አመት ሊሞላው ነው - በ1982 ዓ.ም ተጻፈ። በ1989 ደግሞ 'ዐሻራ' በተሰኘው የግጥም ስብስብ መጽሐፉ ታተመ።
እኔም፣ ከአመታት በፊት አርባኛ አመት በሞላኝ ጊዜ ይህንን ግጥምና የጂጂን (እጅጋየሁ ሽባባው) 'ኢትዮጵያ' የተሰኘውን ዘፈን ነበረ ለራሴ የጋበዝኩት። የጂጂ "ቀስቅሺኝ እስኪ አንቂኝ ከእንቅልፌ፣ ቤቴን ሳላፀዳ እንዳልቀር ሰንፌ" የሚለው ስንኝ
በራሮታዊ ድምፅ ለራሳችን የቤት ስራ እንድንሰጥ የሚያስገድድ ሀይል አለው።
'ክፉ ንጉሥ መጣ፣ ደጉ ንጉሥ መጣ
ሁሉም ይሄዳሉ እንደአመጣጣቸው፣
ሳቅና ልቅሶሽን አይገዙትም ችለው!' ስለሚለው እንጉርጉሮዋ ከዚህ በፊት ሌላ መድረክ ላይ አንዳች ብዬ ነበረ።
እስኪ አሁን ደግሞ (ረጅም እድሜና ጤና እየተመኘንለት) በጋሽ ፈቃደ ፍርሃትና ናፍቆት አብረን እንቆዝም። አሁንስ የት ነን? እንዴት ነን? እየተባባልን።
---
ፍርሃትና ናፍቆት
---
“ሊመጣ ነው ሲሉኝ!”፣
“የመቅሠፍት ጊዜ! የመከራ ዘመን!“
“የት ደርሷል?” ስላቸው፣
“ቀርቧል” ብቻ እያሉኝ፣
“መች ይመጣል”ም ስል፣
“ደርሷል!” ብቻ እያሉኝ፣
ይኸው አርባ ዓመቴ፤ በፍርሃት አለሁኝ፣
ወይ ዘመኑ መጥቶ፤ ደቁሶ አልደቆሠኝ፣
ፍርሃቱ፣ ፍርሃቱ፣ ፍርሃቱ ገደለኝ፡፡
“ሊመጣ ነው!” ሲሉኝ፣
“የሠላም የደስታ - የጥጋብ ዘመን!”፣
“የት ደርሷል?” ስላቸው፣
“ተቃርቧል!” እያሉኝ፣
“መች ይመጣል”ም ስል፣
“ተዳርሷል!” እያሉኝ፣
ይኸው አርባ ዓመቴ፤ በናፍቆት አለሁኝ፣
ወይ ዘመኑ መጥቶ፤ በደስታ አላሻረኝ፣
ናፍቆቱ፣ ናፍቆቱ፣ ናፍቆቱ ገደለኝ፡
Endalegeta Kebede-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 5176 times