Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 January 2012 14:11

ተንከባክባ ያላሳደገችውን ልጅ የእገሌ ልጅ እኩያ ነው ትላለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንዳንድ ታሪካዊ እና አፈ - ታሪካዊ ተረቶቻችን አመጣጣቸው አስገራሚ ነው፡፡ የሚከተለው አንዱ ነው፡፡ ስለ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም የተነገረ ነው፡፡ ከደሴ ወደ መቀሌ ሲኬድ ባለው መንገድ ላይ በምትገኘው ሐይቅ ከተማ የሐይቅ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አለ፡፡ የደሴቱን አፈጣጠር በተመለከተ የሚነገረው ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡ አሁን ገዳሙን ከቦ የምናየው ሐይቅ ከዚህ ቀደም በዚህ መልክ አልነበረም፡፡ አመጣጡ እንዲህ ነው፡፡ እዚያ አገር አንዲት በጣም ሀብታም፤ ትጭነው አጋሰስ፣ ትለጉመው ፈረስ የነበራት፣ ለምድር ለሰማይ የከበደች ሀብታም ሴት ትኖር ነበር፤ ይባላል፡፡ ይህቺ ሴት ከአገልጋዮችዋ አንዷን ትጠራና “ይህንን እህል በዛሬ ሌሊት ፈጭተሽ እንድታድሪ” ስትል ቀጭን ትዕዛዝ ትሰጣታለች፡፡ አገልጋይቱ ቀኑን ሙሉ በዚህም በዚያም ሥራ ተጠምዳ የዋለች በመሆኑ፤ “ይህን ሁሉ እህል በአንድ ሌሊት እንዴት ለመፍጨት ይቻለኛል” ስትል ስትጨነቅና ስትጠበብ ትቆያለች፡፡ ፍቃደ ልቦናው ቢኖራት እንኳ የዛለ ክንዷና የላመ ጉልበቷ የሚታዘዛት አልሆነም፡፡ ስለዚህ፤ ትጨነቅና፤

“ወላዲተ አምላክ፤ እኔ ደክሞኛልና አንቺ ፍጪልኝ” ብላ ተማጥና ትተኛለች፡፡ ጠዋት ተነስታ ወዳስቀመጠችው እህል ብትሄድ፤ እህሉ በሙሉ በሚገባ ተፈጭቶና ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኖ ታገኘዋለች፡፡ ሁኔታው ያልጠበቀችው ነበርና እጅግ አድርጐ ያስገርማታል፡፡ ይህን ወላዲተ አምላክ ያደረገችላት መሆኑን በመገንዘብ ከልቧ በማመስገን የተፈጨውን እህል ወስዳ ለእመቤቷ ባለሟል ትሰጣለች፡፡

ባለሟሉም ለእመቤቲቱ ሲያስረክብ እመቤቲቱ ነገሩን በጭራሽ ለማመን አልቻለችምና አገልጋይቱን ታስጠራታለች፡፡ ከዚያም፤

“ይህን እህል ስትፈጪ እኔም ሆንኩ ሌላ የቤተሰቤ አባል አላየሽም፡፡ በጭራሽ አንቺ የፈጨሺው አይደለም፡፡ ላልሠራሽው ሥራ ደግሞ ሊከፈልሽ አይገባም፡፡ ስለሆነም ደሞዝሽን አልከፍልሽም” ትላታለች፡፡

አገልጋይቱም፤ “የተሰጠኝ የሥራ ኃላፊነት እህሉን መፍጨት ነው፡፡ የሰጠሽኝን እህል በሙሉ ዱቄት አድርጌ አስረክቤያለሁ፡፡ ደሞዜን የምታስቀሪበት ምክንያት የለም” ስትል ትሟገታለች፡፡

ነገሩ በሽማግሌ እንዲታይላትም ትማጠናለች፡፡

ሽማግሌዎቹ ለሀብታሟ እመቤት ያዳሉና “እህሉን በምትፈጪበት ሰዓት ያየሽ ማንም ሰው ባለመኖሩ፣ ባልሠራሺው ነገር ይከፈልሽ ብለን ለመፍረድ አንችልም፡፡ ስለሆነም ሊከፈልሽ አይገባም ነው የምንል” ሲሉ ይፈርዱታል፡፡

አገልጋይቱም፤ “ፍትሕ ተዛብቶብኛል፡፡ እረኞች ይዩልኝ” ስትል ትጠይቃለች፡፡

እመቤቲቱም፤ “መልካም ነው፡፡ እረኞች ይዩልሽ” ብላ ፈቅዳ ወደ እረኞቹ ዘንድ ትወስዳታለች፡፡

እረኞቹ ግራ ቀኙን ካዳመጡ በኋላ፤

“አንቺ ያቀረብሽው እህሉን ነው፡፡ የምትፈልጊው እንዲፈጭልሽ ነው፡፡ አገልጋይቱ የተፈጨውን እህል አምጥታልሻለች፡፡ የትም ትፍጨው የተፈጨውን እህል አስረክባሻለች፡፡ ስለዚህ የፈጨችበትን ልትከፍያት ይገባል” ሲሉ ለአገልጋይቱ ይፈርዳሉ፡፡ እንዲከፈላትም ያደርጋሉ፡፡

“የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚለው ተረት የመጣው እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡

ታሪኩ ይቀጥላል፡፡ ይህ ፍርድ በተሰጠ ሌሊት ከባድ ዝናብ ይጥላል - መብረቅ የቀላቀለ፡፡ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ የሰጡት ሽማግሌዎች ሠፈር፤ በውሃ ይጥለቀለቅና ይሰጥማል፡፡ ከመሬቱ ውሃ ይመነጫል፡፡ ዙሪያ ገባው ውሃ ይሆናል፡፡ እነዚያ የተስተካከለ ፍርድ ለአገልጋይቱ የሰጡት እረኞች መንደር ግን አልሰጠመም፡፡ የዛሬው ገዳም ያለበት ደሴት እነሆ ያ ነው፡፡

***

ስትፈጪ ካላየሁ ሞቼ እገኛለሁ ከሚል ጌታ ይሰውረን፡፡ ለጌታ ካደረ ዳኛ/ የአገር ሽማግሌ ያድነን፡፡ ዕውነተኛ እረኞችን ያበርክትልን፡፡ መንገዶች ሁሉ ወደ ብልጽግና ያመሩ ዘንድ የሚዛናዊ ፍርድ፣ የፍትሕ ርትዕ አስፈላጊነት ዐይንን የማያሳሽ ጉዳይ ነው፡፡ ለጌታ ማደርን፣ ወገናዊነትን፣ እከክልኝ ልከክልህን፣ ሐሳዊ ዲሞክራሲያዊነትን፣ ከመሬት ተነስቶ ዘራፍ ማለትን፣ በጊዜ የምንቀጭበትን ዘዴ መዘየድ ዛሬም አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ፀሐፍት “ከጦርነትና ከሁከት ጊዜ ይልቅ በአሸናፊነትህና በሰላም ወቅት የምታደርገው ሁሉ ለአደጋ የተጋለጠ ነው” ይላሉ፡፡ አሸናፊነት ልብ ይነፋል፡፡ ግራና ቀኝ ከማየት ያግዳል፡፡ መንገዶች ሁሉ ለእኛ ብቻ የተቀደዱና የተቀየሱ፣ ለኛ ብቻ አልጋ በአልጋ የሆኑ እንዲመስለን ያደርጋሉ፡፡ “ሹመት በሸተተው ማግስት አካሄዱና አረማመዱ ሁሉ እንደድመት ኮርማ ይሆናል” እንዳለው አንዱ የኛ ፀሐፊ፤ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አኳያ ወይስ ለግል ዝና የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ “በጊዜያዊ ድል አንኩራራ” ሲል የነበረው ያለፈው ሥርዓት፤

“እንኳን አሁንና ብዙ ትጥቅ እያለን

በጦር በጐራዴ ታንክ እንማርካለን”

እያለ ቆይቶ የሆነውን አይተናል፡፡ “እንኳን አሁንና በራሳችን ገንዘብ የራሳችንን ልማት እያካሄድን ዱሮም በሰው ገንዘብ ብዙ ልማት አይተናል” እንዳንል መጠንቀቅ ያሻል፡፡ በአካልም በመንፈስም ዝግጁ የሆነ ማህበረሰብ ሳንፈጥር ይሄንና ያን እናደርጋለን ብለን መፎከር ወንዝ አያሻግረንም፡፡ ሁሉንም ነገር ከህዝቡ ፍላጐትና ፍቃደ ልቦና ጋር ማድረግና ማሰናሰል፣ ደስታውንም ሆነ ሐዘኑን ለመካፈል ይጠቅማል፡፡ ጥረታችን ሁሉ እንደ ዱሮ ደራሲያን አባባል…”ከዚያም በተድላና በደስታ ለዘለዓለም ኖሩ” የሚል ብቻ እንደማይሆን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ህዝቡ ስሜቱን በየጉዳዩ ላይ መግለፅ ይኖርበታል፡፡ እንዳያማህ ጥራው መሆን ግን የለበትም፡፡ እኔ ብቻ ተናግሬ ተወያዩ ለማለትም መሞከር ምፀታዊ ነው! “ዝም በል ብዬሃለሁ!” አለና አብራራው” (Shut up! He explained) እንደተባለው ይሆናል፡፡

ነገሮች ሁሉ ወደ አንድ አሸንዳ እንዲፈሱ ማድረግ የታሪክ ምፀት ነው፡፡ የሁሉም ጥፋቶች ምክንያት አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም፡፡ አለበለዚያ “እንብላም ካላችሁ እንብላ!” አንበላም ካላችሁ እንብላ” እንዳለው ጅብ እንዳይሆንብን ምክንያቶችን፣ ሰበቦችንና ልምዶቻችንን እንመርምር፡፡ የመናገርን ነፃነት ይበልጥ በመልቀቅ ፍሬ እናፈራለን እንጂ ለጉዳት አንዳረግም፡፡ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ለቁጥጥር ሳይሆን ነፃነትን ለማስፋፊያ ተብለው መቀረፅ ይኖርባቸዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን፤

“በህዝብ ግንኙነት ኢንዱስትሪ ውስጥ ያልተነገረው ታላቅ ስላቅ” የሚለን ሪክ ዴቪስ፤ “በዩናይትድ ስቴስት በ1920ዎቹ የሰፊውን ህዝብ ኢ-ምክንያታዊ ስሜት ለመቆጣጠር የዘረጉት መረብ ሲሆን፤ ውጤቱ ግን በዓለም ጭራሹን ገንኖ እንዲወጣ ማድረግ ሆነ፡፡ የሚለው ዕውን ይሆናል፡፡ “በታፈንክ ቁጥር ነው ድምፅህ ይበልጥ የሚጠራ” እንዳለው ነው የኛ ፀሐፌ ተውኔት፡፡

በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው ረገድ፤ (ያንንም ቢሉ ህዝብ በሚያውቀውና በሚገባው መንገድ) እየተጓጓዝን ኢኮኖሚውን አለመዘንጋት፤ መመሪያዎችን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ስህተትን ለማረም ምንም ጊዜ አይረፍድም፡፡ መዘዘኛው አባዜ የሚመጣው “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ያልን እለት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ህይወቱ ያስመረረው ህዝብ ለብዙ ነገሮች ጆሮው ዝግ ይሆናል፡፡ እንዲያውም ፈረንጆቹ እንደሚሉት፡- “ይሄ ቀን፤ አሣ ቢሆን ኖሮ መልሼ ወደ ውሃው እወረውረው ነበር” የሚልበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ህይወቱን በሚገባ ሳንንክባከብለት፣ “ስትፈጪ አላየሁምና ደሞዝ አይከፈልሽም” እንዳለችው ዕመቤት፤ ብንጫነው፤ ደግ አይሆንም፡፡ ከጎረቤትና ከሌላው ዓለም በኢኮኖሚክስና በስታቲስቲክስ ልናወዳድረው ብንሞክር፤ “ተንከባክባ ያላሳደገችውን ልጅ የእገሌ ልጅ እኩያ ነው ትላለች” እንደሚለው ተረት ይሆንብናል፡፡ ከየትም ከየትም ብዬ ብቻ በልቼ ልደር የሚለው ሰው እየበዛ ነውና!

 

 

Read 3501 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 14:15