Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 February 2012 11:59

ከረጅም ጋር ሲሄድ የዋለ አጭር፣ ሲያቃስት አደረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንዲት አሮጊት ዐይናቸውን በጣም ይታመማሉ፡፡ አንድ ሐኪም ስለህመማቸው ያማክራሉ፡፡ በእማኞች ፊት ውል ይገባሉ፡፡

አሮጊቷ -  እንግዲህ ውላችን ዐይኔን ካዳንክልኝና በደንብ እንዲያይ ካደረግህልኝ ከፍተኛ ገንዘብ እከፍልሃለሁ፡፡ታድነኝካልቻልክግንበነፃትሰናበታለህ፡፡

ሐኪሙ - ባሉት ሙሉ በሙሉ ተስማምቻለሁ፤ ይሄንኑም በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፡፡

ይፈራረማሉ፡፡

ሐኪሙ በውሉ መሠረት መድኃኒት ያዝላቸውና ህክምናቸውን ይጀምርላቸዋል፡፡ በየጊዜው እየመጣም ይጎበኛቸዋል፡፡

ሆኖም መጥቶ በሄደ ቁጥር አንዳንድ የቤት ዕቃ ይዞባቸው ይሄዳል፡፡ ይሄን ዕቃ ይዞ መሄድ በጣም ይደጋግመዋል፡፡

በዚሁ ቀጠለና ልክ መድኃኒቱ ሲያልቅ የቤት ዕቃው ተወስዶ አለቀ፡፡ አሮጊቷ ቤቱ ባዶ እንደቀረ አዩና፤

“አምሥት ሳንቲም አልከፍልህም” አሉት፡፡

 

 

“ሠርቻለሁ፡፡ የሠራሁትን መከፈል አለብኝ” አለ በቁጣ፡፡ ደጋግሞ እንዲከፍሉት ጠየቃቸው፡፡ ደጋግመው፤ “ንብረቴን ዘርፈሃል ስለዚህ ድምቡሎ አልከፍልህም!” አሉት፡፡

“ፍርድ ቤት ወስጄ እገትርዎታለሁ!”

“እሱን እናያለን፡፡ ማን ልብ እንዳለው አሳይሃለሁ”

ከሰሳቸው፡፡

ፍርድ ቤት ቀርበው ተጠየቁ፡፡

ዳኛው  - “ከሳሽ የሚለውን ይቀበላሉ?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡

አሮጊቷ - “ክቡር ፍርድ ቤት! ከሳሼ ያለው ትክክል ነው፡፡”

ዳኛው  -  “ታዲያ ምን ይላሉ? ምንድን ነው መከላከያዎ?”

አሮጊቷ -  “እርግጥ ነው፡፡ እሱ ዐይኔን ሊያክመኝ፤ ካዳነኝ ደህና ገንዘብ ልከፍለው ተስማምተናል፡፡ እሱም በበኩሉ ካላዳነኝ ምንም ላይከፈለውና በነፃ ወደቤቱ ሊሄድ ተስማምተናል፡፡”

ዳኛው - “እሱም ያለው ይሄንኑ ነው፡፡ ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ?”

አሮጊቷ - “አሁን እሱ አድኜሻለሁ ይላል”

ዳኛው  -  “እርስዎስ?”

አሮጊቷ -  “እኔማ፤ አላዳነኝም ጭራሽ የበለጠ አሳውሮኛል ነው የምለው፡፡”

ዳኛው  -  “ለዚህ ኮ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል”

አሮጊቷ -  “አሳምሬ አቀርባለሁ ጌታዬ”

ዳኛው  -  “ጥሩ፡፡ ያቅርቡ”

አሮጊቷ -  “ክቡር ፍርድ ቤት፤ ዐይኔን ባመመኝ ሰዓትና እሱ እንዲያክመኝ በጠራሁት ጊዜ የተወሰነ የማየት ችሎታ ነበረኝ፡፡ ያኔ በማይበት አቅም በቤቴ ውስጥ የተወሰነ የቤት ዕቃና ሌላም ንብረት እንደነበረ እገነዘባለሁ፡፡ አሁን፤ እሱ አድኛታለሁ በሚልበት ጊዜ ግን፤ ምንም ነገር በቤቱ ውስጥ እንደሌለ እስከማላይበት ደረጃ አድርሶኛል፡፡”

 

*   *   *

ከሁሉም በላይ ከዐይን ህመምተኛነት ይሰውረን! ዐይንህን እገልጥልሃለሁ ብሎ የበለጠ ከሚያውር ያድነን፡፡ ያ ሳያንስ ቤታችንን ባዶ ከሚያደርግ ያውጣን፡፡ የሚታዘዝልን መድኃኒት በሙሉ ሁሌም ላያድነን እንደሚችል እንገምታለን፡፡ አንዳንዱ ያድናል፤ አንዳንዱ አያድንም፡፡ መድኃኒት ሰጥቼሃለሁ በሚል የቤት ንብረታችንን ሳይቀር የሚያራቁተን ሀገር - አቀፋዊም ሆነ ዓለም- አቀፋዊ መዝባሪ እንዳይመጣብን ግን ይጠብቀን፡፡ ይሄንኑም የሚያይ ያልታመመ ዐይን ያለው ዳኛ አያሳጣን፡፡

ደህና ዐይን ካለን ታሪካችንን በኩራት እናያለን፡፡ የታሪክ አሻራ አይፋቅም - ከልደት እስከሞት አይለወጥም፤ እንዲሉ፡፡ From the Cradle to the grave

I, grieve, yet I achieve!

(“ከአንቀልባ እስከ መቃብር

ባዝንም ማሸነፌ አይቀር” እንደ ማለት ነው፡፡ “የታሪክ ዝማሬ” ተብሎ የተፃፈ ነው፡፡) ሚኒልክን በአድዋ፣ ኃ/ሥላሴን በአፍሪካ አንድነት (ህብረት)፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን በመሠረተ ትምህርት ማሰብ የበጎ አዕምሮ ሀቅ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ መሬት፣ በቻይና ገንዘብ፤ የተመረቀው የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ፊት የክዋሜ ንኩሩማ ሐውልት ሲቆም የአገራችን መሪዎች ቅር አይላቸውም ለማለት ባያስደፍርም፣ ከሞኝ ደጅ ሞፈር መቆረጡን እንዴት አጡት ማሰኘቱና በማን ተፅዕኖ ተፈፀመ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ ግድ ነው፡፡ ብዙ እጅ በዙሪያው ለመኖሩ መጠርጠር አያቅትም፡፡ ግን ለምን፤ በዋናነት ኃይለ-ሥላሴን ያካተተ ቢያንስ ዋና ዋና የሚባሉ ሌሎች መሪዎችን የጨመረ ምስል እንኳ መቅረፅ አይቻልም?

“ልትዋጉን ስትፈልጉ ዕድል አንሰጣችሁም - ልታገኙን አትችሉም፡፡ እኛ ልንዋጋችሁ ስንፈልግ ግን እንደማታመልጡ እናረጋግጣለን፡፡ ስንመታችሁ ድርግም ነው፡፡ … ከዚያ ድምጥማጣችሁን ነው የምናጠፋው፡፡ … ጠላት ሲገፋ እናፈገፍጋለን፡፡ ጠላት ካምፑ ውስጥ ሲሰፍር፤ እንልቅፍ እንነሳዋለን፡፡ ሲደክም እናጠቃዋለን፡፡ ሲያፈገፍግ ደግሞ እኛ እንገፋለን!”

ምናልባት ዘመኑ የጃፓኖችን ዝነኛ አባባል ያስታውሰን ይሆናል፡፡ Tada yori takai mono wa nai በነፃ ከተሰጠ ስጦታ በላይ፤ ዋጋ የሚያወጣ ምንም ነገር የለም፤ እንደማለት ነው፡፡ ያንን ዋጋ እኛ እየከፈልን ይሆን?

በእርግጥ ትልቅ ዋጋ ነው፡፡ በነፃ ለተገኘ ስጦታ የምንከፍለው የክብር ዋጋ - የክብር መስዋዕትነት! ስምንም ቅስምንም የሚያም መስዋዕትነት! ምናልባትም ለማያባራው የአፍሪካ ችግር ጭምር ተጨማሪ አበሳ የሚያስመረቅዝ መስዋዕትነት፡፡ ሐውልት የማፍረስ ባህል ቢያንስ ከዓመታት ወዲህ አልምተናልና፤ጊዜ ሲፈቅድ፣ ሁኔታዎች ሲከለሱ፤

“ከተመታህ በኋላ መቆጣት፣ ጅብ ከሄደ አጥር ማጠር” ከሚለው ተረት ይገላግለን ይሆናል፡፡ የህንፃው መቆም “ፍየል-ፈጁን አውሬ፣ ፍየል አርደህ ያዘው” ዓይነት እንዳልሆነ ተስፋ እናረጋለን፡፡ “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም፡፡” ቢባልም ከፈረሱ ጋር  የመጣውን ጣጣ ሁሉ ቻል አይባልም፡፡ በእርግጥ ለዘመናት “የመተሳሰር አገልግሎት” ሲሰጥ በቆየው የአገር ወህኒ ቤት ላይ የቆመ ህንፃ መሆኑ፣ የወቅቱ ስብሰባ ተናጋሪ Farewell To Prison (ዓለም በቃኝ ደህና ሰንብት) እንዳሉት ብቻ ነው ባይባልም፤ የአፍሪካን ህንፃ በእሥር ቤቱ ላይ መሥራት ትልቅ ፍሬ ያለው እርምጃ የሚሆነው የህዝቦች ሥቃይ ሲያከትም ነው! የመከራውን ሥር መንቀል እንጂ በላዩ ላይ ረጅም ጣራ ያለው ህንፃ ማቆም፤ የመከራውን አጀንዳ የማያነሳ የመሰብሰቢያ ቦታ ከመፍጠር የበለጠ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በስብሰባው በአፅንዖት እንደተነገረው፤ አጋሮቻችን የተባሉት  ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮርያ እና አሜሪካ ለአፍሪካ ህብረትም ሆነ ለየአገሩ በነብስ-ወከፍ ምኑ ናቸው? ሲባል፤ “ከረጅም ጋር ሲሄድ የዋለ አጭር፣ ሲያቃስት አደረ!“ እንዳያሰኝ ያሰጋል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!!

 

 

Read 3883 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:01