Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 April 2012 12:26

“ከላይ ሲነድ ባታየውም፤ ከውስጥ እሳቱ ተያይዟል” የኢንዶኔዢያውያን አባባል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው አንዲት ወፍ በወጥመድ ይይዛል፡፡ ወፊቱም ምህረት እንዲያደርግላት ትማጠነዋለች፡፡

“ጌታዬ፤ የዛሬን ምህረት ብታደርግልኝ ለህይወትህ ጠቃሚ የሆኑ ሶስት ምክሮችን እለግሥሃለሁ፡-

1ኛውን አሁኑኑ እነግርሃለሁ

2ኛውን አቅራቢያችን ያለው ዛፍ ላይ ሆኜ እነግርሃለሁ

3ኛውን አየር ላይ ስሆን እነግርሃለሁ” ትለዋለች፡፡

ሰውየውም፤

“መልካም ነው፡፡ የመጀመሪያ ምክርሽን አይቼ እወስናለሁ” ይላታል፡፡

ወፊቱም፤

“የመጀመሪያው ምክሬ፡- የማይሆን ነገር ይሆናል ብለህ አታስብ የሚል ነው” አለችው፡፡

ሰውዬው አወጣ አወረደና መልካም ምክር ነው፤ ብሎ ደመደመ፡፡ ስለዚህም፤

“በይ እንግዲህ ቃልሺን አክብረሽ እዚያ ዛፍ ላይ ሆነሽ ሁለተኛውን ምክር ንገሪኝ፡፡ ከዚያ ክሩን ከእግርሽ ላይ እፈታልሻለሁ” አለና ክሩን በእጁ ይዞ ወደ ዛፉ ለቀቃት፡፡ ወፊቱም በርራ እዛፏ ላይ ወጣች፡፡ ከዚያም፡-

“ሁለተኛው ምክሬ፡- ባለፈ ነገር አትፀፀት የሚል ነው፡፡ ይህስ ምክር አይጠቅምህንም?” ስትል ጠየቀችው፡፡ ሰውየው አመዛዘነና፤

“አዎን ጠቃሚ ነው፡፡ በይ ደግሞ ሶስተኛውን ምክርሽን አየር ላይ ሆነሽ ትነግሪኛለሽ” ብሎ ክሩን ከእግሯ ላይ ፈታላት፡፡

ወፊቱ ወደ ሰማይ በረረች፡፡

“የመጨረሻው ምክሬ፤ አንዴ በእጅህ ያስገባኸውን ንብረት ከእጅህ አታውጣ!”

“ለምን እንዲህ አልሺኝ?” ሲል ጠየቀ ሰውዬው፡፡

ወፊቱም፤

“ሩብ ኪሎ አልማዝ ሆዴ ውስጥ ስላለ ነው!” አለችው፡፡

“ወይኔ! የዕድሜ ልክ ሀብት አጣሁ ማለት ነው” እያለ ድንጋይ አንስቶ መወርወር ጀመረ፡፡

“አንተ ሰው ጅል ነህ ማለት ነው! ሌላው ቢቀር ምክሬን ማስታወስ ነበረብህ!”

“የቱን ምክርሽን?”

“ባለፈ ነገር አትፀፀት ብዬህ ነበር!”

“እንዴት አልፀፀትም? ሩብ ኪሉ አልማዝኮ ህይወቴን ይለውጠዋል”

“ጅል ነህ ያልኩህም ለዚህ ነው፡፡ ለመሆኑ እኔስ ራሴ ሩብ ኪሎ የምሆን ይመስልሃል? እንዴት አድርጌ ነው ሩብ ኪሎ አልማዝ ሆዴ ውስጥ የምሸከመው? የማይሆን ነገር ይሆናል ብለህ አታስብ ያልኩህ ለዚህ ነው!” ብላ በዐይኑ እንኳን ሊከተላት ወደማይችልበት ሰማይ ከነፈች!

* * *

የማይሆን ይሆናል ብለን ከመገመት ያውጣን! ሀብታችን ከሆድቃችን በላይ ነው እያልን ከመጃጃል ይሠውረን! ባለፈ ነገር ከመፀፀት ያለፈውን ስህተት አርመንና ችግራችንን አስወግደን ከልቦናችን እንድንሆን እንፀልይ! በእጃችን ያለን አጋጣሚ፣ ወቅት፣ የለውጥ አየር ወዘተ. እንእዳያመልጠን የነቃ አዕምሮና የሰፋ ልቡና ሊኖረን ይገባል! ለውጥን የጉጉት ዐይን ገልጠን በጭለማም ቢሆን ለማየት መቻል ይኖርብናል፡ አገር ማዳን ያለ ንቃተ-ህሊና ሊሳካ አይችልም፡፡ አገር የሁሉም ሀላፊነት መሆኗንና፣ የጥቂቶች ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነች በጥሞና እናስተውል!

በጥሞና እናስተውል!

የጥንቱ የጠዋቱ ማርክስ በፃፈው ግጥሙ፡-

“እኔ መች ፈልጌ፣ ህይወት ያለ ችግር

መንፈሴስ መች ሽቷት፣ ራሷ ግርግር

ለታላቁ ዓላማ፣ ለሰው መልካም ዕድል

ህይወቴ ትሞላ፣ ትሁን የትግል ድል!!” ይለናል፡፡

አገር የተበላ ዕቁብ አይደለችም! በአግባቡ የትምህርት ዕድል ያስፈልጋታል፡፡ ጤና ያሻታል፡፡ ፍትህ ያስፈልጋታል፡፡ አገር የጠለቀች ጀንበር አይደለችም፡፡ ባለኩራዙም፣ ባለሻማውም፣ ባለፋኖሱም … ትበራ ዘንድ አስተዋፅዖ ሊያደርግላት ይገባል፡፡ ለውጥ በእኛ ትክክልነት ላይ እንጂ በሌሎች ስህተት ላይ የተመረኮዘ መሆን የለበትምና በራሳችን ላይ እንተማመን! እናንብብ፣ እንወቅ፣ እንወያይ፣ እንለወጥ! የለውጥ ባህሪ ኢንዶኔዢያውያን እንደሚሉት ነው፡-

“ከላይ ሲነድ ባታየውም ከውስጥ እሳቱ ተያይዟል!” የለውጡ ባለቤቶች ሁላችንም መሆናችንን ልብ እንበል!! ያገር እድር አያሳጣን!!

 

 

 

 

Read 5508 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:32