Friday, 30 October 2026 06:13

የ7 ዓመቱን ሕፃን የገደለው ተጠርጣሪ ሊያመልጥ ሲሞክር በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አለፈ

Written by 
Rate this item
(2 votes)
አዲስ አበባ ውስጥ የ7 ዓመቱ ሕፃን አማኑኤል ሠለሞን በገዛ ቤታቸው ጥበቃ ሠራተኛ ታግቶ መወሰዱን እና አጋቹ 4 ሚሊዮን ብር ካልተከፈለው ልጁን እንደሚገድል ቤተሰቦቹን ማስፈራራቱ ተነገረ። አዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች ክልል ፖሊሶች ጋር በመተባበር ባደረገው ጥብቅ የቴክኖሎጂ ክትትልም፣ ተጠርጣሪውን ግሩም ወርቁ የተባለውን ግለሰብ አፋር ክልል ውስጥ በቁጥጥር ሥር አውሎታል።
በምርመራ ወቅት ተከሳሹ ሕፃኑን “ሳር አጭደን እንመለሳለን” ብሎ ወደ ጫካ በመውሰድ በገመድ አንቆ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንደገደለው አምኗል። ከገደለው በኋላም ልጁ በሕይወት ያለ በማስመሰል ፎቶ እየላከ ገንዘብ ሲጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ ፖሊስም በተሰጠው ቃል መሠረት የሕፃኑን ቀሪ የሰውነት አካላት ከጫካ ውስጥ አስመጥቶ ለቤተሰቦቹ አስረክቧል።
ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ሥራዎችን ለማከናወን ተከሳሹን ይዞ ወደ ወንጀል ስፍራው ባመራበት ወቅት፣ ወንጀሉ ያልጸጸተው ግለሰብ ከሕግ ለማምለጥ ሲል ከፖሊስ አባላት ጋር ግብግብ ፈጥሯል። ገደል ለገደል በፈጠረው የማምለጥ ሙከራ ወቅትም በፖሊስ በተወሰደ ርምጃ በጥይት ተመቷል።
በጥይት የተመታው ተጠርጣሪ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ማዳን አልተቻለም። አዲስ አበባ ፖሊስ ይህንን አሳዛኝ ክስተት አስመልክቶ ሕብረተሰቡ የቤት ሠራተኞችንና ጥበቃዎችን ሲቀጥር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት እንዲሁም ለልጆች ዘወትር ተገቢውን ክትትል ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል።
Addis Ababa Police-
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 7392 times