Sunday, 06 May 2012 14:49

..ሕይወት ለመስጠት ስትል ሕይወቷ ማለፉ ...እንደዜጋም.

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

. ...አይሄይሄ ...አማ አንቺ...እንዲህ እንደዛሬው ቢሆነማ እኔስ ለምን ተሰቅቄ....

ከላይ ያነበባችሁት አባባል የአንድ አባወራ አባባል ነው፡፡ የተገናኘነው በፍኖተሰላም ሆስፒታል ነው፡፡ አባወራው ሁለት ህጻናትን ይዘዋል፡፡ ሴትዋን ልጅ በእንኮኮ አንገታቸው ላይ...ወንድየውን ደግሞ በእጃቸው ይጎትታሉ፡፡ አረማመዳቸውም አስተያየታቸውም የትካዜ መልክ አለበት፡፡ አለባበሳቸውን ልብ ብለን ስንመለከት በኮታቸው የደረት ኪስ ላይ ጥቁር ምልክት አድርገዋል፡፡ ምልክቱ የሀዘን ምልክት ነው፡፡ ታሪካቸውን እንዲያካፍሉን ጠየቅናቸው... እምቢ አላሉም፡፡ እኛም ለአንባቢ ብለነዋል፡፡

.....እኔ የምኖር... ቋሪት በተባለች ገጠራማ አካባቢ ነው፡፡ በግምት ከፍኖተሰላም ወደ ሰማንያ ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡ ስሜም አቻምየለህ ባንተይርጋ ይባላል፡፡ እድሜዬም ወደ ሰላሳው ግድም ነው፡፡ እናም...ከባለቤ ጋር ከተጋባን ይኼው የሚመጣው ጥር ወደ ስምንት አመት ይሆነናል፡፡ እስዋ እድሜዋ ሀያ ሶስት ነበር፡፡ ..

በመሀከል አቋረጥነውና...ምነው ነበር... አልክ...አሁን የለችም እንዴ... የሚል ጥያቄ አነሳን፡፡ ተከዝ እንደማለት አለና...ሀዲያ ብትኖር ብለሽ...ሁለት ልጅ ...አንዱዋን በትከሻ አንዱን በእጄ ይዤ መጎተ...አሁንም የሐዘን ድባብ በአካባቢያችን ሰፈነ፡፡ ቀጣዩን ነገር ለመጠየቅ... እን ዴት...መቼ እንደምንጀምር ግራ ተጋባን፡፡ አቶ አቻምየለህን ለማጽናናት በምን አባባል እንደም ንጀምር አሁንም ግራ ተጋባን፡፡ አቶ አቻምየለህ እራሱ...

....ተውት እሱን... እሱዋ በኖረችና እኔ ምንም በቀረብኝ... አለ፡፡ በመቀጠልም...ልጆቹ በላይ በላይ ነው የተወለዱ፡፡ እነዚህ የምታዩዋቸው ልጆች ...አሁን አንዱ የስድስት አመት አንዱ ደግሞ የአምስት አመት ናቸው፡፡ ሀዲያ ልጅ በላይ በላይ መውለድ ጥሩ አይደለም እየተባለ ትምህርት ሲሰጥ ሰምተን... አራርቀን እንወልዳለን ብለን ...ከበፊተኛው ትንሽ ዘግየት ብላ ነበር የጸነሰችው፡፡ እንግዲህ እሱም ቢወለድ ...እሱዋም ብትኖር ኖሮ ...የስድስት ወር ልጅ ይኖረን ነበር ...ማለትም አይደል... ..

አሁንም አቶ አቻምየለህ ወደመሬት አዘቀዘቀ፡፡ እኛም በመቀጠል...እናስ ምን ተፈጠረ...ብለን ጠየቅን፡፡

.....አሀ...የማይቀረው ምጥ መጣ፡፡ እነዚህን ትልልቆቹንም ያው እቤት ነው... እመይ ገበያነሽ በሚባሉ ...የመንደር አዋላጅ እጅ የወለደች፡፡ ሴትየዋ በጣም ጎበዝ ናቸው፡፡ ነገር ግን የዚህኛው ግዜ..እንጃ ምን እንደሆነ አልቀናም አለ፡፡ ምጥ ከተያዘች ጀምሮ አጥቢያው በሙሉ ቤቱን ለቆ ከኛው ደጅ እዝጊዮ... ቢልም ምንም አልተሳካም፡፡ በሁዋላ የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች መጥተው በፍጥነት ወደሆስፒታል ውሰዱ ቢሉን... እንዲያው ከጎረቤቶቼ ጋር ተጋግዘን በቃሬዛ ተሸክመን ወደዚህ አቀናን፡፡ እንግዲህ እዚህ ስንመጣ ...መቼም የመንግስት ሆስፒታል ብዙም አይጠይቅ ብዬ ...አንዲት ጥገት ላሜን ሸጬ ነበር የመጣሁት፡፡ ለካንስ ሕመሙ ከእነሱም አቅም በላይ ኖሮ...በአስቸኩዋይ  ወደ ደብረማርቆስ ወይንም ወደባህርዳር ይዛችሁ ብረሩ አሉን፡፡ ...ያቆምኩት መኪና የለኝ...በምኔ ልብረር.. የሚወስድ መኪና ኪራይ እስክነጋገር ድረስ እዚሁ ሆስፒታሉ ደጅ እያየሁዋት የምወዳት ባለቤ እጄ ላይ አለፈች፡፡ እህ.ህ.ህ ... ትርንጎዬ...ከወዴት ላምጣት... ..

አቶ አቻምየለህ ጉልበቱን በጉልበቱ መካከል አዘቅዝቆ ማልቀሱን ተያያዘው፡፡ የሚያባብለው ወይንም የሚያጽናናው አልተገኘም፡፡ ሁሉም አብሮት ያለቅስ ነበርና፡፡ ከአፍታ ቆይታ በሁዋላ...

..... እንግዲህ ልብ በሉ... እሱዋ የሞተች የዛሬ ስድስት ወር ነው፡፡ አሁን ደግሞ ስሰማ ...እዚሁ ሐኪም ተመድቦ ይኼው ሴቶቹ እንደልባቸው ይገላገላሉ፡፡ ...አይሄይሄ ...አማ አንቺ...እንዲህ እንደዛሬው በሆነማ እኔስ ለምን ተሰቅቄ ...ለትንሽ ተቀደምኩ...ይኼው ሁለት ልጅ ጥላብኝ ሙታ..እኔንም ሙት አደረገችኝ፡፡ ምን ላርጋቸው...ቤቱ ሙሉ ነው አብሮአት የሞተው፡፡ እናትና አባን ጧሪ ነበረች፡፡ ...አረ ተይኝ.....

የአቶ አቻምየለህን ንግግር ካደመጥን በሁዋላ ወደ ሕክምና ክፍሉ ነበር ያመራነው፡፡ በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል አፋጣኝ እና የተሟላ የማዋለድ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችለውን ስልጠና በመስጠት ላይ ያሉትን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት አነጋገርን፡፡ ዶ/ር ባዘዘው ፈቃደ ይባላሉ፡፡ እሳቸው ወደ ሆስፒታሉ ከመሄዳቸው በፊት የነበረውንና በአሁን ወቅት ያለውን የታካሚና የህክምና ታሪክ ይነግሩናል፡፡

.....እኔ ...በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ውስጥ ያሉ ሁለት የጠቅላላ ሐኪሞችን በጽንስና ማህጸን ሕክምናና በአፈጣኝ የጽንስና የማህጸን ሕክምና ከማሰልጠንም ባሻገር ሕክም ናውን እና የማዋለድ ተግባሩን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ከመምጣ ከሁለት ወር በፊት ማለትም ስልጠና ከመሰጠቱ በፊት ያለውን መረጃ ስናገላብጥ የወላዶች ቁጥር በወር ከሰላሳእና ከአርባ አይበልጥም ነበር፡፡ በዚህ ሁለት ወር ውስጥ ማለትም ጠቅላላ ሐኪሞችን ማሰልጠን ከጀመርኩ በሁዋላ በእጥፍ ጨምሮአል፡፡ የቅድመ ወሊድ ክትትልም በሶስትና በአራት ጨምሮአል፡፡ እናቶች ከዚህ ሆስፒታል ከደረሱ በሁዋላ ለመውለድ ወደሌላ ሆስፒታል እንዲሄዱ ሲነገራቸው በገንዘብ እጦት ምክንያት ወይንም እናትየው በመድከሙዋ አለዚያም ሕይወቷ በማለፉ ምክንያት አብዛኞቹ መሄድ የማይች ሉበት ሁኔታነበር፡፡ መሄድ የሚችሉት እንኩዋን በወር ከሀያ እስከ ሰላሳ የሚደርሱ እናቶች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከመውለድ ጋር በተያያዘ ወደሌላ ሆስፒታል እንዲሄዱ የሚደረግበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦአል ፡፡ ሁሉም እናቶች እዚሁ ሆስፒታል እንዲወልዱ እየተደረገ ነው፡፡ በዋናነት የምመለከተው አንዲት ወጣት የሆነች እናት ሕይወት ለመስጠት ስትል ሕይወቷ ማለፉ ለእኔ እንደዜጋም ...እንደባለሙያም እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ አንዲት ሴት እርጉዝ ሆና ልጄን ወልጄ አቅፋለሁ የሚል ስሜት ይዛ ቆይታ...ነገር ግን መውለድ አቅቶአት ሕይወቷ ሲያልፍ ማየት በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል በዚህ ሁለት ወር ውስጥ አልታየም...ወደፊትም እንዳይታይ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ..

በመቀጠል ያመራነው ወደሆስፒሉ አስተዳደር አካባቢ ነበር፡፡

.....ስሜ በላይነሽ ደምሰው ካሳ እባላለሁ፡፡ በፍኖተ ሰላም የፋይናንስ የስራ ሂደት መሪና ስራ አስኪያጅ በሌለበት ጊዜም ስራ አስኪያጁን ወክዬ የምሰራ ነኝ፡፡ የፍኖተሰላም ሆስፒታል በአማራ ክልል በምእራብ ጎጃም ዞን ብቸኛ የገጠር ሆስፒታል ነው፡፡ ከአሁን ቀደም በሆስፒታሉ በተለይም የጽንስና ማህጸን ሕክምናን በተመለከተ የባለሙያ ችግር ነበረብን፡፡ ችግሩ በጣም የከፋ በመሆኑም ከአሁን ቀደም የውጭ ሰዎች ይህንን ሕክምና እንዲሰጡ አስመጥንተ የነበረ ሲሆን አገልግሎቱ ግን እምብዛም አርኪ አልነበረም፡፡ በመሆኑም እናቶች ሲሞቱ እጅግ አሳዛኝ ታሪክ የነበረ ሲሆን ባለሙያዎቹም አገልግ ሎታቸውን አቋርጠው እንዲሄዱ ተደርጎአል፡፡ በአሁን ወቅት ግን የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ባደረገው ድጋፍ አንድ ባለሙያ ተመድቦ ሁለት ጠቅላላ ሐኪሞችን በማሰልጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን ይኼኛው ባለሙያ ከመጣ ወዲህ ግን ምንም እናት ወደሌላ ሆስፒታል እንድትሄድም አልተደረገም...የሞት ወሬውም በሆስፒታሉ ግቢ አልተሰማም፡፡ ከታካሚዎችም ይሁን ከቤተሰብ እንዲሁም ከአካባቢው የሚሰጠው አስተ ያየት እንደዚህ ያሉ ባለሙያዎችን ...አስፈላጊውን አሟልታችሁ አቆዩልን...የሚል ነው ፡፡ ሆስፒታላችን አገልግሎት የሚሰጠው በአካባቢው ካሉ ሰባት ወረዳዎች ለሚመጡት ሲሆን ቀደም ሲል የሆስፒታሉ አቅም ስለማይፈቅድ ወደሌላ ሆስፒታል እንዲሄዱ ሲነገራቸው በተለያየ ምክንያት አይሄዱም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ከሆስፒታሉ ግቢ ጀምሮ በየመንገዱ እንዲሁም እቤታቸው ከደረሱ በሁዋላ የሚያልቁትን ቤታቸው ይቁጠራቸው፡፡ አሁን ግን ሁኔታው ተለውጦ የሰባቱም ወረዳ እናቶች ተገቢውን ሕክምና ማግኘት ጀምረዋል፡፡ የምእተ አመቱን የልማት ግብ ከማሳካት አኩዋያ አገራችን ትኩረት አድርጋ የምትንቀሳቀስበት የእናቶችን ሞት መቀነስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ቀድሞ የነበረበትን ጉድለት በማሻሻል በአሁን ወቅት በሆስፒታሉ ያሉት የጠቅላላ ሐኪ ሞች ከስልጠናው በሁዋላም እስፔሻሊስት ሐኪሙን ዶ/ር ባዘዘው ፈቃደ ተክተው እንደሚሰሩ እምነታችን የጸና ነው፡፡..

በሆስፒታሉ ያገኘናቸው ታካሚዎች እንዲሁም ከሙያተኞችም ጭምር የተሰነዘሩ አስተያየቶች .. ...ይህ ችግር ተመልሶ እንዳይመጣ እንሻለን፡፡ ቢቻል ሐኪሙን ቢያስቀሩልን ...ከላልሆነም ደግሞ ሌላ ተመሳሳይ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ በሆስፒታሉ ቢመደብልን የሚል ሀሳብ ያላ ቸው አስተያየቶችን ተቀብለናል፡፡

ከላይ የተገለጹትን አስተያየቶች መሰረት በማድረግ አሰልጣኝ ሐኪም ዶ/ር ባዘዘው ፈቃደ የሰጡት መልስ .....ከስልጠናው በሁዋላ ሐኪሞቹ ሙሉ በሙሉ አሁን ከእኔ ጋር አብረው የሚሰሩትን ስራ ያለ ምንም ችግር መቀጠል ይችላሉ፡፡.. ብለዋል፡፡

ዶ/ር መሐዲ በክሪ በኢሶግ ቂስቈሸስቃሰቨ ቄሯቋስቈሽሰ ፤ ቃስቄቃሮሮቁ ሰሮቈስ ፕሮጀክት አስተባባሪ እንደሚገልጹት .. ...ኢሶግ የስልጠናውን ፕሮግራም ያዘጋጀው ለስድስት ወር ሲሆን በዚያ ወቅት በተለያዩ መስተዳድሮች በሚገኙ በዘጠኙም ሆስፒታሎች በመሰልጠን ላይ ያሉት የጠቅላላ ሐኪሞች ስራውን በትክክል እንደሚሰሩ እምነት አለን ..ብለዋል፡፡ ዶ/ር መሐዲ በመቀጠልም እንደገለጹት .....ከአሁን ቀደም በመጀመሪያው ዙር ፕሮግራም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በአገሪቱ በተለያዩ መስተዳድሮች በሚገኙ አስራ ሶስት ሆስፒታሎች ሁለት ሁለት የጠቅላላ ሐኪሞችን በማሰልጠን ለአገልግሎት ያበቃ ሲሆን በዚህ በሁለተኛው ፕሮግራም ደግሞ በዘጠኝ ሆስፒታሎች ተመሳሳይ የስልጠና ፕሮግራም ዘርግቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ተግባር የእናቶችና የህጻናትን ደህንነት ከማስከበርና ሕይወትን ከማዳን አኩዋያ ከባድ ኃላፊነትን መወጣት የሚያስችል ነው፡፡ በእርግጥ የዚህ ዙር ስራ በስድስት ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን የእናቶችን ሞት ከመቀነስ አኩዋያ ውጤት ያስመዘገበ ስለሆነ ...በግሌ ...ቀጣይ የስራ ሂደት ይኖረዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ.....ብለዋል፡፡

 

 

Read 1772 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 16:05