Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 08:45

ታላቁ ሩጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ግርማዊነታቸው የሲዳሞን ጠቅላይ ግዛት ጐበኙ፡፡
በድርቅ ለተጐዱ ወገኖች የእርዳታ እህል መከፋፈል ጀመረ፡፡
መፈንቅለ መንግስቱ ከሸፈ፡፡
የአብዮትን በአል በማስመልከት ካስትሮ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡
በሻዕቢያ ጦር ላይ ትልቅ ኪሳራ ደረሰ፡፡
የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት፤ ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ተቆጣጠረ፡፡
ህገ-መንግስቱ ፀደቀ፡፡
የአልጀርሱን ስምምነት እንዲያከብሩ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ጥሪ ቀረበ፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሲድኒ ኦሎምፒክ ታሪክ ሰሩ፡፡
የጐዳና ላይ ነውጡን በማነሳሳት የተጠረጠሩ የቅንጅት አመራሮችና ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
የሚሌኒየም በአሉ የአገሪቱን ገፅታ ለመገንባትና በውጭው አለም ዘንድ የነበራትን ለዘመናት የዘለቀ የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ መልካም አጋጣሚ ፈጠረ፡፡

…ይህ ሁሉ የሆነው ሟቹ ባለቤታቸው አስር አለቃ ጠና ፈረደ፤ ሬዲዮኑን መጠኑ ባልታወቀ ገንዘብ ንብረታቸው ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መሆኑን የነገራቸው ይህ ሬዲዮ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት አብሯቸው ኖሯል፡፡
ባለቤታቸው አስር አለቃ ጠና ከሞቱ በኋላም አብሯቸው ነው - ሬዲዮው፡፡ እንደተከበረ ዳንቴል ለብሶ መደርደሪያው ላይ ተቀምጧል፡፡ ውርሳቸው ነው፡፡ ምንም ቢቸግራቸው ‘ልሽጠው ይሆን?’ ብለው የማያስቡት ሀብታቸው ነው፡፡ ክፉ ደጉን እየነገራቸው ክፉ ደጉን አብሮአቸው የገፋ ጓደኛቸው ነው፡፡ ይሄው ለስንት ዘመን…
ሬዲዮው ዛሬም ይናገራል፡፡ የአውራሽ እንጂ የሬዲዮው ትንፋሽ ፀጥ አላለም፡፡ የወራሽ እንጂ የሬዲዮው ምላስ አለተኮላተፈም፡፡ ሬዲዮው ይናገራል…
“እስቲ ጠጥታ! ራዲዮናውን እንስማበት!” አሉ እማማ እቴናት ቆጣ ብለው፡፡
”ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነገ ማለዳ መነሻና መድረሻውን በመስቀል አደባባይ በማድረግ ይካሄዳል” አለ ሬዲዮው፡፡ በጠባቧ ክፍል ውስጥ የተቀመጡት ጠጪዎች በሙሉ ጆሯቸውን ወደ ሬዲዮው ቀሰሩ፡፡
ታላቁ ሩጫ ነገ ይካሄዳል፡፡ ከ32 ሺህ በላይ ሰው ይካፈላል፡፡ የውጭ አገር ዜጐች ይሳተፋሉ፡፡ ሩጫው በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽ|ፋን ያገኛል፡፡
”ኤዲያ! እንዲህ ያለ ወግ አይጥመኝም!“ አሉ እማማ እቴናት፤ በውድነህ መለኪያ ላይ አረቄ እየቀዱ፡፡ እርግጥ ነው እማማ እቴናትን እንዲህ ያለ ጨዋታ አይስባቸውም፡፡
”ምናለ ብንሰማበት ጥልቅ ጥልቅ እያሉ ባይበጠብጡን“ አላቸው ውድነህ መለኪያውን ወደ አፉ እያስጠጋ፡፡ የእማማ እቴናት የልጅ ልጅ የሆነው ባቢ፤ ከጠጪዎች በተረፈች በርጩማ ላይ ተቀምጦ የቤት ስራውን ከሚሰራበት ቀና ብሎ ማዳመጥ ጀመረ፡፡ የወያላው ካሳሁን ንግግር በመሃል ጣልቃ ገባ፡፡ ጆሮውን ወደ ሬዲዮው ቀስሮ የተቀመጠውን ውድነህን እየተመለከተ፡፡
“መስማት ምን ትርጉም አለው! ልብ ያለው ሰው ጧት ተነስቶ ነው የሚሮጠው… አንተ…” ከጐኑ የተቀመጠው የታክሲ ሾፌር ጓደኛው ሳይፈልግ ሳቀለት፡፡ ውድነህ ፊት ላይ ንዴት ተነበበ፡፡
“እኔ ነኝ ነገረኛው! ከማንም አረቂያም ጋር እኩል እየተቀመጥኩ ራሴን ያቀለልኩ“ አለ አረቄውን እየጨለጠ፡፡ ዙሪያውን የተቀመጡት ጠጪዎች በሙሉ በክፉ አይን አዩት፡፡ ሁሉም ”የማንም አረቂያም“ በሚል በጅምላ መመታታቸው አስቆጥቷቸዋል፡፡
”ምንድነው እንዲህ ያል ዋዛ?! ሕዝባዳም በእለተ ሰንበት በተስኪያን ህዶ መጠለዩን ትቶ መንገድ ለመንገድ ዘጥ ዘጥ ቢል ለነፍሱ ምን ያተርፋል?“ አሉ እማማ እቴናት፡፡ የሬዲዮው ወሬ አልጣማቸውም፡ሁሉም በታላቁ ሩጫ ዙሪያ የየግሉን አስተያየት መስጠት ስለጀመረ የሚመልስላቸው አላገኙም፡፡
”ከ32 ሺ በላይ ሰው ይሳተፋል መባሉ አይገርምም?“ አለ ከመደርደሪያው ጐን የተቀመጠው ከሳ ያለ ወጣት፡ የታክሲ ወያላው ካሳሁን ነበር ቀድሞ የመለሰለት፡፡
”ምን ማለትህ ነው! ትኬቱ ከማለቁ የተነሳ’ኮ በህገወጥ በእጥፍ ዋጋ እየተሸጠ ነው!“ አለ ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ ሲጓዙ ከአንድ ተሳፋሪ የሰማውን ጠቅሶ፡፡
ሁሉም የየግሉን አስተያየት ይሰነዝራል፡፡ እማማ እቴናት ለአንድ ቀን ሩጫ ይሄን ያህል ገንዘብ መውጣቱ አሳዝኗቸዋል፡፡ “ሰው ለገንዘብ ይሮጣል እንጂ በገንዘብ ይሮጣል?” እያሉ ያስባሉ፡፡ የልጅ ልጃቸው ባቢ ነገ ማለዳ አያቱ ጨርቆስን ተሳልመው እስኪመጡ ላንድ አፍታ ሹልክ ብሎ ሩጫውን ማየት እንደሚችል ያሰላስላል፡፡ ከሰሞኑ የእማማ እቴናት የአረቄ ደንበኛ የሆነው የጐዳና ተዳዳሪ ልጅ እግር፤ በዝምታ ተውጦ ከራሱ ጋር ይነጋገራል፡፡
ምክንያቱ ይለያይ አንጂ ሁሉም የነገውን ታላቅ ሩጫ ለመሮጥ ያልተዘጋጁ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ መሮጥን እንጂ ስለታላቁ ሩጫ የሚሰማቸውን ማውራትን የሚከለክላቸው የለም፡፡
”ወይኔ ውድነህ! ነገ ማለዳ ተረኛ ባልሆን ኖሮ ዘንድሮ መሮጤ አይቀርም ነበር!“ አለ እሁድ ጧት የፋብሪካ ዘበኛነት ተራው የእርሱ መሆኑ ትዝ ሲለው፡፡
” እማማ እቴናት ጧት መሮጥ ያሰበ ማታ አረቄ ሲጋት ያድራል ብሏል እንዴ ሬዲዮኑ?“ አለ ወያላው ካሳሁን፤ ውድነህን የጐሪጥ እያየ፡፡
በታላቁ ሩጫ ዙሪያ ሁሉም የተሰማውን ሲናገር ቆየ፡፡
ምሽቱ እየገፋ በመሄዱ ቀስ በቀስ የጠጪው መጠን መቀነስ ያዘ፡፡ ካሳሁንና ጓደኛው ነገ በሌሊት ተነስተው ታክሲያቸውን ለማንቀሳቀስ ዛሬ በጊዜ መተኛት አለባቸው፡፡
ውድነህም ቢሆን ማልዶ ከጨርቆስ ተነስቶ ኮተቤ ለመዝለቅ፣ ሌሊቱን በእንቅልፍ ማሳለፍ ግድ ይለዋል፡፡
ብርዱን ለመርሳት ያህል ሶስት መለኪያ አረቄ የተጐነጨው ልጅ-እግር የጐዳና ተዳዳሪ፤ ከዚህ በላይ ለመጠጣት ኪሱ በጀ አላለውምና የሶስት አረቄውንና የሁለት ኒያላውን ሂሳብ ከፍሎ ወደ ጐዳና ቤቱ ማዝገም አለበት፡፡
ጠጪው ሲሟጠጥ ያዩት እማማ እቴናት፤ ከዚህ በላይ የሚያስመሽ ጉዳይ የላቸውም፡፡ የልጅ ልጃቸው ባቢ አያቱን ተከትሎ ወደ አልጋው ማምራት ይኖርበታል፡፡
ጧት ላይ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው ታላቁ ሩጫ ተጀመረ፡፡ ተሳታፊው በሙሉ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ከሌላው ቀድሞ ለመገኘት ትንፋሹ እስኪቆራረጥ ይሮጣል፡፡ ጐዳናውን ሞልቶ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚተመው ቁጥር ስፍር የሌለው ሯጭ ያቅሙን ያህል ይሮጣል፡፡
የሯጩ ሕዝብ የፊተኛ ጫፍ ባምቢስ አካባቢ ሲደርስ፤ እማማ እቴናት የቅዳሴ ጠበል በብልቃጥ ይዘው ከቂርቆስ ተነስተው ቤታቸው ደረሱ፡፡ የልጅ ልጃቸው ባቢ ቤት ወስጥ አልነበረም፡፡ ደነገጡ፡፡ ነጠላቸውን ጣል አድርገው ፍለጋ ሲወጡ፣ የማታው አረቄ በፈጠረበት ድካም እንቅልፍ ጥሎት አርፍዶ የነቃው ውድነህ፤ እያለከለከ ወደ ስራው በመጓዝ ላይ ነበር፡፡
በሩጫው ሰበብ መንገድ በመዘጋቱ እንደልባቸው በርረው ከስቴዲየም አራት ኪሎ፣ ከኡራኤል መገናኛ እየተወነጨፉ በታክሲያቸው ሕዝቡን ማጓጓዝ ያልቻሉት ወያላው ካሳሁንና ጓደኛው፤ መንገድ እያሳበሩ ውስጥ ውስጡን መሽሎክሎክ ይዘዋል፡፡
ባቢ ከሚተራመሰው ሯጭ መሀል ድክ ድክ ማለቱን ቀጥሏል፡፡
የማለዳ ብርድ ከእንቅልፉ ጋር ያጣላው ልጅ እግር፣ ሯጮች ለድካማቸው ማለዘቢያ የሚጐነጩትን የታሸገ ውሃ ጨልጠው ወርወር የሚያደርጉትን የፕላስቲክ ዕቃ እየለቀመ አብሮ ይሮጣል፡፡ ውድነህ የታክሲ እጦት አዘግይቶት የእንጀራ ገመዱ ሲበጠስ እየታየው እየሮጠ ያስባል፡፡
የታክሲው ሾፌር በተሳፋሪና በመንገድ እጦት የዕለቱ ገቢ መጉደሉን እያሰላሰለ ታላቁ ሩጫ ተጠናቆ እንዳሻው እየሞላ እስኪበር ውስጥ ውስጡን እያሳበረ ያሽከረክራል፡፡
ባቢ እርካታን፣ እማማ እቴናት ባቢን ፍለጋ ሳይመዘገቡ ታላቁን ሩጫ ይሮጣሉ፡፡ ልጅ-እግሩ የጐዳና ተዳዳሪ፤ የተጣሉ የውሃ ፕላስቲኮችን እየለቀመ፣ ሸጦ ሳንቲም እንደሚያገኝ እያለመ ከሯጮች ጋር ይሮጣል፡፡
ሰልፉ በቁመት አይደለም፡፡ የሩጫው ቀስት ወደ አንድ አቅጣጫ የሚወነጨፍ አይደለም፡፡ አይደለም፡፡
ወያላው መንገድን፣ እማማ እቴናት ባቢን፣ ባቢ እርካታን፣ ልጅ እግሩ ሳንቲምን፣ ውድነህ በጊዜ መድረስን ፍለጋ ሁሉም በየፊናቸው ይሮጣሉ፡፡
ታላቁን ሩጫ ለመሮጥ በህይወት እንጂ በሯጮች መዝገብ ላይ መስፈር ግድ አይልም፡ ሩጫው ውስጥ አሉበት - ትኬትም ተስፋም ያልቆረጡት፡፡
ሁሉም እየሮጡ ናቸው፡፡

 

Read 3861 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:50