Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 September 2012 09:17

“አንተ”…“አንቺ”…“አንቱ” ማለት ሲቸግር…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

‘ዩ’ የሚለው የፈረንጅ አፍ በአማርኛ ውስጥ ይካተተልንማ! ልክ ነዋ…ተቸገርን እኮ፡፡ “አንተ”፣ “አንቺ”፣ “አንቱ”… ምናምን ድብልቅልቁ ወጥቷል፡፡ ‘ዩ’ ብሎ መገላገል እያለ፡፡ ልክ ነዋ… እነ ‘ዋው’ እንኳን የቋንቋችን አካል ሆነው የለ! (እኔ የምለው ማስታወቂያ የምታሠሩ አምራቾች ወይም አገልግሎት ሰጪዎች ለማስታወቂያ ሠሪዎቹ “‘ዋው’ የሚለውን ቃል ካላስገባህ ኮንትራቱን ሰርዤ ለሌላ ሰው ነው የምሰጠው…” የሚል ግዴታ ታስፈርማላችሁ እንዴ!)

ስለዚህ ለ‘ዋው’ የተፈቀደ በር ለ‘ዩ’ም ይፈቀድልንማ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

‘አዲሱ ዓመት’ እንዴት ይዟችኋልሳ!

መስከረምም ሊገባደድ ነው…ጥቅምትም ሊመጣ ነው፣ ኅዳር ይከተላል…እንዲህ፣ እንዲህ እያለ የጦቢያችን ኑሮ ይሽከረከራል እላችኋለሁ፡፡ ዘንድሮማ… “ብቻ ትንሽ ‘ጨበስ’ የምንልበት ዕድል አመጣልንማ!” እያልን የምንጸልይ ነው የሚመስለው፡፡ በፊት ዝም ብለን እንደ ‘አንድ ሌላ ቀን’ እናያቸው የነበሩት ቀናት ሁሉ አሁን፣ አሁን ባንዲራ እየተሰቀለላቸው፣ “ቡጊ፣ ዉጊ…” እየተባለላቸው…ብቻ የሆኑ ሊገቡን ያልቻሉ ወይም ሊገቡን የማይችሉ ነገሮች በዝተዋል፡፡ የምር እኮ ኮሚክ ነገር ነው… እንደ እኛ ባለች ቺስታ አገር በየምክንያቱ የምናየው ‘እሼሼ ቅዳሜ መቼ ነው ቅዳሜ’ አይነት ፈንጠዝያ…አለ አይደል…ግራ ይገባችኋል፡፡

ይቺን ነገር ስሙኝማ…ሰውየው ጓደኛው ምን ይለዋል መሰላችሁ “ጓደኛህን ላያት እፈልጋለሁ” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም “እሺ ሦስት ፎቶዎቿን እልክልሀለሁ” ይለዋል፡፡ ሰውየውም “ለምንድነው ሦስት ፎቶ የምትልክልኝ?” ብሎ ሲጠይቀው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “ሙሉ ሰውነቷን አንድ ፎቶ ላይ ብቻ ማካተት አይቻልማ!”

እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ ምነዋ ብዙዎቻችን ነገረ ሥራችን ሁሉ መላው ጠፋሳ! የምር…ጠቅላላ ህዝቤ እኮ ከራሱ ለመሸሽ እየተሯሯጠ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ከሩቅ አይቶ “ያቺን ልጅ አካሄዷን አየሀት!”   “አንተ…ባለ ጂንሷን እያትማ፣ እንደ ክሊንት ኢስትዉድ የቴክስ ፊልም በግራና በቀኝ ሁለት ሽጉጥ የታጠቀች ነው እኮ የሚመስለው!” ምናምን መባባል ‘ድሮ’ እየቀረ ነው፡፡(አንዳንዶቻችን የሆነ ነገር “ድሮ ቀረ” ሲባል ለምን እንደማይመቸን ግርም አይላችሁም፡፡) ልክ ነዋ…እንኳን ከርቀት ከቅርብም ማንን “አንተ…” ማንን “አንቺ…” እንደምንል ግራ እየገባን ነዋ!

ለምሳሌ የሆነ ቦታ ላይ አንዲት ዳሌ ምናምን ነገር ያላት ሴትዮ ፊት ለፊታችሁ ሆና ማለፊያ ታጣላችሁ፡፡ (የዘንድሮ እንትናዬዎች እኮ እንኳን ወፍረው ‘ሲምቢሮ’ አክለውም ‘መንገድ መዝጋት’ ይችሉበታል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ እሷዬዋ መንገድ እንዳታሳልፋችሁ…አለ አይደል…ዲፕሎማትነት ነገር እየቃጣችሁ…“የእኔ እህት አንድ ጊዜ ታሳልፊኛለሽ?” ትሏታላችሁ፡፡ ይሄኔላችሁ… የኪንግ ኮንግን ድምጽ በሚያስንቅ አስገመጋሚ ድምጽ “እኔንም አላሳልፍ ብለውኝ ነው…” ስትላችሁ…ይቅርታ…‘ሲላችሁ’ በቃ ድንጋጤ ይሰፍርባችኋል፡፡ ለካስ እሷዬዋ…አለ አይደል… “እሱዬው” ኖሯል!

ሀሳብ አለን፡፡ ‘ዩ’ የሚለው የፈረንጅ አፍ በአማርኛ ውስጥ ይካተተልንማ! ልክ ነዋ…ተቸገርን እኮ፡፡ “አንተ”፣ “አንቺ”፣ “አንቱ”… ምናምን ድብልቅልቁ ወጥቷል፡፡ ‘ዩ’ ብሎ መገላገል እያለ፡፡ ልክ ነዋ… እነ ‘ዋው’ እንኳን የቋንቋችን አካል ሆነው የለ! (እኔ የምለው ማስታወቂያ የምታሠሩ አምራቾች ወይም አገልግሎት ሰጪዎች ለማስታወቂያ ሠሪዎቹ “‘ዋው’ የሚለውን ቃል ካላስገባህ ኮንትራቱን ሰርዤ ለሌላ ሰው ነው የምሰጠው…” የሚል ግዴታ ታስፈርማላችሁ እንዴ!) ስለዚህ ለ‘ዋው’ የተፈቀደ በር ለ‘ዩ’ም ይፈቀድልንማ!

እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ማንን “አንቱ…” እንደምንልም ግራ እየገባን ነው፡፡ ልጄ ቲንኤጀር ልጆችን በስንት እጥፍ የሚያስከነዱ ማዘሮች እየበዙ ነው፡፡ እናትና ልጅ አብረው ሲሄዱ ድሮ ድሮ እናት… “ልጄን የጠገበ ጎረምሳ ይተናኮለብኝ ይሆን!” እያለች በጭንቀት ራስ ምታት ይነሳባት ነበር “እነ ጆኒ እማዬን ኩክ እናድርጋት ብለው ይልፏትና…” ብላ ልጅት የምትጨነቅበት ዘመን ላይ ደርሰናል እላችኋለሁ - ለመጨነቅ ጊዜ የሚሰጥ አንጐል ፈጥሮባት ከሆነ ነው፡፡ ዛሬ ግን!

‘ሄይር ዳይ’ የምንጠቀመው ሰዎች ከመብዛታችን የተነሳ… አለ አይደል…“የሀበሻ ዘር ሽበት ማውጣት አቆመ እንዴ!” ሊያስብል ምንም አልቀረው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ለ‘ሄይራችሁ’ የጫማ ቀለም የምትጠቀሙ አላችሁ የሚባለው ነገር እውነት ነው እንዴ! አሀ… ተቸገርና…የአንዳንዶቻችን ‘ሄይር’ ከትናንት ወዲያ ገብስማ ሆኖ ዛሬ ደግሞ ‘ድፍን ጥቁር’ ሲሆን…አለ አይደል… “እዚህ ነገር ውስጥ የፒያሳ ሊስትሮዎች እጅ አለበት እንዴ!” ያስብላል፡፡ ብቻ ከእለታት አንድ ቀን ፒያሳ አሥራ ዘጠኝ ቁጥር አውቶብስ የሆነች ‘አዲስ ሪክሩት’ እንትናዬ ከጎናችን ሻጥ አድርገን ስንሄድ… አንዱ ሊስትሮ ጠጋ ብሎ “ጋሼ ጸጉርዎን ልቦርሽ!” ያለ ለታ! ቂ…ቂ…ቂ…

የሄይር ነገር ካነሳን አንዲት ነገር ትዝ አለችኝማ! ልጅ እናቱን ምን ይላታል መሰላችሁ…  እማዬ አባዬ ለምንድነው ምንም ጸጉር የሌለው?

እናት፡- ብዙ ስለሚያስብ ነዋ የእኔ ልጅ፡፡

ልጅ፡-  አንቺ ታዲያ ይሄ ሁሉ ጸጉር ያለሽ ለምንድነው?

እናት፡-  አይ…እንግዲህ ሂድና ጥናትህን አጥና!

እናላችሁ የማይሆን ጥያቄ ሲጠየቅ “አይ…እንግዲህ ሂድና ጥናትህን አጥና!”

እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የድሮ ሰዎች ምን ይሉ ነበር መሰላችሁ

ዘንድሮስ ለጉዴ ቁመቴ ረዘመ

ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ፡፡

እናማ…ምን መሰላችሁ… ብዙ ነገሮች አልጥም ሲሉን፣ ወይ ግራ ሲገባን… ወይ መርከቡ (መርከብ ካለ!) ወደየት አቅጣጫ ሊሄድ እንደሚችል ግራ ሲገባን ‘ያም አገር ያም አገር’ ይታየን ጀምሯል፡፡ በፊት… አይደለም አንደ አገር እንደ መንደር የማንቆጥራቸው ሁሉ ቦታዎች ‘ለጉዳችን ቁመታችን እየረዘመ’ ይታዩን ጀምረዋል፡፡

ስለሚታዩ ነገሮች ካነሳን አይቀር እግረ መንገዴን…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡ እነዚህ ሚኒባስ ታክሲዎች ውስጥ የምናያቸውና የምንስማቸው ነገሮች…አለ አይደል…የምርም ሁሉም ነገር ባለቤት የሌለው አይነት ነገር እያስመሰለ ነው፡፡ ሾፌሩ የፈለገውን ሬዲዮ ጣቢያ፣ ወይ ራፐር ወይ ኃይማኖታዊ ስብከትና መዝሙር እስከ ጥግ ይለቀዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ ጊዜ ወይ “ቀንሰው” ወይ “ዝጋው” ወይ “ጣቢያውን ለውጠው” በሚል ጭቅጭቆች ይነሳሉ፡፡

በተለይም በእምነት ዙሪያ ሚኒባስ ታክሲዎች ውስጥ አልፎ፣ አልፎ የሚለጠፉ ነገሮች…አለ አይደል “ሀይ” የሚል ከሌለ በኋላ ማጣፊያው እንዳያጥር ፍሩልኝማ፡፡ በቀደም አንድ የፒያሳ - ቦሌ ታክሲ ውስጥ አንድ ጽሁፍ ምን ይላል መሰላችሁ… (ባዶው ቦታ ውስጥ የሃይማኖት ስም ሞልታችሁ አንብቡት) “ጊዜው የ…ነው፡፡…ን - ሳይቀበሉ ሞት እንዳይቀድመዎት፡፡” በመሠረቱ አንድ ሰው በራሱ እምነት ውስጥ ሌሎችን አሳምኖ ማስገባቱ ችግር የለውም፡፡ ሆኖም የህዝብ መገልገያ በሆኑ ተቋማት አካባቢ ግን ሊደረጉ የሚችሉና የማይችሉ ነገሮች መስመር ካልተበጀላቸው … አስቸጋሪ ነው፡፡

ለነገሩ ምንስ ሆነ ምን ማናቸውም መኪናዎች ውስጥ ምንስ ነገር ለምን ይለጠፋል፡፡ የኋላ መስታወቱን በአርሴናል ቡድን ፎቶ ግጥም ያደረገ ባለታክሲ፣ ጠያቂ ሲያጣ…በቃ ግራ የሚገባችሁ ነገር ነው፡፡ የትራፊክ ህጉ ውስጥ ይህን የሚመለከት ምንም ነገር የለም ማለት ነው!

እናላችሁ ‘አንተ’፣ ‘አንቺ’ና ‘አንቱ’ ሲያስቸግር ዘዴ መፈለግ አሪፍ ነው፡፡ ሰውየው ሪዙ በጣም ረጅም ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… “ለምንድነው ሪዝህን ይህን ያህል ያሳደግኸው?” ብለው ሲጠይቁት ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“ሚስቴ ሱሪ መልበስ ስላበዛች ሰዉ ቤታችን ውስጥ ወንድ ማናችን እንደሆንን ግራ እንዳይገባው ብዬ ነው” ብሎ አረፈላችሁ፡፡

የምትመሳሰሉ ‘ሀዝባንድ’ና ‘ዋይፍ’ ማን ምን  እንደሆነ ለመለየት አንዳችሁ ሪዝ አሳድጉማ! ልክ ነዋ…ምን ችግር አለው፡፡እናላችሁ… “አንተ”…“አንቺ”…“አንቱ” በ‘ዩ’ ይጠቃሉልንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

Read 3596 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:30