Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 07 April 2012 08:09

“ያ ንሥር እንደኔ ዓይነት ሆኖ ምን አየር ላይ አወጣው?” አለ ዶሮ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አባትና ልጅ ወደ አንድ ማህበር ስብሰባ ለማድረግ በፈረስ ሆነው ይሄዳሉ አሉ፡፡ መንገድ ላይ ሳሉ ክርክር ያነሳሉ፡፡

አባት - ይሄ ፀሐይ እየጠነከረ ሲመጣ የፈረሱ ጥላ በስተቀኝ በኩል ይሆናል

ልጅ - የለም በግራ ነው የሚሆነው

አባት - አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ዳገቱን ከወጣን በኋላ እኛ ወደ ግራ ስለምንዞር ፀሐይ ጀርባውን ሳይሆን ጐኑን ነው የምትመታው፡፡ ግራ ጐኑን ስትመታው ጥላው ወደ ቀኝ ይወድቃል፡፡

ልጅ - የለም የለም፡፡ ፀሐይ ወደ መሀል ሰማይ እየወጣች ስለምትሄድ የፈረሱ ጥላም አቅጣጫውን ይቀይራል

አባት - እኛ ፈረሱ ላይ ስላለን ጥላው በደምብ አይታየንም

ልጅ - እንግዲያው ወርደን እንየዋ?

አባት - ልክ ነው፡፡ ብንወርድ በደምብ ይታየናል

ከፈረሱ ወርደው ፈረሱን ጉብታው ላይ አቆሙት፡፡ ፈረሱ መሳቅ ጀመረ፡፡

አባት - ይሄ ፈረስ ምን የሚያስቅ ነገር አግኝቶ ነው የሚስቀው?

ልጅ - ለምን አንጠይቀውም?

አባት - እሺ እንጠይቀው

ወደ ፈረሱ ተጠጉ፡፡

አባት - አንተ ፈረስ ምን የሚያስቅ ነገር አግኝተህ ነው የምትስቀው?

ፈረሱም እንዲህ ሲል መለሰ:-

“የምስቀው ስለገረማችሁኝ ነው”

አባት - ምናችን ነው ያስገረመህ?

ፈረስ - ከቤት ከወጣችሁ ጀምሮ ስለእኔ ጥላ ስትጨቃጨቁ ሳዳምጥ ነበር፡፡ አሁን የእኔ ጥላ በቀኝ ወደቀ በግራ ፋይዳው ለእናንተ ምንድን ነው? ስንት ቁም ነገር ልትሰሩበት የምትችሉበትን ጊዜ በከንቱ ጭቅጭቅ ስታባክኑት ማየቴ ሲገርመኝ፤ ጭራሽ መሬት ወርዳችሁ ጥላዬን ለማየት ስትሞክሩ ተመለከትኩ፡፡ የሚያሳዝነኝ ለስብሰባ የሚጠብቃችሁ ማህበርተኛ ህዝብ ነው፡፡

አባትና ልጅ ፈረሱ ስለታዘባቸው በጣም ተናደዱ፡፡

አባት - አንተን በማያገባህ ገብተህ በእኛ ላይ በመሳቅህ መቀጣት አለብህ፡፡ እንዲያውም ካሁን ወዲያ እንዳትናገር አፍህ መለጐም አለበት፡፡

ፈረሱን አፉን ለጐሙት፡፡ ፈረሱ ግን በሆዱ መሳቁን ቀጠለ፡፡ እነሱም ስለጥላው አወዳደቅ ንትርካቸውን ቀጠሉ፡፡

*    *   *

በህዝብ ጊዜ፤ በሀገር ሰዓት የሚቀልዱ አያሌ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ እንዳላጠፉ በመቁጠር መልሰው ህዝቡን ይወቅሳሉ፡፡ ዞረው ሀገርን ያማርራሉ፡፡ በተናገሩት ሲያፍሩ ያዳመጣቸውን ጥፋተኛ ያደርጋሉ፡፡ ፀሐፌ-ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፤

“የሚያባርረኝ ጠላት እንቅፋት መቶት በሞተ አርበኛ ተብዬ ታሰርኩ እንጂ እኔስ አርበኛ አልነበርኩም” እንዳለው መሆኑ ነው፡፡ ባጠፉት ጥፋት ሌሎችን መራገም የዛሬ ህመማችን ብቻ አይደለም፡፡ የቆየ፤ የሰነበተ ደዌ ነው፡፡ በእንቶ ፈንቶውና በአርቲ-ቡርቲው ዘመን እያሳለፍን ለሀገር እንደሰራን አድርገን ስንገበዝ ውዱ ጊዜ ይነቅዛል፡፡ ድምር ውጤቱ የኢኮኖሚው መንኮታኮት፣ የፖለቲካው መላ-ማጣት የማህበራዊ ኑሮው መመሰቃቀል ይሆናል፡፡

የባህል መሸርሸር አደጋ፣ የትምህርት መውረድ አባዜ፣ የሃይማኖት ግጭት ሥጋት፣ የንግድ ሥርዓት ቅጥ-ማጣት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የፍትሕ መዛባት፣ ዐይን-ያወጣ የሙስና ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ቁጣ፣ የእከክልኝ - ልከክልህ ወገናዊነት ፖለቲካዊ ዘይቤ፣ የትውልድ ንቅዘት (degeneration)፣ የዘመቻ ሥራና መንገኝነት… ምኑ ቅጡ! ድምር ውጤታቸው ከቤተሰብ እስከ ህብረተሰብ የሚያናጋ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዶች ክስተቱን መግለፅን እንደ አሉታዊነት ያዩታል፡፡ እውነታው ግን ድክመታችንን አይተን መላ እንፍጠር የሚል ነው፡፡ “…ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” የሚል የማስጠንቀቂያ ደወልም አለው፡፡ “አትፍረድ ይፈረድብሃል” የሚል አንድምታም አያጣም! “መሄድ ቢሉሽ መሄድ ነወይ…” ብንልም ያስኬዳል፡፡

“አንተም እሳት ነበርክ እሳት አዘዘብህ

እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብህ” የሚለውን ለማስተዋል ጭንቀላትን ይዞ መተከዝ አይጠይቅም!

መልካም የተሰራን ማመስገን ደግ ነው፡፡ የሚያስወቅሰው፣ አድሮም የሚያስጠይቀው እንከን - የሞላውን ነገር እንከን - የለሽ ነው ማለት ስንጀምር ነው! ፍፁም ነው ማለት ስንጀምር አዛዥ ናዛዥ እንሆናለን! ይሄኔ ግራ የገባው የራስ ወገን ሳይቀር፤

“ያ ንሥር እንደኔ ዓይነት ሆኖ ምን አየር ላይ አወጣው?” ይለናል፤ እንደ ዶሮው!

 

 

 

 

Read 4187 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:12

Latest from