Saturday, 09 June 2012 07:19

“ለአዳር ነው ለትዳር!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለእ
Rate this item
(20 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ይኸው እንግዲህ ሰኔም ግም አለ፡፡ ብርድም እየመጣ ነው…የዳግም አረቄ ዋጋም እየጨመረ ነው፡፡ ብቻ…የከርሞ ሰው ይበለንማ!ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በቀደም የወጣውን የቪያግራ ገበያ መጦፍ ዜና አነበብኩና ምን አልኩ መሰላችሁ…“ጠጅ ላይም ምቀኛ ተነሳባት!” ልክ ነዋ…ለስንት ዘመን ‘አቅፎ ደግፎ የያዘን’… “ግዴለም ማታ ጠብቂኝ” እያለች ስታስፎክረን የነበረችውን ጠጅንም በክፉ ዓይን አዩብን! ነገርየው…

አለ አይደል…“የጠጅን ውለታ ወሰደው ቪያግራ…” ምናምን እየሆናላችሁ ነው፡፡እኔ የምለው…ካነሳነው አይቀር…አንድ ጊዜ ቦክስ ኦፊስን ተቆጣጥሮ የነበረ ‘ሴክስ ኤንድ ዘ ሲቲ’ የሚል ፊልም ትዝ አይላችሁም! እናማ…የውጪ ምንዛሪ በጣም ስለሚያስፈልገን… አለ አይደል…

ተከታዮቹ የፊልሙ ክፍሎች እኛ ዘንድ ይሠሩልንማ! ልክ ነዋ…ሁሉም ነገር ተሟልቷሏ! እነ አቫታርን መሥራት ያቅተን እንጂ ለ‘ሴክስ ኤንድ ዘ ሲቲ’ አይነት ፊልሞች…ተዋናይ በሉ፣ ዳይሬክተር በሉ፣ ፕሮዲዩሰር በሉ…አይደለም ለእኛ ለሌሎችም እንተርፋለን፡፡እናማ…ነገርየው በዚሁ ከቀጠለ… እነ ቪያግራ የአምፒሲሊንን ቦታ ባይወስዱ ምን አለ በሉኝ፡፡ ምን ቅር ይልሀል በሉኝ… የብሔራዊ ትያትር አካባቢ ልዩ መፋቂያ ገበያ አደጋ መጣበት! አንድ

ሰሞን…“የሀበሻ የ‘እንትን’ ፊልም አለ…” እንደሚባለው ሁሉ ልጆቹ ጠጋ ይሉና “መፋቂያ ይፈልጋሉ!” ይሉ ነበር፡፡ አሁን ሰለጠንና…እኛስ ለምን ይቅርብን!እናማ… አገር ሁሉ ‘ሰለጠነና’…አለ አይደል…ነገርዬው ሁሉ ባለ ሱቆቹ ‘እጅ በእጅ ፍቅር እንዲደረጅ’ እንደሚሉት እየሆነ ነው፡፡ (‘ፍቅር እንዲደረጅ’  የምትለዋን ቆርጣችሁ አውጡልኝማ! አሀ…‘ታሪክ’ እየሆነ በመጣ ነገር ተረትና ምሳሌ አሪፍ አይደለማ!)

ይቺን ታሪክ ሳትሰሟት አትቀሩም…ሰውየው የዘመኑ ጨዋታ ያልገባው ኖሮ እንትናዬዋን ለማለስለስ ዙሪያ ጥምጥም ይሽከረከራል፡፡ “ምን መሰለሽ… እኔ አንቺ…” ምናምን እያለ የአሥር ዓመት መርሀ ግብር አይነት ነገር ይደረድራል፡፡ እሷየዋ ዝም ብላ ታዳምጥና ነገሩ ስልችት ብሏት ምን አለችው አሉ

መሰላችሁ…“ለአዳር ነው ለትዳር!”

እናላችሁ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ዘንድሮ ነገሩ ሁሉ እንደ ‘ሴክስ ኤንድ ዘ ሲቲ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) “ለአዳር ነው ለትዳር!” ሆኗል፡፡ አለ አይደል…ሁሉም ነገር እዛው በእዛው ማለቅ አለበት፡፡ ልክ ‘ነገ’ የሚባለው ነገር እንደሌለ ሁሉ… ሥራዎች የሚሠሩት ለ‘አሁን’ ብቻ ሲሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ መንገዱ በተሠራ በሁለተኛው ወር ሀይቅ የሚያበጀው፣ ቤቱ አለቀ በተባለ መንፈቅ ሳይሞላው ጣራው የሚቀደደው፣ ከብዙ ጥናት በኋላ የወጣ የተባለው መመሪያ በስምንተኛ ቀኑ በሌላ የሚተካው…ነገራችን ሁሉ “ለአዳር ነው ለትዳር!” የሚያሰኝ በመሆኑ ነው፡፡ “ለእኔ ብቻ ይመቸኝ እንጂ ነገ የራሱ ጉዳይ…” አይነት አስተሳሰብ ቋሚ ነገር እንዳይኖር እያደረገ ነው፡፡እኔ የምለው…አይገርማችሁም! ምን ያህል ሆድ ቢብሰን ነው ለረጅም ጊዜ ማሰብ የሚባል ነገር የተውነው?  ሁሉም ነገር እዛው ሞላ እዛው ፈላ ሆነ’ኮ!…አለ አይደል “ቢያንስ ቢያንስ ለአንድ ሦስት አራት ዓመት ምንም አይሆን…” ያላችሁት ነገር በስምንተኛው ቀን ሲገለባበጥ ስታዩ የምር የቀረቻችሁ እንጥፈጣፊ ተስፋ ‘ዜሮ ባላንስ’ ነገር ትሆናለች፡፡ ዛሬ የሄዳችሁበት መሥሪያ ቤት የዛሬ ሳምንት ስትመለሱ የአዳዲስ መመሪያ መአት ግድግዳውን አዥጎርጉሮት ታገኛላችሁ፡፡ ቀደም ያሉት መመሪያዎች እኮ በመስክ ጥናት፣ በውጪ አገር የልምድ ልውውጥ፣ በወርክሾፕ ምናምን ዳብረው የወጡ ናቸው እየተባላችሁ በኮክቴል ግብዣ በሚጠናቀቁ ስብሰባዎች ላይ ሲነገራችሁ ከርሟል!

ስሙኝማ…ነገሬ ብላችሁ እንደሆነ የተለመደች ነገር ምን አለች መሰላችሁ…በወረቀት ላይ ማቀድ፡፡ “በዘንድሮ ዓመት አንድ ሚሊዮን ብር ለማስገባት እቅድ ተይዟል…” ያለው መሥሪያ ቤት ልክ የዛሬ ዓመት የአንድ ሚሊዮን ብሩ ዕቅድ ለምን መቶ ሦስት ሺህ ብር ላይ እንደቆመ ለማስረዳት ሌላ ስብሰባ ይጠራል፡፡ እኛም ‘ዘጋቢዎች’ እንሄድና ቢያንስ ‘ቦትልድ ወተር’ ግጥም አድርገን እንመለሳለን፡፡ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሀሳብ አለንማ… “በሚቀጥለው ዓመት መሥሪያ ቤታችን በተገልጋዮች ላይ የሚያደርስውን መጉላላት አሁን ካለበት ዘጠና አምስት በመቶ ወደ ሰባ ሦስት በመቶ ለመቀነስ ዕቅድ ተይዟል ምናምን ይባልልን፡፡ ልክ ነዋ… ሁሉም ነገሩ ሁሉ ለትዳር ሳይሆን ለአዳር እየሆነ መጫወቻ እየሆንን ነዋ! (የምር ግን…ስሙኝማ፣ በተከታዩ ዓመት ክፋትን አሁን ካለበት ዘጠና ሰባት ከመቶ ወደ ሃምሳ አምስት ከመቶ ለማውረድ እየተሠራ ነው…ምናምን የሚባል ነገር ቢኖር እንዴት አሪፍ ይሆን ነበር!)እናላችሁ…በ‘ናፍቆት ስትጠብቁት’ የከረማችሁት የምናምን መቶኛ ዕቅድ ውሀ በልቶት ምክንያት ድርደራ የሚመጣው ከዘለቄታዊ ጥቅም ይልቅ…አለ አይደል… በባንዲራና በመፈክር በተንቆጠቆጠ አዳራሽ የሚቀርብ ሪፖርትና የቲቪ ካሜራ እየታሰበ ነው፡፡እኔ የምለው…የፍቆት ነገር ከተነሳ አይቀር… የማናውቀውን ነገር መናፈቃችን ለአንዳንዶቻችን የሚታየንው እንዴት ነው! “በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው የ ሽንጡ ዘ ዶሮማነቂያልብአንጠልጣይ የፍቅር ፊልም ይመረቃል…” ምናምን የሚባለው፣ አይደለም ፊልሙን…ሽንጡ ዘ ዶሮማነቂያ ማነው! ኮሚክ እኮ ነው…ዘንድሮማ የምርት ስም ሁሉ እየተጠቀሰ ‘በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው ምናምን ገበያ ላይ ውሏል…” አይነት ነገር በሽ በሽ ሆኗል፡፡ አይደለም እኛ… የፋብሪካው ባለ አክስዮኖችም ስለ ምርቱ ሰምተው አያውቁም ይሆናል!እናማ…እኛም ነገርዬው ሁሉ ለአዳር ብቻ ሲሆን ከሰው ለመቀላቀል አብረን እናጨበጭባለን፡፡ ስለማጨብጨብ ካነሳን አይቀር… ቀሺም ትያትር ነው አሉ.፡፡ እናላችሁ…ሁለቱ ጓደኛሞች እያዩ እያለ አንደኛው መዳፎቹ የዝንጀሮ እንትን እስኪመስሉ ድረስ ያጨበጭባል፡፡ ጓደኝዬውም “ለዚህ ቀሺም ትያትር እንዲህ ታጨበጭባለህ?” ቢለው ምን ብሎ ቢመለስለት ጥሩ ነው…“ሞኞ፣ የማጨበጭበው እንቅልፍ እንዳይወስደኝ ብዬ ነው…” እናማ… በየአዳራሹ ነገሩ ሁሉ ለአዳር ሲሆን የምናጨበጭበው በድራማው እርፍና ሳይሆን እንቅልፍ እንዳይወስደን ሊሆን እንደሚችል ይታወቅልንማ!እናማ የቪያግራን ያለ ሀኪም ትእዛዝ ገበያ መድራት ስናይ...የ‘ሴክስ ኤንድ ዘ ሲቲ’ ነገር የት

እንደሚያደርሰን እግዜሐር ይወቀው የሚያሰኝ ነው፡፡ (እነ እትና…ይሄንንም ዘመናዊነት ነው ምናምን በሉና!) ደግሞ እየተለመደ ያለ ምን አለ መሰላችሁ…እንደ ‘ፈረንጆቹ’ አገር እዚህም ‘ነገርየው’ በስልክ ሁሉ ተጀምሯል አሉ፡፡ የምር…ይቺ ከተማ… ‘ኤ ቴል ኦፍ ምናምን…’ የሚል ልዩ መጽሐፍ ያስፈልጋታል፡፡ እኛ “መስመሮች በሙሉ ተይዘዋል…” ምናምን ሲባል ሰዋችን ስለ አውሮፓ የገንዘብ ቀውስ ምናምን ምክክር የያዘ የሚመስለን ለካስ ነገርየው ሌላ ነው!እናማ ስልክ ተደውሎ በስህተት እንኳን የሆነ ሰው ‘ዋይፍ’ ብታነሳው ይቅርታ ብሎ መዝጋት ቅሽምና የሚሆንበት ዘመን እየቀረበ ነው፡፡ “ምን መሰለሽ…” ምናምን ብሎ ይጀመራል አሉ፡፡ ከዛማ ደረጃ

በደረጃ ጨዋታው ይቀጥላል፡፡

“የለበስሽው እንትን ስስ ነው?”

“አዎ፣ በጣም ስስ ነው፡፡”

“ቀለሙ ምን አይነት ነው?”

“ደማቅ ቀይ ነው…አሁን ወደ ሻወር ልገባ ስለሆነ እያወለቅሁት ነው…”  ምናምን እየተባለ ነገርዬው በስልክ ተጀምሮ በስልክ ይጨረሳል አሉ፡፡ (እነ እንትና…ኮንግራ! ‘በየጊዜው እያሻቀበ’ ለሄደው የ‘ቤድ’ ዋጋ መፍትሄ ተገኝቷል! ደግሞ በደረቅ ሌሊት መለፍለፍ ስለሌለ ጎረቤትም አይረበሽም! ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ…ለቁም ነገር ስንፈልገው አልገኝ እያለ በንዴት የሚያጦዘን ስልክ ለ‘ሴክስ ኤንድ ዘ ሲቲ’ አሪፍ ሆኖላችኋል፡፡ “ባሌ ድንገት በሩን በርግዶ ቢገባስ!” የለ፡፡ “ገርል ፍሬንዴ እጅ ከፍንጅ ብትይዘኝስ!” የለ፡፡ “እንትናዬህን ጉዱ ካሳን ከሚመስል ሰው ጋር አየኋት…” ብሎ የሚያሳብቅ የለ…“”ሀሎ!” ማለት ብቻ ነው፡፡ስሙኝማ…ይሄን ጉዳይ ካነሳን አይቀር…ነገርየው እኮ ከማስገረምም እያለፈ ነው፡፡ ልክ ነዋ…አንዳንዶችን “ሴት ልጅ አትስጠኝ” እስከ ማለት የሚያስደርሳቸው እኮ የተሲያት እንትን አጠናፍሯቸው ሳይሆን… እየሆነ ያለውን ነገር ሲሰሙ ነው፡፡ህብረተሰብን ማክበር፣ ህብረተሰብ ለሚሰጠው አስተያየት ጀርባ ማዞር ሲመጣ…ፍሬን ተበጠሰ ማለትም አይደል! እናማ ፍሬን ተበጥሶብናል፡፡ ድሮ እኮ “የዕድራችን ፀሀፊ ድንገት ቢያዩስ…” “የመሥሪያ ቤት ባልደረባ ድንገት ከች ቢልስ…” “ከፊዚክስ አስተማሪ ጋር ፊት ለፊት ብገጣጠምስ…”

እየተባለ ‘ነገርየውን ለማግኘት’ ከአጠና ተራ ወደ ካራ፣ ከሹሮ ሜዳ ወደ ብስራተ ገብርኤል፣ ከአዲሱ ገበያ ወደ ቃሊቲ ፍተሻ አካባቢ በአውቶብስም በምንም ተብሎ ይኬድ ነበር፡፡ እሱ ሁሉ ቀረላችሁና ‘ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ’ ሆኖ አረፈው፡፡እኔ የምለው…የምር እንናገር ከተባለ “የተፈጠረው እኮ ተከርችሞ ሊቀመጥ አይደለም…” እየተባለ ሚጢጢዎቹ ህጻናት ሁሉ ‘ዕለታዊ ተግባር’ አይነት ነገር ሲያደርጉት “ኧረ ይሄ ነገር ቆይቶ አገር ያፈርሳል!” የሚል መጥፋቱ አያሳስባችሁም! እኔ የምለው…ያለ ሥራ ቢቀመጥ ብል የሚበላው ነገር ያለ ይመስል የምናምን ‘ዝክር’  አታስመስሉታ!ደግሞላችሁ… ትንሽ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ በአንዳንድ ሰው በማይበዛባቸው አካባቢዎች ደገፍ መባያ ግንብ ከተገኘ በቃ…‘ኖ ፕሮብሌማ’ ነው አሉ፡፡ እናማ ድንገት ሰው እንኳን ቢደርስ…ነገሬ የሚለው የለም አሉ፡፡ የምንሰማው ሁሉ የማንነገረው ሆኖብን እንጂ በብዙ ቦታ ቡሎኖች ላልተው እየወለቁ ስለሆነ የጠጋኝ ያለህ እያልን ነው፡፡ከ‘አዳርና ከትዳር’ ለአገርና ለህዝብ የሚበጀውን መክረን፣ ዘክረን መፍትሄ ለማምጣት ፍላጎቱም ዝግጁነቱም ከሌለን… አለ አይደል… ጦር ሰብቆ ከመጣው ደርቡሽ የምንለየው በፓስፖርት ቀለም ብቻ ይሆናል፡፡ (በዛ ዘመን ፓስፖርት ነበር እንዴ!)

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

 

 

 

 

Read 15491 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 12:06