Saturday, 08 October 2011 10:40

“..ልጅዎን... በቅርበት...ያናግሩ..”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

በአሁኑ ወቅት በአለማችን ልጆች ለብዙ መረጃዎች የተጋለጡ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ልጆች በአለም ዙሪያ የሚሰራጩ የመገናኛ ብዙሀንን የመከታተል እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙሀኑ አይነትና ጥራት መለወጥና ለአጠቃቀም ምቹ መሆን አለም ወደ አንድ ጎጆነት ተለውጣለች ከሚያሰኝ ደረጃ ያደረሳት ሲሆን፤ በአለም ዙሪያ ስላሉ እውነታዎች ለመረዳት ልጆች ምንም የሚያዳግታቸው ነገር የለም፡፡ የፊልም፣ የቲአትር፣ የትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴና ሕጻናቱ ከተለያየ ቤተሰብ ወጥተው በትምህርት ቤትና በአንድ አካባቢ መገኘታቸው የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑ እሙን ነው፡፡

ልጆች ከተለያየ አቅጣጫ በተለይም ስለ ስነተዋልዶ አካላት እና ስለኤችአይቪ ኤድስ የሚያገኙት መረጃ ምን ያህል ትክክል እንደሚሆን ለማወቅ ካለመቻሉም በላይ አስተማሪነቱንም መቀበል ያዳግታል፡፡ ከዚህም የተነሳ ልጆች ብዙውን ጊዜ ፍርሀት እና ጥርጣሬ የሚያድርባቸው፣ ደህንነትን የማያገኙ የሚመስላቸው እና በአካባቢያቸው ስላለው ነገርም ሆነ ስለወደፊት ማንነታቸው እምነት የማያድርባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው በእድሜያቸው ደረጃ ትክክለኛ እና ተከታታይነት ያለው ትምህርት ሊያገኙ እንደሚገባ ምሁራኑ የሚመክሩት ልጆቻቸውን ወደ ትክክለኛው መስመር ለመመለስና በጥሩና በተስተካከለ መንገድ እንዲያድጉ ለመርዳት እንዲችሉ ነው፡፡ ወላጆች ጤናማ፣ በራስ የመተማመን ብቃት ያላቸው፣ በአስተሳሰባቸውም የበለጸጉ ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ስለሕጻናት አሁኑኑ በሚል በKaiser Family Foundationበሚመራው ድርጅት Lynne S. Dumas የተባሉ“Talking With Your Child About a Troubled World,”የሚለውን እውቅ መጽሐፍ የጻፉት ዶ/ር እንደሚገልጹት ሕጻናትን በኤችአይቪ ኤድስ ወይንም በግብረስጋ ግንኙነት ዙሪያ ባጠቃላይም ስለ ስነተዋልዶ ጤና ጉዳይ ጊዜ ሳይፈጁ ወይንም ልጆቹ እድሜያቸው በጣም ከፍ ሳይል ጀምሮ ማወያየት ይገባል የሚል ምክር ለወላጆች አስተላልፈዋል፡፡ ይህ አምድ ነጥቦቹን ለአንባቢዎች ያካፍላል፡፡
ልጅዎ ፍርሀት ሊያድርበት እንደሚችል አስቀድመው ይረዱ
ሕጻናት በመገናኝ ብዙሀን ወይንም በተለያዩ አጋጣሚዎች በቀጥታ በአይናቸው የተለያዩ ጉዳቶች በህጻናት ላይ ሲፈጸም ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ጉዳት ወደ እነርሱም ለደርስ እንደሚችል በመገመት የማይገልጹትን ፍርሀት በውስጣቸው ሊያዳብሩ እንደሚችሉ ወላጆች አስቀድሞ መገመት ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ለልጅዎ ሊሉት የሚገባው በአየኸው/በአየሽው ነገር ፍርሀት ሊኖር እንደሚችል... አውቃለሁ... ነገር ግን ስላየሽው/ስላየኸው ነገር በግልጽ እንነጋገርና መፍትሔውንም እንወያይ በማለት በልጆቹ ላይ ያደረውን ስጋት ማስቀረት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በውይይቱ ወቅት ልጆቹ የሰጉበት ነገር ምን እንደሆነና ያ ችግር የሚከሰትበትን ምክንያት እንዲሁም እንዳይከሰት ምን ማድረግ እንደሚገባ የመሳሰለውን እውቀትና ዘዴ እንዲጨብጡ ስለሚያስችላቸው ልጆቹ ምንጊዜም እራሳቸውን ለማዳን ዝግጁ እንዲሆኑ ይረዳል፡፡
ከልጅዎ ጋር መነጋገርን በጊዜ ይጀምሩ
ልጆችን በተለይም ስለጾታ ጥያቄ ጊዜ ሳይፈጁ በግልጽ እና በተከታታይ ማነጋገር ጠቀሜታ አለው፡፡ አንድ ልጅ በተፈጥሮአዊው ሁኔታ ሊያውቀው የሚገባውን ነገር በጊዜ ማወቅ መቻል አለበት፡፡ ለምሳሌ “ይህ አፍንጫ ነው፣ ይህ ደግሞ ከንፈር ነው” እየተባለ በአካሉ ላይ ስላሉት ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች በግልጽ እንደሚነገረው ሁሉ “ይህ የወንድ አካል ወይንም ብልት ነው፣ ይህ የሴት ብልት ነው” እየተባለ መነገር አለበት፡፡ ልጆች እያደጉ በሄዱም ቁጥር የውይይቱ እድገት እየጨመረ መሄድ አለበት፡፡
ልጆች ጥያቄ ባያነሱም እርስዎ ጥያቄ ይፍጠሩ
ለምሳሌ የልጅዎ ጓዋደኛ እናት እርጉዝ ልትሆን ትችላለች፡፡ ልጅዎ ምናልባት የ7 ወይንም የ8 አመት እድሜ ያላት ብትሆን ጥያቄውን በሚከተለው መልክ ሊጀምሩት ይችላሉ፡፡ “የጓደኛሽ እናት ሆድዋ ለምን ትልቅ እንደሆነና እያደገም እንደሚሄድ ታውቂያለሽ? አየሽ እሷ እርጉዝ ስለሆነች ነው፡፡” እርጉዝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ሴት መቼ እንደምታረግዝ ...የመሳሰሉትን ነገሮች በልጅቷ እድሜ መጠን መነጋገር ይገባል፡፡ ልጅዎ በምታየው ነገር ግራ እየተጋባች ወይንም እየተደነቀች ከምትቀጥል ይልቅ ሁኔታውን እንድታውቅ መደረጉ እርካታን ይሰጣታል፡፡ ባየችው ነገር እንዳትጨነቅም ይረዳታል፡፡
በግልጽ ከሚታየው ነገር ወጣ ብለው ልጆችዎን ያነጋግሩ
በተፈትሮአዊ አካላት ምንነት ዙሪያ ከተደረገው ውይይት ወጣ በማለት ጾታዊ ግንኙነትን በሚመለከት ውይይት ከልጆች ጋር መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ የተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት ጥንቃቄን፣ ኃላፊነትን፣ ትኩረትን የሚሻ እና ግንኙነቱን ለማድረግም የራሱ ጊዜ ያለው መሆኑን እንዲሁም ምን በጎ ነገርና ምን አደጋ እንዳለው ሁሉ ልጆች በተለይም በታዳጊነት የእድሜ ክልል ሲገቡ ወላጆች በግልጽ ሊያጋግሯቸው ይገባል፡፡ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚደረግ የጓደኝነት ቀጠሮን፣ ወደ ፊልም ቤታ አብሮ መግባትን፣ ክንድ ለክንድ ተያይዞ መሄድን የመሳሰሉትን ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም መቼ በየትኛው እድሜ ሊደረግ እንደሚገባ በግልጽ ለይቶ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ልጆች እንደዚህ ያለውን ግን ኙነታቸውን በእርጋታና በጥንቃቄ ሊይዙት የሚገባ መሆኑን አውቀው ማደጋቸው ለወደፊቱ ህይወታቸው ስኬት ይረዳቸዋል፡፡
ልጆች እንደእድሜ ደረጃቸው የሚኖረውን ተፈጥሮአዊ ለውጥ እንዲያውቁ ይርዷቸው
ልጆች በሚያድጉበት ወይንም ወደጉርምስናው በሚደርሱበት ጊዜ የሚኖራቸው የስነተዋልዶ አካል እድገት ሊደናገሩባቸው የማያስችሏቸው ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህ ከልጆች ጋር ሲነጋገሩ በወቅቱ ስላሉበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት ስለሚደርሱበት ደረጃም ማስረዳት ይገባል፡፡ ሴቶች የስነተዋልዶ አከል እድገታቸው ምን እንደሆነ እና በቀጣይነትም የወር አበባ የሚባል ተፈጥሮአዊ የእድገት ደረጃ የሚከተል መሆኑን እንዲሁም ወንዶቹም የዘር ፈሳሽ ማየት የመሳሰሉ ሁኔታዎች የሚከሰቱ  መሆኑንና ያ ወቅትም ምን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው በዝርዝር ከወላጆች ቢነገራቸው እራሳቸውን ለመምራት ይረዳቸዋል፡፡
ወላጆች ከተቃራኒ ጾታ ልጆቻቸው ጋር ሊቀራረቡና ሊነጋገሩ ይገባል
አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ከተመሳሳይ ጾታ ልጃቸው ጋር ካልሆነ በስተቀር ተቃራኒ ጾታ ልጆቻቸውን አቅርበው የማያነጋግሩበት አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ አባት ከሴት ልጁ እናትም ከወንድ ልጁዋ ጋር በተለይም ጾታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ልጆቹ በአንድ ወላጅ ብቻ የሚያድጉ ከሆኑና አሳዳጊዋ እናት ብትሆን ከወንድ ልጇ ጋር ምንም አይነት ውይይት ሳትፈጥር ወይንም ስለምንም ጉዳይ እንዲያውቅ ሳትረዳው ልጁ ቢያድግ የተለያዩ ችግሮች ወይንም ግራ መጋባት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ስለዚህ ምናልባት እናትየው ወንድ ልጄን በምን ሁኔታ ማነጋገር ይገባኛል የሚል ስጋት እንኳን ቢኖራት የተለያዩ መረጃዎችን ማገላበጥ ወይንም አማካሪዎችን፣ ሐኪሞችን በማነጋገር ትክክለኛውን ሐሳብ ማግኘት እንደሚቻል ከወዲሁ ማወቅ ይገባል፡፡ ይህ ካልተቻለም በቤተሰብ ውስጥ ያሉ የቅርብ ዘመዶች ለምሳሌ አጎት ወንድም ወይንም የቅርብ ጓደኛ የሆነ ወንድ በመፈለግ ልጇን እንዲያማክሩላት አስፈላጊውን መንገድ እንዲመሩላት ማድረግ ከእናትየው ይጠበቃል፡፡ በቤት ውስጥ በተሟላ ሁኔታ ማለትም እናትም አባትም የሚኖሩ ከሆነ ግን እናትየው ሴት ልጇን አባትየው ደግሞ ወንድ ልጁን ስለማንኛውም ሁኔታ እንደልጆቹ የእድሜ ደረጃ እንዲያስረዱ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ግልጽነት ካለና የማይቸገሩ ከሆነ ወላጆች በጋር በሚኖሩበት ቤትም ቢሆን አባት ከሴት ልጁ እናት ደግሞ ከወንድ ልጇ ጋር መነጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወላጆች ለጾታዊ ግንኙነት ያላቸውን ግምት ለልጆቻቸው ያሳውቁ
ልጆች ስለወላጆቻቸው የጾታ ግምት እና አስተሳሰብ እንዲያውቁ ለማድረግ ወላጆች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን አስተሳሰብና እምነት ማወቃቸው በቀጣዩ የህይወት ጊዜያቸው ባህሪያቸውን በምን መልክ ሊያስተካክሉ እንደሚችሉ ሊመራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን አስቀድሞውኑ የመግራት ኃላፊነት አለባቸው፡፡   
ከልጆች ጋር ለመወያየት አይጨነቁ
ልጄ ጥያቄ ቢጠይቀኝ ምን አይነት መልስ እመልሳለሁ ከሚል መጨነቅ አይገባም፡፡ ምንጊዜም ቢሆን በተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ወላጆች ከልጆች የተለየ የሕይወት ልምድ እንደሚኖራቸው አይጠረጠርም፡፡ ለማንኛውም ስለማንኛውም ነገር የእራስን እውቀት ለመገንባት የሚያስችሉ ዘዴዎችን ሁሉ መጠቀም ይጠቅማል፡፡

 

Read 3741 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:44