Saturday, 23 June 2012 07:32

የስራ ፈጣሪዎች አጋር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ወይዘሮ መቅደስ ኃይሌ መኩሪያ፤ GWIN ከተባለ ለስራ ፈጣሪዎች የገበያ ዕድል ከሚፈጥር ዓለም አቀፍ ተቁዋም ልዩ የክብር ሽልማት ያገኙት ከወር በፊት ነበር - በጋና፡፡ በስራ መደራረብ ሳቢያ በጋና ተገኝተው ሽልማታቸውን መቀበል እንዳልቻሉ የነገሩን ወይዘሮ መቅደስ፤ በጋና የኢትዮጵያ አምባሳደር  የተከበሩ ወይዘሮ ጊፍቲ አባሲያ ሽልማቱን እንደተቀበሉላቸው ገልፀዋል፡፡ ወይዘሮ መቅደስ ለሽልማቱ የበቁት አፍሪካውያን ሴት ስራ ፈጣሪዎችና ነጋዴዎች ዓለም አቀፍ እውቅናና ገበያ እንዲያገኙ  ባደረጉዋቸው ጥረቶች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የ58 ዓመቷ ወይዘሮ መቅደስ ሃይሌ፤“ወርልድ ውሜን ትሬድ ፌር አፍሪካ” የተባለ ተቀማጭነቱን በአዲስ አበባ ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅና ክልላዊ ተወካይ (Regional Representative) ናቸው፡፡ ለፈጠራ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች መጠነ ሰፊ ድጋፍ የሚያደርገው ድርጅቱ   ፤የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፤ ኮንፍረንሶች በማዘጋጀት፤ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች  ባዛሮች ላይ እንዲሳተፉ በማገዝ፤የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበትን እድል በመፍጠር እንዲሁም ገበያን በማፈላለግ እና በሽርክና የሚሠሩበትን መንገድ በማመቻቸት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

በ60ዎቹ መጨረሻ በአስተማሪነትና በሌሎች የተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩት ወይዘሮዋ፤ ከአገራቸው በመውጣት ለ22 ዓመታት በውጭ አገራት የኖሩ ሲሆን የቢዝነስ ትምህርት በመማር በዓለም አቀፍ  ደረጃ የታወቁ  የንግድ ባለሙያ ሆነዋል፡፡ ወይዘሮ መቅደስ ሃይሌ በዓለም አቀፍ የንግድ ስራዎችና በፈጠራ ስራዎች ባለሙያነታቸው በ1992 (እኤአ) በሎስአንጀለስ ተሸልመዋል፡፡  በነዳጅ ዘይት ንግድ፤በተለያዩ የሸቀጥ ግብይቶች፤ በግብርና፤ በንግድ ግንኙትና ልውውጦች እንዲሁም ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ በከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጥ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ኤክስፐርት ሆነው እየሰሩም ይገኛሉ፡፡

ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችንና ባለሙያዎችን ልምድ በማጋራትና በእውቀት በማጎልበት ከፍተኛ እድገት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት ያላቸው ወይዘሮ መቅደስ፤ በአፍሪካ ለስራ ፈጣሪዎችና ለነጋዴዎች ዓለም አቀፍ ገበያን በመፍጠር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ይታወቃሉ፡፡ Agoa በተባለው የአሜሪካና የአፍሪካ አገራት የንግድ ትብብር መድረክ አማካኝነት ከ5ሺ በላይ የአፍሪካውያን ምርቶች፤ በአሜሪካ ህጋዊ እውቅና እንዲኖራቸው በተደረገው እንቅስቃሴ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ተመስግነዋል፡፡

እሳቸው በሚመሩት በ“ወርልድ ዉመን ትሬድ ፌር አፍሪካ” አማካኝነት በኢትዮáያ በያዝነው ዓመት  3ሺ የሚደርሱ በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ኢንተርፕራይዝ (MSME’s) የታቀፉ ሴቶች ዘለቄታ ያለው የንግድ ሥራ ባለቤት ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርጸው በመንቀሳቀስ ላይም ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በ2015 (እኤአ) 15ሺ ሴቶችን የራሳቸው የንግድ ሥራ ባለቤት ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ወይዘሮ መቅደስ ይናገራሉ ፡፡

የቆዳ ጠበብቱ ዘካርያስና የባልትና ባለሙያዋ ሰብለወንጌል

ዘካርያስ ግርማ፤ በቆዳ ላይ የስነጥበብ ስራዎችን የሚሰራ ወጣት ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ሙያውን ካስተማረው ታላቅ ወንድሙ ጋር በመሆን የበግ ወይም የፍየል ቆዳን በመፋቅ የሚሰራቸውን የጥበብ ውጤቶች በርካሽ ዋጋ ሲሸጥ ነበር የቆየው፡፡ በመጀመርያ ቆዳውን በ30 ብር ይገዛል፡፡ ቆዳውን በመፋቅ የኢትዮጵያን ነገስታት፤ የቱሪስት መስህቦችና ልዩ ልዩ የሃይማኖት ስእሎችን በመስራት ከ150 ብር ጀምሮ ለገበያ ያቀርብ ነበር፡፡

ወይዘሮ መቅደስ ሃይሌ፤ በዘካርያስ የተሰራ አንድ የቆዳ ምስል ለመጀመርያ ጊዜ የተመለከቱት በስራ አጋጣሚ አውሮፓ በነበሩበት ወቅት ነው - በትልቅ የንግድ ባዛር ላይ ተሰቅሎ፡፡ የቆዳ ላይ ስዕሉን ዋጋ ሲጠይቁ 200 ዶላር ተባሉ፡፡ ሻጩ ኢትዮጵያዊ ስለነበር የቆዳ ላይ ስእሉን የሰራው ማነው ብዬ ጠየቅሁት፤ ሆኖም ፈጣን ምላሽ አላገኘሁም የሚሉት ወይዘሮ መቅደስ፤ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ የዚህን የፈጠራ ሥራ ባለቤት ለማግኘት ያላሰስኩት ባዛርና ኤግዚብሽን አልነበረም፤በመጨረሻም አራት ኪሎ አካባቢ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተዘጋጀ ባዛር ስጎበኝ በመጀመርያው ድንኳን ውስጥ አገኘሁት ይላሉ፡፡

“እኔ የምመራው ድርጅት እንዳንተ ዓይነት ወጣቶች ለሚሠሩት ስራ ዕውቅና በመስጠት፤የሙያ ብቃታቸውን አሻሽሎ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለለውጥ እንዲሰሩ የሚያነሳሳ ነው” በማለት ወ/ሮ መቅደስ እንዳስረዱት ያስታውሳሉ፡፡

የዘካርያስን ችሎታ ለመፈተን የፈለጉት ወይዘሮዋ፤ እቤታቸው የነበረ የሮሚዮና ጁሊዬት ምስልን በቆዳ ላይ መስራት ይችል እንደሆነ ጠየቁት፡፡ ወጣት ዘካርያስ የተሰጠውን ፈተና ያለማመንታት ተቀበለ፡፡ በሳምንቱ ጨርሶ  ሲያመጣ የፖስተሩን የሮሚዮና ጁሊዬት ምስል በቆዳው ላይ እንዳለች ቁጭ አድርጐ በመስራቱ ተደነቅሁኝ ያሉት ወ/ሮ መቅደስ፤ፈተናውን በአጥጋቢ ሁኔታ ማለፉን ይገልፃሉ፡፡

ከአገራችን አርቲስቶች በቆዳ ላይ የጥበብ ስራ የማደንቀው አርቲስት ለማ ጉያን ነው የሚለው ወጣት ዘካሪያስ፤ሙያውን የቀሰመውና የተለማመደው ከታላቅ ወንድሙ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የጥበብ  ስራውን ለመስራት ብዙ መሳሪያ አያስፈልግም የሚለው ወጣቱ፤ ዋና መሳሪያቸው ምላጭ እንደሆነ ይናገራል፡፡  “ቆዳውን በምላጭ እየፋቅን ነው የምንሠራው” ብሏል፡፡

ከወ/ሮ መቅደስ ጋር መስራት ከመጀመሩ በፊት ገቢው በጣም አነስተኛ እንደነበር ይናገራል - ዘካሪያስ፡፡ “ሰው ትዕዛዝ ሰጥቶን ካልሰራን በቀር ብዙ ፈላጊ አልነበረንም፤ አንዳንዴ በየክልሉ እየተዘዋወርንም ገዢ እናፈላልግ ነበር” የሚለው ወጣቱ፤ወ/ሮ መቅደስን ካገኘሁ በኋላ ግን ሙያዬ አድጉዋል ገበያም ሰፍቶልኛል ብሎዋል፡፡ “ወ/ሮ መቅደስ ለቡና ባንክ ስዕሎቼን አቅርበውልኝ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቻለሁ” የሚለው ወጣት ዘካርያስ፤ የንግድ ፍቃድ አውጥቼ መስራቴ ሙያዬን ለማሳደግ አስችሎኛል ባይ ነው፡፡የጠ/ሚ መለስ ዜናዊና የታላቁ ህዳሴ ግድብን በቆዳ ላይ በመፋቅ ሰርቼ ነበር፤ሆኖም በአንድ የባህርዳር አርቲስት የባለቤትነት መብቱ ተነጥቆብኛል ያለው ወጣት ዘካርያስ፤ የጥበብ ስራዎቼ በሌሎች ሰዎች ተሰርተው ለመላው አገሪቷ ቢስፋፋ ደስ ቢለኝም የፈጠራ መብቴ እንዲነጠቅ ግን አልፈልግም፤ አሁን ከወ/ሮ መቅደስ ጋር መስራቴ እንዲህ ዓይነት መጭበርበር እንዳይፈጠር ያግዘኛል ብሏል፡፡

የፈጠራ ስራውን ከእኔ ወስዶ የእኔን ስም ፍቆ የራሱ ያደረገው ታዋቂ አርቲስት፤ በሚዲያ ላይ ሁሉ ወጥቶ ስራውን እንደራሱ ፈጠራ ሲገልጽ ማመን አልቻልኩም የሚለው ዘካርያስ፤ ወደፊት ይህ አይነቱ ጉዳት ሙያዬ ላይ እንዳይደርስ መጠንቀቅ እንዳለብኝ አጋጣሚው አስተምሮኛል ብሏል፡፡ “ስራችን በእጃችን እንዲቀር ፍላጐት የለኝም፡፡ ሌላ ሰው የፈጠራ ውጤቱን ኮርጆ እንዳይነግድበት ግን እፈልጋለሁ፡፡ ፈቃድ አውጥቶና ህጋዊና መሠረት ይዞ መስራቱ ይህን ችግር ያቆመዋል” ይላል - ወጣቱ፡፡

ከስራዎቼ ውስጥ በተለይ የመድሃኒዓለም እና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምስሎች ተፈላጊ ናቸው የሚለው ወጣት ዘካርያስ፤ ለስራው የሚያስፈልገውን ጥራት ያለው ቆዳ ለማግኘት እንደሚቸገር ይናገራል፡፡

“አንዳንዴ የተበላሹ ቆዳዎች ሲገጥሙን በስዕል ስራው በማጥበብና በማስፋት ችግሩን ለመፍታት እንሞክራለን”

ዘካሪያስ የፈጠራ ችሎታውን ማሳደግ እንዳለበት አሳምኜው መስራት ሲጀምር ህጋዊ ፈቃድ አውጥቶ  መስራት ከፍተኛ ግብር ይዳርግሀል ተብያለሁ ብሎ አልተቀበለውም ነበር የሚሉት ወ/ሮ መቅደስ፤ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ መስራት ሲጀምር ወዲያውኑ ከቡና ባንክ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በወቅቱ ባንኩ ለስራው ማበረታቻ እንዲሆነው የሰጠው 15ሺ ብር ነበር ያሉት ወ/ሮ መቅደስ፤ ያን ጊዜ የተሰማው ደስታ ቀላል እንዳልነበር ያስታውሳሉ፡፡

ከልጅነቷ ጀምሮ በንግድ ስራ መሰማራት ትፈልግ እንደነበር የምትናገረው ወይዘሮ ሰብለወንጌል በበኩሉዋ፤በባልትና ንግድ መንቀሳቀስ ከመጀመሯ በፊት ያልሞከረችው የንግድ ሙያ እንዳልነበር ትገልፃለች - ሱፐር ማርኬት፤ አትክልት ማከፋፈል፤ ከዚያም በመኪናዎቿ የተለያዩ ስራዎችን ሞክራ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመት ወዲህ የጀመረችው የባልትና ውጤቶችን ማምረትና መነገድ እንደተስማማት የምትገልፀው ወይዘሮ ሰብለወንጌል፤በመጀመሪያ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከተሞች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የባልትና ምርቶቿን በመሸጥ ነው ዕውቅና ማግኘት የጀመረችው፡፡

የባልትና ውጤቶች - እነ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቡላ፣ ጌሾ፣ ቅመማቅመም፣ ሚጥሚጣ እና ሌሎችን ያካትታል፡፡ ለሆቴሎች የተሠሩ የተለያዩ የቤት ዕቃዎችና የምግብ ቁሳቁሶችም ታቀርብ ነበር፡፡ ጀበና፣ ጣባ፣ድስት ወዘተ ተፈላጊዎች እንደነበሩ ትናገራለች፡፡ ሰብለወንጌል  የባልትና ውጤቶቿን የምታዘጋጀው በቤቷ ውስጥ ሲሆን ሠራተኞቹዋ ደግሞ ወንድሞቿ እና መላው የቤተሰቡ አባላት ናቸው፡፡

ከአራት ወንድሞቼ እና የቤት ሰራተኛችን ጋር ሆነን በመኖርያ ቤታችን ውስጥ የባልትና ውጤቶችን እናዘጋጃለን፡፡ በዝግጅታችን ወቅት ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት እናደርጋለን የምትለው ወ/ት ሰብለወንጌል፤ የባልትና ሙያውን ከእናቷ መማራቸውን ትገልፃለች፡፡

የባልትና ምርቶችን የምናሰናዳው በየጊዜው አዳዲስ ሙከራዎችን በማድረግ ነው የምትለው  ሰብለወንጌል፤ በቅርቡ የሠራነው ሚጥሚጣ ልዩ አይነት ቃና ተጨምሮበት ከተዘጋጀ በኋላ በተለይ ለቁርጥ ስጋ እና ለተለያዩ ምግቦች ማባያ ተወዳጅ ሆኗል ስትል በምሳሌነት ጠቅሳለች፡፡

ከወ/ሮ መቅደስ ድርጅት ጋር መስራት ከጀመረች በሁዋላ የምርቶቿን ብራንድ ለመፍጠር እየጣረች  መሆኑዋን የጠቆመችው ሰብለወንጌል፤ምርቶቿ በአሜሪካ እንደተመዘገቡና ፈቃድ እንደተሰጣትም ገልጻለች፡፡

እንደእነዚህ ያሉ ስራ ፈጣሪዎችና ባለሙያ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ገበያውን እንዲፎካከሩ የባንክ ተቋማት ልዩ አስተያየት በማድረግ ያለኮላተራል የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ሊግዙዋቸው ይገባል ይላሉ - ወይዘሮ መቅደስ፡፡

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለወ/ሮ ሰብለወንጌል የ50ሺ ብር ድጋፍ እንዳደረገላት የሚናገሩት ወ/ሮ መቅደስ፤እኔ እንደ 500ሺ ብር እቆጥረዋለሁ ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ባንኮች ዓለምአቀፍ የውጭ ንግድ ፈቃድዋንና የስራ ልምድዋን በማቅረብ የጠየቀችውን የብድር ድጋፍ ያለ መያዣ ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡

ቡና ባንክ ግን የልጅቱን ሙያና የፈጠራ አቅም ተገንዝበውና ከወርልድ ውሜን ትሬድፈር ጋር ለዕድገት ለመሥራት ባላቸው መልካም ፍቃደኝነት ያለኮላተራል ብድር መስጠቱ አርዓያነት ያለው ተግባር እንደሆነ ጠቁመዋል - ወ/ሮ መቅደስ፡፡ ወርልድ ወሜን ትሬድ ፌር ለብድሩ መከፈል አስፈላጊውን ክትትልና ስልጠና ጭምር እንደሚሰጥ አክለው ገልፀዋል፡፡አላማችን ኢትዮጵያ የወለደቻቸው ልጆች ሁሉ እንደሰው ማደግና እንደ ሰው ቦታ መልቀቅ አለባቸው የሚል ነው ያሉት ወ/ሮ መቅደስ፤ አገር የምታድገው በዚህ ዓይነት ድጋፍና የዕውቀት ሽግግር ነው ብለዋል፡፡

ዘካርያስ ከ“ወርልድ ውሜን ትሬድ ፌር አፍሪካ” ጋር መስራት ከጀመረ በኋላ ምርቶቹን ለዓለም አቀፍ ገበያ በተሻለ ጥራትና ዋጋ እንዲያቀርብ እየጣርን ነው ያሉት ወ/ሮ መቅደስ፤ ለወይዘሮ ሰብለወንጌል ደግሞ ያላትን የዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነት ለመጨመር በአፍሪካ ከፍተኛ ዕውቅና እንዲኖራት እያገዝናት ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ ለአንዲት ታዋቂ የሆሊዉድ አክተር በቆዳ ላይ ማስታወቂያ የመስራት እድል ማግኘቱን የጠቆመው ወጣቱ፤ ከአንድ ዓመት በፊት የአንድ የቆዳ ላይ ስዕል አማካይ ዋጋ 150 ብር እንደነበርና አሁን ግን እስከ 2500 ብር እንደደረሰ ይናገራል፡፡ “ወርልድ ውሜን ትሬድፌር አፍሪካ” ኢትዮጵያ በጋና በሚካሄደው 18ኛው WASME International Conference ላይ እንድትሳተፍ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ማህበራት ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ኮንፈረንሱ የዓለም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የት እንደደረሱና ምን እየሰሩ እንደሆነ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት ነው ተብሎዋል - ከJuly 25-29 የሚካሄደው ኮንፈረንስ፡፡

 

 

 

Read 4243 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:55