Thursday, 29 October 2026 16:25

"የትላንት የቤት ስራ ነው ዛሬ የሚያተራምሰን"

Written by 
Rate this item
(4 votes)
(የግል ምልከታ እንደወረደ)
ከ3ኛው ሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ በጉጉት የምጠብቀውና ቢሆን ብዬ የምመኘው ትልቅ ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሩሲያ ሸምጋይነት የሰላም ስምምነት ላይ ደርሰው አሁንም አንድ የድሃ ልጅ ነፍሱንና አካሉን ሳይገብር ሰላም እንዲወርድ ነው።
ደግሜ ማስመር የምፈልገው ነገር ቢኖር "ኢሳይያስ አረጀ" በሚል እሳቤ መንግስትን በጦርነት ወደብም ሆነ ቦኖ ውሃ እንዲወስድ መገፋፋት ለአፍታ ድል ቢመስልም፣ ነገ አብይም ያረጃል! ያኔ ደግሞ ተረኛው በአዲስ ጉልበት ሌላ እልቂት ይዞ ይነሳል። ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር አስከፊ አዙሪትና የጥፋት ቤት ስራ ማስቀመጥ እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጣም። የትላንት የቤት ስራ ነው ዛሬ የሚያተራምሰን።
ወደብ ያስፈልገናል። በጣም ያስፈልገናል...ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ዶ/ር ዐብይ ፓርላማ ላይ ስለቀይ ባህር እና ወደብ ስለማግኘት ያቀረቡት "ሰጥቶ የመቀበል" ሰላማዊ መንገድ የተሻለው አማራጭ ነው። ምን እንስጥ መነጋገር ነው። "የግድ ደም በውሃ ካልተለወጠ" ብሎ መመናቸክ በፍጹም የአገር ፍቅር መገለጫ ሊሆን አይችልም።
በሌላ በኩል፣ አቶ ኢሳይያስም ቢሆኑ አጉል መመናቸክንና፣ በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበዱ አገራትን ግፊትና ጭብጨባ ወደጎን ብለው በብዙ ነገር ለተሳሰረው የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ የሚጠቅመውን የሰላም፣ የጋራ እድገትና የአጋርነት መንገድ ቢመርጡ የተሻለ ነው። የጦርነትን ዘግናኝ ገጽታ ከእርሳቸው በላይ የሚያውቅ የለም።
Alex Abrham-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 7212 times