በዓዲግራት ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ህብረተሰቡ በቀንም ሆነ በሌሊት በታጠቁ ቡድኖችና ግለሰቦች ሳቢያ በከባድ ስጋት ውስጥ ወድቆ እንደነበር የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አታክልቲ ገብረህይወት ገልጸዋል።
በትግራይ ተፈጥሮ የነበረው ፖለቲካዊ አለመግባባት ወደ ጦርነት ሲያመራ ከ600 በላይ ወንጀለኞችና ከ150 በላይ ተጠርጣሪዎች ከእስር እንዲፈቱ በመደረጉ እና የጸጥታ መዋቅሩ በመበተኑ ችግሩ ተባብሶ እንደነበር ተብራርቷል። ከእስር የተለቀቁት እነዚህ ቡድኖች ከ5 እስከ 20 ሰዎችን በማደራጀትና የተለያዩ መሳሪያዎችን በመጠቀም በመንግስትና በህዝብ ተቋማት ላይ ስርቆትና ዘረፋ ሲፈጽሙ እንደነበርም ተመልክቷል።
በዚህ ከባድ ሁኔታ ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ነጋዴዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሚሊሺያዎች ዘረፋን ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ ችግሩ ከህብረተሰቡ አቅም በላይ በመሆኑ የተቀናጀ አሰራር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ዓዲግራት ኮሚኒኬሽን እንዳመለከተው፣ በተደረገው ጥሪ መሰረት ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላት ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ወደ ሥራ ተመልሰዋል። በተጨማሪም በከንቲባው ከሚመራው አመራር፣ ከፖሊስ ማኔጅመንትና ከጸጥታ አካላት ጋር በተደረገ ስምምነት ሚሊሺያዎችን፣ ወጣቶችንና የፖሊስ ኮሚኒቲ አባላትን ያካተተ ቡድን በየቀጠናው በማደራጀት የጸጥታ መዋቅሩ የመልሶ ማደራጀት ሥራ ተከናውኗል።
በተከናወነው የመልሶ ማደራጀት ሥራና በተደረጉ ድንገተኛ ፍተሻዎች ከ32 በላይ ፍርደኞች፣ 47 በስርቆትና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሰዎች እንዲሁም 6 በጥብቅ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋል ችለዋል። ኢንስፔክተር አታክልቲ፣ የጸጥታ ሥራው ዘላቂ ይሆን ዘንድ ቀጣይነት ያለው ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የጸጥታ መከበር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ የሁሉም አካል ኃላፊነት መሆኑን በማስገንዘብ ለከተማዋ ነዋሪዎችና አጋር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

