Saturday, 08 October 2011 10:01

የአይዶል የጨረባ ተዝካር

Written by  በፍቃዱ አባይ
Rate this item
(0 votes)

ይህንን ጽሁፍ እጽፍ ዘንድ መነሻ የሆነኝ የ2003 ዓ.ም የኢትዮጵያ አይዶል የሽልማት ስነ-ስርዓት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪiን በቀጥታ በተሰራጨውና በዕለተ መስቀል የተካሔደው ውድድርና ሽልማት ስፍራ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ሲሆን የታዘብኳቸውንና በግሌ ስሜት የሰጡኝን ጉዳዮች እነካካለሁ፡፡ ቅድሚያ የምሰጠውም የኢትዮጵያ አይዶል በየዓመቱ ለሀገራችን የኪነ-ጥበብ ዕድገት እያበረከታቸው ያሉትን ወጣት ከያንያንንና በእነርሱም እያስገኛቸው ያሉ ትሩፋቶችን በማወደስ ነው፡፡ በዘመናዊና የባህል ዘፋኞች (የፈረንጅ አፎቹን ሳንዘነጋ)፤ የባህልና ዘመናዊ ውዝዋዜና ዳንስ ረገድም እንዲሁ ባለፉት ዓመታት ጥቂት የማይባሉ ባለሙያዎችን አሳይቶናል፡፡

ለወደፊቱም ይህ መልካም ፍሬው ሰፍቶ እንደማይም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የ2003 ዓ.ም የመጨረሻ የሽልማት ዝግጅትም ይህንን እምነቴን ይበልጥ አበረታ ዘንድ ጠንካራ ምርኩዝ ሆኖኛል፡፡ ታድያ በእነዚህ አክብሮቶቼና አድናቆቶቼ መሐከል ነው ሌሎቹን የዕለቱን ድክመቶች የማነሳው፡፡
ስርዓት አልባው መስተንግዶ
በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍ ያሉና መሰል ጥበባዊ ዝግጅቶች ላይ በስራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ እታደማለሁ፡፡ በአብዛኛዎቹ ዝግጅቶች ላይም የሰዓት አለማክበር፤ የፕሮግራም መንዛዛት፤ የዝግጅቱን ዓላማና ግብ መሳትን የመሳሰሉ እንከኖችን እታዘባለሁ፡፡ እነዚህ የበርካታ መሰል ዝግጅቶች የጋራ ባህሪት በመሆናቸው የአይዶል ሾው የመዝጊያ ዝግጅት ላይ የተለየ ዕይታ የለኝም፡፡ ከላይ የገለጽኩት ዝግጅት የታዘብኩት ችግር የሚጀምረው ለእንግዶቻቸው ተገቢውን ክብር በመንፈግ መሆኑ ግን ቀዳሚው ችግር ነበር፡፡ የጥሪው ወረቀት በሚገልጸው ሰዓትና ስፍራ የተገኙ በተለያዩ ሙያዎች ላይ አንቱታን ያገኙ ግለሰቦች ጭምር በመግቢያ በሩ ላይ በተፈጠረ የመስተንግዶ ችግር ከፍ ያለ መጉላላት ሲደርስባቸው ተመልክቻለሁ፡፡ ስርዓት ባለው ሁኔታ እንግዶችን ማስተናገድ ያለመቻሉ ችግርም በስተመጨረሻ በጉልበት በር ጥሶ መግባትንም አስከትሏል፡፡ በዚህም ጉልበት ያለው ሲጠቀም በተለይም ከላይ የገለጽኳቸው ግለሰቦች የዳር ተመልካች መሆንን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል፡፡ የችግሩ ማጠንከሪያም ወደ አዳራሹ ከተገባ በኋላ ለእንግዶቹ ወንበር ለማስለቀቅ በአዘጋጆቹና በተቀሩት እንግዶች መካከል ወከባ መፈጠሩ የመስተንግዶውን ችግር አጉልቶታል፡፡ ደጋሹና እንግዳው ያልተለየበት ይህ ዝግጅት በስተኋላ በመድረክ ላይ ለተፈጠረውም የጨበሬ ተዝካር ትርምስ መነሻ ይመስለኛል፡፡የመድረክ አመራር መዝረዝረክ ታያቷል
የድግሱ ባለቤት ማነው?
ከላይ በመግቢያውና በመድረኩ ላይ ያነሳኋቸው ችግሮች በመላው አዳራሹ ውስጥም ታይቷል ሲባል በወንበር አደላደል፤ ለእንግዶች ተገቢውን ክብር መስጠትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማሳየት ይገለጻል፡፡ ከመድረክ ጀርባ በክብር እንግዶች ፊት ለፊት፤ በዳኞች አካባቢ፤ በመድረክ መሪዎች ዙሪያ... ወዘተ የነበረው የአተናጋጅ ብዛት፤ የሐሳብ ሰጪና ትዕዛዝ አስተላላፊ ግርግር እንዲሁ የዝግጅቱ ሌላኛው ድክመት ስለነበር በርካቶች ደጋሹን እንዳያውቁ አድርጓቸዋል፡፡ የዚህ ዝግጅት ባለቤትስ ማነው? ስንል ጥያቄ እናነሳ የነበረው ለዚህ ይመስለኛል፡፡ በሽልማት አሰጣጡ ስነ-ስርዓት ወቅት የታየው መዝረክረክም የዕውነተኛው ደጋሽ ያለመታወቅ ውጤት ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ሸላሚ ሲጠፋ ለተሸላሚው ሽልማቱን ሸልማ የተመለሰችው ሽልማት አቅራቢንም ማንሳት ይቻላል፡፡ እናቶቻችን አንድን ዝግጅት የሚያሳምረውም የሚያበላሸውም አሳላፊው ነው ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከድግሱ ባልተናነሰ አስተናጋጆቹን ለመምረጥ ብዙ ይለፋሉ፡፡ ውጤታቸውም በውሳኔያቸው ይለካል፡፡ ድግሱ ጥሩ ነበር አስተናጋጁ ረበሸው እንጂ! እንዳይባሉ ታላቅ ጥንቃቄም ያደርጋሉ፡፡ በእውነት ግን ለዕለቱ ድግስ ባለቤቱ ማነው? ለወደፊት መመለስም መታሰብም የሚያስፈልገው ጥያቄ ይመስለኛል፡፡
ዳኝነት
በኢትዮጵያ አይዶል ያለፉ አመታት ጭምር ሲነሱ ከነበሩ ጥያቄዎች መሐከል ዳኝነቱ አንደኛው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስለዳኝነት ስናነሳም የስሜት ዳኝነትና የዕውቀት ዳኝነትን መለየት ግድ ይመስለኛል፡፡ በአሜሪካው አይዶል ሾው ጨምሮ በተለያዩ መሰል ሐገራት በሚደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮች ዘንድም በህዝብና በባለሙያዎች አማካኝነት መሰል ያለመስማማቶች ይከሰታሉ፡፡ በእኛው ሐገር ውድድርም ይህ ቢያጋጥም ብዙም አይደንቀኝም፡፡ ያም ሆኖ ታድያ በግል ዕይታዬ ይህ ውድድር በድምጽ ዳኝነቱ ዙሪያ አሁን ድረስ ያለውን ዕድለኝነት ያህል በባህላዊ ውዝዋዜና ዘመናዊ ዳንስ ላይ በሚሰየሙ ዳኞች ዘንድ እድለኛ ሆኗል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የድምጹን ዳኞች የተሻሉ ስላቸው ሙያተኛ ሆኜ ያለመሆኑን ያህል እንቅስቃሴዎቹ ላይም ተመሳሳይ ነው፡፡ በባህላዊ ውዝዋዜ የሚመደቡት ዳኞችን በየሳምንቱ በዝግጅቶቹ ላይ ስናገኛቸው ለተወዳዳሪዎች ከሚሰጧቸው አስተያየቶች መደጋገም፤ አስተያየቶች በተግባር ያልተደገፉ መሆናቸው፤ የዳኞቹ ዕይታ ከተራው ተመልካች ያለመለየቱና ተግባር ተኮር ያለመሆኑ ሁሌም የሚያሳስበኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እንደውም አንዳንዴ ተወዳዳሪዎቹ ከዳኞቹ ሲበልጡ ሁሉ ይሰማኛል፡፡ በአልባሳት፤ በውዝዋዜ ዘይቤ፤ በፈጠራ ችሎታና በመሳሰሉት መለኪያዎች ተወዳዳሪዎቹ ዳኞቹን ሲቀድሙአቸው በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ፡፡ በመዝጊያው ዕለትም ቆሜ እስካጨበጭብ ድረስ የሚያስደምሙ የፈጠራ ስራዎችን ማየቴ ሐሳቤ ይበረታ ዘንድ አግዞኛል፡፡
ይህ ትዝብት ሁሉንም ባለሙያዎች ይመለከታል የሚል እምነት ባይኖረኝም የሚዘፍኑ፤ ማንጎራጎር ሲያሻ የሚያንጎራጉሩ፤ ዘፈንን ለማድመጥ ስል (sharp) ጆሮ ያላቸው የድምጽ ዳኞችን አይዶላችን የመታደሉን ያህል የንስር አይን ያላቸውን፤ በእኩል ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉትን ዳኞች ያድለው ዘንድ ብመኝ ክፋት የለውም፡፡
ቅምሻ
በዘመናዊም ሆነ በባህላዊ ውዝዋዜ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያየኋቸው ወጣት ተወዳዳሪዎችን እጅ ነስቼአለሁ፡፡ በየቴአትር ቤቱ ቦታ ይዘው፤ ፔሮል ላይ ለመፈረም ለሚሽቀዳደሙ ታላላቆቻችሁም መልዕክት አስተላልፋችኋል፡፡ መድረኩ አዳዲስ ፊቶችንና የፈጠራ ስራዎችን እየናፈቀ ስለመሆኑ ህዝብም ባለሙያም መስክሮላችኋል፡፡ እናንተ የምትፈልጉት መድረኩን ማግኛ አንድ እድል ብቻ ነው፡፡
ለክሊፕ ሰሪዎቻችን
በየቴሌቪiኑ፤ በየሲኒማ ቤቱ፤ ወደንም ሆነ ተገደን የምናያቸው የዘፈን ማጣፈጫ ክሊፖችም አሁን መፈተሻቸው ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ከዘፈኑ ግጥም ሐሳብና መልዕክት ጋር የማይሔዱ መወራጨቶች ስፍራ እንደሌላቸውና በፈጠራ ስራ የተጉና ታሪክ ያለው ትርዒት የሚያቀርቡ አዳዲስ ፊቶች በክሊፖቻችን ላይም አስታዋሽ እንደሚያስፈልጋቸው ማሳያዎቹ የአይዶል ፍሬዎች ይመስሉኛል፡፡ (ፕሮዲዩሰሮቹስ ምን ተሰማችሁ?) ቀሪውን ለሌሎች ትቼ እኔ በዚህ ልሰናበት፡፡ እስኪ እንወያይ!

 

Read 2017 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:04