Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 March 2012 09:34

“ሠይጣን ከመታው ፓርቲ የመታው!”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አንበሳ፤ በአንድ መስክ ላይ እየጋጠ ያለ አንድ የሰባ በሬ፤ ያይና ካሉት መንጋዎች ሁሉ ለይቶ ልቡ ይጓጓለታል፡፡ ስለዚህ ጦጣን ይጠራና፤

“እሜት ጦጣ፤ በመስኩ ላይ ያየሁትን በሬ - `አያ አንበሶ ግብር ሊያበላ ያስባልና መጥተህ የደስታዬ ተካፋይ እንድትሆን` ብሎሃል፤ ብለሽ ጋብዢልኝ” ይላታል፡፡ ጦጣም፤

“አያ አንበሶ፤ በሬው በጣም ተቀልቦ የሰባ ነው፡፡ “እስካሁን የበላሁት ይብቃኛል” ቢለኝስ?”

አንበሶ፤

“እስካሁን የበላኸው እንዳሰባህ አይቻለሁ፡፡ አድናቂህ ነኝ! ሆኖም እኔ የበላሁትን አልበላህም፡፡ ደሞም እስከዛሬ የቀለበህ፤ ሰው ነው፡፡ ሰው ደግሞ አስብቶ አራጅ ነው፡፡ እኛ እንስሳት የሰው መጫወቻ የሆነው የሚያሰባን ለእኛ ጥቅም ስለሚመስለን ነው፡፡ ዕውነቱ ግን ይህ አይደለም! አውሎ አሳድሮ ያርደናል! ይበላናል! ይህንን ግልፅ አድርገሽ እንድታስረጂዉ!” ይላታል፡፡

ጦጣም፤

“እሺ አያ አንበሶ! መቼም እርሶ ካሉኝ ቃል አልወጣም” ትልና ወደ በሬ ትሄዳለች፡፡ በሬ ዘንድ እንደደረሰችም፤

“በሬ ሆይ! አያ አንበሶ ግብር ላገባ ነውና መጥተህ ድግስ እንድትበላ ብለውሃል” ትለዋለች፡፡

በሬም፤

“ምን ዓይነት ግብር ነው?” ሲል ይጠይቃታል፡፡

ጦጣ፤

“ዓይነቱ አልታወቀም፡፡ ብቻ የሰው ልጆች እኛን እንስሳትን አብልተው አወፍረው ሲያበቁ ያርዱናል፡፡ ሆዳችንን ለመሙላት ብለን እንጠቃለን፡፡ የእኛ ድግስ ግን የወንድማማችነት መግለጫ ነው ያሉኝ መሰለኝ!”

በሬ፤

“ሀሳቡ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከመንጋው ሁሉ ለይቶ ለምን እኔን ብቻ የጋበዘኝ ይመስልሻል?”

ጦጣ፤

“ምናልባት በመልክህ ማማር፣ በግርማ - ሞገስህ፣ በአካልህ መስባት ምክንያት የመንጋዎቹ ተወካይ ለመሆን ትችላለህ ብሎ ሊሆን ይችላል” አለች ጦጣ እየጨነቃት፡፡

በሬ፤

“ለመሆኑ ድንኳን ተጥሏል?”

ጦጣ፤

“አልተጣለም”

“እነ በግ፣ እነ ዝንጅሮ፣ እነ ድመት፣ እነ ጆቦ፤ እየኸተፉ ምግብ ለመዘጋጀት መጥተዋል?”

“አልመጡም”

“ታዲያ ወይ መጥተህ ስራ አግዘኝ አላለኝ፡፡ ወይ ናና ድንኳን እንጣል አላለኝ፡፡ ግብር አገባለሁና ድግስ ብላ ብሎ እንዲሁ ከጠራኝ ነገር አለ ማለት ነው! ስለዚህ “አያ አንበሶ በጣም አዝናለሁ፡፡ አሳዳሪዬ አስተዳዳሪዬ የሰው ልጅ፤ “ያልተዘጋጀ ድግስ እበላለሁ ብለህ ራስህ እንዳትበላ!” ብሎ ወደ ድግስህ እንዳልመጣ ከለከለኝ፤ በጣም አዝናለሁ” በይልኝ አላት፡፡

ጦጣም እንደተባለችው ሄዳ ለአንበሶ ነገረችው፡፡ አንበሶ በጣም ተናደደና “እንግዲህ በክብር መበላት ካልወደደልህ፤ ተዋርደህ፣ አፍንጫህን ተሰንገህ ትበላታለህ!” አለ፡፡

ጦጣም፤ “እኔም የፈራሁት ይሄንኑ ነበር፡፡ እንዲያውም ጦስህ ለእኛም እንዳይተርፍ፤ ብዬዋለሁ” አለች ይባላል፡፡

***

ጦሳቸው ለኛ ከሚተርፍ ይከልለን!! ከጦጣ መልዕክተኛ ይሰውረን! ከአስብቶ አራጅ ያድነን! በክብርም ሆነ በውርደት ለመበላት፣ ለነገር ከሚጠራ ይገላግለን!!

“ፍየል ፈጁን አውሬ ፍየል አርደህ ያዘው” የሚለው ተረት፤ መልካም ተረት ነው፡፡ ግን ሁል ጊዜ አይሠራም፡፡ ፍየል ፈጁ አውሬ ፍየሉ የታረደው እሱኑ ለማጥመድ መሆኑን ያስተዋለ ለታ፣ ለሆዱ ብሎ ሆዱን ላለመወጋት ጥንቃቄ ያደርጋል! ይሄ ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀው፤ ጊዜ የሞረደው ብልህነት ነው፡፡

“ወዳጅህን ከጎረቤት ታገኛለህ፡፡ ጠላትህን እናትህ ትወልድሃለች” የሚለውን ተረት ምን ጊዜም ልብ እንል ዘንድ፤ ልብ አይንሳን!

በዛሬ ዘመን ቋንቋ፤ ሁኔታውን እናስቀምጠው ብንል “እገሌ ለግምገማ ቀረበ” ሲባል፤ “ለአውጫጭኝ ታሰበ” እንደማለት ነው፡፡ አውጫጭኝ ደግሞ ህዝብ ተሰብስቦ “ሌባውን ለይ” የሚባልበት ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡ አፈርሳታ ነው፡፡ ወንጀል የሠራውን ሰው፣  ህዝብ ተሰብስቦ እንዲያጋልጥ የሚደረግበት ዘዴ ነው፡፡ ወይም በዱሮው አነጋገር “ጥቆማ” ነው! ይሄን ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ይኖር ዘንድ፤ ዘመን ይባርከን፡፡ ዛሬ መንገዱ ሁሉ የግልፅነት (transparency) ነው ብንልም፤ በተግባር እዚያ ለመድረሳችን የሚያመላክቱ  አስረጆች የሉንም፡፡ ለዚም ያድለን ዘንድ እንፀልይ!

የፖለቲካ ጠበብት፤ “ፍላጎትህን ደብቅ” የሚል የአመራር /የአገዛዝ/ ዘዴ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ይኸውም፤ “በተቻለህ ሁሉ ከድርጊትህ በስተጀርባ ድብቅ-አላማ እንዳለህ ህዝብ እንዳያውቅ አድርግ፡፡ ያሰብከውን ካላወቁ የመከላከል ዝግጁነት አይኖራቸውምና ወደተሳሳተው አቅጣጫ ምራቸው፡፡ በቂ ጭስ ውስጥ ክተታቸው፡፡ ጭሱ ዐይናቸውን እንዳይገልጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ጭሱ ገለል ሲል ዐይናቸውን ሲገልጡ እንኳን ጊዜው ረፍዷል፡፡ አንተ የልብህን ፈፅመህ ጨርሰሃል!” ይላሉ፡፡ ይህንን የአበው ፖለቲከኞች አነጋገር ልብ ያለ ከጥቃት ይድናል!

ለዘመናት ያየናቸው የፓርቲ መንገዶች /አሸንዳዎች/ ድቅድቅ ጨለማ ነበሩ/ናቸውም፡፡ ስንመታም ሆነ ሌላው ሲመታን የማንተያይባቸው የሚስጥር መሳለጫዎች (Cross - roads) ናቸው፡፡ ዐይኑን ያልገለጠ ይታወርባቸዋል፡፡ ዐይኑን ሳይገልጥ ይለፋል፤ ዐይኑን ሳይገልጥም ያልፋል፡፡ የልማትና የልፋት ትርጉም ሳይገባው አለሁ እያለ ይጠፋል፡፡ ላኪውም፤ ተላላኪውም ተቀባዩም የሚጠፉበት ሁኔታ እንዳይከሰት እንፀልይ፡፡ ላኪው ጉልበተኛ ነውና ይጠፋል፡፡ ተላላኪው አቋም የለውምና ይጠፋል፡፡ ተቀባዩ ዞሮ ዞሮ በጉልበተኞች እጅ ነውና መጨረሻቸውን አያውቀውም፡፡ ተመቺው ሁልጊዜ መጨረሻውን አያውቅም! “ሠይጣን ከመታው ፓርቲ የመታው” የሚባለው የዘመኑ ብሂል፤ እናቱም፣ አባቱም ይሄው ነው!!

 

 

 

Read 5785 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 09:37