Saturday, 28 April 2012 13:01

የቁሻሻ አብዮት

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

የምክንያታዊነት ዘመን እየበቃ ይመስለኛል አንዳንዴ … በበለጠ ይህ ስሜት ደግሞ የሚያጣድፈኝ ወደ መሐል አዲስ አበባ በታክሲም ሆነ በእግር ስገባ ነው፡፡ የፎቅ መብዛት ከምክንያታዊነት እጥረት ጋር ማን በይሆናል ምልክት እንዳስቀመጠው አላውቅም፡፡ለጊዜው ተከራይቼ የምኖረው ወሰን ግሮሰሪ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ ብዙ ዛፎች እና ብዙ ፀጥታዎች ያሉበት ሰፈር ነው፡፡ ዛፍ እና ሰላም አንድ ከሆነ … የዛፍ ችግኝ መተከል ያለበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ሰላም እና መረጋጋት የጠፋበት ስፍራ ላይ፡፡

በታክሲ ውስጥ ሆኜ ብዙ ነገር እየተመለከትኩኝ ወደ መገናኛ የቀለበት መንገዱ ጋ እደርሳለሁ፡፡ ከወሰን ግሮሰሪ ይዤ የመጣሁት ሰላም ከታክሲ ስወርድ አብሮ ይወርዳል፡፡

ከዛ በኋላ ሁሉም ነገር ብዙ ይሆናል፡፡ ብዙ ፀጉር ያለበት ብዙ እራስ ያላቸው ብዙ ሰዎች ጋር በብዙ የመኪና ጡሩንባ ቀለም፣ ድምፅ፣ ሰበቃ፣ ሲቃ፣ … ተጠቅልዬ አቅጣጫዬን ለመወሰን እሞክራለሁ፡፡ የበላሁት ቁርስ ብዙውን ጊዜ በመገናኛ ድልድይ ስር በሆዴ እንደሸሸግሁት ተሻግሮ አያውቅም፡፡ … በአይን  የሰውን ሆድ መስለብ ሳይጀመር አይቀርም፡፡ እንደገና ወደምሄድበት የሚያደርሰኝ አዲስ ቁርስ መመገብ አለብኝ፡፡ መንገዶቹ ሰፋፊ ሆነዋል፡፡ መኪናዎቹ በጣም ምቹ እና ፈጣን ሆነዋል፡፡

መኪናዎቹ አንዳንድ ጊዜ የሰው አካል ይመስሉኛል፡፡ መኪናዎቹን የሚያሽከረክሩት ሾፌሮች ደግሞ አካሉ ውስጥ ያሉ ነብሶች፡፡ አንዳንድ ጊዜ አካልና ነብስ ተመሳስለው አገኛለሁ፡፡ አዲስ እና ቆንጆ መኪና ውስጥ ወጣት እና ውብ ልጃገረድ መሪውን እየጠመዘዘች ስታሽከረክር … ሌላ ጊዜ ደግሞ አካል እና ነብስ ተቃራኒ ይሆኑብኛል፡፡ ቆንጆ አዲስ መኪናን አስቀያሚ ሽማግሌ ሲነዳት አያለሁ፡፡

አውቶብስ አንዳንዴ መንግስትን ይመስለኛል፡፡ በአካሉ ወይንም እጁ ትልቅነት/ሰፊነት ብዙ ህዝብን ተሸክሞ … ከነበረበት ወደ ሚደርስበት የሚያጓጉዝ … የህዝብ አገልጋይ፡፡ የአውቶብስ ሾፌሩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆንብኛል፡፡ … ግን ዘግይቶ ለሚደርስ ተጓዥ በር ቢደበደብለትም አልከፍትም የሚል የአውቶብስ ሾፌርም አለ ለካ፡፡ የግሬደር ነብስ ያለውም ይታያል፤ የገልባጭ፣ የቦቴ፣ የሞተር ብስክሌት … ብዙ አይነት አካል እና ነብስ ያለው አለ፡፡

ወዲያው ደግሞ አንድ የሚያስደንቅ ነገር እመለከታለሁ፤ መኪናና ሰው ያላቸውን ግንኙነት ረስቼ፤ ሰው እና ሞት ያላቸውን ግንኙነት ማገናዘብ እጀምራለሁ፡፡

ከፕላዛ ሆቴል በታች ያለው ድልድይ ስር አንድ ሰው ተጠቅልሎ በጀርባው ተኝቷል፡፡ “ያለው ሀብት የተኛበት መሬት ብቻ የሆነ ብዙ ሰው አለ፡፡ አካሉን ለማኖር ሲል ነብስ እንዳለው የዘነጋ ያጣ የነጣ ሰው፡፡ … የዚህ ሰውዬ አተኛኘትም ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ግን ሰው ተሰብስቦ ቆሞ እያየው ነው፡፡ … ሰውየው የተኛው የድልድዩ የብረት መከለያ ጥግ ነው፤ ግን ጥጉ በእግረኛው መንገድ ጐን ያለው ሳይሆን በገደሉ በኩል ባለው አቅጣጫ ነው፡፡ ከአስፋልቱ የተረፈችው ለወገቡ በማትበቃ ትንሽ ጠርዝ ላይ በጀርባው ብጥስጣሽ ጨርቁን ተሸፋፍኖ ተኝቷል፡፡ በእንቅልፉ ማህበረሰቡን ሰቆቃ ውስጥ ከቶታል፡፡ “ምነው በደረቱ እንኳን ቢተኛ” ይላል፤ ታክሲው ውስጥ ያለው ሰው፡፡ ፖሊሶች ሊቀሰቅሱት ይሞክራሉ፡፡ ቆፍጠን ለማለት ቢጥሩም ሲቀሰቅሱት አስደንግጠው ገደል እንዳይከቱት መስጋታቸው ግን ያስታውቅባቸዋል፡፡

ምክንያታዊ ብሎ ነገር የለም፡፡ እንደ ካርቱን ፊልም፡፡ ከእኔ ጀምሮ ብዙዎቹ የወር ደሞዛቸው፣ ወር ቀርቶ ሳምንቱን በደንብ የሚያስተዳድራቸው አይደሉም፡፡ ግን ወር ሙሉ ይኖራሉ፡፡ ጭራሽ እንዲያውም ሁለት ቁርስ ይበላሉ (እንደኔው) መጠጥም ይጠጣሉ፡፡ ሚስትም አያጡም፡፡ ልጅም የሆነ ቦታ ወልደዋል፡፡ አፈር መስለዋል እንጂ ገና አፈር ተምሶ አልተቀበሩም፡፡

ደሞ ሙዚቃ አለ፤ ዋናው ማደንዘዣ … አንዱ ዘፍኖ ሲጨርስ … ሌላው ይተካል፤ ቀኑን ሙሉ፡፡ አንደኛው የሬዲዮ ጣቢያ ከነታክሲው ጥለነው ስንሄድ፣ ሌላኛው በወረድኩበት ቦታ ላይ በአነስተኛና ጥቃቅን ሱቅ፣ ካፌ፣ ቡቲክ፣ የሞባይል መሸጫ ይቀበልሀል፡፡ በተጨማሪ በአንድ የጆሮ ማዳመጫ ሁሉም የሆነ ነገር ያዳምጣል፡፡ “የምናሰራጭበትን ምክንያት አናውቀውም … የምታዳምጡበትን ምክንያት አትወቁ” የሚል መልዕክት ከጆሮ ማዳመጫው ጋር አብሮ የተሸጠ ይመስላል፡፡ ምክንያት የለውም፤ የት እንደምሄድ አንዳንድ ጊዜ አላውቅም፡፡ ብቻ ሰላሳ ሳንቲም ወያላው ሲመልስልኝ ሶስት ብር ሰጥቼው እንደነበር ይገባኛል፤ ከሀሳቡ ለጊዜው መለስ እላለሁ፡፡

አሁን ደግሞ ሌላ ታክሲ ውስጥ ነኝ … ጋቢና ነው የተቀመጥኩት፡፡ ዞር ብዬ ሾፌሩን ተመለከትኩት፡፡ ለአስር አመት ጓደኛዬ የነበረ ልጅ ነው፡፡ ታክሲ ውስጥ አይደለሁም ያለሁት ወይንም ጓደኛዬ ታክሲ ሾፌር ሆኗል ማለት ነው፡፡ … ሰላሳ ሳንቲም አልተመለሰልኝም፤ ስለዚህ ጉዞው በነፃ ነው፡፡ ሌላ ተሳፋሪም የለም፡፡ … በስራ እንዴት ሲደክም እንደዋለ እያወራልኝ ነው፡፡ ቢራ ልጋብዝህ እፈልጋለሁ ሲል እንደገና ነቃሁ፡፡ ምክንያታዊ ባይሆንም አነቃኝ፡፡ እኔ ከሱ ጋር በስራ ስደክም አልዋልኩም፡፡ ግን ሳልለፋ ሊጋብዘኝ ነው፡፡

አሁን ደግሞ ከምሽቱ አምስት ሰአት ሆኗል፡፡ ብዙ ቦታ መዞራችንን ያወቅሁት ያለሁበት ቦታ ስለጠፋኝ ነው፡፡ ብዙ ያዞረኝ የጓደኛዬ መኪና ይሁን ጓደኛዬ ያጠጣኝ ቢራ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምክንያታዊ ባልሆነ አለም ላይ እርግጠኛ መሆን አደገኛ ነው፡፡ በቢራው እየነዳ ሲያዞረኝ … ሌላ መኪና ውስጥም ገብቻለሁ … ነጭ መኪና ነው፡፡ “አብስሉት ቮድካ” ሲለኝ ትዝ ይለኛል፡፡ የምሄድበትን አላወቅሁም፡፡ ከምሽቱ አምስት የሚለው አስራ አንድም ማለት ነው፡፡ የፈረንጅ መጠጥ ነው የፈረንጂ መኪና … ፈረንጅ የሚበዛበት ቤት ውስጥ ነኝ … ምናልባት ፈረንጅ ሀገር ገብቼ ይሆን? … በፈረንጅ ስካር ነው እንዴ ፈረንጅ ሀገር የሚፈጠረው?

ቤቱ በሰው ተሞልቷል፤ ሰው ወደ አንድ አቅጣጫ አፍጥጦ እየተመለከተ ነው፡፡ ከፍ ብለ የተሰራች መድረክ አለች፡፡ … አንዳንዴ በታክሲ ውስጥ እየሄድኩ ከፊቴ የተቀመጠውን ሰው ድንገት ብኮረኩመው ምን ይለኛል? ብዬ የምወሰወሰው ነገር አለ፡፡ በዛው መጠን አንዳንዴ ደግሞ ካልታሰበ አቅጣጫ የድራፍት ጠርሙስ ተወርውሮ ሊበረቅሰኝ መስሎኝ ውቃቤዬ ሽምቅቅ የሚልባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ አሁን መድረኩ ላይ እንዲወጣ የሚጠብቀውን ነገር በማሰብ፣ የሁለቱ ስሜቶች ድብልቅ ተሰማኝ፡፡ የቢራው እና የአብሱሉት ቮድካው መኪና ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ የሄዱት እኔነቶች ድንገት ተጋጩብኝ፡፡ ወደ ውጭ የማስታውክበት አቅም ግን አጣሁ፡፡

ስትጠበቅ የነበረችው “ጉዳችን” ወጣች Pole dancer … የአበሻ ሴትን ሰውነት የትም ቦታ ባየው አውቀዋለሁ፡፡ ባታቸው ቁጥር ያለ ነው፡፡ ቆዳቸው ተለጥጦ የተመለሰ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ ሁሉም ወፍረው የከሱ ናቸው፡፡ ሁሉም ከሆነ ባህር ማዶ የተመለሱ ናቸው፡፡ ሲመለሱ ወፍረው ነው፤ ቆየት ሲሉ የብረት ዘንግ ፈልገው ይንጠለጠሉበታል፡፡ ቂጧን መስበቅ ጀመረች፡፡፡ ያላትን ነገር ሁሉ አሳየችን፡፡ እናቷ የሰጠቻትን ሀብት ሁሉ፡፡ ቻይና ራቁት ገላዎች አካባቢ ለምን እንደማይጠፋ አይገባኝም፡፡ አሁን ህንድም ተጨምሮበታል፡፡ ፓንቷ ውስጥ መቶ ብር እየጨበጡ ይወሽቁላታል፡፡ “የኢትዮጵያዊ ሴቶች …ናቸው” ሲለን ልንደበድበው የደረስነው ጀርመናዊ ትዝ አለኝ፡፡ መድረኩ ላይ የለቀመችው ብር ስላልበቃት፣ ዘመናዊዋ እማማ ኢትዮጵያ ከመድረኩ ወርዳ እያንዳንዱ ሰው ጭን ላይ እየተቀመጠች በመውረግረግ የስሜት ኪስ ማውለቅ ጀመረች፡፡ እኔ የነበርኩበት ቦታ ላይ ስትመጣ … ሽንት ቤት ውስጥ (እያስመለስኩ) ስለነበረ … ሳላገኛት ቀረሁ፡፡ ከሄድኩባቸው የተለያዩ የስካር መኪናዎች ወርጄ በጓደኛዬ አግባቢነት ኮንትራት ታክሲ ያዝኩ፡፡ … ታክሲ ሹፌሩ ሰላሳ ሳንቲም ሳይሆን ሰላሳ አይነት ነገር አወራልኝ፡፡ መለሰልኝ፡፡ የሆነ መጠነኛ ምክንያታዊነት ወዳለው … ዛፍ ወደ በዛበት ሰፈሬ እየተቃረብን ስንወጣ፣ የታክሲ ሾፌሩ ወሬ እየቀነሰ የእኔ ደግሞ ከፍ እያለ ሄደ፡፡  ወደ ሰላማዊ ቤቴ ገባሁ፡፡ ገብቼ ግን አልቀርም፡፡ ነገ በዞረ ድምር የወፈረ ጭንቅላቴን ይዤ ተመልሼ እወጣለሁ፡፡

ለመውጣት መግባት፣ ለመመለስ መሄድ … ለመኖር መሞት … ላለመሆን መሆን … ይሄ ሁሉ እንቆቅልሽ ለምን ይሆን? ብሎ ለመጠየቅ እንኳን ፋታ የለም፡፡ … ነብሴ በእንቁላል መምቻ ውስጥ ገብቶ እየተበጠበጠ ነው፡፡ …. አስኳልነቱን ከእንግዲህ የፈለገ መበጥበጡ ቢሰክን ተመልሶ አይገኝም፡፡ … ወደ ልጅነቴ ተመልሼ ማልቀስ ወይንም መሳቅ ፈለግሁ፡፡ … “ከሰማይ በታች አዲስ ነገር የለም” ያለው ሰውየው በእኛ አይነት የጭንቀት ዘመን ውስጥ ሆኖ አይደለም፡፡ የማያውቀውን ስሜት ግን እንዴት እንደዛ ብሎ በጥሩ ቃል ገለፀው? ይሄም ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ይኼንኑ ምክንያት አልቦ ታሪኬን እንደሚከተለው ለመግለፅ በእንቅልፍ ልቤ ተነሳሁ፡፡

የሰው ልጅ ታሪክ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ሰባት ኪሎ አመትም … እንደ ዝግመተ ለውጡ ሁለት ሚሊዮን የዝንጀሮ ዘመንም አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ ሰላሳ አራት አመቱ ነው፡፡ የተወለደው እኔ የተወለድኩ እለት ነው፡፡ የሚሞተው ግን እኔ ሳልሞት በፊት ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ ታሟል፡፡

ነፍስ ካላየሁበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ታሪክ ከታላቅነት ወደ ታናሽነት ሲቀየር ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ ከአውራሪስነት ወደ ዝንብነት የመቀየር አቅም እንዳለው ማወቅ እስኪሳነኝ ድረስ … ማስተዋሌ ተቆጣጥሮ እንደ ጅማት ሲገመድ ተመልክቻለሁ፡፡ የቱ ጋ ቆሜ እንደተመለከትኩ ብቻ አላውቅም፡፡

አንበሣ አህያ መጀመሪያ ስትጮህ የሰማ ጊዜ ተደብቆ ነበር አሉ፡፡ እንደዛ አይነት ሀያል ድምፅ የሚያወጣ ፍጥረት በአካል ምን ሊመስል እንደሚችል በፍርሀቱ አውቆ ተደበቀ፡፡ እኔም ታሪክን ፈርቼው ነበር፡፡ የሚያወጣው ድምፅ ከጆሮዬ የድፍረት አቅም በላይ ሆኖብኝ ተደብቄ … ተንበርክኬ ነበር፡፡ ለካ ታሪክ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ ጋር ነው የተወለደው፡፡ ከእስትንፋሴ ትንሽ ቀደም ብሎ፡፡

አባቴ ከየት እንደመጣ አላውቅም፡፡ ምናልባት እኔ ነኝ እድሜውን ጨምሬ የወለድኩት፡፡ ስለዚህ እኔም የሱ፣ እሱም የኔ አርአያ ልንሆን አልችልም፡፡ ታሪክ ሰላሳ አራት አመቱ ነው፡፡ የታሪክ ተስፋና ትዝታ ደግሞ ወልጄ ጐዳና ላይ እንዲያድጉ የጣልኳቸው ልጆቼ ናቸው፡፡ … በየቀኑ ሳንቲም ይለምኑኛል፡፡ በኩርኩም ልቀጫቸው እሞክራለሁ፡፡

ታሪክ ከአውራሪስነት ወደ ጅብነት አልተቀየረም፡፡ ታሪክ ድሮውኑ ዝንብ ነው፡፡ ይበርራል፤ የሚበርረው በአውሮፕላን ውስጥ ሆኖ እንደሆነ ሊያስብ ይችላል፡፡ አውሮፕላኑን እሱ የሰራው ይመስለዋል እንጂ ተሰርቶለት የተሰጠው ነው፡፡ በማን? ካላችሁኝ መልስ የለኝም፡፡ ከዝንብ የአስተሳሰብ ምህዳር ውጭ ለማሰብ በመሞከር ነው ድሮውኑ ታሪክ ራሱ ሰባት ኪሎ አመት አድርጐ ራሱን የመዘነው፡፡ ራሱን በራሱ እጅ ላይ አድርጐ የመዘነ ማነው? … ዝንብ? … አባቴ የእኔ እንቁላል ነው፡፡ እናቴ ደግሞ የአባቴ እንቁላል ትዝታ ነች፡፡

ቃላቶቻችንም ከአውራሪስነት ወደ ዝንብነት ተቀይረዋል ይባላል፡፡ ማን እንደሆነ ይሄንን ያለው ባላውቅም  እኔ  እንዳልሆንኩ ግን  እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔ ነኝ ታሪክ፤ እኔ ካልሆንኩ ቃላቶቹን ከአውራሪስ ወደ ዝንብ የቀየሩት ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል፡፡ እግርን በጭንቅላት ላይ ከማሸት ውጭ/የበለጠ ሙከራ አድርጌ አላውቅም፡፡ ማድረግም አልችልም፡፡ የሚያሰናክል በዝቷል፡፡

የማያውቅ እንደሚያውቅ በሆነበት ጊዜ ላይ ራስን ማወቁ ጥቅም የሌለው ነገር ነው፡፡ የዝንብ አብዮት የሚፈነዳው ከቁሻሻ ስፍራ ላይ ነው፡፡ እሽ! ሲባል አብዮቱ ይበተናል፡፡ ቁሻሻው እስካለ አብዮቱ በመሰብሰብ እና በመበተን መሀል ሲወራጭ ተተኪ የዝንብ እንቁላሎች ከእጭ … እስከ አዋቂ ዝንብ ያድጋሉ፡፡ እሽ ካላሉኝ የእኔም ታሪክ አያልቅም፡፡ ግን እኔ “እሽ” ከመባሌ ቀደም ብሎ ተነስቼ በራሴ ፍርሐት አባራሪነት በርሬአለሁ፡፡

የዝንብ ህልውና ላይ በርሮ እስከ መጨረሻው መሰወርም … ወይንም እስከ ሁሌ አርፎ መቀመጥም አይቻልም፡፡ በተለያየ ቁሻሻ አብዮት ላይ ማረፍ እና ቁሻሻን መሞቅ … በሙቀቱ ላይ መውለድ … ከዛ ደግሞ በእንቢታ ውስጥ ከእለታት አንድ ቅፅበት “እሽ-ታ” ሲመጣ በፍርሀት ደንብሮ ተነስቶ መብረር፡፡

ይኸው ነው የዝንብ ታሪክ በአጭሩ … ታሪኬ በአጭሩ፡፡ የተዋጣላት የዝንብ አብዮተኛ ገድሉን ትልቅ የሚያደርገው … የፍሊት እቃ ላይ በማረፍ ነው፡፡ ወይንም በሽቶ እቃ ላይ … በንፁህ ህሊናው ንፁህ ነገር ላይ ከማረፍ እና በአረፈበት ነገር ምክንያት እንዲሞት ከመጓጓት በስተቀር ገድል የለውም፡፡

የእኔ ታሪክ የሁሉም ነው፡፡ … የዝንብ ታሪክ አንድ ነው፡፡ ይኼንን አንድ ታሪክ ብዙ አድርጐ በመተረክ የታሪክ እድሜ ይረዝማል፡፡ መጀመሪያ የዝንብ ዘር መገኛ ከሆነችው የዝንብ አፅም ጀምሮ እኔ ድረስ ተረት ይተረተራል፡፡ ይተረታል ሳይሆን ይተረተራል፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ ታሪክ የሚሰፋው በተተረተረው ክር ነው፡፡ ቀለሙም … ርዝመቱም .. አንድ አይነት የሆነ ክር፡፡ ታሪክ ታሟል፤ የእድሜውን ነገር ተገንዝቧል፡፡ እድሜው ሰላሳ አራት ነው፡፡ እድሜው ቢረዝምም ቢያጥርም ዝንብነቱን ወደ አንበሳ ወይንም አውራሪስ አይቀይርለትም፡፡

ዝንብን እባብ ሲያሳስተው … ተሳሳቹ እውነትም ድብን አድርጐ ተሳስቷል፡፡ የተሳሳተው በሁሉም ነገር ነው፡፡  ለመሳሳት ራሱ ከፍ ያለ ፍጥረት መሆን ይጠይቃል፡፡ ለህዝብ ስህተት የለም፡፡ ሁሉም ትክክል ነው፤ ስህተቱን በመሳሳት ነው የሚያርመው፡፡ የሚያርመው እና ትክክል የሚያደርገው፡፡ ዝንብን እባብ አያሳስተውም፡፡ ዝንብን እባብ ስራ ፈትቶ አያየውም፡፡

ሰው ነኝ ብሎ የሚያስብ ዝንብ ግን እባቡ ሳያየው ታይቻለሁ ብሎ መፅሐፍ ለመፃፍ … ይቆጣል፡፡ … ቁሻሻ አብዮቱን ያፋፍማል፡፡ ቁሻሻ እንኳን መፍጠር የማይችል ዝንብ እንዴት አድርጐ ነው የቁሻሻ አብዮት ቀሰቀስኩ የሚለው? …

ስለዚህ ታሪክ አያስፈልገኝም … ታሪክ እኔ ነኝ … 34 አመታት ሆኖታል የሰው ልጅ የቁሻሻ ታሪክ፡፡ … ዝንብ ተወልዶ ለመብረር ሲሰለጥን አርጅቶ ህይወቱ አልፏል፡፡ ታሪኩ በጣም አጭር ከመሆኑ የተነሳ … መነሻውን ወይንም መድረሻውን ቁብ ሊሰጠው አይችልም፡፡ መነሻውን ለማየት አንገቱን ሲዞር መድረሻው የሸረሪት ድር ሆኖ ይቀልበዋል፡፡

 

 

Read 2979 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 13:10