መካንነት አብዛኛውን ጊዜ በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት ችግር ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም፣ ከጠቅላላው የመካንነት ችግር እስከ 18 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዙት ወንዶች መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። ሁለት ጥንዶች ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ ሳይጠቀሙ ከአንድ ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ እርግዝና ካልተፈጠረ የመካንነት ችግር ተብሎ እንደሚገለጽ የሚታወቅ ሲሆን፣ የወንዶች መካንነት በዋናነት ከዘር ፍሬ (ስፐርም) ምርት ብዛት፣ ጥራት እና እንቅስቃሴ ሂደት ጋር የተያያዘ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር ዙቤይዳ ሁሴን እንደገለፁት ከሆነ፣ የወንድ የዘር ፍሬ ጤናማ እና ጥራት ያለው ስፐርም ማምረት የሚችለው ከሰውነት መደበኛ ሙቀት በቀዘቀዘ አካባቢ ነው። ላፕቶፕን እግር ወይም ጭን ላይ አድርጎ መጠቀም የወንድ ዘር ፍሬ የሚፈልገውን መደበኛ ሙቀት የሚጨምር በመሆኑ፤ የስፐርምን ብዛት፣ የመንቀሳቀስ ብቃት እና ቅርፅ ስለሚጎዳ የወንዶችን የመውለድ አቅም በመቀነስ ለመካንነት ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ዶክተር ዙቤይዳ አስገንዝበዋል። በመሆኑም ላፕቶፕን ሁልጊዜም በጠረጴዛ ወይም በሌላ ጠፍጣፋ ነገር ላይ አስቀምጦ መጠቀም እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም የሆርሞን መዛባት፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲሁም የሚያጣብቁ የውስጥ ሱሪዎችን ማዘውተር ወንዶችን ለመካንነት ከሚያጋልጡ ሌሎች ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን የህክምና ባለሙያዎች አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAd
Wednesday, 28 October 2026 06:32
ወንዶች ሊያውቁት የሚገባ መረጃ፡ ላፕቶፕን እግር ላይ ማድረግና የሚያጣብቁ ሱሪዎች ለመካንነት ሊያጋልጡ ይችላሉ
Written by Administrator
Published in
ኪነ-ጥበባዊ ዜና

