Saturday, 23 June 2012 07:42

የድሬዳዋ የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

“የሐረር መፋቂያ ጥርስ ያነጣል አሉ

ደብዳቤ ላኪልኝ ለሚመጣው ሁሉ”

የዚህ ስንኝ የመጀመሪያውና ሁለተኛው መስመር ምን አገናኛቸው ብዬ መገረሜ ባይቀርም፤ የሐረር መፋቂያ ጥርስ ማንጣቱ የማይካድ ይመስለኛል፡፡ ያፈቀራት የሐረር ሴት በየጊዜው ደብዳቤ ብትልክለትና ቢያነብ አለመሰልቸቱ የትኩስ ፍቅረኛ ወግ መሆኑ ባያጠያይቅም፤ የሚመጣው የሐረር ሰው ሁሉ ደብዳቤ እሺ ብሎ ለሱ ማምጣቱ ግን “ወይ ደግ ጊዜ?” ሳያሰኝ አይቀርም፡፡ የሐረር ሰው ደግ መሆኑን ግን ያመላክታል፡፡ ዞሮ ዞሮ የፍቅሩን ጥንካሬ በሐረር መፋቂያ አስታኮ ዘፍኗል - ያ አፍቃሪ፡፡ ልብ ብላችሁ እንደሆነ ሐረር - ድሬዳዋ ደረስ ብዬ መጣሁ የሚሉ ሰዎች ከሁለቱ ከተሞች ዝምድና ይሁን ከጂኦግራፊያዊ ቀረቤታቸው ባይታወቅም፤ እንደ ስምና ያባት ስም ሳይለዩ ነው የሚጠሯቸው፡፡

ድሬዳዋን እንደዛሬ ባጃጅ ሳይወራት ነው የማቃት - ፔጆ ታክሲ ሳለ፡፡ ሙቀቷ እንዳሁኑ 39-40oc ሳይደርስ - በልጅነቷ ነው የማውቃት፡፡ እጅግ ሞቃ ሳትለበልብ፣ ብዙ ሹም ሳይቀያየርባት - በ1960ዎቹ መጨረሻ፡፡ ዛሬ አየሯ ያቃጥላል - ይወብቃል - ላዲሳባ ሰው ይከብዳል፡፡ ናዝሬት ተወልጄ ክርስትና የተነሳሁት ሐረር ቁልቢ ገብርኤል መሆኑን አባቴ በማይጠፋውና በማይታጠፈው ዳዊቱ ሽፋን ላይ በውስጥ በኩል ፅፎታል! የዛሬ 57 ዓመት ገደማ በድሬ ላይ በአንቀልባ ታዝዬ አልፌያለሁ ማለት ነው፡፡ ያኔ ድሬ ነፋሻ፣ ቆንጅዬ፣ የአትክልትና የፍቅር አገር መሆኗን እናቴም አድንቃ ነግራኛለች፡፡ የድሬዳዋ ሰው ፀባይ ግን እንዳየሯ አልተለወጠም፡፡ እንደጋራው ጐርፍ አልሸረሸረውም! ጊዜ፣ እንደድህነት፣ ድንቅ ባህሪውን አላራቆተውም፡፡

የድሬዳዋ ሰው ግልፅ ነው ሲባል እሰማለሁ፡፡ ፊት ለፊት ተናጋሪ ነው ሲባልም ሰምቻለሁ፡፡ አንዳንድ አዲሳባ የመጡ የድሬዳዋ ልጆች ወዳጆቼ እነዚህ ፀባዮች ሲንፀባረቁባቸው አስተውያለሁ፡፡ ስድብ እንደ ሰላምታ የሚቆጠርለት ሰው የድሬ ሰው ነው፡፡ ነገር አያካብድም፡፡

እንደዛሬ ባቡር ሳያንቀልፋ ይዤ ከተፍ እያለ ወደ አዲሳባ ሲመጣ የድሬን ኮንትሮባንድ ሸቀጥ በብስክሌት እንደሰርከስ በሚያስገርም ቅብብሎሽ ተሸክመው ከሚበኑባት ናዝሬት፤ ሙልሙል እስከሚሸጥባት ዱከም ድረስ፤ ይሄው መንፈስ በሚነፍስበት ዘመን፤ የድሬዳዋ ሽታና የድሬዳዋ ፀባይ፤ ሐዲድ ተከትሎ በመፍሰስ ባህላዊ ተጋቦትን እያጋባ መቀጠሉን አስተውያለሁ፡፡

የባቡር ነገር ካነሳሁ አይቀር፤ አዶልፍ ፓርለሳክ የተባለው የቼክ ፀሐፊ፤ “የሀበሻ ጀብዱ” በተባለው መፅሐፉ ላይ ስለባቡር የፃፈውን ሃሳብ ተጫነ ጃብሬ መኮንን ተርጉሞ ባሳየኝ መሰረት የጣመኝን ፍሬ ሃሳብ ላካፍላችሁ፡፡

“ድሬዳዋ የብረቱ አውራሪስ” ይላል ምዕራፉ፡፡

…አዎ የባቡር መንገድና ባቡር ባይኖር ኖሮ ዛሬ የመላው ዓለም ህዝብ ይኼን ያህል ባልተቀራረበና ባልተዋወቀ ነበር፤ ባቡር ባይኖር ኖሮ ዛሬ ከደረስንበት የስልጣኔ ደረጃ ላይ ባልደረስን ነበር፤ ባቡር ባይኖር ኖሮ በሌላው በሞቃቱ የዓለም ክፍል የሚበቅሉትን ፍራፍሬዎችን እንኳን ሳይቀር ለመብላት ባልቻልን ነበር፤ ባቡር ባይኖር ኖሮ በመላው ዓለም የሚኖሩትን ህዝቦች ባህል፣ ሃይማኖትና አኗኗር ባላወቅን ነበር፡፡ አዎ እነዚህ ዕድሜ ልካቸውን እንዳይነጣጠሉ ሆነው ጐን ለጐን የተዘረጉ ሁለት ጠፍጣፋ ብረቶች የዓለምን ህዝብ አገናኝተውታል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

ከጅቡቲ እስከ ድሬዳዋ ድረስ ባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች “ፈረስ አል ሼይጣን”፤ በብረት ላይ የሚሄድ የሰይጣን ፈረስ ይሉታል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ባቡር እንደማንኛውም የቤት እንስሳ ማለትም አህያ፣ ፈረስ፣ ግመልና በቅሎ ሁሉ ፍጡር ነው፡፡ በሳርና በቅጠል ፈንታ ከሰል በልቶ ውሃ ጠጥቶ እንፋሎት የሚተፋ፤ በሁለት ብረቶች ላይ የሚጋልብ፣ መንፈስ ያለፈ ፍጡር፣ የሰይጣን ፈረስ ነው፡፡ “ሁሉም መንገዶች ወደ ሮማ ይወስዳሉ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚወስደው መንገድ ግን አንድ ብቻ ነው፡፡ ያቺም መንገድ ይቺ የባቡር ሃዲድ ብቻ ነች”…

እንደ ድሬዳዋ ጨርቅ የሰው ፀባይ ዥጉርጉር አለመሆኑ ምናልባት የንግድ መናኸሪያነቷ በቀላሉ የመግባባት ባህልን አጐናፅፎት ይሆን? እያልኩ ጠይቃለሁ፡፡ አንድ የድሬ ወዳጄ ለምን እንዲህ ሆነ? ለምን ፀባዩ እንዲያ አልሆነም?” እያልኩ ስጨቀጭቀው፤ “ወለበላ! አቦ አትመራመርብና? ወስዋስ ምን ያረግልሃል ሳ?!” ብሎኝ፣ አሁን እንኳን ይሄን ፅሁፍ ስፅፍ ትዝ እያለኝ ፈገግ እላለሁ፡፡ የድሬ ሰው ነገር ማካበድ አይወድም! የሚሉት እውነት ነው፡፡ ቅልል ያለ፣ ለመግባባት የማያስቸግር ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ድሬዳዋ ሄጄ ያየሁት ግን ከማውቀው በላይ ነው፡፡ “የድሬዳዋ ሰው ለካ ከማውቀው በላይ ነው!” ብዬ ለወዳጆቼ ነግሬአለሁ፡፡

“ለምን?” አሉኝ፡፡ እንደዚህ መለስኩ:-

“አርብ ማለዳ 12 ሰዓት ከሩብ፡፡ ከእየሩሳሌም የሕፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአቶ ሙሉጌታ ገብሩ ጋር ተቃጥረን፤ በሰዓቱ ደርሼ እየጠበኩት ነበር፡፡ የምጠብቀው ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፊት ለፊት ነው - ካዛንቺስ፡፡ እንደተለመደው ወደ ዐረብ አገር ለመሄድ የሚርመሰመሱት እህቶቻችን ዛሬም አገር ምድሩን አጣበውታል፡፡ ፎቶ ኮፒ ያስነሳሉ፡፡ ይጠያየቃሉ፡፡ ፓስፖርት ያገላብጣሉ፡፡ As a blessing in disguise (አበሻ ሳይደግስ አይጣላም እንደሚለው) ትኩስ ሻይና ቡና አዘጋጅተው ከንጋቱ በ11 ሰዓት ከች የሚሉት ታታሪ ሴቶች፤ ዱሮ ጃፓን የምንለውን ብስኩት፤ ዛሬ እንደዘመኑ ፈቃድ በአምባሻ አጅበው ለሳውዲ ተጓዦች እየሸቀሉ ቢዝነሳቸውን ያጧጡፋሉ፡፡ ወይ አገራችን! እያልኩ አንዴ እሰይ! አንዴ ውይ! እያልኩ፤ ፀጋዬ ገ/መድህን ስለ አባይ ሲፅፍ

“እዚህ ደማም፣

እዚያ ተማም!” ያለውን በሀዘንና በምፀት አስታውሼ አንዲት ግጥም ጫርኩኝ!

 

ብቻ ይሰውርህ በሉኝ!

ህጋዊ ስደት ሆነና

የህጋዊ ባርነት ፋና

አገሬ ልጆቿን ስትሸኝ

የዋኔ ዐይኔ አስተዋለና

አገር እያለ አገር ሲታጣ… ደሀ ልብ ሲያጣ ሲነጣ

በእግር ላይ እግር አብቅለን

አገር ፍለጋ አገር ጥለን

ለዚያው ላንድ ሆድ ልዕልና

ገድለን አንዳች ህልውና

ይኸው ጐህ ሲቀድ ነቅተን

አገር ላገር እንዞራለን!

ብቻ ይሰውርህ በሉኝ፣ ከክፉ ዘመን ዕጣ ፍርድ

ልጆቼን ልፈልግ ብላ፣ አገሬም ጥላኝ እንዳትሄድ!

(ለሠራተኛና ማህበራዊ መ/ቤት፤ ለስደት ዘማቾችና ለድሬዳዋ ልማት)

8/10/04

ሥራ አስኪያጁ ወዳጄ ጥቂት ዘግይቶ ደረሰ፡፡ ገና የመኪናውን በር ከፍቼ ስገባ፤ የፍርድ ቤት መጥሪያ ሳይደርሰው መልስ እንደሚሰጥ ተከሳሽ፤ “ምን ሆኖ መሰለህ የዘገየሁት? መንገዴ ላይ አንድ ሚኒባስና ሀይገር ተጋጭተው ሲጨቃጨቁ በየት እንለፍ? እዚህ አገር ግጭቱ በዝቷል!” አለ፡የሳይጂን አሰፋ መዝገቡ ጆሮ አይስማ፣ አልኩኝ በሆዴ!

ትንሹንም ትልቁንም የሀገር ጉዳይ እያወጋን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደረስን! ትኬቴን ሰጠኝ - አየሁት፡፡ ወደ ውስጥ መግቢያው (check in) 1፡15 ነው፡ በረራው ሁለት ሰዓት ላይ ነው፡፡ ወደ ድሬዳዋ የሚወስደን ወደ ጂጂጋ የሚዘልቀው አውሮፕላን ነው፡፡ ወደ ጂጂጋ ከሚዘልቁት ሰዎች መካከል የማዕከላዊ እሥር ቤት ወዳጄን ማህተመን አገኘሁት፡፡ ከተገናኘን ቆይተናል፡፡ ዱሮ እሥር፣ ዛሬ ጉዞ አገናኘን፡፡ እስከድሬዳዋ አብረን በረርን፡፡ አውሮፕላን ላይ አንድ ቁርስ የሚመስል ቁርስ አብልተውናል፡፡ (ምንነቱን ለምግብ ተመራማሪዎች ብተወው ይሻላል)

ከመነሻችን ዘግይተን ነው የተነሳነው፡፡ ግን በጣም አይደለም (ዱሮ EAL (Ethiopian Air Line) የሚለውን እንግሊዞች አህፅሮተ - ቃሉን ሲፈቱት - Ethiopians Always Late እያሉ (አበሻ ሁሌ ወደኋላ መዘግየት ማለት ነው) ይዘባበቱብን ነበር፡፡ መልስ የማያጣው አበሻ ታዲያ የእንግሊዝ አውሮፕላንን አህፅሮተ- ቃሉን BOAC ሲፈታው Better On A Camel [ከእናንተስ በግመል መሄድ ይሻላል! እንደማለት ነው] ይል ነበር!)

በ3፡30 ድሬዳዋ ገባን፡፡ ድሬዳዋ መሞቅና መወበቅ ጀምራለች፡፡

የድርጅቱ ንቁና ደግ ሁለ-ገብ ሾፌር አውሮፕላን ማረፊያው ደጃፍ ይጠብቀን ነበረና ሻንጣችንን ተቀብሎ አስገባ፡፡

ወደ ሆቴል ሾፈረን፡፡ ራስ ሆቴል ገባን - የጥንቱ የጠዋቱ ሆቴል! አልኩኝ በሆዴ፡፡ የዛሬው ድህነት በጣም ስለከፋ ነው መሰለኝ፤ ፈርዶብኝ የጥንት ነገር ሳይ ሆዴ ይባባል! አንድ ጊዜ በሰለጠነችው፣ የአውሮፓ ፓርላማ መቀመጫ በሆነችው ቤልጅየም ዋና ከተማ ብራሰልስ ለጉብኝት አንድ አራት ጋዜጠኞች ሄደን ነበር (አንዱ እዚያው ቀረ መሰለኝ - የቤልጅየም ፖሊስ ይጭነቀው) ታዲያ የተለያዩ ቦታዎችን እያየን ሳለ፤ ድንገት የጥንቱ የጠዋቱ ኮሙኒስት ማኒፌስቶ የተፃፈበትን ቤት፤ ህንፃ አየን፡፡ እኔና አቶ አማረ አረጋዊ (የሪፖርተር አዘጋጅ) ህንፃው ፊት ለፊት ተገትረን ቀረን፡፡ የአማረን አላቅም፣ እኔ ግን እንባዬ ቀረረ - አይ የልጅነት ፍቅር?! አልኩ፡፡ በኋላ የMeet ETVው ተፈራ ገዳሙ ስንዘገይበት መገተራችንን አይቶ ኖሮ፤

“እናንተ አጁዛዎች! ለዚህ ይሄን ያህል ትቆማላችሁ?” ብሎ ተረበን፡፡

ቀልደኛውና ፌዘኛው አማረ ሲመልስለት፤

“ሽንት የሚሸና ህፃን ልጅ ለማየት ምን ያስቸኩለናል - ከዛ ይሄ አይሻልም?” አለው፡፡ በቤልጂየም እንደ ታሪክ የሚቆጥሩትን፣ ሽንቱን የሚሸና ህፃን ልጅ ሐውልት፣ ቀጥሎ ስለምንጐበኝ ነው - አማረ እንደዛ ያለው፡፡

ራስ ሆቴል የጥንት ትዝታዬ ነው፡፡ ዱሮ ያራዳ ልጅ ሲፎክር “ዋ! እንደራስ ሆቴል በር ነው የማሽከረክርህ!” ይል ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አንድ ወዳጄ ሲያጫውተኝ “አንዱ ማታ ሰክሮ ወዳድቆ ፊቱ እዚህም እዚያም ተገጣጥቦ መስሪያ ቤት ሲመጣ እስካፍንጫው ድረስ ባርሜጣውን ደፍቷል፡፡ አለቃው “ባርኔጣህን አውልቀው እንጂ?” አለው ቢሮው ሲገባ፡፡ አወለቀው፡፡ አለቃው ያን ፊቱን ቆሳስሎ አየና፤

“አንተ ምን ሆነህ ነው?” አለው በድንጋጤ፡፡

“በር ገጭቶኝ ነው!” አለ ግጥብጥቡ

“እ?! በር?! የራስ ሆቴል በር ነው እንዴ የገጨህ?” አለውና ተሳሳቁ!

ድሬዳዋ ራስ ሆቴል የታደሰ ይመስላል፡ ዋጋው ግን አለቅጥ ንሮ አስደንግጦናል! እንደውም ወዳጄ “ለሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ መንገር አለብን!” አለ፡፡

ሆቴል ግማሽ ሰዓት ያህል ቆይተን ወደ ኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ቢሮ ሄድን፡፡ ሥራ አስኪያጁ ከሠራተኞቹ እያስተዋወቀኝ ሲስተር ትዕግሥት ቢሮ ገባን፡፡ ሲስተርን ከዚህ ቀደም አግኝቻታለሁ፡፡ ሲስተር ትዕግሥት ትጉህ ሠራተኛነቷንና ቀናነቷን፣ እንዲሁም ለምትናገረው ሁሉ ታማኝ መሆኗን፣ የሚያሳብቅ ፊት ያላት፤ ቆፍጣና ሴት ናት፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ የሚለው ተረት ምን ያደርጋል? አልኩ በሆዴ፡፡ ምክንያቱም ፍትፍቱ ፊቷ ላይ ነው ያለው፡፡

“ነቢይ የሚፈልገውን አነጋግሪው” አላት ሥራ አስኪያጁ፡፡

“የነገው ፕሮግራም እየተዘጋጀ ነው፡፡ እሱን ይዘን ብንነጋገር ይሻላል” አለች፡፡ እምቢ በማይባል ፈጋግ ፊት፡፡ “ዶሮው እየበሰለ ነው ዞር ዞር በሉና ኑዋ” እንደምትል የቤት እመቤት ስሜት ነው ቃናዋን ያነበብኩት፡፡

“እንግዲያው የቲቶሪያሉን ክፍሎችና ሰርቶ ማሳያ ጣቢያውን ከነከብት እርባታው ጐብኝተን እንመለሳለን” አለና ሥራ አስኪያጁ ወደዚያው አመራን፡፡ ይሄ ድርጅት በእንግሊዝኛው Jerusalem Children and Community Development Organization ወይም በአህፅሮተ ቃሉ Jeccdo የሚባል ሲሆን ድሬዳዋ ውስጥ ተአምራዊ ለውጥ እያመጣ ያለ ድርጅት ነው ቢባል አንዳችም ግነት የለውም! በዐይኔ የጐበኘሁትና በአዕምሮዬ ያተምኩት ይህን ይመሰክራል፡፡

የመደበኛ ት/ቤቶች ማገዣ የሆነው የቱቶሪያል ፕሮግራም የሚተገበርባቸውን ክፍሎች ጐብኝተን ስናበቃ፣ ሀዲድ ሀዲዱን ይዘን ጥግ ጥጉን ሽቅብ ሄደን፣ ሀዲዱን አቋርጠን ጋራው ሥር ወዳለው ሠርቶ ማሳያ ጣቢያና ከብት እርባታ ገባን፡፡

የላሞቹ ማማር፣ የሚሰጡት የዕለት ወተት ብዛት፤ የመኖው አዘገጃጀት (የጋራውን ጐርፍ ለመከላከል የተተከለው ሳር አድጐ ታጭዶ መኖ በመሆን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ተገሏል) የጥጆቹ ተስፋ ሰጪ ቁመና፣ ግቢው ውስጥ ያለው አትክልት… የሰርቶ ማሳያው የርሻ መደብ በተለያዩ ኃይል ሰጪ አትክልቶች ጢም ማለት፤ በተለይ ካሣቫ የሚባል በብዛትና እንደ ልብ የሚበቅል እንደመጣጢሽ ወደ መሬት የሚበቅል ተክል (አራት አመት የሚቆይ፤ ከአንዱ ሄክታር እስከ 250 ኩንታል የሚሰጥ እንደ እንጀራ፣ ገንፎ ወዘተ አሥር የምግብ አይነት ሊሆን የሚችል)፣ እንደማንጐ፣ መንደሪን፣ ያሉ የሚበቅሉበት እጅግ የሚያስደንቅ ቦታ ከጋራው ሥር ውሃ ተቆፍሮ ፓምፕ ተደርጐበት የሚለማ ህይወት፤ በእውነት ፍቅር ያስይዛል፡፡ ምነው ያ ተሾመ ምትኩ -

“በእጆቼ እየዳሰስኩ እንዳላጫውትሽ

ጋራ ስር ነው ቤትሽ” ያለው ለዚህ በሆነ ያሰኛል፡፡ ምነው ኦሮምኛ በቻልኩና ተርጉሜ ለነዚህ ቀናና ታከተኝ፣ ሰለቸኝ የማይሉ፣ ሰውን ከነሙሉ ክብሩ የሚቀበሉ ከብት-አርቢና አትክልተኛ ገበሬዎች በሰጠኋቸው አልኩኝ፡፡

ጉብኝታችንን ጨርሰን ወደ ዋናው ጉዳይ ማለትም የፕሮግራም ቅደም-ተከተልና ሲስተር ትዕግሥትን ወደማነጋገር ሄድን፡፡

የፕሮግራሙ ዝርዝር ተዘጋጅቷል፡፡ ተሰጠን ርዕሱ “በየኢየሩሳሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት (ኢህማልድ) እና በጐሮና ቡቲጂ ሁለገብ ኃ/የተ/ኅ/ሥ/ማህበር መሀከል የሚደረግ የፕሮጀክት ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ፕሮግራም - ሰኔ 09-2004 ጐሮ ቡቲጂ ድሬዳዋ” ይላል፡፡

“ጄክዶን በሚመለከት ነቢይ የሚጠይቅሽ ካለ እንይ” አለ ሥራ አስኪያጁ፡፡

ጥያቄ ጀመርኩ፡፡

“የእየሩሳሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት ዋና ዒላማ በከተማ ውስጥ ያሉ እጅግ የተጐዱና የተጐሳቆሉ፣ ውሃ ያጡ፣ ትምርት ያጡ፤ ጤና ተቋም የሌላቸው ማ/ሰቦች መኖሪያዎች ናቸው” ትላለች ሲሰተር፡፡ “አስቀድመን ፕሮግራሙን የማስተዋወቅ ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ ከዚያ ችግሮቹን መለየት፣ ፕሮጀክት መቅረፅ፤ የተቀረፀው ፕሮጀክት ከህዝቡ ችግር ጋር መጣጣሙን ማረጋገጥና ተጠቃሚው ህዝብ በሙሉ ፈቃደኝነት ፕሮጀክቱን ለማቀፍና ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ማየት፤ ከዚየም የማስተባበርና የማቀናጀት ሥራውን መቀጠል፤ ጉልበት እነዲፈጥር ማድረግ ነው፡፡”

“ህዝቡ ፕሮጀክቱን መቀበሉን ማረጋገጥ፣ ባለቤትነቱን ማረጋገጥ ነወይ?” ብዬ ጠየቋት፡፡

“ከህዝቡ ከራሱ የሚመረጥ ማህበር አለ፡፡ ይህ ማህበር የተጠናከረና ፕሮጀክቱን ለመሸከም ብቃት ያለው ነው! ህዝቡ ያምነዋል፡፡ እንቅፋት የሚሆን አባል ካጋጠመው ደግሞ በደምብ ተከታትሎ እስከማባረር ድረስ እርምጃ ይወስዳል፡፡ ሲወስድም ታይቷል፤ ማህበሩ ከኛ ጋር አብሮን ይሰራል፡፡ ሙሉ በሙሉ ራሱን ሲችልና ህዝቡን የመምራት አቅም እንዳለው ሰናረጋገጥ፤ ለምሳሌ ነገ እንደምናደርገው፤ በድርጅታችንና በጐሮ ቡቲጂ መካከል የሚደረግ  የርክክብ ሥነ ስርዓት ይካሄዳል፡፡ ከዚያ እኛ ከዚያ ማ/ሰብ እንወጣና ወደ ሌላ ችግር ወዳለበት ማ/ሰብ እንሄዳለን፡፡

“ያ ማለት ምን ማለት ነው?” አልኳት፡፡

“ለህዝቡ ባለቤትነት ሰጠን ማለት ነዋ!”

“ማን ይቆጣጠረዋል ማህበሩን?”

“በወሳኝነት ህዝቡ አለ፡፡ መንግሥትና ለጋሽ ድርጅቶችም ይከታተሉታል”

“ከምር ባለቤትነቱን ይቀበሉታል?”

“እንዴታ! ሥራ ከመጀመራችን በፊት ለረዥም ጊዜ የአዕምሮ ለውጥ እንዲያመጣ (Pattitude ለውጥ) በጣም አጥብቀን እንሠራለን ያልኩህ ለዚያ ነው፡፡ የማይታይ ሥራ ነው የሚባለው  Pawareness (ግንዛቤ) ፈጠራ እውነቱን ልንገርህ ለምሳሌ ገንደ-ምስኪን የሚባው ቦታ የነበሩ ሥራ የሌላቸው፣ ጐዳና ተዳዳሪ ወጣቶችና ሴቶች፣ ህፃናት የመጨረሻ ደሀ የሆነ ማ/ሰብ ጋር ሰርተናል፡፡ ዛሬ ስሙ አዲስ ዓለም ተብሏል፡፡ አዲስዓለም ገብቼ ስወጣ እንደምደሰት ምንም አያስደስተኝ!

የእኛን ድርጅት ሀዝቡ “የደሀ ድርጅት” ነው ይለዋል፡፡ የምንሰራው ከደሀው ህዝብ ጋር ነው! የሚፈልገውን እንዲያውቅ እንረዳዋለን፡፡ አውቆም አካባቢውን በባለቤትነት እንዲመራው፣ እንዲጠይቅ ነው፡፡ ለምሳሌ መብራት ይግባልን ብሏል፡፡ በኮብል ስቶን እንሥራ ብሏል፡፡ የቦታ ካርታ ጠይቋል ወዘተ የጋራው፣ የከብቶቹ፣ የት/ቤቱ፣ የጤና ማዕከሉ፣ የመንገድ ደህንነቱ፣ የአካባቢ ጥበቃው ሁሉ ተሳታፊና ባለቤት እንዲሆን ነው አላማችን፡፡ ነገ የሚከበረውን የርክክብ ሥነ ስርዓት ታያለህ ነቢይ፡፡ ለጐሮ ቡቲጂ ሁለገብ የኅ/ሥ ማህበር ድርጅታችን ኃላፊነቱን የሚያስረክብበት ቀን ነው፡፡ የዚህ የባለቤትነት መንፈስ አንዱ ማረጋገጫ ነው!” አለችኝ ሲስተር፤ በመንፈሰ ምሉዕ ቃና፡፡

“በዚህ ሂደት ውስጥ ወጣቱ ይሳተፋል ወይ?” አልኳት፡፡

“በጣም እንጂ! የበጐ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አራማጆች በቅጡ የተደራጁ ወጣቶች አሉ፡፡ ብዙዎቹ ሥራ አግኝተዋል Voluntary Community Development Facilitators ይባላሉ፡፡ ሲስተም ዘርግተን እስከ ኦዲተር ድረስ እውነተኛውን የልማቱን ባለቤት እስክናጠናክር መሬት ወርደን እንሠራለን!” አለችኝ፡፡

ሲስተር ትዕግሥትን አመስግኜ ወጣን፡፡

ወደማታ የድሬዳዋው የእየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ቅርንጫፍ ቢሮ ሥራ አስኪየጅ አቶ አበበ መኮንን ትንሽ አመም አድርጐታል ስላሉን ከዋናው ሥራ አስኪያጅ ጋር ልንጠይቀው ሄድን፡፡ አቤ ወዳጄ ነው፡፡ ሳቂታ፣ ተጨዋች፣ ሰው ወዳጅ፣ አንደበተ-ርቱዕ፣ የማይደክም ሰራተኛ፣ አዋቂና አስተዋይ ሰው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም አግኝቼው ስለሥራው ብዙ አስተዋውቆኛል፡፡ የድሬዳዋ ህዝብ እንዴት እንደሚወደው በዐይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ከህዝብ ጋር እየኖሩ እውነተኛ ልማት ማምጣት ምን ማለት እንደሆነ አሽትቼና ዳስሼ እንዳምን አፈሩ ላይ አስቀምጦ አሳይቶኛል፡፡ አቤ መሬት የቆመ ሰው ነው - Down to earth እንደሚሉት ፈረንጆቹ! አቤ መታመም የለበትም፤ አልኩኝ በሆዴ፡፡

ከተኛበት ተነስቶ አጫወተን፡፡ እኛን ሲያገኝ ኃይል ያገኘ ይመስላል፡፡ የተሻለውም ይመስላል፡፡ ይህን ያነበብኩት ከፎለፎል ባለቤቱና ከሁለት ልጆቹ ፊት ላይ ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ተኝቶ ስለዋለ መነሳቱ በጣም አስደስቷቸዋል፡፡ አጫወተን - ስለትውልድና ስለትውልድ - ዝቅጠት (Generation and degeneration) ስለ በሽታና በገዛ ሰውነታችን የሚሰጠንን መልዕክት ስለ ማዳመጥ፣ ጤናችንን ራሳችን ስለማወካችን (abuse ስለማድረጋችን) ስለ አዲሳባ ወቅታዊ ቀልዶች… ተጨዋወትን፡፡ ቡና ጠጥተን የነገ ሰው ይበለን ተባብለን ተለያየን፡፡

እኔና ሥራ አስኪያጁ ራት ፈላልገን በልተን፣ ጥቂት ተዝናናንና ወደ ሆቴላችን ገባን፡፡

እኔ እንደተለመደው የጉዞ ማስታወሺያዬን ከታትቤ ሳበቃ፤ ወደነገው የህዝብ ባለቤትነት የርክክብ ሥነ ስትዓት ፊቴን አዙሬ ተኛሁ!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 2577 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 10:34