Saturday, 28 July 2012 11:31

ሐበሻ ቢራ ለባቫሪያ ኤን ቪ 35 በመቶ አክስዮን አስተላለፈ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ሐበሻ ቢራ አ.ማ የ300 ዓመት ልምድ ካለው ግዙፍ የኔዘርላንድ ኩባንያ ጋር ለመሥራት ከመስማማቱም በላይ ማኅበሩ ለሽያጭ ካቀረባቸው አክሲዮኖች ውስጥ 35 በመቶ ለባቫሪያ መሸጡን አስታውቋል፡፡ ሐበሻ ቢራ በ250 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል በ2010 ዓ.ም የተቋቋመ አዲስ ኩባንይ ሲሆን እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ እያንዳንዳቸው 1000 ብር ዋጋ ያላቸው 162,580 አክሲዮኖች በአገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማስተላለፉ ታውቋል፡፡ ቀሪዎቹን 87,500 አክሲዮኖች ለባቫሪያ ኤን ቪ በመሸጥ የአክሲዮን ሽያጭ ማብቃቱን ማኅበሩ ገልጿል፡፡

በ120 አገሮች በጣም ተወዳጅ የሆኑ የተለያዩ ቢራዎችና ለስላሳ መጠጦች በማቅረብ ውጤታማ የሆነው ባቫሪያ ኤን ቪ በኔዘርላንድ፣ ከአርሶ አደሮች ኀብረት ሥራ ማኅበር ጋር በሽርክና ግዙፍ የብቅል ፋብሪካ አቋቁሞ ምርቱን በመላው ዓለም እያሰራጨ የሚገኝ ትልቅ ኩባንያ ነው፡፡ ባቫሪያ ኤን ቪ በኔዘርላንድና በሌሎች አገሮች ከ1000 በላይ ሠራተኞች እንዳሉትና በዓመት 6.5 ሄክቶ ሊትር ቢራ እያመረተ 70 በመቶ ምርቱን ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡

የባቫሪያ ኤን ቪ ሐበሻ ቢራ ፋብሪካን መቀላቀል፣ የኩባንያው አመራሮች በፋብሪካው የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንት ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽአ ያደርጋል ያለው የሐበሻ አክሲዮን ማኅበር ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ ባቫሪያ ኤን ቪ በቢራና በብቅል ምርት በዓለም ጉልህ ድርሻ ስላለው፣ ሐበሻ ቢራ ፋብሪካ፣ አስተማማኝ የገበያና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ዕድል ይኖረዋል ብሏል፡፡

 

 

Read 4553 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:42