Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 30 June 2012 10:33

ኃይሌ ገ/ስላሴን ቢዝነስ ላማክረው ይሆን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለመሆኑ ኃይሌ ራሱስ ልጆቹን የአማርኛ ቴአትርና ፊልም የት ይሆን የሚያሳያቸው?

“እንዴ አባዬ መሽቷል እኮ?” ስለው “ወንድ አይደለህ?” ያንጠለጠልከው ምናምን ነው? ሂድ ብያለሁ ከበላህም ይብላህ!” አለኝ፡፡ እያለቀስኩ ነው የሄድኩት፡፡ በተለይ ወንዙን ስሻገር እግርና እጄ እየተንቀጠቀጠ በስቃይ ነበር ሞቼ የደረስኩት፡፡ በኋላ ሰውዬው ቤት ደርሼ ስጣራ ተደግናጠው ሁሉም ወጡ፡፡ ምን አደጋ ደረስ ብለው ደነገጡ፡፡ “አባቴ ይህን ስጥ ብሎኝ ነው” አልኳቸው፡፡

ተክሉ ጥላሁን የተባለ ወጣት ፀሃፊ በ1998 ዓ.ም አሳትሞ ለንባብ ካቀረበልን “ከስኬት በስተጀርባ” መፅሃፉ፤ የኃይሌ ገ/ስላሴን የገንዘብ ጥንቁቅነት በተመለከተ ከራሱ ከኃይሌ አንደበት ያደመጠውን እንዲህ ያስነብበናል፡-

አባቴ በገንዘብ ላይ ያለው አመለካከት ጠንከር ያለ ነው፡፡ ሁሌም የሰው አይፈልግም፡ የራሱንም አያስነካም፡፡ አባቴ የአቦ ማህበር ይጠጣ ነበር፡፡ እና ለእዛ የሚከፈለው አንድ ብር ከ5 ሳንቲም ነበር፡፡ አባቴ አንድ ብር ይዞ አምስት ሳንቲም ዝርዝር ያጣል፡፡ አንድ ወዳጁ አቶ ታፈሰ ይባላሉ፤ ከሳቸው አምስት ሳንቲም ይበደርና “በል ጋሼ ያበደርከኝን ሳንቲም ማታ ለልጅ እልክልሀለሁ” ይላል፡፡ “ኧረ ግድ የለም” ብሎ ያበድረዋል፡፡ ያው ማህበሩ ሲያልቅ አባቴ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ይሆናል ይመጣል፡ በኋላ አባቴ ዝርዝር አምስት ሳንቲም ከቤት ሲያገኝ “በል አሁኑኑ ውሰድና ስጥ” ይለኛል፡፡ የአቶ ታፈሰ ቤት ከእኛ ከአምስት ኪሎ ሜትር ያላነሰ ርቀት ያለውና ሁለት ወንዝ ተሻግረህ የምትሄድበትና እጅግ ጅብ የሚበዛበት ነው፡ “እንዴ አባዬ መሽቷል እኮ?” ስለው “ወንድ አይደለህ?” ያንጠለጠልከው ምናምን ነው? ሂድ ብያለሁ ከበላህም ይብላህ!” አለኝ፡፡ እያለቀስኩ ነው የሄድኩት፡፡ በተለይ ወንዙን ስሻገር እግርና እጄ እየተንቀጠቀጠ በስቃይ ነበር ሞቼ የደረስኩት፡፡ በኋላ ሰውዬው ቤት ደርሼ ስጣራ ተደግናጠው ሁሉም ወጡ፡፡ ምን አደጋ ደረስ ብለው ደነገጡ፡፡ “አባቴ ይህን ስጥ ብሎኝ ነው” አልኳቸው፡፡ ተገርመው “አይ የእሱ ነገር መች ይሆን ይህን አቋሙን የሚለውጠው?” አሉኝ፡፡ አሁን ሳድግ ነው ምስጢሩ የገባኝ፤ ያኔ በድርጊቱ እጅግ ተበሳጭቼ ነበር፡፡

ኃይሌ ይህንን አስገራሚ የልጅነት ገጠመኙን ሲነግረን በተመስጦ ሆነን እናዳምጠዋለን፡፡ “ይህ ሰው ለገንዘቡ ጥንቁቅ ቢሆን አይፈረድበትም” ብለንም ድንገት እንፈርድለታለን፡፡ ገንዘቡን የሰራው ላቡን ጠብ አድርጎ፤ ወሽመጡን በጥሶ፤ እግሩ እያነከሰ ባጠቃላይ ከሰውነት ጎዳና ወጥቶ እንደሆነ ስናስብ ደግሞ ይበልጥ ስለጀግንነቱ ለማውራት እንገደዳለን፡፡

ስለዚህ ይህ ሰው ጨምሮ ጨማምሮ ሃብት ይሰጠው ዘንድ መመኘታችን ምንም ሃጢያት የለውም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ፊቱን ከሩጫው ለየት ባሉ አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ (ቢዝነስ) ያዞረ ይመስላል፡፡ ይህም ትክክለኛ ውሳኔ ይመስለኛል፡፡ እኔም ለራሴ ስል ሃይሌ ወደፊት ቢሰራቸው ያልኳቸውን አንዳንድ የቢዝነስ ሃሳቦች ላጋራው ወደድኩ፡፡ ሃሳቦቹን ከወደዳቸው ለአማካሪነቴ ምንም መክፈል ሳይጠበቅበት ወደ ተግባር ሊመነዝራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በኃይሌ በኩል የሚመጣ የትኛውም ዓይነት ጥቅም ለአገርም ጥቅም ይሰጣልና!

ለዓለም አገራት ከውጤታማ ልምዱ ማካፈል

ኃይሌ ንግግር አዋቂ ነው፡፡ በበርካታ የዓለም አገራት በተለይም በዩኒቨርሲቲዎችና በልዩ ልዩ ማሰልጠኛ ተቋማት በመዘዋወር ከሰፊ የስኬትና የፅናት ተሞክሮው እየመዘዘ ንግግር በማድረግ፣ ወጣቶችን ማነቃቃትና ወደ ስኬት መምራት ይችላል፡፡ በወር ውስጥ በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ እንኳን ይህንን ሊያደርግ ቢሞክር ባጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ የገቢ ምንጩን ሊያዳጉስ እንደሚችል ጥርጥር የለኝም፡፡ አንቶኒ ሮቢንሰንና ማይክል ሞሮንን የመሳሰሉ ንግግር አዋቂዎች ስለስኬት ሚስጥር በመተንተን ለንግዱ ማህበረሰብና ለሌሎችም ተቋማት የሚያዘጋጁት አነቃቂ ሴሚናሮች ውጤታቸው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ዓለም ይመሰክራል፡፡ ስለዚህም ኃይሌ በተግባር በተፈተነ የስኬት ልምዱ በርካታ አድናቂዎችን ሊያፈራ እንደሚችል አምናለሁ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስታወቂያ ስራውን ማጠናከር

ኃይሌ ይህንን ሃሳብ አስቀድሞ ያሰበበት ቢመስልም ስራውን ግን ያለአማካሪ ሰርቷል የሚያስብል ስህተት አይቼበታለሁ፡፡ እንደ ምሳሌ ሁለት ማሳያዎችን ልጥቀስ፡፡ አንዱ ከአገር ውጪ፤ ሁለተኛው ደግሞ የአገር ውስጡን፡፡

የውስኪ ማስታወቂያ፡- የስኬት ሚስጥሩን ይናገር፤ ለወጣቶች ዓርዓያነቱን ያሳይ የምንለው ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ስፖርትና አልኮል ፈፅሞ አብረው እንደማይሄዱ እያወቀ  ውስኪ ለማስተዋወቅ መፍቀዱ

የአምቦ ውሃ ማስታወቂያ፡- ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች ኃይሌ አምቦውሃን የሚያስተዋውቅበት ቢልቦርድ ተሰቅሎ ተመልክተናል፡፡ ኃይሌ አምቦውሃን ማስተዋወቁ ክፋት የለውም፡ ቢሆንም ግን በቢልቦርዱ ላይ ያለው ምስል ሃይሌ ነጭ በነጭ የባህል ልብስ እንደለበሰ ጭራ ይዞ ጥሬ ስጋ እየቆረጠ ሲበላ የሚያሳይ ነው፡፡  እንደ ሃይሌ በስፖርቱ ዘርፍ ታዋቂ የሆነ ሰው ባህላዊ እንጂ ሳይንሳዊ ተቀባይነት የሌለውን ጥሬ ስጋ ሲበላ መታየቱ የሚያስነቅፈው ይመስለኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገዱ ዓይነት ማስታወቂያ ደግሞ የሚያስደንቀውና በአገርም በዓለም አቀፍ መድረክም ብዙ ማስታወቂያዎችን የሚያጐርፍለት ነው፡፡ ስለዚህ ሀይሌ ስለሚሰራው ማስታወቂያዎች ባለሙያዎችን እያማከረ በዘርፉ ቢቀጥልበት ምን ያህል አዋጭ እንደሚሆን መገመቱ ከባድ አይሆንም፡፡

የሕፃናት ቴአትር/ፊልም ቤት

ኃይሌ ዓለም ሲኒማን ከከፈተበት ቀን አንስቶ ፊልምን በተመቻቸ ሁኔታ ለማየት የሚያስችለንን ተጨማሪ አቅም ፈጥሮልናል፡፡ ዓለም ሲኒማም በገቢ በኩል የሚታማ አይደለም፡፡

ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት በአገሪቱ ያለውን ብቸኛውን የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር የሚያግዝ ዘመናዊና ሁለገብ የህፃናት ቴአትር/ፊልም ቤት ቢያቋቁምስ? … ውዱ አትሌታችን እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ወላጆች፤ ልጆቻችንን የት ወስደን በኪነ-ጥበብ እንደምናዝናናቸው ግራ ይገባናል፡፡ ስለዚህ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች በዚህ ቢዝነስ መሰማራቱ ገቢን ከማሳደጉም በላይ የወላጆችን ጭንቀት በማቅለሉም ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለመሆኑ ሀይሌ ራሱስ ልጆቹን የአማርኛ ቴአትርና ፊልም የት ይሆን የሚያሳያቸው?

የኃይሌ መፅሃፍና ፊልም

አለም፤ “ከሌላ ፕላኔት የመጣ አትሌት” እያለ የሚያደንቀውን የዚህን ሰው ታሪክ በመፅሃፍ ለማንበብና በፊልም ለማየት መጓተቱ አይቀሬ ነው፡፡ ኃይሌ ከሆሊውድ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከፍተኛ ክፍያ ተከፍሎት ፊልሙ ሊዘጋጅለት እንደዚሁም ስመጥር በሆኑ ደራሲያን ታሪኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ተፅፎ ሊታተምለት ይችላል፡

ይህም ለራሱ ለኃይሌ ታሪክን በዘመናዊ መንገድ ከማቆየትም ባሻገር ገቢ በማስገኘቱም ረገድ ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ እነዚህን የቢዝነስ ሃሳቦች ያቀረብኩት የሀይሌ የቢዝነስ አሰራር ስኬታማ መሆኑን በመረዳቴ እንጂ በዘርፉ ሊቅ ሆኜ አይደለም፡፡ ሃይሌ ሃሳቦቹን አምኖባቸው ከተገበራቸው ግን ተጠቃሚው ራሱ ብቻ ሳይሆን አገርም ነው፡፡ ስለዚህ በርታ እለዋለሁ፡፡

 

 

 

Read 1713 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 13:23