Print this page
Saturday, 10 September 2011 12:35

መጥላት የማልወዳቸው

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

መልካም አዲስ አመትን በመመኘቴ አዲሱ አመትመልካም     እንደሚሆን ማረጋገጥ    አልችልም፡፡ መልካም መመኘት ግን ለማንኛውም ይሻላል፡፡ እውነትን ያጣ ህልውና ምኞቱን አራርቆ እንዲወልድ አይገደድም፡፡ ምኞት ራሱ፤ ውበት ገና ያላቆጠቆጠበት የጥበብ አይነት ነው፡፡ የተሻለ ነገርን የሚፈልግ ግን ፍላጐቱን ከአፈላለጉ ዘዴ መለየት የማይችል የደቦ ፈጠራ ምንጭ፤ ምኞት ነው፡፡ ግዴለም፤ መልካም አዲስ አመት ተመኝተናል፡፡ አዲስ አመትም አዲስ ምኞት በድሮው ላይ የመደረቻ አጋጣሚ ነው፡፡ ይሁን፡፡ አዲስ አመት ለኔ የንብረት ቆጠራ ወቅት ነው፡፡ የምወዳቸውን እና የምጠላቸውን ነገሮች እንደ አዲስ አራግፌ የምንደረድርበት የጽዳት ጊዜ፡፡
መጥላት እና መውደድ በቀጥታ የሚገናኘው ከዋጋ ጋር ነው፡፡ ዋጋ ያለው ነገር ይወደዳል፤ የሌለው  ደሞ ይጠላል ማለት ነው፤ በአጭሩ፡፡

ለምሳሌ፤ መጪው አመት ካሳለፍኩት የተሻለ ሳይሆን የባሰ እንደሚሆን እያወኩ የተሻለ ነገር እንዲከሰት የምጠብቅ ከሆነ፤ መጠበቁ ዋጋ የለውም፡፡ ምኞቴም የሚወደድ ሳይሆን የሚጠላ ወይንም የሚያስጠላ ነው (ማለት ይቻላል)፡፡
የሚያስጠላው ምኞቴ ብቻ ሳይሆን፤ አብሮ መጪው አመትም ያስጠላል፡፡ የሚያስጠላ ነገር ዋጋ የለውም፡፡ በሚያስጠላ አመት ውስጥ ተስፋን መዝራት ይከብዳል፡፡ ከተዘራው ተስፋ ውስጥም የሚታጨድ ተወዳጅ ነገር ይበቅል ይሆን ብሎ መጠበቅም አብሮ ያስጠላል፡፡
ታዲያ እንዴት ነው በሚመጣው አስጠሊታ አመት ውስጥ የምወዳቸውን ነገሮቼን እንዳይጨፈለቁ ተጠንቅቄ የማሳልፋቸው?
ብዙ የምወዳቸው ነገሮች አሉ፡፡ ልጠላቸው የማልፈልግ፡፡ ዋጋቸው ላይ አዎንታዊ እድገት ላክልባቸው እንጂ ልቀንስባቸው የማልፈልጋቸው ..መውደዶቼ..፡፡
ውድ ዋጋዎች በተከታታይ እና ያለማቋረጥ ርካሽ በሆነ የአመት ሰንሰለት ውስጥ ሲያልፉ ማንፀባረቃቸው ይፈገፈጋል፡፡
ጥበብን እወዳለሁ፤ ማስገባቱን እወዳለሁ፤ ማስወጣቱን ደግሞ የበለጠ፡፡ ማሰብ እወዳለሁ፣ ባልተያዘ አየር ውስጥ እየተነፈስኩ መጓዝ እወዳለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ያላየሁትን ነገር ማየት መስማት እና መቅመስ ...፣ ከዚህ በፊት ያየሁት እና የቀመስኩትን ደግሞ በአዲስ መንገድ ማጣጣም እወዳለሁ፡፡
መጥላት አልወድም፡፡ ስጠላም ለምወደው ነገር ስል ነው፡፡ የምወዳቸው ነገሮች እንዳይጐዱብኝ ጐጂውን በጥላቻ ማራቅ አለብኝ፡፡ እውነተኛ መውደድ ከብዙ ቅርፊት የተሰራ ነው፡፡ አንደኛው ቅርፊት በወረት ወይንም በጥላቻ ተቀርፎ ሲወድቅ አዲስ የመውደድ ቆዳ ከስር ብቅ ይላል፡፡
ለሰው ልጅ ያለኝ ጥቅል ውዴታ የዚህ ተምሳሌት ነው፡፡ ብዙ አይነት ስም ያላቸውን ግለሰቦች ወድጄ ጠልቻለሁ፡፡ እንደ ቅርፊቱ፡፡ በሰው ልጅ ስም የሚጠራውን ማንነት ግን ልጠላው አልችልም፤ አልፈልግምም፡፡
የጥበብ ስራን እወዳለሁ፤ ስለ ጥበብ ሰሪው ግን ግድ የለኝም፡፡ የጥበብ ስራውን በመውደዴ የጥበብ ሠሪው ተወዳጅ እንዲሆን ሊያደርግልኝ የቻለ ማንም የለም፡፡...ስሪቱ ከሰሪው በላይ ነው፡፡  
ከማውቀው ሰው ይልቅ የማላውቀውን ሰው የበለጠ እወዳለሁኝ፡፡ ሰውየውን ሳላውቀው እኔ ነኝ በምናቤ የቀረጽኩት፤ የተጠበብኩበት፡፡ ሰውዬውን ሳውቀው እኔ የሰራሁት መሆኑ አከተመ፡፡
የተፈጥሮው ሰው፡፡ ሆዳም ነው፣ ራስ ወዳድ ነው፣ ፈሪ ነው፣ ወይንም ሞኝ ነው፣ ሲያወራ ይጮሃል፣ ሲያላምጥ ይንጣጣል፣ ውሃ ካጣ ይግማማል... ማለቂያ የለውም... ወዘተ ወዘተርፈ፡፡ ከሰው ሰው ከስህተት የስህተት አይነት ይለያያል፡፡ ከጥላቻ በራቀበት እና ወደ መውደድ በቀረበበት መጠን የተሻለ ሰው ይባላል እንጂ ትክክል ግን የለም፡፡ የተሻለ ስህተት ትክክል አይደለም፡፡
የማላውቀውን ሰው እንጂ የማላውቀውን ስራ ግን ወድጄ አላውቅም፡፡ ስራውን ለመውደድ ስራውን ከሰራው ሰው ጋር ሳይሆን ከስራው ብቻ ጋር መተዋወቅ አለብኝ፡፡ መዋደድ በእዳ መልክ ግንኙነት በተቆራኙት መሀል ሊፈጥር ይችላል፡፡   
የማይነጠል ቁራኛን መጥላት አያዋጣም፡፡ መውደድ ብቻ ከሆነ አማራጩ መዋደዱ የዕዳ ባህርይ የተላበሰ ይሆናል፡፡ የስጋ ዝምድና ወይንም የስጋ ዝምድናን ለመመስረት ሲባል የሚፈጠር የስሜት ቁርኝት፤ ..መውደድ.. በእዳ ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ መውደድ በዕዳ እንጂ መጥላት በዕዳ ግን የለም፡፡
ጥበብን መውደድም እዳ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ በተለይ በሚያስጠላ አመት ውስጥ መውደድን ተሸክሞ መጓዝ ግዴታ ሲሆን፡፡
ሰማዩን አሁንም እወደዋለሁ፡፡ (እርግጥ ካየሁት ወደ አንድ አመት ከመንፈቅ አልፎኛል እንጂ፡፡ ቀና ብዬ ሰማዩን ባየው እንደ ድሮው በክዋክብት አበባ እና በፌንጣ ጩኸት እና በልብ ፀጥታ የተሞላ ሳይሆንልኝ ቢቀር፤  እጠላዋለሁ፡፡ ከምጠላው በድሮ ትዝታዬ ሆኜ መውደዴን ብቀጥል ይሻላል)
ለውጥን እወዳለሁ፡፡ ግን የምወደው በምኞት ብቻ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ በጽንሰ ሐሳብ፣ በቲዎሪ ብቻ፡፡ ቲዎሪው ተግባር ሆኖ ለውጥ ሲመጣ ግን ሆዴን ባር ባር ይለኛል (Bar ፈልጌ ፉት እልለታለሁ)
ድሮ ያደኩት ሰፈር መንገዱ እንዴት እንደነበር ማስታወስ ተስኖኛል፡፡ መለወጡን በተስፋ ወድጃለሁ፡፡ ሲለወጥ ባዶ ሆኖ አስጠልቶኛል፡፡
መውደድ እና መጥላት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ወይ? ብዬ ግር እሰኛለሁ፡፡ ምኞትን መውደድ? ምኞቱ ተወልዶ በእግሩ ሲሄድ ለመጥላት ነው እንዴ? በምኞት ደረጃ የተወደደ ምኞቱ የተሳካ ለት ይጠላል፡፡ በምኞት ደረጃ የተጠላ በስኬት ደረጃ ይወደዳል ማለት ነው፡፡ ምን አይነት ዲያሌክቲክስ ነው ጃል? ይኼ ማለት እኮ በምኞት ..መልካም አዲስ አመት.. ያልነው ምርቃት መጥፎ አሮጌ አመት ሆኖ በእርግማን ይሸኘናል ማለት ነው፡፡
ለማንኛውም ግን ጥበብን እወዳለሁ፡፡ መጥላት የምወዳቸው ብዙ ሌላ መውደዶች አሉኝ፡፡ ግን ለጥበብ ይሄ አይሰራም፡፡ ጥበብን ስመኘውም እንደ ተግባሩ እወደዋለሁ፡፡ ጥበብን ከእውነታ ጋር ለማቆራኘት መሞከሩን ነው የምጠላው፡፡
ጠዋት በእግሬ እያዘገምኩ ማሰብ እወዳለሁ፡፡ የምጠላው ከብዙ ጉዞ በኋላ የሚሰማኝን ድካም ነው፡፡ ፎቶግራፎችን በሙሉ እወዳለሁ፡፡ ዘመናት ባለፉ ቁጥር ጥበብ ይሆናሉ፡፡ ባዶ ክፍል ውስጥ ከሀሳቤ ጋር መቀመጥ እወዳለሁ፡፡ ሌላ ጭንቅላት ሲያንኮራፋ በማልረበሽበት፡፡ የአሮጌ መጽሐፍትን ሽታ እና ክብደት እወዳለሁ፡፡ ቴሌቪዥን እየተመለከትኩ በቴሌቪዢኑ ውስጥ የራሴን ቴሌቪዥን ከፍቼ መመልከት እወዳለሁ፡፡
ጭንቅላት ካላቸው ሴቶች ጋር መናበብ እወዳለሁ (ጭንቅላት ያላቸው ሴቶች ብዙ አለማግኘቴን እጠላለሁ) የአበሻን መልክ እወዳለሁ (በተረፈ መውደድ የምጠላው ነገር ብቻ ነው ያለው ስለ አበሻ)
ትርጉም ያላገኘሁላቸው መውደድ እና ጥላቻዎችም በብዛት አሉ፡፡ እንዴት ልደረድራቸው፣ ወይንም ላስወግዳቸው እንደምችል ፍቺ ያላገኘሁላቸው ነገሮች፡፡ ትርጉም የዋጋ መለኪያ አንዱ መስፈርት ነው፡፡
የሰዎችን (የሰው ልጆችን) ቆራጥነት፣ ታጋይነት፣ ጠንካራነት፣ ቀዳዳ ፈላጊነት ብዙ አዎንታዊ መገለጫዎቹን እወዳለሁ፡፡ ግን አንዳንዴ ደግሞ ቆራጥ፣ ታጋይ፣ ጠንካራ የሆኑለት ነገርን (አላማን) የተሳሳተ እምነት ሲሆን እጠላለሁ፡፡ የምወደውን ነገር ከምጠላ ግን የጠላሁትን ነገር በአዲስ እይታ ተመልክቼ ብወድ ይሻለኛል፡፡ መውደድ ከመጥላት ይሻላል፡፡ ምናልባት ወዳጅም ደግሞ ከጠላት፡፡
የጥበብ አናት እየሆነ ለመፍረድ ያስቸገረኝን ሙዚቃ እወዳለሁ፡፡ ብቻዬን ሆኜ መስማት የምወደውን ሙዚቃ፤ ከሰው ጋር አብሮ በማድመጥ ጠልቼም አውቃለሁ፡፡ ወይንም ከምወዳት ጋር አብሬ በማድመጥ አብሮኝ ያለውን ነብስ እና ሙዚቃዋን አፍቅሬም አውቃለሁ፡፡ ያፈቀርኳት ነብስ ስትለይ ሙዚቃው ወደ ስቃይ ተቀይሮብኝ መውደድም መጥላትም ሲያቅተኝ አይቻለሁ፡፡
አሁን የፍቅር ስቃይ የሚወደድ ነው ወይንስ የሚጠላ ነገር? የቱ ቦታ ላስቀምጠው? ትርጉም ያላገኘሁላቸውም ብዙ ነገሮች አሉ ብያለሁ፡፡ ስቃይ ከእነሱ ነገሮች አንዱ ነው፡፡
በሙሉ የተከማቸውን ላወጣው አልችልም፡፡ የምወዳቸው እና የምጠላቸው ነገሮች የተከማቹት ትዝታዬ ውስጥ ነው፡፡ ከላይ  ያለውን እንዳሁኑሀ ካስተካከልኩ ለዛሬ ይበቃኛል፡፡ የተቀረውን በአዲሱ አመት ሂደት ውስጥ አስተካክላለሁ፡፡ ለማንኛውም፤ የጠላሁቸውንም ነገሮች መልሼ የምወድበት ጊዜ ሊመጣ ስለሚችል ጠርጌ ባላስወግዳቸው ይሻላል፡፡ አንድ ቦታ ልቆልላቸው፡፡ በመሰረቱ የትዝታን ቁሻሻ መጥረግ እና ማከማቸት እንጂ አውጥቶ እስከወዲያኛው መጣል አይቻልም፡፡ የትዝታ ንጽህናም ሆነ ቁሻሻ ይባዛል እንጂ አይወገድም፡፡ ወደ ሰው በማስተላለፍ ማባዛት ይቻላል፡፡ ለዚህም ጥበብ ዋነኛ መሳሪያ እና ስራው ነው፡፡
ለአዲስ አመት የተመኘሁላችሁን በልቤ ይዣለሁ፡፡

 

Read 1923 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 12:37