Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 12:33

የማህጸን ፈሳሽ..Vaginal Discharge…

Written by 
Rate this item
(20 votes)

“እኔ የ28 አመት ሴት ነኝ፡፡ ከአንድ አመት ወዲህ የወንድ ጓደኛ አለኝ፡፡ ከጓደኛዬ ጋር መገናኘት በጀመርኩ በስድስት ወር ገደማ አንድ የማያስደስት ነገር ገጠመኝ፡፡ ከማህጸኔ አይቼው በማላውቀው መንገድ ፈሳሽ ይፈሰኝ ጀመር፡፡ የፈሳሹ መልክ የዘንጋዳ ውሀ እንደሚሉት ይመስለኛል፡፡ ጠረኑ ደግሞ ጥሩ አይደለም፡፡ የፈሳሹ መጠን የውስጥ ሱሪዬን ስለሚያረጥብብኝ በአንድ የውስጥ ሱሪ ቀኑን ሙሉ መዋል አልችልም፡፡ የግድ ግማሽ ቀን ላይ ሌላ የውስጥ ሱሪ መለወጥ ይጠበቅብኛል፡፡ ከማህጸኔ በሚፈሰው ፈሳሽ ምክንያትም ከጓደኛዬ ጋር ቀጠሮ መያዝ አቅቶኛል፡፡ ስለዚህም ጓደኛዬ እንገናኝ በሚለኝ ጊዜ ምክንያት እየፈጠርኩ ቀጠሮውን ስለማዛባ... በቃ... አትወጂኝም ማለት ነው ወደሚል አስተያየት እየመጣ ስለሆነ ከእሱም ልለያይ ነው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ እኔም እወደዋለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ምን ብዬ ልንገረው?... ሁኔታው ስለጨነቀኝ ነው ወደ እናንተ ይህንን መልእክት የላክሁት፡፡ እባካችሁ ባለሙያ አነጋግራችሁ መልሱን ንገሩኝ፡፡”

ስሜን አትግለጹ
“የወር አበባዬ መፍሰሱን ያቋረጠው እድሜዬ ገና አርባ አመት ሳይሞላ ነው፡፡ ወደ ሀምሳው አመት ስገባ ደግሞ የገጠመኝ ነገር ከማህጸኔ ፈሳሽ መፍሰስ ነው፡፡ ፈሳሹ አረፋ የመሰለ ነገር ሲሆን ጠረኑም ጥሩ አይደለም፡፡ አንዳንድ የእድሜ አቻዎቼን ሳነጋግራቸው “የተፈጥሮ ጉዳይ ነው” እኛም ፈሳሽ እናያለን እያሉ ወደ ሐኪም እንዳልሄድ አዳከሙኝ፡፡ እኔ ማረጋገጥ የፈለግሁት ይህ ፈሳሽ እውነት የተፈጥሮ ጉዳይ ነውን? ከሆነስ ለምን ጠረኑ ጥሩ አይሆንም? ወይንስ ሕመም ነው?”
አለም ታደለ - ከቀራንዮ
“በሕይወት ዘመኔ አረፍ ብዬ አላውቅም፡፡ ኑሮዬ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ከጠዋት እስከ ማታ ስቀመጥ ስነሳ ሳጎነብስ ስቃና ነው የምውለው፡፡ ባለቤቴ በመኪና አደጋ ከሞተ ቆይቷል፡፡ የጉልት ነጋዴ ነኝ፡፡ እቃ መግዛት መሸጥ፣ መሸከም ማውረድ፣ ማውጣት ማስገባት... ኧረ ምኑ ቅጡ... ይኸው አባት የሌላቸው አራት ልጆች አስተምሬ አስመረቅሁ፡፡ አሁን የቸገረኝ ነገር ከማህጸኔ የሚወጣው ፈሳሽ እና አየር ነው፡፡ አየሩና ፈሳሹ ግንኙነት አለውን? በኑሮዬ ውጣ ውረድ ምክንያት ይሆን ይህ የተከሰተው? እባካችሁ የዚህን ነገር መልስ ንገሩኝ፡፡”
የውብነሽ አስቻለው - ከሳሪስ
ከላይ ያነበባችኋቸው ደብዳቤዎች የደረሱን በተለያየ ጊዜ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ባለሙያ አፈላልገን እንዲሁም መረጃ አገላብጠን አጠቃላይ ሁኔታውን ለንባብ ብለናል፡፡ ማብራሪያውን የሚሰጡን ዶ/ር ኢያሱ መስፍን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡
***
ኢሶግ - የማህጸን ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ነው?
ዶ/ር - በእንግሊዝኛው Vaginal Discharge የሚባለው ከማህጸን የሚወጣው ፈሳሽ በእርግጥ
ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮአዊነቱ የማይቀጥል እና የጤና መጓደልን የሚያመለክት ሁኔታም የሚታይበት ደረጃ አለ፡፡ ተፈጥሮአዊ የሚባለው ሁሉም ሴቶች በተወሰነ ደረጃ የሚያመነጩት በአብዛኛው ውሀማ ወይም ወተትማ መልክ ያለው እና የመጎተት ባህርይ ያለው ሲሆን ብዛቱም በሀያ አራት ሰዓት ውስጥ ከአንድ እስከ አራት ሲሲ የሚደርስ ነው፡፡ ጠረኑን በሚመለከትም በመጠኑ የሚሸት ነገር ሊኖረው ይችል እንደሆን እንጂ በአብዛኛው ምንም ሽታ የለውም፡፡ በእርግጥ ምንም ሽታ የለውም ሲባል እንዲያው በደፈናወ ውሀ ውሀ ይላል ማለት አይደለም፡፡ የራሱ የሆነ ጠረን ይኖረዋል፡፡
ኢሶግ - ተፈጥሮአዊው የማህጸን ፈሳሽ ምንጩ ከየት ነው?
1. የማህጸን በር ከሚያመነጨው እጢ ወይንም ሴል፣
2. ከማህጸን ግድግዳው ላይ እየተቀረፉ የሚወጡ ሴሎች፣
3. በግብረስጋ ግንኙነት መሟሟቅ ጊዜ ከደም ወደ ብልት የሚፈስ ፈሳሽ ወዘተ የማህጸን ፈሳሽን ይፈጥራሉ፡፡
ኢሶግ - የፈሳሹ መጠን በምን ሊለካ ይችላል?
ዶ/ር - በእርግጥ መለኪያው በውል አይታወቅም፡፡ ነገር ግን የውስጥ ሱሪን በሚነካበት ጊዜ ምን ያህል እንደሚያረሰርሰው ሴቶቹ ያውቁታል፡፡ የማህጸን ፈሳሽ ተፈጥሮአዊውም ቢሆን ከፍና ዝቅ የሚልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በእርግዝና ጊዜ ከሰውነት ተፈጥሮአዊ ቅመሞች መጨመር ጋር ተያይዞ ወይንም የእርግዝና መከላከያ ማለትም ሆርሞን ያያዙ መከላከያዎችን የሚጠቀሙ ሴቶች የፈሰሹ መጠን ሊጨምርባቸው ይችላል፡፡ በአብዛኛው ፈሳሽ የሚጨምርበት ጊዜ በወር አበባ ዑደት ግማሽ ላይ በአስራ አራተኛው ቀን አካባቢ እንቁላል አኩርታ የምትወጣበት ጊዜ ስለሆነ የማህጸን ፈሳሹም ይጨምራል፡፡ የዚህን ወቅት ፈሳሽ ብዛት፣ ጥንካሬውንና ጥራቱን በመከታተል የማኩረት አቅምን ለመገምገም የሚያስችል የምርመራ ውጤት ለማግኘትም ይረዳል፡፡
ኢሶግ - የማህጸን ፈሳሽ መፍሰስ የሚጀምረው ከስንት አመት እድሜ ጀምሮ ነው?
ዶ/ር - የማህጸን ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ እንደመሆኑ በዚህ ጊዜ ይጀምራል የሚባል አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ገና የተወለደች ሴት ሕጻን የተወሰነ ፈሳሽ ሊኖራት ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ከእናትየዋ በወሰደችው አካላዊ ቅመም ምክንያት ነው፡፡
ኢሶግ - የማህጸን ፈሳሽ ተፈጥሮአዊው አይደለም የሚባለው ምን ሲታይበት ነው?
ዶ/ር - ከላይ ከተጠቀሱት ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ውጭ በሆነ መንገድ ፈሳሹ የሚታይ ከሆነ ከተፈጥሮአዊው ማለትም ከጤነኛ ፈሳሽነት ተለውጧል ማለት ይቻላል፡፡ የፈሳሹ መልክ እንዲሁም ጠረኑ እና ብዛቱ ከተለመደው ውጭ ከሆነ ትክክል አይደለም፡፡
ኢሶግ - ጤነኛ ያልሆነው የማህጸን ፈሳሽ ቀለሙ ምን አይነት ተብሎ ይገለጻል፣
ዶ/ር - ተፈጥሮአዊው የማህጸን ፈሳሽ ጤነኛ አይደለም የሚባልበት ቀለም ብጫ፣ ነጭ አረፋ፣ አረንጓ፣ ቡናማ... ወዘተ የመሳሰሉትን ሊመስል ይችላል፡፡
ኢሶግ - ተፈጥሮአዊ የሆነው የማህጸን ፈሳሽ ጤነኛ አይደለም ከሚባልበት ደረጃ የሚደርሰው በምን ምክንያት ነው?
ዶ/ር - ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆኑም በሁለት ሊከፈል ግን ይችላል፡፡ አንዱ ከጀርም ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ከጀርም ጋር ያልተያያዘ ነው፡፡ ለፈሳሽ ጤነኛ አለመሆን እንደ አንድ ምክንያት የሚቆጠረው በማረጥ ምክንያት የሚከሰተው ነው፡፡ በእድሜ ወይንም በተፈጥሮ ምክንያት የወር አበባ ሲደርቅ ከማረጥ በኋላ ሴቶች የሰውነታቸው ቅመም ስለሚያንስ ብልታቸው ወደ መድረቅ ያደላል፡፡ አንዳንዴ ግን ወደፈሳሽ የማምራት ሁኔታዎችም ይስተዋላሉ፡፡ ሌላው ሴቶች ኬሚካልን በብልታቸው አካባቢ የሚጠቀሙ ከሆነ ኬሚካሎቹ ፈሳሽን የሚያበዙበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሰውነት ተስማሚ ያልሆኑ ልብሶችን ማለትም የውስጥ ሱሪ እና ሱሪ በጣም ሰውነትን የሚያጠብቁ ወይንም ናይለን የሆኑ... የመሳሰሉትን ከመጠቀምም የማህጸን ፈሳሽ ጤናማነቱ የሚበላሽበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማህጸን በር ላይ ወይንም የሴት ብልት ውስጥ እጢዎች ካሉም የማህጸን ፈሳሽን ይበዛል፡፡
በብዛት በInfection ወይንም በጀርም አማካኝነት የሚመጣው ፈሳሽ እንደመንስኤው ሁኔታው ይለያያል፡፡ ይህ ችግር በአባላዘር በሽታ ወይንም ከአባላዘር በሽታ ጋር ባልተያያዘ መንገድ ሊከሰት ይችላል፡፡
የሴት ብልት ውስጥ ብዙ ጀርሞች እና ባክሪያዎች አሉ፡፡ እነዚያ ባክሪያዎች የራሳቸውን ቁጥር የጠበቁ እና ተመጣጥነው ያሉ ናቸው፡፡ ከባክሪያዎቹ ውስጥ በብዛት የሚገኘው lactobacillus የሚባለው ሲሆን ይህ ባክሪያ ዋና ስራው ከማህጸን ግድግዳ ውስጥ ያለውን ግሉኮስ በመጠቀም አሲድ ማመንጨት ነው፡፡ ያ አሲድ ደግሞ የሴትን ማህጸን ወይንም ብልት ከተለያዩ ጀርሞች ይከላከላል፡፡ lactobacillus የተሰኘው ባክሪያ ቁጥሩ የሚያንስ ከሆነ ግን ሌሎቹ ማለትም የማይ ፈለጉት ባክሪያዎች ይበልጥ ይራቡና ወደ ፈሳሽ ይለወጣሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ መጥፎ ጠረን ያለው እና ብዛት ያለው ፈሳሽ መፍሰስ ይጀምራል፡፡ ጤነኛ ያልሆነው ፈሳሽ ጠረኑ አሳ አሳ የሚል ሲሆን ቀለሙም ከላይ እንደተገለጸው በተለያየ መልክ ማለትም አረንጓዴ፣ ቡናማ፣ ብጫ ወይንም ነጭ ሲሆን መጠኑም ከተለመደው ውጭ በዛ ያለ ይሆናል፡፡
ይቀጥላል

 

Read 31800 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:42