Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 09:07

“በጭማሪው ያልተቀየመ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መምህር -

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የገመና 2 መምህር”

“ለተማሪ መቶ አይሰጥም”…”ለመምህር መቶ አይሰጥም”

“ይሄን ትውልድ በ65 ብር ምላጭ እየቀረጽኩት ነው”

“ስራ አገኘህ፣ ወይስ አሁንም አስተማሪ ነህ?”

የደመወዝ ጭማሪው

አስተማሪው ቂም የያዘበት፣ ተማሪው “ሙድ” የያዘበት (ወግ)

“አንድ አስተማሪ አለ

ከጃፓን የመጣ

ማስመሪያውን ጥሎ

በቦክስ የሚማታ፣

ታናግሪኝና አናግርሻለሁ

ባማሪካ ሽጉጥ

አዳንፍሻለሁ፡፡”

የምትል የድሮ መዝሙር ነበረች፡፡

ልጅ እያለን በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ደጋግመን የምናቀነቅናት፡፡

“በየካቲት ወራት

ቦንብ ፈንድቶ

አገሬ ታጠቀች

የህብረት ቀበቶ”…ከሚለው `አብዮታዊ መዝሙር` ሆነ

“ሳይንስ ሳይንስ

መድሃኒቴ

አስታወሰኝ

ጤንነቴን

እጄን ታጥቤ

ቁርሴን ስበላ

ሳይንስ ትዝ አለኝ

ከጤና ጋራ…” ከሚለው “ሳይንሳዊ መዝሙር” ይልቅ የጃፓኑን አስተማሪ መዝሙር ለዚህ ጽሑፍ መግቢያነት ብጠቀማት የተሻለ ይሆናል፡፡

ለመፃፍ ያሰብኩት ስለ አስተማሪዎች በመሆኑ ነው “አንድ አስተማሪ አለ” የምትለዋን “አስተማሪ ተኮር” መዝሙር ለመግቢያነት የመረጥኳት፡፡

እርግጥ በአገራችን አስተማሪዎች ሰሞንኛ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን ወግ፣ ከጃፓን ስለመጣ የሰው አገር አስተማሪ በሚያወራ መዝሙር መታጀቡ አግባብ ላይሆን ይችላል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ከጃፓን የመጣው መምህር ለመልካም ተሞክሮነት የሚበቃ ሰው አይደለም፡፡ በቴክኖሎጂ ከተራቀቀች አገር እንደመምጣቱ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረጉን ትቶ የድብደባ ሽግግር ሲያደርግ የታየ ለሪፈራንስ የማይበቃ ሰው ነው፡፡

በማስመሪያ ከመማታት በቦክስ ወደ መማታት ከተሸጋገረ አስተማሪ ሊቀሰም የሚችለው ተሞክሮ “ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ በአሜሪካ ሽጉጥ ማዳፈን የተሻለ መላ ነው” የሚል ብቻ ነው፡፡

ለዚህ ነው ሃሳቤን ቀይሬ ከመዝሙር ይልቅ “አስተማሪ ተኮር” ሰሞንኛ ወጌን በቅርቡ መንግስት በለቀቃት ነጠላ ዜማ ለመጀመር (?) የወሰንኩት፡፡

“ምድረ አስተማሪ

ኩሪ ኩሪ

አሻርኩሽ በጭማሪ”

ይህቺን አስደሳች ነጠላ ዜማ የሰማ ምድረ - አስተማሪ፣ በደስታ ተቃቅፎ “ያዝ እንግዲህ” ሊል የተዘጋጀባት ታሪካዊት ሳምንት፣ ለመምህርነት ሙያ ተገቢው ክብር የተሰጠባት መሆኗ ተነግሮ ሳያበቃ ሌላ ጉድ ይዛ መጣች፡፡

“ለሙያችሁ ክብር፣ ለአንተ ብር አፍሼ ሰጠሁህ” በመባሉ የተደሰተ ምድረ አስተማሪ፣ እዚህ ግባ የማይባል የደመወዝ ጭማሪ እንደደረሰው ሰማና አኮረፈ፡፡

“ለመምህራን ደመወዝ ሊጨመር ነው” መባሉን ሰምቶ “እኛስ የእንጀራ ልጅ ነን እንዴ?” ብሎ የጠየቀ ቅናት የተሰማው መሀንዲስ ሊኖር ይችላል፡፡

ለመምህራን ባዳላ መንግስት ላይ  “ከልጅ ልጅ ቢለዩ፣ አመትም አይቆዩ” ብላ  የተረተች ሒሳብ ሰራተኛም አትጠፋም፡፡

ኧረ…የምን “አመትም አይቆዩ” ነው እሱ?....

ለመምህራን ብቻ ለይቶ የደመወዝ ጭማሪ በማድረጉ “ከልጅ ልጅ ለየ” ተብሎ የታማ፣ “ለሙያው ክብር ሰጠሁ” ብሎ በአደባባይ ያወጀ መንግስት….አመትም ሳይሆን ሳምንት ሳይቆይ በድርጊቱ መኮነን ጀመረ፡፡

መንግስት የተናገረውን ሰምተው የተደሰቱ መምህራን የሰፈረውን አይተው በሀዘን የተኮራመቱት በዚያች ታሪካዊት ሳምንት ነው፡፡

“አሁን ገና አሳቢ አገኘን” አሉ መምህራን፡፡

“እንዲህ ነው እንጂ ለሙያ ክብር መስጠት!” አለች መምህርነት፡፡

ሙያና ሙያተኛ ተቃቅፈው ሲፈነድቁ አየሁ፡፡

ይሄን እያየሁ የድሮ መምህሮቼ ትዝ አሉኝ፡፡

እነ ጋሽ ዋለ፣ እነ ጋሽ አማረ፣ እነ እትዬ ጉዳይ፣ እነ እትዬ ውብ ሐረግ…ሌሎች ሌሎችም ሁሉ….መምህርነት ትልቅ ቦታ ይሰጠው በነበረ ጊዜ፣ ወደ ሙያው የገቡ የድሮ አስተማሪዎቼ ትዝ አሉኝ፡፡

መምህርነት ከክብር ቦታው ተነስቶ ወደ መናቅ ሲወርድ አይተው ያዘኑባቸው የቅርቦቹ አመታት አልፈው፣ ወደ ክብር የመመለስ ጊዜ መምጣቱን ሲሰሙ ምን እንደሚሰማቸው አላውቅም፡፡

መንግስት ለሙያው ክብር መስጠቱን ሲያውጅ የሰሙ፣

“የእኛ ሙሽራ

ኩሪ ኩሪ

ወሰደሽ አስተማሪ” ተመልሶ መዘፈኛው፣ መምህርነት እንደ ድሮው መከበሪያው፣ መምህርም የላቡን ያህል ተገቢ ገቢ ማግኛው ሸጋ ዘመን እንደመጣ ሳይጠረጥሩ አልቀሩም፡፡

የደመወዝ ጭማሪው ዝርዝር መረጃ ይፋ ሲደረግ ግን ያልተጠበቀው ነገር መጣ፡፡

ለመምህራን የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡ መምህራን “እዚህ ግባ” የማይባል ብር “ጨመርኩላችሁ” ባላቸው መንግስት ላይ አኮረፉ፡፡

ጭማሪውን በመቃወም ስራ ለማቆም የሞከሩ መምህራን መኖራቸውም በየጋዜጦች ላይ ሲዘገብ ሰነበተ፡፡

መምህራን “መንግስት ጉዳዩን እንደገና ይመልከተው” በሚል የንዴት ተቃውሟቸውን እያሰሙ፣ መንግስትም “ያለቀለት ነገር  ነው” እያለ ሀሳቡን እንደማይቀይር ሲናገር ሳምንታት አለፉ፡፡

መምህራን በመንግስት ላይ ቂም ሲይዙ፣ ተማሪዎች በመምህራን ላይ “ሙድ ያዙ” ተማሪዎች ከመምህራን ፊት ላይ የሚያነቡትን ቅሬታ በመለካት፣ ለእያንዳንዱ መምህር የሚገባውን ማዕረግ መስጠት ጀመሩ፡፡

“ቲቸር እከሌ 50 አለቃ ሻረ”

“ቲቸር እከሊት 100 አለቃ ነከሰች” እያሉ መመደብ ያዙ፡፡

“ቲቸር እከሌ 50 አለቃ ሆነ” ማለት “በአዲሱ የደመወዝ ጭማሪ 50 ብር አገኘ” የሚል ትርጓሜ አለው - በሙደኛ ተማሪዎች ቋንቋ፡፡

“መምህርነት የድሮ ክብሯን መልሳ ልትይዝ ነው” ተብሎ መወራት በጀመረ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደገና ሙድ ይያዝባት ጀመር፡፡

መምህር በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማው ደጋግሞ የሚናገር ወዳጅ አለኝ፡፡

መምህርነቱን ትቶ በሌላ ሙያ ቢሰማራ የተሻለ ገቢ ሊያገኝ እንደሚችል ለሚመክረው ሁሉ የሚሰጠው ምላሽ “ሙያዬን እወደዋለሁ፡፡ መምህርነት እኮ ትውልድን የመቅረፅ ጉዳይ ነው” የሚል ነው፡፡

ከደመወዝ ጭማሪው ጋር በተያያዘ የተፈጠረበትን ስሜት ለመረዳት ፈለግሁና ስልክ ደወልኩለት፡፡

“ስራ እንዴት ነው ታዲያ?” ስል ጠየቅኩት፡፡

“አሪፍ ነው! … ይሄን ትውልድ በ65 ብር ምላጭ እየቀረፅኩት ነው” አለኝ መምህሩ ወዳጄ - እሱም በራሱ ላይ ሙድ እየያዘ (በደመወዝ ጭማሪው 65 ብር እንዳገኘ ለመገመት አላዳገተኝም)

በቃ … መምህርነት ሙድ እንደተያዘባት ልትቀጥል ነው ማለት ነው? ከትናንት ወዲያ “ትታፈርና ትከበር” የነበረች ክቡር ሙያ ትናንት መሳለቂያ ሆነች፡፡

ዛሬ ደግሞ ሙድ መያዣ! ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ጓደኛሞች ከተለያዩ ከሁለት አመታት በኋላ በድንገት ተገናኙ አሉ፡፡

አንደኛው መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በመምህርነት ሙያ ተሰማርቷል፡፡ የመጀመሪያው እንዲህ ብሎ ጠየቀ፤

“እኔ እምልህ … ስራ አገኘህ፣ ወይስ አሁንም አስተማሪ ነህ?”

ይህ ቀልድ ሊመስል ይችላል፡፡ ቀልድ ግን አይደለም፡፡ ቀልድ ቢሆን እንኳን የተናጋሪውን የቀልድ ችሎታ ሳይሆን ማህበረሰቡ በመምህርነት ሙያ ላይ ያለውን አመለካከት ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ “ቀልድ” ሆኖ ነው የሚሰማኝ (ሶሪ ነገርዬውን አካበድኩት መሰለኝ)፡፡

በነገራችን ላይ …

ድሮ ድሮ … “ለተማሪ መቶ አይሰጥም” የሚባል “አንፌር” ህግ (?) እንደነበረ ትዝ ይላችኋል? … አቦ ምን አይነት ኮሚክ ህግ ነበረች! … እውነቴን እኮ ነው! … የድሮ መምህራን ግን ምን ነካቸው? … ጐበዝ ተማሪ ሲገኝ “መቶ” ቢሰጡት ምን ይጐዳሉ? … ለነገሩ የእነሱ ግፍ ሳይሆን ይቀራል በዛሬዎቹ መምህራን ላይ የደረሰው? … ይሄው ዛሬ “ለመምህር መቶ አይሰጥም” ተባለና ስልሳና ሰባ (ብር) ተለቀቀባቸው!

እኔ እምለው … የድሮ ህፃናት “ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ “አስተማሪ” ብለው ይመልሱ ነበር አይደል? የዘንድሮውን የደመወዝ ጭማሪ የሰሙ የዘንድሮ ልጆች ግን ሲያድጉ ምን መሆን እንደሚፈልጉ ቢጠየቁ፣ ሲያድጉ ምን መሆን እንደማይፈልጉ መናገር የሚቀልላቸው ይመስለኛል - “አስተማሪ!”፡፡

እውነቴን እኮ ነው … ቲቸር ሰለሞን “ኖርማል በርገር” እንኳን መግዛት የማይችል ብር እንደተጨመረላቸው እየሰማ፣ መምህር ለመሆን የሚመኝ “ኖርማል ተማሪ” ይኖራል ብሎ የሚያስብ ሰው “ኖርማል” አይመስለኝም፡፡

“የዘንድሮው የደመወዝ ጭማሪ ለብዙዎቹ መምህራን የጨመረው አዲስ ነገር ቢኖር ቅፅል ስም ብቻ ነው” የሚሉ ታዛቢዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡

የሚያሳዝነው እንደ “ቲቸር እንትና” ያሉ አንዳንድ መምህራን ዕድል ነው፡፡ “ቲቸር እንትና” አዲሱ ጭማሪ ጠቅሞ ላይጠቅማቸው አጉል ቅፅል ስም አሰጣቸው ተብሎ ይወራል፡፡

መንግስት ለመምህሩ 77 ብር ጭማሪ ብሎ ሰጣቸው፣ ተማሪውም ይህን ሰምቶ ለመምህሩ አዲስ ቅፅል ስም ሰጣቸው - “ቲቸር 77!”

እስቲ አስቡት … ተማሪው ለመምህሩ “ቲቸር 77” የሚል ቅፅል ስም የሰጣቸው፣ ሰውዬው የእኔ ቢጤ ከሲታ በመሆናቸው በ77 ዓ.ም ከተከሰተው ድርቅና ርሃብ ጋር በማያያዝ አይመስልም?

ምናለበት መንግስት አንዲት ብር እንኳን ጨምሮ ቢሰጣቸው ኖሮ? … ወይም ደግሞ አንዲት ብር እንኳን ቀንሶ “ይሄው ነው ጭማሪው” ቢላቸው ምን ነበረበት? …

ያም ሆነ ይህ ግን የመምህራን የደመወዝ ጭማሪ ጉዳይ እንዲህና እንዲያ እያባባለ ነው ይባላል፡፡ “መንግስት በመምህራን ላይ ድራማ ሰራ” ይባላል፡፡

ድራማው “ታሪካዊ ነው”፣ “ኮሜዲ ነው”፣ “ትራጀዲ ነው፣ “ልማታዊ ነው” … የሚሉ የተለያዩ ብያኔዎችን የሚሰነዝሩ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉም ይነገራል፡፡

“በመንግስት የደመወዝ ጭማሪ ያልተበሳጨና ደስተኛ ሆኖ በቀጣይም “ሳይማር ያስተማረውን” ወገኑን ውለታ፣ በሙያው ለመክፈል ቆርጦ የሚነሳ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ መምህር ቢኖር፣ “ገመና 2” የኢቴቪ ድራማ ላይ የምናውቀው መምህር ብቻ ነው” የሚሉም ጆከኞች ተፈጥረዋል፡፡

“እሱ ራሱ ይህቺ አገር ለመምህር እንደማትሆን የሚያሳይ ምሳሌ አይደለም እንዴ?” የሚሉ ነገረኞችም አልጠፉም፡፡

አጀብ!

 

 

 

Read 2851 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 09:18