Saturday, 08 October 2011 09:52

የፕሮፌሰር አንህ መልዕክት

Written by  መስተሐልይ ፀጋዬ
Rate this item
(0 votes)

ሰሞኑን ታትመው ለገበያ ከቀረቡት መጽሐፍት መካከል፤ “ፕሮፌሰር አንህ” የሚለው መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ እኔም ስለዚህ መጽሐፍ የተወሰኑ ሀሳቦችን ለማንሳት እና መጽሐፉን ለመገምገም ወደድሁ፡፡
የመጽሐፉ ይዘት
መጽሐፉ ወጥ ልብ - ወለድ ሲሆን 187 ገጽ ይዟል፡፡ የፊት ገጽ ሽፋኑ ያን ያህል ሳቢ እና ዓይነ ግቡ ባይሆንም፤ ከመጽሐፉ መልዕክት እና ታሪክ ጋር ስለሚያያዝ ትርጉም አለው፡፡ እንደውም ደራሲው ባስቀመጡት የግጥም የቃላት ፍቺ ታግዘን የመጽሐፉን ዋና ገፀ ባሕሪያት ትርጉም ከተረዳን በኋላ፤ የፊት ገጹን ምንነት በይበልጥ እንረዳለን፡፡ እንደዚህ ትርጉም ያላቸውን የመጽሐፍ ሽፋኖች የሚጠቀሙ ደራስያን እንደኔ አመለካከት ደረጃቸው እና እሴታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ገበያን ሳይሆን ማንነትን እና ትርጉም አዘልነትን አስቀድመዋልና፡፡

ሌላው የመጽሐፉ ዋጋ ጥሩ የሚባል እና ሁሉም ሰው ሊገዛው በሚችል ዋጋ መታተሙ (25ብር) ደራሲውን የማያስመሰግን ሥራ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሕትመት ዋጋ እንዲህ በናረበት ሰዓት በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ገበያ የሚቀርቡ ደራሲዎች በሙሉ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ደራሲው በመጽሐፉ “መቅድም” ላይ የሰው ልጆች ለዘመናት በተለያዩ ምክንያቶች ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም ሁኔታው እንደቀጠለ እና ልክ እንደሌሎች መልካም አሳቢ ደራሲዎች ሁሉ እሳቸውም ይህን መጽሐፍ የሰው ልጆች ወደ መልካም ሕይወት እንዲሸጋገሩ ምኞታቸውን የሚገልጹበት እንደሆነ አስፍረዋል፡፡ የሰው ልጅ እግዚአብሔር በጥበብ ያስቀመጠለትን የተደበቀ ሀብት አውጥቶ እንዲጠቀም እና ይህ ሀብት መኖሩን በመጠቆም መልካም ትንቢታዊ ምኞት እንደተመኙ በመጥቀስ ጭምር፡፡
የመጽሐፉ “መቼት” ጣሊያን ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረበት እና ለአምስት ዓመታት በቆየበት ጊዜ እና ከዛ በኋላ ባሉ ዓመታት ገፀ ባሕሪዎቹ በኖሩበት ዘመን ላይ ያጠነጥናል፡፡ እነዚህ የመጽሐፍ ገፀ ባሕሪያት ታሪኮች የሚተረኩበት መንገድ ደግሞ “ተረት ቀመስ” በሆነ መልኩ ነው፡፡ ከመጽሐፉ አጋማሽ በኋላ የሚካተቱት የገፀ ባሕሪያቱ የጉዞ ማስታወሻዎቹ፤ በ”ሀገርሕን እወቅ ፕሮግራም” ጉዞ ማምሻ ላይ የሚተረኩት ለመጽሐፉ ተጨማሪ ጉልበት ሰጥተውቷል፡፡ እነዚህ ከዋናው የመጽሐፉ ታሪክ እና መልዕክት ጐን ለጐን ዋናውን ታሪክ ባላወከ መልኩ መቅረባቸው፤ ለአንባቢው ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥሩለታል፡፡
አቶ ድረስ ከበደ፣ እማሆይ አይምሬ ጉዲት፣ ዶክተር አወቀ እና ፕሮፌሰር አንሕ የመጽሐፉ ዋና ታሪክ የሚያውጠነጥንባቸው አውራ ገፀ ባሕሪያት ናቸው፡፡
አቶ ድረስ ከበደ ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ጊዜ አገሪቱን ከጠላት ለመታደግ በየገዳማቱ በመዞር ታጋዮችን በማደራጀት ትልቁን ሥራ ሲሰራ የነበረ ገፀ ባሕሪ ነው፡፡ እማሆይ አይምሬ ጉዲት ደግሞ፤ ከስማቸው መረዳት እንደሚቻለው፤ አይምሬ፣ ሃይለኛ እና ጨካኝ የነበሩ ሴት ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ለጣሊያን ባንዳ የነበሩ በኋላ ግን አቶ ድረስ ከበደን ካገኙ በኋላ ተለውጠው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን የሚረዱ ይሆናሉ፡፡ ፕሮፌሰር አንህ እና ዶክተር አወቀ ደግሞ የትምህርት እድል (Scholarship) አግኝተው አሜሪካ በመሄድ የተማሩ እና በአእምሮ ንቃታቸው እና ብቃታቸው የተመሰከረላቸው በመሆን እንዲሁም በብዙ ውጣ ውረድ ሀገራቸው በመምጣት “ማሰብ” ከተባለው ኢትዮጵያውያን ካቋቋሙት ድርጅት ጋር በመሆን ወገናቸውን የሚረዱ ገፀ ባሕሪያት ናቸው፡፡
መልዕክቶቹ ሲዳሰሱ
የፕሮፌሰር አንህ ዋና መልዕክት የሆነው እና ደራሲው ለአንባቢያን ሲገልፁ የፈለጉት እውነት (ምኞት)፤ ከጥፋት ውሃ (ከኖሕ ዘመን) በፊት የዩኒቨርስ (ሁለንታ) አዛዥ በጊዜው በነበረው ከአሁኑ እጅግ በሚበልጥ ቴክኖሎጂ የተሰሩ ብዙ ጥበቦችን እና ሀብቶችን ወደ ምድር በመቅበር እና የት ቦታ ምን እንደተቀመጠ፣ ለኖሕ የተሰጠን ሰነድ፣ እንዲሁም ይኸ ሰነድ ኢትዮጵያ ውስጥ አዜብ በምትባል ንግስት እጅ መኖሩን እና ይህን እውነታ የተረዱ የዓለም ኃያላን መንግስታት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር እና ለመሰለል ብሎም በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚውተረተሩት ሰነዱን ፍለጋ መሆኑን መግለጽ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ዓለም በጥፋት ውሃ ከመጥፋቷ በፊት በመጻፉ በዛ ዘመን የነበረውን ቋንቋ የሚችል ሰው አለመኖሩ ደግሞ ሰነዱን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት አድካሚ ያደርገዋል፡፡ ሰነዱ የያዘውን መልዕክት መፍታት የሚችሉ በዐይን የማይታዩ ረቂቅ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ገዳማት እንደሚገኙ፤ እነሱንም በፆም በፀሎት ቀርቦ የሰነዱን ሃሳብ ማስፈታት ደግሞ ገፀ ባሕሪያቱ የሚያጋጥማቸው ሌላኛው ራስ ምታት ነው፡፡ በዛ ላይ ይህን ሰነድ የሚፈልጉ የተለያዩ የውጭ አካላት መኖራቸው ሲጨመርበት ነገሩ ምን ያህል አዳጋች እንደሚሆን መገመት ከባድ አይደለም፡፡
በሰነዱ ከተካተቱ እና ፕሮፌሰር አንህ ከደረሰባቸው እውነታዎች አንዱ እና ለዶክተር አወቀ ከተገለጹት መካከል ገጽ 109 እና 110 ላይ የሚገኘው እንዲህ ሰፍሯል፡፡ “...ዶ/ር አወቀ ከእንቅልፉ በመባነን ሞባይሉን አነሳ፡፡ ፈጠን ብሎ ሀሎ ማን ልበል አለ፡፡ እኔ ነኝ የድስ ልጅ አንህ፡፡ ከየት ነው አለ አወቀ፡፡ ከላይ ከዩፎዎች ከበራሪ ዲስኮች አገር ከዩኒቨርስ ማዕከል፡፡ ምን ልታዘዝ አለ፡፡ የምነግርህ ቁም ነገር አለኝ፡፡ ከዚህ በፊት እንደነገርኩህ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተሰራ ንጹህ ወረቀት እና ቀይ ጥቁር፣ የቀይ ዳማ ቡኒ ቀለም የሆነ እስክሪብቶ ያዝ፡፡ ፈጥነህ ፃፍ፡፡ በኢትዮጵያ ጥንት ከጥፋት ውሃ በፊት አሁን ከተደረሰበት መቶ ጊዜ እጥፍ መጥቆ ስልጣኔው አድጐ ነበር፡፡ ያኔ በዚያን ዘመን በምድር ውስጥ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው የሚያገናኝ የምድር ባቡር ለምቶ አድጐ ነበር፡፡
ዛሬ ያለው የዋሻ በር የባቡር መንገድ የነበረበት ምልክት ነው፡፡ መግቢያውን በር ለምልክት በመተው የሰው ልጆች ከመጥፋታቸው በፊት ንብረት ሁሉ በከርሰ ምድር ሲቀበር የሐዲዱ ብረት በድንጋይ እና በአፈር ተሸፍኖ እንዳይታይ ተደረገ...”
በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ከጥፋት ውሃ በፊት የነበሩ ሀብቶቹን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት በሚደረገው ጥረት እና በውጭ ኃይሎች ሰነዱን ለመውሰድ በሚደረገው ትግል መካከል የመጽሐፉ ገፀ ባሕሪያት ይዋልላሉ፡፡
ፕሮፌሰር አንህ እና ዶክተር አወቀ ከሚለዋወጧቸው አገራዊ መልዕክቶች ባሻገር፤ የሀገርህን እወቅ አባላት የጉዞ ማስታወሻዎች የሀገሪቷን የተለያዩ አካባቢዎች በመዳሰሳቸው እና በጥሩ አቀራረብ በመተረካቸው ፋይዳቸው የጐላ ነው፡፡ ለዋናዎቹ ታሪኮች እና የመጽሐፉ መልዕክቶች እንደ ደጋፊ በመግባት ለመጽሐፉ መነበብ ሁነኛ ሚናን ይጫወታሉ እነዚህ ታሪኮች፡፡
የመጽሐፉ ድክመቶች
ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፉን በጐ ጐኖች እና ይዘቱን የሚገመግሙ ሀሳቦች ናቸው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጉልህ የሚባሉት ስህተቶቹ ሲጠቀሱ ደግሞ፤ አንደኛ ጽሑፎቹ በትልቅ ፎንት (font size) መቀመጣቸው እና መታተማቸው የመጽሐፉን እሴት ይጐዱታል፡፡ የአንባቢን የማንበብ ፍላጐት ከጅምሩ ሊገቱ የሚችሉ የፎንት ምጣኔ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህም በመጽሐፉ ላይ ትኩረት እንዳልተደረገበት እና እንደነገሩ ነው የታተመው የሚያስብል ትችት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ይኼ ደግሞ የመጽሐፉ ይዘት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ሁለተኛ አንዳንድ ገፀ ባሕሪያት ላይ የሚታየው የዘመን መፋለስ እና አለመጣጣም ነው፡፡ እንዲህ ህይነቱ ሁኔታ ሲከሰት ደግሞ የመጽሐፉን ተዓማኒነት የመፈታተን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ታሪኮቹ እጅግ አጫጭር መሆናቸው እና ከምዕራፍ ምዕራፍ በፍጥነት ስለሚሸጋገሩ ትኩረትን የማሳት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የቃላት ግድፈቶች እና የአፃፃፍ ስህተቶች መጽሐፉ የኤዲቲንግ ችግር እንዳለበት የሚጠቁሙ እውነታዎች ናቸው፡፡ መጽሐፉ ለሁለተኛ ጊዜ ሲታተም እነዚህን ችግሮች ሊያስተካክል ይገባዋል፡፡
ማጠቃለያ
መጽሐፉ ባጠቃላይ መልካም የሚባል ነው፡፡ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በቁጭት መጻፉና በተለያዩ ዘመናት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ማንነቶች መዳሰስ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ችግር መፍትሔ ይሆኑ ዘንድ ሕልም እና ምኞትን ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ያለውንም እውነታ እና ገጽታ ደራሲዎቻችን ቢጽፉልን መልካም እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ፕሮፌሰር አንህ የመጽሐፉ ዋና ገፀ ባሕሪ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በከርሰ ምድሯ ተቀብሮ ያለው ሀብት መውጫው ጊዜ እንደደረሰ እና ለሁሉም ሥራ የሚሆኑ ወጣቶች ተመልምለው ወደ ስልጠና መላካቸውን  ለሌላኛው የመጽሐፉ ገፀ ባሕሪ ለአቶ አወቀ በተደጋጋሚ ገልፀውለታል፡፡ ይኸ ምኞት እውን ይሆን ዘንድ ከደራሲው ጋር የመመኘት ዕድልን በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ለመጠቀም ይፈቀድልኝ፡፡

 

Read 1764 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:00