Saturday, 19 November 2011 15:06

“... የጡት ወተት ...ለተወለዱ ልጆች በቂ ነው”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

“አንዲት እናት ከወለደች በሁዋላ ልጅዋን ለተወሰኑ ወራት ጡት ብቻ የማጥባት የውዴታ ግዴታ አለባት፡፡፡ እኔ በእርግጥ የወለድኩት አንድ ልጅ ነው፡፡ ነገር ግን የአንዱን ልጄን ጡት የመጥባት ፍላጎት ሳስተውለው የወለድኩት መንታ ቢሆን ኖሮ እንዴት አደርግ ነበር ? የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ ለእራሴ አነሳለሁ፡፡ የላንቺና ላንተ አምድ አዘጋጆች ... ሕጻናቱ መንታ ሆነው በሚወለዱበት ጊዜ የጡት ወተቱ በበቂ ሁኔታ ለልጆቹ እንዲዳረስ ለማድረግ እናቶች የሚከተሉት የአጠባብ ስርአት ይኖር ይሆን?”

መቅደስ አበባው ከደብረብርሀን
ከላይ ያነበባችሁትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ አንዲት የመንታ እናት እንዲሁም የህጻናት ሐኪም የሆኑ ባለሙያ ሀሳብ እንዲያካፍሉን ጋብዘናል፡፡ የህጻናት ሐኪሙ ዶ/ር አበበ ከተማ ይባላሉ፡፡ University of California Sandiago Ethiopia በኤችአይቪ ህክምናና ሌሎችም የጤና ሁኔታዎች ላይ የሚሰራ ሲሆን ዶ/ር አበበ ከተማ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍና የህጻናት ኤችአይቪ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ጸጋ ገ/ሚካኤል እድሜዋ 32 አመት ደርሶአል፡ መንታ ልጆች የወለደችው ከስድስት አመት በፊት ሲሆን በወለደችበት ወቅት የሀያ አምስት አመት ወጣት ነበረች፡ የወለደቻችው ተመሳሳይ መንታ ሳይሆኑ የተለያዩ ናቸው፡፡ መንትያዎቹ ናታን ሳሙኤልና መክሊት ሳሙኤል የሚባሉ ወንድና ሴት ናቸው፡፡ በእርግዝናው ወቅት ወ/ሮ ጸጋ ክብደትዋ 42/ ኪሎ የነበረ ሲሆን በእርግዝናው ወቅት ከባድ ጊዜን እንዳሳለፈች ትገልጻለች፡፡ በእርግጥ ወ/ሮ ጸጋ ክብደ ዛሬ ይሻላል ትበል እንጂ ዛሬም ቢሆን ክብደትዋ ከአርባዎቹ ኪሎ አልዘለለም፡፡ በእርግዝናው ወቅት ሁኔታውን መቋቋም ስላቃታት እርግዝናው ለወሊድ ሳደርስ ገና በሰባት ወር ከአስራ አምስት ቀን ገደማ ወደሆስፒታል ገብቶ መተኛት ግድ ነበር፡፡ ለህክምና ክትትል እንደገባችም 1.6/ እና 1.5/ ኪሎ የነበሩትን መንትያ ልጆችዋን ተገላግላለች፡፡
ወ/ሮ ጸጋ እንደገለጸችው ባለቤትዋ አቶ ሳሙኤል ሀደራ በስራ ምክንያት አጠገብዋ መሆን ስላልቻለ በወለደች በሶስት ቀን ተመልሶ ወደስራው ከሄደ በሁዋላ ወደእስዋ የተመለሰው ከሶስት ወር በሁዋላ ነበር፡፡ እናም ሲወለዱ አይቶአቸው የነበሩትን መንትያ ልጆቹን ክብደትና ገጽታ ተለውጦ እና ወፍረው ስላገኛቸው ማመን አቅቶት ነበር፡፡ ወ/ሮ ጸጋ ገ/ሚካኤል መንትያ ልጆችዋን ከወለደች በሁዋላ ለልጆቹ ክትትል ማድረጉ ከበድ የሚል ስራ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
ናታን ሳሙኤልና መክሊት ሳሙኤል የተባሉት የወ/ሮ ጸጋ ገ/ሚካኤልና የአቶ ሳሙኤል ሐደራ ልጆች ሲወለዱ የነበራቸውን ክብደት በቅርብ ጊዜ የመለወጥ ምክንያት የነበረው አመጋገብና አያያዝ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በጊዜው ደግሞ ይወስዱ የነበረው የጡት ወተት ብቻ እንደነበር ወ/ሮ ጸጋ ገልጻለች፡፡ ነገር ግን የጡት ወተት መስጠቱ ከሁለት ወር በላይ መዝለል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ሕጻናቱ በየጊዜው ለክትትል ወደሐኪም ቤት ይሄዱ የነበረ ሲሆን በሁለት ወር እድሜያቸው ጡቱ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ሐኪም ተጨማሪ ምግብ አዞላቸው ነበር እንደ ወ/ሮ ጸጋ ገ/ሚካኤል እማኝነት፡፡
“በጊዜው ሕጻናቱ እንዲጠጡ የተደረገው ናን የተባለውን የዱቄት ወተት ሲሆን የልጆቹ ፍጆታም አንድ ጣሳ ናን ለአንድ ቀን ተኩል ብቻ ነበር፡፡ ጡት ማጥባቱ ቶሎ በመቋረጡና ጡጦ መጥባት ስለጀመሩ እንጂ ገና ሲንቀሳቀሱ በተራ በተራ እያነሳሁ በማጥባት እረፍትን አጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ጡጦ መጥባት በመጀመራቸውና በቤትም ውስጥ የሚረዱኝ ሰዎች ሰለነበሩ እንዲሁም በጊዜው የምሰራው ስራም ቀለል ያለ ስለነበር አልተቸገርኩም፡፡ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ አይደለም መንታ አንድ ልጅም በትክክል ማሳደግ ከባድ ነበር”
ዶ/ር አበበ ከተማ የህጻናት ሕክምና ባለሙያ እንደሚሉት ለተወለደ ልጅ የማይበቃ የእናት ጡት ወተት የለም፡፡ የእናት ጡት ወተት አንድ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ ጤናማ በሆነ መልኩ እንዲያድግ ተፈጥሮ ያዘጋጀችው በሁሉም ንጥረ ነገሮች የበለጸገ እና ጤናማ ነው፡፡ የእናት ጡት ወተት ኢኮኖሚ የማይፈልግና ለማዘጋጀት ጊዜ የማይጠይቅ እንዲሁም ልጅ እና እናትን ለማቀራረብ ከፍተኛ ሚናን የሚጫወት ነው ፡፡
አንድ ህጻን የእናቱን ጡት በሚስብበት ጊዜ የጡት ጫፉና ዙሪያውን ጠቆር ያለው የጡት ክፍል አካባቢ ያሉት ነርቮች ይነቃቃሉ፡፡ በዚህን ጊዜ መልእክት ወደ አእምሮ ስለሚተላለፍ አእምሮ የጡት አካሉ ወተትን እንዲያመነጭ ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡ በእነዚህ መልእክቶች በዋናነት የወተቱ ምርት የሚካሄደው በሁለት መንገድ ሲሆን አንደኛው ወተቱ እንዲመረት ትእዛዝ የሚያስተላልፍ ሌላው ደግሞ የተመረተው ወተት ወደጡቱ ጫፍ እንዲደርስ ቱቦዎቹን እየጨመቀ እንዲወርድ የሚያደርግ ነው፡፡
ዶ/ር አበበ እንደሚገልጹት የጡት ወተት መመረት የፍላጎትና የአቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ ልጁ ጡቱን በሳበው ቁጥር ወተት ስለሚመረት ልጁ እስከጠገበ ድረስ መጥባት ይችላል፡፡ የእናት ጡት ወተት ሁለት አይነት ባህርይ አለው፡ በመጀመሪያው በሚጠ ባበት ወቅት ልጁ የሚያገኘው ወተት የስብ መጠኑን የቀነሰ ውሀ ነው፡፡ ያ ውሀ የልጁን የውሀ ጥም ይገታለታል፡፡ ውሃውን ከጨረሰ በሁዋላ የሚያገኘው ግን በመጠኑ ወፈር ያለ የስብ መጠኑ በርከት ያለ ለእድገቱና ለጤንነቱ የሚረዳውን ንጥረ ነገር የያዘውን ወተት ይሆናል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰውም በተፈጥሮ ለህጻን ልጅ የማይበቃ ጡት የለም፡፡ ምናልባትም የእናትየው ጤና ማጣት ወይንም መጨነቅና በቂ ጊዜ ማጣት የመሳሰሉት ነገሮች እውክታን ካልፈጠረ በስተቀር ወተት በተጠባ ወቅት ስለሚተካ የመጠን ችግር አያጋጥምም ብለዋል ዶ/ር፡፡
ልጆች መንታ ሆነው ሲወለዱ የጡት ወተት የማጥባት የተለየ ህግ የለም፡፡ በእርግጥ እንደተወለዱ ለመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሶስት ሳምንታት ለሁለቱም ልጆች ጡት በመስጠቱ ረገድ የተወሰነ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡ ለምሳሌ መንትያዎቹ በተመሳሳይ ጊዜ ሁለቱም ጡት መጥባት ሊፈልጉ ይችላሉ፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ምናልባት ለእናትየው ሊከብድ ይችል ይሆናል፡፡ መንትዮቹ ሁለት ከሆኑ በአንድ ጊዜ መጥባት ቢፈልጉ የተለያየ ጡትን በተመሳሳይ ጊዜ መስጠት ይቻላል፡ ነገር ግን ከሁለት በላይ ከሆኑና ወተቱን ሌሎቹ ጠብተው ከጨረሱ በሁዋላ ሌላው ቢፈልግ ወዲያውኑ ተተክቶ ላያገኘው ይችል እንደሆን እንጂ በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ማጥባት ይቻላል፡፡ ለማንኛውም ልጆቹ ሁለት ሆኑም ከሁለት በላይ ጡት የሚጠቡበትን ሰአት ማስተካከል ይገባል፡ አንዱ ጠብቶ ከጨረሰ በሁዋላ ሌላውን የማጥባት ሂደት ከተለመደ ለእናትየው እረፍት የምታገኝበትን ሁኔታም ያመቻቻል፡፡ መንትዮችን የማጥባቱ ሂደት በተለይም ሁለት ከሆኑ ከእናትየው ጤንነትና እረፍት ማግኘት ጋር በተያያዘ ካልሆነ በስተቀር በወተቱ መመረት በኩል ምንም እጥረት አይኖርም፡፡ የጡት ወተት ልጆቹ በጠቡት ቁጥር እራሱን የሚተካ በተፈጥሮ ዝግጁ የሆነ ነው፡፡
ዶ/ር አበበ ከተማ የህጻናት ሕክምና ባለሙያ አክለውም የእናት ጡት ወተት በተለይም በመጀመሪያው ስድስት ወር ጊዜ ለእድገቱ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለልጆች የሚያሟላ ነው፡ ለምሳሌ እናቶች ጡት ብቻ የሚጠባ ልጅ ውሀ ይጠማዋል ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ወተቱ ከሰማንያ እስከሰማንያ አምስት ከመቶ ውሀ ነው፡፡ ስለዚህ ሕጻናቱ በመጀመሪያው ስድስት ወር በውሀ የመጠማት ችግር አይገጥማቸውም፡፡ ከዚህም በላይ የህጻናቱ ጨጉዋራ የሚይዘው የተወሰነ መጠን ሲሆን ከጡት ወተት ውጭ ሌላ ነገር የሚሰጣቸው ከሆነ አስፈላጊውን ነገር ሳያገኙ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ተጨማሪ ውሀንና ሌላ ምግብን በመስጠት ወቅት የንጽህና ጉዳይ አስተማማኝ የማይሆንበት አጋጣሚ ስለሚከሰት ልጆቹን ለሕመም ይዳርጋል ፡፡ ስለዚህ አንድ ልጅ መንታም ሆነ አልሆነ እስከ ስድስት ወር ድረስ ጡት ብቻ መጥባቱ በጣም ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ ይረዳዋል፡ አንድ ህጻን ስድስት ወር ከሆነው በሁዋላ ግን የጡት ወተቱ ለእድገቱ የሚፈልገውን ካሎሪ ሀምሳ በመቶ ብቻ የሚያሟላለት በመሆኑ ሌላውን የቀረውን ሀምሳ ከመቶ ከሌላ ምግብ እንዲያገኝ ተጨማሪ ምግብን ማግኘት ይፈልጋል፡ ስለዚህ መንታም ሆነ አንድ ልጅ እስከ ስድስት ወር ድረስ ሌላ ምግብ መመገብ የማይገባው እንደመሆኑ ከስድስት ወር በሁዋላ ደግሞ ተጨማሪ ምግቡ ሳይዘገይ እንዲሰጥ ያስፈልጋል ፡፡ ለአንድ ሕጻን ከስድስት ወር እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲሁም ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ አመት ድረስ ደግሞ በቀን አራት ጊዜ ተጨማሪ ምግቡን መመገብ ተገቢ ነው፡፡
የእናት ጡት ወተት የለም ወይንም አንሶአል ከሚባልበት ምክንያት አንዱ እናቶች ጡታቸውን ለልጆቻቸው የሚያጠቡበት ወቅት መቀነስ ነው፡፡ እናቶች ስራ የሚውሉ ከሆነ ወይንም በተለያየ ምክንያት ልጆቹ ጡቱን የሚያገኙበት ወቅት ውስን ስለሚሆን እና ወተቱ ደግሞ ካልተጠባ ስለማይመረት ለወተቱ መቀነስ ትልቅ ምክንያት ስለሚሆን እናቶች ፕሮግራማቸውን እንዲያስተካክሉ ያስፈልጋል፡ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር በቅርበት መዋል በማይችሉበት ሰአት የጡት ወተትን በማለብ እንዲሁም በማቀዝቀዣ ውስጥ በማስቀመጥም ቢሆን ልጆች እንዲጠጡት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ በጤና ሁኔታ እና በመሳሰሉት የጡት ወተቱ ቢቀንስ ምክንያት የሆነውን ነገር አስወግዶ ወተቱ እንዲመረት ማገዝ ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ምንጊዜም ... መንታም ይሁኑ አይሁኑ ...የእናት ጡት ወተት ለተወለዱ ልጆች በቂ ነው... እንደ ዶ/ር አበበ ከተማ የህጻናት ሕክምና ባለሙያ ማብራሪያ፡፡

 

Read 5681 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 15:08