Print this page
Saturday, 21 January 2012 10:45

የሁለት ዓለም ሰው

Written by  ዮናስ ኪዳኔ Facebook-yonas A. Kidane
Rate this item
(0 votes)

በጠባቧ ቤት ውስጥ እናትና ልጅ ቁጭ ብለዋል፡፡ እናት ትሪያቸውን ይዘው ምስር ይለቅማሉ፡፡ ሳልሳዊ ከእናቱ በጥቂት ርቀት ላይ በምትገኝ ትንሽ ጠረጴዛ ላይ ነጭ ወረቀቱን አስቀምጦ እየሰበቀ ምን ብሎ እንደሚጀምር ማሰላሰል ይዟል፡፡ እናት የልጃቸውን መመሰጥ ተመልክተው “ደግሞ … መቸክቸክህን ልትጀምር ነው?” አሉት፡፡ የሰማቸው አይመስልም፡፡ “ኤዲያ … መቼም ያንተ ፅሁፍ ማብቂያ የለው” “እንዴ እማ አሁንማ አለቀ፡፡ ስንት የለፋሁበትን የፊልም ድርሰቴን ፅፌ ጨረስኩ እኮ” አለ ሳልሳዊ፡፡ “እና አሁን የምትሰናዳው ለምንድነው?”

“የድርሰቴን አፅመ-ታሪክ ለመፃፍ ነዋ”

“አፅመ ታሪክ ደግሞ ምንድነው?” አሉ እናት “ያንተ ጣጣ መች ያልቅና” የሚል መልዕክት ባዘለ ድምፀት፡፡ “አፅመ ታሪክ ማለት በአንድ ገፅ ላይ የሚፃፍ የድርሰቱን አጠቃላይ ታሪክ ባጭሩ …” ንግግሩን ሳይጨርስ የጠባቧ ቤታቸው በር ተከፍቶ አንዲት ወጣት ሴት ገባች፡፡ የሆነ ያበሳጫት ነገር እንዳለ ሁኔታዋ ያሳብቃል፡፡ በሩን ከፍታ እንደገባች ከበሩ ጋር የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ያለበት ወንበር ተቀበላት፡፡ ተቀመጠች፡፡ ታናሽ እህቱ ማህሌት ነች፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት ተማሪ ነች፡ “ዛሬ ደግሞ ሰላምታም የለ?” አሉ እናት፤ የሴት ልጃቸው ሁኔታ ግር ቢላቸው፡፡

ሳልሳዊ ትኩረቱን ከመቸር በቀር እህቱን ምንም አልተናገራትም፡፡ የእህቱን ፀባይ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ፍላጐት እንጂ ጉትጐታ የእህቱን አንደበት የማሸነፍ ኃይል የለውም፡የሚኖረው መጠጋት በምታበረታታ፣ መራራቅን በምታወግዝ ጠባብ ቤት ውስጥ ባይሆን ኖሮ በዚህ ቅፅበት ከእናትና እህቱ ራቅ ብሎ ከተቻለም መኝታ ቤቱ ውስጥ ገብቶ ለመፃፍ በሞከረ ነበር፡፡ ሀሳቡን እንደምንም አሰባስቦ መፃፍ ጀመረ፡፡

“አቤነዘር ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የመጀመሪያ አመት ተማሪ ነው፡፡ የሆነ የሚያስጨንቀው ነገር በመኖሩ ትምህርቱን ስለማቋረጥ ያስባል፡፡ ፈተና በመፈተን ላይ ሳለ ድንገት ስለተረበሸ ፈተናውን አቋርጦ ይወጣል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተነሳ ትምህርቱን ለማቋረጥ ቢወስንም የወንድም ያህል በሚቀርበው መምህሩ ብልህነት ትምህርቱን ለመቀጠል ቻለ፡፡”  “በዚህ ሁኔታዬ ትምህርቴን ብቀጥልስ ምን ዋጋ አለው?” አለች ማህሌት፤ የእናቷ ምክር እንዳልተዋጠላት እንባ ያቀረሩ አይኖቿ ላይ እያስነበበች፡፡

“የኔ ልጅ በትምህርትሽማ እንዳትቀልጂ … በሰላምሽና በትምህርትሽ የሚመጣ ጥንቅር ብሎ ይቅር” አሉ እርጋታ በተላበሰ እናታዊ ድምፅ፡፡

ሳልሳዊ ከእናትና ከእህቱ ንግግር ቀልቡን መልሶ ወደ ፅሁፉ አቀረቀረ፡፡ “መክሊት ከአቤነዘር ጋር ክፍል የምትጋራ ቆንጆ ከሚባሉት ተርታ የምትመደብ ተማሪ ነች፡፡ አንድ ቀን አቤኔዘር ሲተክዝ ስላየችው ተጠግታው “የሚያስጨንቅህን ነገር ምንድነው?” ብላ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ሰበብ ተግባቡ፡፡

“ቀድሞውንም ባልግባባው ይሻለኝ ነበር፡፡ እራሱ ተለማምጦ ተግባብቶኝ አሁን ሰላሜን ይንሳኝ?” አለች ማህሌት፡፡ “… አይ የልጅ ነገር፤ ከሰው ጋር እየኖሩ ከሰው ጋር ያለመግባባት እንዴት ይቻላል” አሉ እናት፡፡ ሳልሳዊ መፃፉን ቀጥሏል፡፡

“በሌላ በኩል አዲስ አበባ የሚኖሩት የአቤነዘር እናት እንዲሁም ሶስት ወንድሞቹና አንድ እህቱ “ዝቅተኛ” ኑሮን የሚገፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቤታቸው ሁሌም በሳቅና በጨዋታ የደመቀች ናት፡፡ “ሀዘን ትካዜን አያውቁትም፡፡ በማጣታቸው ይቀልዳሉ፣ በጐዶሏቸው ሳቅ ይፈጥራሉ፡፡”

“መስሎሽ ነው የኔ ልጅ፡፡ እንጂማ የተፈጠረውን ቀለል አድርጐ እያየ ባያልፍ አንድም ጤነኛ ሰው ባላገኘን ነበር፡፡” አሉ እናት፤ የለቀሙትን ንፁህ ምስር ወደ ሌላ እቃ እየገለበጡ፡፡

“አቤኔዘር መክሊትን ያስጠናታል፡፡ ለትምህርቷ ግድ ባይኖራትም ተባርራ ወላጆቿን ማሳዘን ፈፅሞ አትፈልግም፡፡ አብረው መዋል፣ አብረው መማር ጀመሩ፡፡ የጀመሩት ጓደኝነት ሁለቱንም ፍፁም ደስተኞች አደረጋቸው፡፡ ቅርርባቸው ወደ ፍቅር የማምራት አዝማሚያ እያሳየ የመጣ ይመስላል፡፡”

“መስሎኝ ነበር” አለች ማህሌት “ነገር ግን በመሀላችን የሚያግባቡን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚያን ነገሮች አስቤ ልርቀው እሞክራለሁ፡፡ ነገር ግን አያስችለኝም መልሶ ይናፍቀኛል”

“የነ አቤኔዘር ዶርም የተለያየ ባህሪያት ያላቸው ጓደኛሞችን የምታኖር ሚጢጢዬ ቤተ-ተውኔት ናት፡፡ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በመተራረብና አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ተንኮል በመስራት ነው፡፡ በቁም ነገር ሰዓት ግን የዶርም ጓደኞቹ አማካሪዎቹም ናቸው፡፡ “ጓደኞቼ ማ የሚመክሩኝ እንድርቀው ነው” አለች ማህሌት፤ ጭንቅላቷ የከበዳት ይመስል በመዳፏ እየደገፈችው፡፡ ሳልሳዊ የታናሽ እህቱ ሁኔታ ያሳሰበው አይመስልም፡፡ ከሚሞነጫጭረው ወረቀት ውስጥ ካሉት ገፀ ባህሪያት እንደ አንዳቸው ሳይቆጥራት አልቀረም፡፡ እየፃፈበት ያለውን ድባብ ወዶታል፡፡ ሲያሻው በገሀዱ ዓለም ሲያሰኘው ደግሞ በገዛ ፍጡራኑ መንደር የመመላለስ ልዩ ስልጣን ያለው ልዕለ-ሰብ የሆነ መሰለው፡፡ እናም መፃፉን ቀጥሏል፡፡  መክሊት በጣም ቆንጆ ነች፡፡ ከተማሪዎች አልፎ መምህራንን ምራቅ ያስዋጠ ውበት ያላት፡፡ ውበቷ ጠላቷ ሆኖባት በአንድ መምህሯ አይን ውስጥ ገባች፡፡ ዘለቀ የተባለ መምህራቸው ቢሮ ድረስ ጠርቷት ለአንድ ምሽት የአንሶላ መጋፈፍ ጥያቄውን እንድትቀበል ካልሆነ ግን “F” እንደሚሰጣት ያሰጠነቅቃታል፡፡ ለአንድ ኮርስ፣ በተለይ በዘለቀ ኮርስ “F” ካመጣች ውጤቷ ከዩኒቨርሲቲ እንደሚያስባርራት ታውቃለች፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ለአቤኔዘር ምንም አልነገረችውም፡፡

“… እና የገጠመኝን ሁሉ ሄጄ ለሱ መዘክዘክ አለብኝ?” አለች ማህሌት፡፡ “ወደደኝ እንጂ አልወለደኝ፡፡ ካንቺ ጋር ካልሆነ በቀር ሚስጥሬን ገላልጬ ከማንም ጋር በነፃነት ማውራት አለብኝ ብዬ አላስብም” አለች ጉዳይዋን ጉዳዬ ብለው እንደ እኩያ ጓደኛ የሚያማክሯትን እናቷን እያየች፡፡ “ከልክ በላይ ድብቅ ሆነሽበትስ እንደሆነ?” አሏት በጥርጣሬ አይን እየተመለከቷት፡፡

አንድ የአቤኔዘር የዶርም ጓደኛ በሆነ አጋጣሚ የአቤኔዘርን ዳያሪ አነበበው፡፡ ዳያሪው ውስጥ አንድ አስደንጋጭ ሚስጥር አነበበ፡፡ ያነበበውን ነገር በማውራቱ ወሬው ተዛምቶ ሁሉም ተማሪና መምህራኑ ጋ ደረሰ፡፡ መክሊት ግን ነገሩን አልሰማችም - ሊነግራት የደፈረ አንድም ተማሪ አልነበረም፡፡ በርግጥም ስለ ፍቅረኛዋ አቤኔዘር እየተወራ ያለውን ነገር ለመክሊት ለመንገር ድፍረትን ይጠይቃል፡፡ ከአቤኔዘር ጓደኞች አንዱ መክሊት ከዘለቀ ጋር ስትሳሳም በማየቱ የመክሊት ድርጊት የሀሜተኞች ወሬ ማጣፈጫ ሆነ፡፡ አቤኔዘር ግን ወሬውን የነገረው ስላልነበር አልሰማም፡፡ አንድ ቀን ከመ/ር ዘለቀ ጋር ቢሮ የሚጋራ መምህራቸው ዳስተር ረስቶ በመምጣቱ ቢሮ ሄዶ እንዲያመጣለት ከፊት የተቀመጠውን ተማሪ ያዘዋል - አቤኔዘርን፡፡ አቤኔዘር የተባለውን እቃ ለማምጣት ወደ ቢሮው ሲገባ ዘለቀ መክሊትን ሊስማት ሲንደረደር ይደርሳል፡፡” ደነገጠ፡

“…. በእርግጥ ልክ ነሽ አንዳንዴ ሁኔታዎች እንዳሻነው አይሆኑልንም ቢሆንም ለፍቅር አጋራችን እንደምንታመን የምናሳይባቸው መንገዶች አሉ” አሉ እናት፡፡ “ለምሳሌ?” አለች ማህሌት፡፡ በተለያየ መንገድ ልታገኘው ብትሞክርም አቤኔዘር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፡፡ በያሉበት ሆነው መነፋፈቃቸው ግን አልቀረም፡፡ አንድ ቀን ናፍቆቱ አላስቀምጥ ሲለው ከዚህ በፊት ከመክሊት ጋር ወደተዝናኑበት መናፈሻ ሲሄድ መክሊትም ትዝታ ጐትቶ ወስዷት ኖሮ ተገናኙ፡፡ ሲተያዩ ደነገጡ፡፡ መክሊት ይቅርታ የመጠየቅያ ቃላት አጥታ ስትንተባተብ “ፈልገሽ እንደማታደርጊው አውቃለሁ ስለዚህ ማስተባበል አይጠበቅብሽም” አላት አቤኔዘር፡፡ የሰማችውን ለማመን ተቸገረች፡፡ “… ድሮውንስ እንዳምነው ይፈልጋል?” አለች ማህሌት፡፡ የማይታመን ሰው ሰውን አያምንም፡፡ ሁሉም ሰው እንደራሱ ይመስለዋል፡፡ ስለዚህ እሱም ስልክ ባናገርኩ ቁጥር በቅናት ፊቱ የሚለዋወጥ ከሆነ ችግር አለበት ማለት ነው” አለች ማህሌት፡፡ “እንደዛ ብሎ መደምደምም ይከብዳል፡፡ የሁለታችሁን አብሮነት የማይሻ ሌላ ሰው ውሸት እያቀናበረ ይነግረውስ እንደሁ?” አሉ እናት፡፡ “እማ ደግሞ እንዲህ ቢሆንስ፣ እንዲያ እንደሆነስ ማለት ትወጃለሽ፡፡ የውሸት ወሬ ፈጥሮ ሊያጣላን የሚፈልግ ሰው አለ ብዬ አላስብም፡፡ አለ ቢባል እንኳን የማንንም ወሬኛ ሳይሆን እኔን ነው ማድመጥ ያለበት፡፡ እንደዚሁም ለመጣላት እያኮበኮብን ነው፣ እንኳን የሰው ወሬ ተጨምሮበት” አለች ማህሌት፤ ስለመጣላት ማውራቷ ስሜቷን እያደፈረሰው “… መደማመጥማ አለባችሁ፡፡ አለመደመማጥ መራራቅን ያስከትላል፡፡ መራራቅ ደግሞ መለያየትን” አሉ እናት፤  የለቀሙትን ምስር ይዘው ከተቀመጡበት እየተነሱ፡፡

ሳልሳዊ ወደሚፅፈው ታሪክ ተሰደደ፡፡ አቀረቀረ፡፡ “ታድያ ከተረዳኸኝ ለምን ትርቀኛለህ” አለችው መክሊት፡፡ “ማኪ ቀድሞውንም የፍቅር ግንኙነት መጀመር አልነበረብንም” አላት አቤኔዘር፤ አይኖቿን ለማየት ድፍረቱን እያጣ፡፡ “ማለት?” አለች ድምጿ እየከዳት …” ከእናቱ እጅ ሸፍቶ የወደቀው የድስት ክዳን የፈጠረው ድምፅ ከገባበት የምናብ ዓለም መንጭቆ አስወጣው፡፡ ቀና ብሎ የሆነውን ካየ በኋላ በድጋሚ አቀረቀረ፡፡ “ደስ የማይል ነገር ልነግርሽ ነው፡፡ እንዳጠፋሽ አጥፍቻለሁ፡ በድዬሻለሁ ማኪ፡፡ ስለኔ የማታውቂው ነገር አለ፡፡ በፍቅር ካንቺ ጋር መቀጠል አልችልም” አላት አቤኔዘር፡፡ “ተረድቼሻለሁ ያልከኝ ውሸትህን ነው ማለት ነው?” አለች መክሊት፤ ማልቀስ እየቃጣት፡፡ “አልገባሽም ማኪ … ዶክተሮች የሞት ቀነ ቀጠሮ የቆረጡልኝ ሰው ነኝ” አለ አቤኔዘር፤ ሳግ እየተናነቀው፡፡ “ምንድነው የምታወራው አቤኒ?” አለችው መክሊት ክፉኛ ደንግጣ፡፡ አቤኔዘር ካቀረቀረበት በቀስታ ቀና አለ፡፡ “ካንሰር አለብኝ” አላት፤ ዝግ ባለ ድምፅ፡፡ መክሊት መናገርም መቆምም ተሳናት፡፡ በቆመችበት ትቷት ሄደ፡፡ “… የለብኝም በፍፁም የለብኝም! ማጥፋቱ ሳያንስ ይቅርታ ጠይቂው ትይኛለሽ?” አለች ማህሌት፤ እናቷ ላይ እያፈጠጠች፡፡ “ይቅርታ ማለት ያለበት እሱ ነው” አለች፤ ቀዝቀዝ ብላ፡፡

መክሊት አቤኔዘርን ልታገኘው ብትሞክርም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ የምርቃት ጊዜያቸው ደረሰ፡፡ አቤኔዘርና የዶርም ጓደኞቹ በሙሉ በሙሉ ልብስ ዝንጥ ብለው በመዝናናት ላይ ነበሩ፡፡ የአንዳቸው ስልክ ጠራ፡፡ በጓደኞቻቸው የሚገርም ድራማዊ ቅንብር አቤኔዘርና መክሊት ለመታረቅና ፍቅራቸውን ለመቀጠል ቻሉ …”

“ቢንጐ!” አለ ሳልሳዊ ካቀረቀረበት ቀና እያለ፡፡ ሁኔታው ማህሌትን አበሳጫት “ቆይ አንተ የኔ ጉዳይ አያሳስብህም? ያለ ሀሳብ ትፅፋለህ?” ብላ ወረቀቱን ከጠረጴዛው ላይ አንስታ አጨራምታ በቅርብ የተገኘ የውሀ ባልዲ ውስጥ ከተተችው፡፡

 

 

Read 4224 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:49