Print this page
Saturday, 28 January 2012 12:14

የህልሜ መስተዋት

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(0 votes)

መነሻ ሃሳብ

(የሳሙኤል ኮልሪጅ “በህልምህ የቀጠፍከውን አበባ ስትነቃ እጅህ ላይ ብታገኘውስ” የሚለው የግጥም ሃሳብ)

ጠዋት ላይ ይመስለኛል - ከቁርስ በፊት፡፡ ሥራ የለኝም፤ የእረፍት ቀን ነው፡፡ ቅዳሜ ወይም እሁድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከተገዛች ብዙ ዓመታት ያስቆጠረች የእንጨት አልጋዬ ላይ ቁጭ ብያለሁ እያሰብኩ፡፡ እኔ መስተዋቱ ፊት ልቀመጥ ወይም መስተዋቱ እኔ ፊት ይቀመጥ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እንዲህ ዓይነት ትልቅ የፊት መስተዋት አይቼም አላውቅም፡፡ ፊቴን ብቻ ሳይሆን ልቤንም ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡ የልብ መስተዋት አይታችሁ ታውቃላችሁ?

ጭብጥ የምታህለው ልቤ ንጥር ንጥር ስትል በመስተዋቱ አየኋትና ነገረ ስራዋ አሳቀኝ፡፡

እኔ ብስቅባትም እሷ ግን ነገሬ ያለችኝ አትመስልም፡፡ ዝም ብላ ትዘላለች፡፡ ሥራዋን እየሰራች መሰለኝ፡፡ ልብ ጋ መዝናናት የለማ! እሷ ልዝናና ያለች ቀን እኔ ቀጥ እላለሁ፡፡ ድንገት መስተዋቱ ላይ ባየሁት ነገር ድንግጥ አልኩኝ፡፡ ፊቴም ልቤም የሉም፡፡ በእነሱ ምትክ የፍቅረኛዬ ፊት እንደ ፎቶ ጉብ ብሏል፡፡ ቆንጆ ክብ ፊቷ ይታየኛል - በመስተዋቱ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ የት ነው ያለሁት? ቀስ ብዬ ዙሪያዬን ቃኘሁት፡፡ እዚያችው የተከራየኋት ጠባቧ ክፍሌ ውስጥ ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር እንዳለ ነው - የፍቅረኛዬን ጉርድ ፎቶ ጨምሮ፡፡ ዓይኔን ወደመስተዋቱ መለስኩ፡፡ የፍቅረኛዬ ክብ ፊት የለም፡፡ በቦታው የእኔ ቅርጽ የለሽ ፊት ተተክቷል፡፡

“ዘባራቂ መስተዋት” አልኩና ወደተለመደው ሃሳቤን የማመንዠክ ሥራ ገባሁ፡፡ አሮጊቷ እናቴ ፍቅረኛዬን ካየቻት ጀምሮ አንድ ክፉ አመል አምጥታለች፡፡ “ውለዱ እንጂ!”፣ “አታስረግዛትም እንዴ?” ትለኛለች - በወጣሁ በገባሁ ቁጥር፡፡

ውትወታዋ ሲበዛብኝ እኔው ራሴ አርግዤላት ቁጭ አልኩኝ - ልጅ ሳይሆን ሃሳብ፡፡ የአብራኬን ክፋይ ሳይሆን የጭንቀቴን ክፋይ አረገዝኩላት፡፡ ደስታ ራቀኝ፡፡ በጭንቀት ሰለልኩ፡፡ ወልደው የማይገላገሉት ሃሳብ ደስታዬን ቀማኝ፡፡ ሁለመናዬ በጥፋተኝነት ስሜት ተሞላ፡፡ ተስፋና ደስታ ራቀኝ፡፡ “ደስታ ለምን ከእኔ ራቀ?!” ስል ጮህኩኝ - ወደ  ትልቁ መስተዋት እያየሁ፡፡ የእኔን ያረጀ ፊት መስተዋቱ ውስጥ ጉብ ብሎ ተመለከትኩት፡፡ ተጠራጥሬ ትክ ብዬ አየሁት፡፡ የእኔን ፊት ይመስላል እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ እኔ የ35 ዓመት ጐረምሳ (ጐልማሳ!)፣ መስተዋቱ ውስጥ ያለው የ75 ዓመት  አዛውንት፡፡ “ቅዠት ነው?” አልኩኝ በሆዴ፡፡ “እውነት ነው” የሚል ድንገተኛ ድምፅ ሰማሁ፡፡ ድምፁ የአዛውንት ነው፡፡ ደንግጬ ሳፈጥበት ደንግጦ አቀረቀረ - መስተዋቱ ውስጥ የሚታየው ሽማግሌ ፊት፡፡

“ምንድነህ? ከየት መጣህ?” አልኩኝ ወደ መስተዋቱ እያየሁ፡፡

“የወደፊት ትዝታ አትፈልግም?” አለኝ፡፡ አሁን ገባኝ፡፡ ሳረጅ ምን እንደምመስል እያሳየኝ ነው - የእኔን ፊት የሚመስለው ሽማግሌ፡፡ እኔ ግን ለጊዜው የወደፊት ትዝታዬ አላስጨነቀኝም፡፡ እኔን ያስጨነቀኝ አሁን ደስታዬን መነጠቄ ነው፡፡ እኔን ያስጨነቀኝ ያረገዝኩት ሃሳብ ነው፡፡

“ደስታዬን ለምን ተቀማሁ?” አልኩኝ ለሽማግሌው ሳይሆን ለራሴ፡፡ ቀና ብዬ መስተዋቱን ስመለከት ማንም የለም፡፡  ባዶ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባዶ መስተዋት አይቼ አላውቅም፡፡ የት ገባ ሰውየው?  ሽማግሌው የት ተሰወረ? ለአፍታ በሃሳብ ተዋጥኩኝ፡፡ “ይቅርታ ለውሃ ሽንት ሄጄ ነው” ድምፁን የሰማሁት ከመስተዋቱ ውስጥ ነው፡፡ ቀና ስል ሽማግሌውን አየሁት፡፡

“ሰምቼሃለሁ” አለኝ መስተዋቱ ውስጥ ጉብ ያለው ፊት፡፡ “ደስታህን ማንም አልቀማህም”

“ጅል ሽማግሌ” አልኩ በልቤ፡፡ የሰማኝ አልመሰለኝም፡

“ታስሮ እኮ ነው -  ደስታህን አስረኸዋል”  አለኝ ሽማግሌው፡፡ የሚያሾፍብኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን ፊቱ ላይ ሹፈት አይታይም፡፡

“የት ነው ያሰርኩት?” ከጥያቄ ይልቅ ግራ መጋባቴን የሚያስተጋባ ጥያቄ ሰነዘርኩ

“ልብህ ጓሮ!” መለሰልኝ ሽማግሌው፡፡ ዝም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡

“ተረጋግተህ አስብ…ወደ ውስጥህ ተመልከት” አከለ ሽማግሌው

ለእንዲህ ዓይነቱ እልህ አስጨራሽ ምክር ቅንጣት ትዕግስት እንደሌለኝ ልነግረው ፈልጌ፤

“የእኔ ወንድም እኔ ቅኔ አልፈልግም …ትዕግስቴ ተሟጧል” አልኩት

“አትማረር! ገና ልጅ እኮ ነህ”

“የሚያጽናናኝም አልፈልግም” በቁጣ መለስኩ

“ማረጋጋቴ እንጂ ማጽናናቴ አይደለም” አለ ተረጋግቶ፡፡

“ሙግትም አልሻም መልሱን ብቻ”

“ኧረ ሽማግሌ አይሟገትም” አለኝ በሚያሳዝን ቅላፄ፡

በመሃላችን ለአፍታ ዝምታ ነገሰ፡፡ ቀና ብዬ መስተዋቱን ተመለከትኩ፡፡ ሰውየው ለመናገር አፉን ሲያሞጠሙጥ አየሁትና ዝም አልኩ፡፡

“ልብህ ሁለት ቦታ ደም ቋጥሯል”

ይሄ ሽማግሌ ምናባቱ ነው የሚዘባርቀው ስል - አሰብኩ፡፡

“አልዘባረቅኩም ከልቤ ነው”

ቢቸግረኝ ማሰብ ተውኩ፡፡ እንደቅድሙ መስተዋት አዕምሮዬን ባዶ አደረኩት፡፡ ሃሳብ አልባ አዕምሮ፡፡

“የተቋጠረውን ደም ፍታው” አለኝ ሽማግሌው የምክር ቃና ባዘለ ድምፅ፡፡

“እንዴት?” ሳላስበው ከአፌ ያፈተለከ ጥያቄ ነው፡፡

“በረከቶችህን ቁጠራቸው!” አለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ ብሎ፡፡ የምን በረከት እንደሚያወራ አልገባኝም፡፡

አዕምሮዬን ከሃሳብ ነፃ ማውጣት ስለፈለኩኝ ዝም አልኩት፡፡ ዝም ሲባል አዕምሮ ባዶ ይሆናል የሚል ሳይንሳዊ ጥናት ባይኖርም ለዛሬ ሰርቶልኛል፡፡ ሽማግሌው መዘባረቁን ቀጠለ፡፡

ያው እኔም ሳረጅ እንዲሁ ልዘባርቅ አይደል! የወደፊቱ እኔ እኮ ነኝ መስተዋቱ ውስጥ የምታየው፡፡ የ75 ዓመቱ አዛውንት እኔ፡፡ ሰውን በምክር የማሰለቸው እኔ ቅጂ ነው አሁን የሚያወራኝ፡፡

“ከራስህ ጋር አውራ! ከልብህ ጋር ተማከር … ያኔ የምናብህን አበባ ታገኛለህ”

የመጽሐፍ ጥቅስ የተናገረ ነው የመሰለኝ፡፡ አባባሉን በአዕምሮዬ እያብሰለሰልኩ ቆየሁና ገርሞኝ ወደ መስተዋቱ ተመለከትኩ፡፡

መስተዋቱ በተለያዩ የጽጌረዳ አበቦች ተሞልቷል፡፡ ቀይ፣ ሮዝ፣ ነጭ፣ ሐምራዊ…ገና ያልፈነዱ፣ በከፊል የፈነዱ፣ ሙሉ በሙሉ የፈነዱ … ደሳስ የሚሉ የአበባ ቤተሰቦች፡፡

ለምን እንደሆነ እንጃ አበቦቹ ፍቅረኛዬን አስታወሱኝ፡፡ አንድ ንብ አበቦቹ ላይ እየተፈናጠረች ቆይታ ከመስተዋቱ ወጣችና ከንፈሬ ላይ አረፈች፡፡ በድንጋጤ እየተርበደበድኩ ከከንፈሬ ላይ ላላቅቃት ሞከርኩ፡፡ “እንቅልፋም” አለችኝ - ንቧ ሳትሆን ከጐኔ የተጋደመችው ፍቅረኛዬ፡፡ ከእንቅልፌ ነቅቼ በደንብ አየኋት፡፡

በህልሜ መስተዋት እንዳየኋቸው ውብ አበቦች ፈክታለች፡፡ ደምቃለች፡፡ “የምስራች ልንገርህ?” አለችኝ ልብ በሚሰረስር ጣፋጭ ድምጽ፡፡

“ደስ ይለኛል” አልኳት - በጉጉት

ከንፈሯን ለዓመል ያህል ከንፈሬ ላይ አሳረፈችና “አርግዤአለሁ” አለችኝ፡፡

 

 

Read 4291 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 13:11