Monday, 26 October 2026 16:55

የሴት ልጅ! ከአባቶች ጋር ብቻ ያደጉ ሴቶች ---

Written by 
Rate this item
(13 votes)
(የግል ምልከታ እንደወረደ)
ልጆች ከእናት ጋር ብቻ ማደጋቸው እንደ ስድብ የሚቆጠርበት ጊዜ ነበር። "ነበር" አልኩ እንጂ ከድሮው ቢሻልም አሁንም "የሴት ልጅ" የሚለውን አገላለጽ እንደ ስድብ የሚቆጠረው ብዙ ነው። የልጅ አስተዳደግ ስኬት ወይም ውድቀት የሚወሰነው በአባቱ ወይም በእናቱ ብቻ ማደግ ላይ ሳይሆን፣ የወላጆች አቅም፣ የፍቅር ስሜት፣ የሞራል እሴቶች እና የሚሰጡት ተገቢ ክትትል ላይ ነው።
አባቶች ጋር ያደጉ ሴቶች ጠንካራ፣ ራሳቸውን የቻሉ እና በራስ መተማመናቸው የጎላ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፤ በእናቶች ደግሞ ስሜታዊ ጥንካሬን፣ ማህበራዊ ግንኙነትን እና የህይወት መሰረታዊ እሴቶችን በማስተማር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው የሚል "አጠቃላይ" እይታ አለ።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን "ሁሉም" ከሚል በደፈናው ውጡና ብዙ አባታቸው ጋር ያደጉ ሴቶች ልጆችን ታዘቡ፤ ሲጀመር የልጅ አስተዳደግ ለሴቶች በተተወበት አገር ወንዶች ዱብእዳ ካልሆነባቸው በስተቀር በብቸኝነት ልጅ አያሳድጉም። ሲያሳድጉ እንደሆነ ተዓምር ጀግንነት ነው የሚታየው።
የሆነ ሆኖ ወንዶች ጋር የሚያድጉ የሚበዙት የአገራችን ሴቶች የተሳሳተውን ወንዳወንድነት የሚወርሱበት ጊዜ ብዙ ነው። የወንድና ሴት ድንበሩ የተፋለሰባቸው፣ አጉል ጀግና ጀግና የሚጫወቱ፣ የተጋነነ ኮንፊዲየንስ የሚያሰቃያቸው ወይም የተጋነነ ፍርሃት ውስጥ የሚኖሩ፣ ዝም ብለው ባህሉም ወጉም ማህበረሰቡም ጋር የሚጋጩ፣ የነፃነት ታጋይ፣ ፆታዊ ጉዳይ የተምታታባቸው፣ አባታቸው ጀግና ሌላው ወንድ ደፋሪ ባለጌ ምናምን ሆኖ የሚታያቸው ሆነው ታገኛቸዋላችሁ። (ወንዶች ነፍሳቸው ለጦር የሚፈላለግ ስለሆነ ሰላም ቢመስሉም ውስጣቸው ዝቅ የማለት ተፈጥሮ የለውም፣ ሌላውን የማናናቅ ተፈጥሮ ውስጣቸው አለ አቅም ሲያንሳቸው ራሳቸውን የሚያሳምኑበት መንገድ ነው) ለሴት ለልጆቻቸውም የሚያወርሷቸው በጣም ድብቅ ባህሪ ይህ ነው። ስለዚህ ብዙ አይወራም።
ማንም ወዶ በነጠላ ወላጅ አያድግም፤ ግን አጋጥሞ ይነጻጸር ከተባለ፣ እናታቸው ጋር ያደጉ ሴቶች አባታቸው ጋር ካደጉት ሴቶች የተሻለ በሳልና ትክክለኛውን የህይወት ገጽታ መረዳት የሚችሉ፣ ከአጉል ጀብደኝነት የራቁ፣ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው።
የእናንተስ ሃሳብ ምንድነው?
Alex Abrham-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 9953 times