Saturday, 26 November 2011 08:42

“...40 ከመቶ ወላዶች... በግል የጤና ተቋማት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚያስችለውን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በሚመለከት ከግል የጤና ተቋማቱ ጋር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ፕሮጀክት በሚመለከት እንቅስቃሴውን ለመገምገም አመታዊ ስብሰባውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥቅምት 25/04 አካሂዶአል፡ በፕሮጀክቱ ስብሰባ አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ከአሁን ቀደም ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ስለነበረው አሰራር እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ያለውንና ለወደፊቱ በተሻለ መንገድ ለመንቀሳቀስ ምን መደረግ አለበት የሚለው በውይይቱ ከተነሱ አበይት ሃሳቦች መካከል ነው፡፡

ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ከአጋር ድርጅቶችና ከግል የጤና ተቋማቱ ተወካዮች በተገኙበተ በተካሄደው ስብሰባ የአለም ጤና ድርጅት በPMTCT ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ አሰራር ላይ አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ተገልጾአል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መመሪያ በሚመለከትና ስለአጠቃላዩ ሁኔታም የሚያብራሩ ሁለት የህክምና ባለሙያዎች በዚህ እትም ተጋብዘዋል፡፡ ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ በJHU TSEHAY ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ መከላከልን በሚመለከት የሚሰሩ ናቸው፡ JHU TSEHAY ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማበር ጋር በመተባበር የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ 
እንደ ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ በተለይም በአዲስ አበባ ወደ 25 የሚሆኑ እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት ለክትትል ወደ ግል የህክምና ተቋማቱ ይሄዳሉ፡፡ የማዋለድ አገልግቱንም በሚመለከት ወደ 40 ያህሉ በግል የህክምና ተቋማቱ እንደሚወልዱ ተረጋግጦአል፡፡ ቀደም ሲል ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያደርገው ይህ አገልግሎት በግል ጤና ተቋማቱ ስለማይሰጥ እናቶች የማይሄዱ የነበረ ሲሆን አሁን ግን አገልግሎቱ መሰጠት በመጀመሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል ዶ/ር ዳንኤል፡፡
በግል የጤና ተቋማቱ ውስጥ ባለፉት የስራ ወቅቶች እንደታየው ከሆነ እንደ አንድ ችግር ተቆጥሮ የነበረው የባለሙያ ከቦታ ቦታ ስራ የመለወጥ ሁኔታ ነው፡፡ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ በመከላከሉ ረገድ ተገቢውን ስራ ለመስራት ሙያተኞች ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ በዚህም መሰረት በየወቅቱ ከግል የጤና ተቋማቱ ባለሙያዎች የሚሰለጥኑ ሲሆን የሰለጠኑት ባለሙ ያዎች በነበሩበት የግል የህክምና ተቋም ሳይቆዩ ወደሌላ ተቋም የመሄድ ሁኔታ በስፋት አጋጥሞአል፡፡ በተጨማሪም በቋሚነት ሳይሆን በምሽት እንዲሁም በእረፍት ቀናት በተቋማቱ ተቀጥረው የሚሰሩት ሙያተኞች ለስልጠና ስለማይላኩ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት የጣለበት ሁኔታ ነበር፡፡ ስለዚህ የተሻለ የሚሆነው ስልጠናውን በስፋት መስጠት መሆኑ ታምኖበታል፡ይህ ከተደረገ ባለሙያው በግል ምክንያቱ ስራውን ከቦታ ቦታ ቢቀያየርም እንኩዋን እውቀቱን ይዞ ስለሚሄድ እና ለህብረተሰቡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት መስጠት ስለሚችል ከኤችአይቪ ነጻ የሆኑ ልጆችን ለማፍራት የተተለመው እቅድ ከግቡ እንደሚደርስ እሙን ነው እንደ ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ፡፡
ዶ/ር ዳንኤል በግል የጤና ተቋማቱ ሌላው የታየውና መስተካከል የሚገባው በተለይም የእና ቶችና የህጻናት ሕክምና የሚሰጥባቸው ክሊኒኮች የኤችአይቪ ሕክምና ለእናትየው ወይ ንም ለልጅየው በሚሰጥበት ጊዜ በተለይም ልጅየው በቫይረሱ ከተያዘ እድሜ ልክ ጸረ ኤችአይቪ መድሀኒቱን ማግኘት የሚገባው ሲሆን አገልግቱ ባለመገኘቱ ግን ወደሌላ የጤና ተቋም እንዲሄዱ ይደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን ማንኛውንም አገልግሎት በአንድ የጤና ተቋም ማግኘት ይገባኛል የሚሉ ወገኖች በመኖራቸው አልፎ አልፎ ወደተላኩበት ሌላ የህክምና ተቋም ሳይሄዱ የሚቀሩ እንደሚኖሩ ይገመት ነበር፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በግል ሆስፒታሎችም ሆነ በእናቶችና ሕጻናት ክሊኒኮች የህጻናቶች የኤችይቪ ሕክምና ባለመኖሩ ትልቅ ችግር የነበረ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አሁን በአዲስ አበባ በግል ሆስፒታሎች የህጻናቶች ጸረ ኤችአይቪ ሕክምና የተጀመረበት ሁኔታ ስላለ አገል ግሎቱን ለማስፋፋት እንዲቻል ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ከማድረግ ባሻገር እናቶቹንም ማከም ተገቢ በመሆኑ በተቻለ መጠን በግል የህክምና ተቋማቱ አገልግሎቱ የተሟላ እንዲሆን አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልጆቹን ከኤችአይቪ ቫይረስ ነጻ ሆነው እንዲወለዱ ለማድረግ ጥረቱ ቢኖርም አልፎ አልፎ ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሊኖሩ ስለሚችሉ ህክምናውን መስጠት ተገቢ በመሆኑ በግል የህክምና ተቋማቱ በተሟላ መልኩ አገልግሎቱን መስጠትን ማጠናከር በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዙ እቅዶችን በመድረስ ረገድ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው እንደ ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ፡፡
WHO የአለም የጤና ድርጅት የPMTCTን ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ እንቅስቃሴ ለማገዝ የሚያስችል አዲስ የአሰራር እቅድ አውጥቶ ለሀገራት አስተላልፎአል፡ ይህንን በሚመለከት ማብራሪያቸውን የሰጡን ዶ/ር ታደሰ ከተማ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የእናቶች ጤና አማካሪ ናቸው፡፡
እንደ ዶ/ር ታደሰ ባጠቃላይ የ ሓልማ ም ሆነ ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን በሚመለከት የአለም የጤና ድርጅት ካለው የቅርብ ሳይንሳዊ ግኝቶችና ከተለያዩ ተሞክሮዎች በመነሳት ለተለያዩ ሀገሮች ምን አይነት የህክምና አገልግሎቶች ተካተው ቢሰጡ ለህብረተቡ ይጠቅማሉ በሚል ምክር የሚሰጥ ሲሆን ሐገሮች ደግሞ ወደራሳቸው አሰራር በመቀየር ተግባራዊ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የPMTCT አገልግሎት በምን መልክ ቢሰጥ የተሻለ ይሆናል የሚለውን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2004 ጀምሮ የተለያዩ አሰራሮችን ተግባራዊ እንዲሆን አድርጎአል፡፡
በኤችአይቪ ቫይረስ የተያዙ እናቶችም ሆኑ ልጆች ቀደም ሲል ይወስዱ የነበረው ኔቨርአፒን የሚባል መድሀኒት ሲሆን በልጆቹ የጡት አጠባብም ላይ ከወቅቱ ሳይንሳዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምክሮች ይሰጡ ነበር፡፡ አሁን በአገልግሎት ላይ ያለው አሰራር ደግሞ በ2007 ከአለም የጤና ድርጅት የተሰጠ ሲሆን በእርግዝናው ወቅት 28ኛው ሳምንት ላይ መድሀኒት ይጀመራል፡፡ በምጥ ጊዜ ሶስት መድሀኒት፣ ከምጥ በሁዋላ ደግሞ ሁለት መድሀኒቶች ለሰባት ቀን ይሰጣል፡፡ ልጁ እንደተወለደ ሁለት መድሀኒት እና ከተወለደ በሁዋላም ለሰባት ቀን መድሀኒቱን ይቀጥላል፡፡ እናትየው በእርግዝናው ወቅት በቂ መድሀኒት ካላገኝች ግን ለአንድ ወር ያህል መድሀኒቱን ልጁ እንዲያገኝ የሚያ ደርገው አሰራር እስከአሁንም በተግባር ላይ ያለ ነው ዶ/ር ታደሰ ከተማ እንደገለጹት፡፡
WHO እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 የአገሮችን ነባራዊ ሁኔታ በማየት እና በሁዋላ ላይ ከመጡ ሳይንሳዊ ግኝቶች በመነሳት አዲስ አሰራር እንዲጀመር መመሪያ አውጥቶአል፡ ከእናት ወደልጅ ኤችአይቪ እንዳይተላለፍ በማድረግ ረገድ መድሀኒት ወይንም የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ብቻ ሙሉ በሙሉ መከላከል ሳይሆን መቀነስ ነው የሚቻለው፡፡ ቀደም ባለው አሰራር 28ኛው ሳምንት ላይ እናትየው የምትጀምረው መድሀኒት አሁን ግን በ14ኛው ሳምንት እንድትጀምር ሲሆን የልጁ የመድሀኒት አወሳሰድ ደግሞ በተለይም ጡት የሚጠባ ልጅ ከሆነ ጡት በሚጠባበት ወቅትና ጡት መጥባቱን ካቆመ በሁዋላ ለአንድ ሳምንት ቆይቶ መድሀኒቱን አንዲያቆም ይመክራል አዲሱ መመሪያ፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው አዲሱ አሰራር በተጨማሪ ያካተተው ጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት እናቶች የሚወስዱ ከሆነ ከሌሎች ሰዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ በ2010 የወጣው የአሰራር መመሪያ የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ የሚያስችል በመሆኑ ኢትዮጵያም የተቀበለችው ሲሆን ወደስራው ለመግባት ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡፡
የሳይንስ ምርምር ማብቂያ የለውም፡፡ ሳይንሳዊው ምርምር የመድሀኒቶችን ውጤት እንዲሁም መድሀኒቱ ለህዝብ በሚሰጥበት ጊዜ የሚያመጣው ለውጥ ምን እንደሆነ የሚመረምር ሲሆን ከተለያዩ አገሮች እንዲሁም ከብዙ ሰዎች ወይንም ሁኔታ በመነሳት በሚገኝ ውጤት የሚወሰን ነው፡፡ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚሰጥ አገልግሎት ሲባል በቅድሚያ ለእናቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም እናቶች የጤና አገልግቱን የሚፈልጉት ቅድመ ወሊድ በወሊድና በድህረ ወሊድ ጊዜ ስለሆነ ነው፡፡ በአገራችን የቅድመ ወሊድ የጤና አገል ግሎት ሽፋን የጨመረና የወሊድ ሽፋንን የሚያገኙት እናቶች ቁጥር ደግሞ ውስን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅድመ ወሊድ ጊዜ ወደህክምና ተቋም የሚመጡት እናቶች ለኤች አይቪ የመመርመራቸው ሁኔታና ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ እናቶችን ለይቶ በማውጣት ላይ ገና ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ የታመነበት ነው፡፡ ይህንን ለማሻሻል የተለያዩ እቅዶች ተይዘው ለመተግበር ቅድመ ሁኔታዎች በመመቻቸት ላይ ናቸው፡፡ ቅድመ ወሊድ ላይ የኤችአይቪን የምክር አገልግሎት እና የኤችአይቪን የህክምና አገልግሎቶች በአጠቃላይ ለእናቶች ለማድረስ የሚያስችል አዲስ እቅድ ወጥቶ ለመተግበር በኢፊድሪ ጤና ጥበቀ ሚኒስር በኩል ሁኔታዎች በመመቻቸት ላይ ናቸው ዶ/ር ታደሰ ከተማ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የእናቶች ጤና አማካሪ እንደገለጹት፡፡

 

Read 2653 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:45