Wednesday, 04 April 2012 08:49

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነብይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

“ዝምታ ወርቅ አይደለም!”

“ስጦታ ሰጥተህ ካልረሳኸው ስጦታ አይደለም!”

“ይሄን ያህል ዓመት እኔ ስሸከምህ ነበር፡፡ እስቲ ደሞ ዛሬ አንተ ተሸከመኝ”

የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ተገልጦ የማያልቅ የአለት ገፅ ነው፤ የቋጥኝ ምዕራፍ ነው ብለናል፡፡ ማሠሪያው ፅኑ ማተብ፣ የማይበጠስ ክር ነውም ብለናል፡፡ ውስጥ ለውስጥ በአለት ፍልፍል አሸንዳዎች የተሳሰሩትና በደረጃዎች የሚገናኙት ቤተ-ክርስቲያኖች የእኒያን ሁሉ አመታት ዕድሜ አስቆጥረው ለተዓምርነት የበቁት ያለ ነገር እንዳልሆነ ለመመስከር ዐይንን አስቆጥረው ለተዓምርነት የበቁት ያለ ነገር እንዳልሆነ ለመመስከር ዐይንን ማሸት አያሻም፡፡ ፀሐፍት እንዳስቀመጡት ቤተ-መድኃኔ ዓለም በመጀመሪያ የሚገኘው ቤተ-መቅደስ፣ በስፋቱና በአሠራር ጥበቡ የሚስተካከለው የሌለ ነው፡፡ የአለት ምሠሦዎች ጠንካራ አቅም፣ ጣራውን ደግፈው ተሸክመው ለዘመናት የኖሩ ናቸው፡፡

ብዛታቸው 72 ነው - ከውጪ የአራት ማዕዘን ቅርፅ ያላቸው፡፡ አንድ ወጥ የሆኑና በመጨረሻ የመስቀል ቅርፅ የሚይዙ ናቸው፡፡ አሞራ ክንፍ፣ ጣራ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ አምስት የቅኔ ማህሌት መተላለፊያ ክፍሎች ያሉት ባለልሙጥ ጣራ ሰፊ ክፍል አለው፡፡ ብዙ ጌጣጌጦችና የቅብ ሥራዎችን ያልያዘው ይህ ቤተ ክርስቲያን፤ ለብርሃን ማስገቢያ የሚያገለግሉና በመስቀል ቅርፅ የተሠሩ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የታነፁ መስኮቶች አሉት፡፡ በኖራ መሰል ማጣበቂያ የተያያዙ ማራኪ ቀለም ያላቸው መስታወቶቹ ዐይንን ይስባሉ፡፡ “አፍሮ አይገባ” በመባል የሚታወቀው ከሰማይ የወረደው ድንቅ መስቀል በሚል አያሌ የታሪክ ተመራማሪዎት የተናገሩለት መስቀል፤ የሚቀመጠው በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ቤተ መድኃኔ ዓለም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በተነሳው በግራኝ መሀመድ አማካኝነት መጠነኛ ጥቃት እንደደረሰበት ይነገራል፡፡

 

ከቤተ መድኃኔዓለም በስተ ምዕራብ በኩል አጭር የዋሻ ውስጥ መንገድ አልፈን በአራቱም አቅጣጫ በአብያተ ክርስቲያናት የተከበበችውን ቤተ ማርያምን እናገኛለን፡፡ በምሥራቅ ቤተ መድኃኔ ዓለም፣ በምዕራብ ቤተ ጐልጎታ፣ በደቡብ ቤተ ደናግል፣ በሰሜን ቤተ መስቀል የሚያዋስኗት ይህች ቤተ ክርስቲያን፤ በመጀመሪያ የታነፀች ናት ይላሉ ፀሀፍት፡፡ ቅዱስ ላሊበላ አብልጦ ይወዳት ነበር የምትባለው ይቺ ቤተክርስቲያን፤ ወለሏ ከጥንታውያን ምዕራባውያን አብያተ - ክርስቲያናት አሠራር ጋር ይመሳሰላል ይባላል፡፡ በምሥራቃዊው ግድግዳዋ አካባቢ የመጠመቂያ ገንዳ አለ፡፡ ፀበሏ ለደዌዎች ፈውስ ነው የሚባል ሲሆን በተለይ የመካን እናቶች ማህፀን ዘር እንዲቋጥር ይረዳል የሚል የመዛግብት ምሥክርነት መኖሩን ብዙዎች ይገልፃሉ፡፡ ቤተክርስቲያኗ ከጣሪያዋ በስተቀር በቀላል የመስቀል ቅርፅ የተጌጠች፣ ልዩ ውበት ያላቸው አግዳሚ ቅርፆችን የያዘች፣ ልሙጥ የመግቢያ በሮች ያሏት ስትሆን፤ በውጪው ግድግዳ በምዕራቡ ገፅ ላይ ጦር የያዙ የሁለት ፈረሰኞች ምስል ተቀርፆ ወጥቶ ይታይባታል፡፡ ሁለቱ ፈረሰኞች እሳት ከሚተፋ ፍጡር ጋር ሲፋለሙ ይታያል፡፡ ከፈረሰኞቹ ራስ ላይ የሚታዩትን ዝርግ ነገሮች የፀሀይ ምልክት ነው የሚሉ ተርጓሚዎች አሉ፡፡ በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ያሉት የመስቀል ዓይነቶች ከላቲኖችና ከግሪኮች መስቀል አሠራር ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡

ባለአንድ ፎቅ ህንፃ የሆነችው ቤተ-ማርያም እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት አምዶች ያሏቸው ሦስት ደጃፎች ያሉት ቤተ መቅደስ አላት፡፡ በተለያዩ መንፈሳዊ ጌጣጌጦች ያሸበረቀች ናት፡፡ የዋሻ ቅርፅ ባለው ግርዶች የተለያዩ የቅኔ ማህሌት ቤቶች ሲኖሩት በመስኮት ቅርፅ ከተሰሩት ጌጣጌጦች መዋቧና ከአክሱማውያን የጥበብ ሥራዎች ተቀራራቢነት አላቸው በሚባሉት የበር ገጽታዎች መግዘፏ ልዩ ያደርጋታል፡፡

በመቅደሱ ውስጥ ባለው ደጃፍ ታልፎ ወደ ላይኛው ፎቅ ይወጣል፡፡ በመንበሩ ግራና ቀኝ ሁለት ደጃፎች አሉ፡፡ የታቦተ ዮሐንስ መጥምቅ መግቢያ አንደኛው ደጃፍ ነው፡፡ በመቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ቁመታቸው ከ4 ሜትር የበለጠ፣ ወርዳቸው 45 ሳንቲ ሜትር የሆኑ 6 አምዶች ይታያሉ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጠኛ ክፍል እጅግ ሲዘልቁ በጨርቅ የተሸፈነ ምሰሶ ይገኛል፡፡ በጨርቅ የተሸፈነው በአፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት በነበሩ ሊቀ ካህናት ዜና በሚባሉ የደብሩ አስተዳዳሪ እንደሆነና ተምሳሌትነቱም የዕምነት አንድነት መገለጫ እንደሆነ የሃይማኖት አባቶቻችን ይናገራሉ፡፡ የምሰሶው በጨርቅ መሸፈን ሚሥጥር፣ የሰው ልጅ በአምላክ የተሰጠውን እውነታ ለመሸከም ደካሚ እንደሆነ ለማሳየት ሲባል ነው ይላሉ አበው፡፡ ይህ እሳቤ በራሱ አንዳች ዕፁብ እሴት አለበት፡፡ ሥጦታን መሸከም አለመቻል እረቂቅ ፅንሰ-ሀሳብ አለበት፡፡

ይህን ጉዳይ ሳውጠነጥን አንድ ወዳጄ ጅቡቲ ውስጥ ያገኘው አንድ ሶማሌ ያደረገውን ያጫወተኝን አስታወሰኝ፡፡ ከመለኮታዊው አጀንዳ ጋር ባይያያዝም ውስጥ ውስጡን የሚሰጠው መልዕክት ከቶም ታላቅ ነው ቢባል አያንሰውም፡፡

ኢትዮጵያው ጅቡቲ ሄዶ ገንዘብ ያጣል - በጣም “ይቸስታል”፡፡ የሚላስ የሚቀመጥ ያጣል፡፡

አንድ ሶማሌ ያገኛል፡፡

“ወሪያ እንዴት ነህ?” ይላል ሶማል፡፡

“ደህና ነኝ ወዳጄ፡፡ ከሶማሌ ነህ?”

“አዎን፡፡ አንተም ከኢትዮጵያ ትመስለኛለህ?”

“እርግጥ ነው - አበሻ ነኝ” ይላል ሐበሽ፡፡

“ጥሩ ገምቻለሁዋ! ከሩቅ ሳይህ ኢትዮጵያዊ መሆንህን ጠረጠርኩ! ተሳካ!”

“ትክክል ነህ! በጣም ደስ ብሎኛል ስላገኘሁህ!”

“እኔም!”

“አንድ ችግር አለብኝና ላዋይህ?”

“ምን?”

“ከኢትዮጵያ ከመጣሁ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል፡፡ ገንዘቤን ሁሉ ጨርሻለሁ፡፡ መቃሚያም የለኝም!”

ሶማል፤ “አብሽር አብሽር! ይሄ ምን ችግር አለው?” አለና አሥር ብር አውጥቶ ይሰጠዋል፡፡

አበሽ አመስግኖ ይሄዳል፡፡ ከዓመት በኋላ ይገናኛሉ፡፡

“ኦ ሶማል! ባለውለታዬ! የማይታመን ነገር ነው! ያኔ የሰጠኸኝ አሥር ብር የዋዛ እንዳይመስልህ፡፡ ለችግሬ በሰዓቱ ደርሶልኛል! ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ! ውለታህን እንዴት እንደምከፍል እንጃ!”

“ኧረ ምንም አይደለም! ይሄ በጣም ቀላሉ ነገር ነው!” አበሻው ብዙ ምሥጋና ካቀረበ በኋላ ይለያያሉ፡፡

አበሻው ግን ማመስገኑ አልበቃውም፡፡ ሌላ ቦታ ሶማሌውን ያገኘዋል፡፡

“በዕውነት ያኔ ስላደረግህልኝ ውለታ በጣም ነው የማመሰግነው!” ይለዋል፡፡

“አቦ በቃ! ምሥጋናው በቃኝ!” አለ፡፡

አበሽ አሁንም አልረካም፡፡

“የውልህ ሶማል፤ አንተ እንደቀላል አየኸው እንጂ የሠራህልኝ ሥራ በጭራሽ ቀላል አይደለም!?” አለው፡፡

ሶማል መረረው፡፡

“አቦ ይሄ አበሻ ምን ነካው?!” በእኛ በሶማሌያውያን ዕምነት፤ አንድ ስጦታ ለአንድ ሰው ሰጥተህ ካልረሳኸው ልባዊ ስጦታ አይባልም! ይሄ ዋናው መርሃችን ነው!” አለው፡፡

አበሽ የዚህ ፍልስፍና ውስጠ - ነገር አልገባውም፡፡

“ግን’ኮ በቀላሉ የሚረሳ ገንዘብ አይደለም የሰጠኸኝ የስጦታዎች ሁሉ ስጦታ ነው እንዴት ብዬ እንደማመሰግንህ አላውቅም” ይላል፡፡

ሶማል የመጨረሻ መረረው፤

“አቦ ይሄ አበሻ መቶ ብር ብሰጠው ምን ሊሆን ነበር?” ብሎ ጥሎት ይሄዳል፡፡

እዚህ ትረካ ውስጥ የማረከኝ፣ ሰው ስጦታ ሰጥቶ ካልረሳው ስጦታ አይባልም የሚለው ሐሳብ ሲሆን፤ አንዳንድ ስጦታ ምን ያህል ሊከብድ እንደሚችል ጭምር ለማሳየት ነው፡፡ ይኸው ስጦታ ከአምላክ ሲሰጥ ደግሞ ምን ያህል እንደሚከብድ ለማፀህየት (Verification) ነው!

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ከሚታዩት ስዕሎች ውስጥ፤ “ቅድስት ኤልሳቤጥን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልትጐበኛት በመጣች ጊዜ፤ ሁለቱ ተቃቅፈው ሰላምታ ሲለዋወጡ፤ እመቤታችን ጌታን የመፀነሷን ዜና ከመልአኩ በሰማች ጊዜ፣ በኢትዮጵያውያን አሳሳል ጥበብ በትልልቅና በጥቋቁር ዐይኖች መልዐኩን በመገረም ስትመለከተው፤ ያሳያሉ፡፡ ስዕሎቹ በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመን (1434-1468) እንደተሳሉ ታሪክ ይመሰክራል፡፡

“የእመቤታችን የግብጽ ስደት ሌላው የስዕሉ ገጽታ ነው፡፡ በሥዕሉ ላይ እመቤታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጣ ትታያለች፡፡ የተምር ዛፎች በደረቁ መሬት ላይ ተንዠርገው በልምላሜዎቻቸው እመቤታችንን ሲቀበሏት፤ ሳምራዊቷ ውሃ ቀጂ ሴት ከጉድጓድ ውኃ ልትቀዳ ስትጣጣር፤ እየሱስ ክርስቶስ ከውኃው እንደድታጠጣው በጠየቃት ጊዜ በመካከላቸው የነበረውን የቃላት ልውውጥ የሚያመለክት ስዕል፤ 38 ዓመት ሙሉ የአልጋ ቁራኛ የነበረው መፃጉዕ በክርስቶስ ፈውስ አግኝቶ እንዲሄድ ሲያዘው ይተኛበት የነበረውን ድንክ አልጋ ተሸክሞ ሲጓዝ የሚያሳይ ስዕል ከጣሪያው ሥር ይታያል፡፡

ይሄ ሥዕል አንዶች ሃሳብ ጫረብኝ፡፡ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ አንድ ጊዜ “ዝምታ ወርቅ አይደለም” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ታላላቅ ፀሐፍት በተፃፈ ሥራ ላይ ያየሁት ሙግት!

ነገሩ እንዲህ ነው!

የዶክተር ጌታቸው ሙግት ያነጣጠረው “ግዕዝ የቤተክርስቲያን የሃይማኖት ቋንቋ ብቻ ነው!” የሚሉት ወገኖች ላይ ነው፡፡ መጽሐፉ “Silence is not Golden”  ይባላል፡፡ ዝምታ ወርቅ አይደለም እንደማለት ነው፡፡

ይህንኑ ለማስረዳት ለዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ የቆየው በሽተኛ፤ “ተነስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ባለው ሰዓት፤ ከመኝታው ተነስቶ አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ፤ አልጋይቱ እንዲህ አለችው:-

“ይሄን ያህል ዓመት እኔ ስሸከምህ ነበር! እስቲ ደግሞ ዛሬ አንተ ተሸከመኝ?!” የሚል በግዕዝ ተጽፎ ይገኛል፡፡

በዚሁ ጽሑፋቸው፤

ሎጥ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከሴት ልጁ ጋር ተኝቶ ነበር የሚለውን ለሚቃወሙ፤ አንድ ነገር ልብ ይበሉ፡፡ እስከ ሰባተኛ ትውልድ የመጋባት ነፃነትን መሠረት በማድረግ ሎጥን ለሚረግሙ ወገኖች ግዕዙ፤

“የሥጋ ቅርበት/ዝምድናን/ በተመለከተ ከሆነማ አዳም ራሱ ከግራ ጐኑ ከወጣችው ከሄዋን ጋር ተኝቶ የለምን?” ይላል፤ ሲሉ ያብራሩታል፡፡

ተቀብለናቸው የቆየነውን ሁነቶች ማቆየት ግዴታችን የመሆኑን ያህል ለውጪ ሰዎች ጥቃት ዒላማ የሚያደርጉንን ሁኔታዎች መመርመርም ደግ ነው፡፡

“ሁሉንም ሞክሩ፤ የተሻለውን አጽኑ” የሚለው አባባል፣ ሥርወ ሀረጉ በግዕዝ ነው የተፃፈው

“ኩሉ አመክሩ፤ ወዘሰናየ አጽንዑ” ሲል፡፡

ቀጥለን ቤተ - መስቀልን፣ ቤተ - ደናግልን፣ ቤተ ደብረ - ሲናንና ቤተ ጐለጐታን እናይና፤ በሥላሴ ቤተ - መቅደስ፤ በአዳም መካነ መቃብር፣ በቤተ አማኑኤል አድርገን ፤ ቤተ - መርቆርዮስንና ቤተ አባሊባኖስን በአጭሩ ዳስሰን፤ በቤተልሄም በኩል ቤተ - ገብርኤል ወሩፋኤል እንገባና ወደቀጣዩ የባህር ዳር መንገድ እናመራለን!

መንገድ/መጓዝ ማወቅ ነው!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 2562 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 08:52