Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Tuesday, 01 November 2011 14:08

የ11 ዓመት እስር በመጽሐፍ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ምክንያት ለ11 ዓመታት በእስር ከቆዩት ኢትዮጵያዊያን አንዷ የነበረችው ከበደች ተክለአብ፤ በ1983 ዓ.ም አሳትማ ለአንባቢያን ያቀረበችው መጽሐፍ “የት ነው” የሚል ርዕስ የተሰጠው የግጥም መድበል ሲሆን በሥነ ግጥምም ቢሆን ርዕሰ ጉዳዩን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ላይ በማድረግ በአገራችን ፈር ቀዳጅ መፅሀፍ እንደሆነ ይነገራል፡፡


ከሶማሊያ ወረራና ከኢትዮጵያ የድል ታሪክ ጋር በተያያዘ ሁለተኛውን መጽሐፍ ያሳተሙት ሻለቃ ሽፈራው ተክሉ ሲሆኑ “የሶማሊያ ወረራና ሽንፈቱ” በሚል ርዕስ በ1999 ዓ.ም ያወጡት መጽሐፍ በጦርነቱ ወቅት ወታደራዊ እንቅስቃሴው ምን ይመስል እንደነበር ይተርካል፡፡ ፀሃፊው አስቀድመው ባሰፈሩት ማስታወሻም “እኔ ከነበርኩበት ግንባር አንፃር ያየሁትና ያለፍኩበትን ብቻ ነው” የሚል ማሳሰቢያ ከትህትና ጋር አስቀምጠዋል፡፡
የ1969/70 ዓ.ም የኢትዮ - ሶማሊያ ጦርነትን በተመለከተ ሦስተኛውን መጽሐፍ አዘጋጅተው ያሳተሙት የውጭ አገር ዜጋ ናቸው፡፡ በጦርነቱ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጐን ተሰልፈው የተዋጉት ኩባዊው ሌተናል ኮሎኔል አርናልዶ ካርሎስ፤ በሶማሊያ እስር ቤት ስላሳለፉት ሕይወት የሚተርክ መጽሐፍ ማሳተማቸው ይታወቃል፡፡
በቅርቡ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነትን መነሻ አድርጐ ለንባብ የበቃው መፅሃፍ ደግሞ “ሐበሻ በሶማሊያ እስር ቤቶች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የታተመ አራተኛው መፅሃፍ ሆኗል፡፡ በ268 ገፆች የተቀነባበውን ይሄን መጽሐፍ ያዘጋጁት በሶማሊያ እስር ቤቶች ለ11 ዓመታት በእስር ያሳለፉት አቶ ጥላሁን አትሬሶ ናቸው፡፡
በ1952 ዓ.ም ነፃ መንግሥት ሆና የተመሠረተችው ሶማሊያ፤ ሉአላዊነቷን ያረጋገጠችበትን ሃያኛ ዓመት ሳታከብር ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያን የመውረር ሙከራ አድርጋ ጥረቷ እንደከሸፈ ይታወሳል፡፡ የ1969 ዓ.ም ወረራ በብዙ የተዘጋጀችበት ስለነበርና በኢትዮጵያ ከነበረው የሥርዓት ለውጥ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት ስላመቻት ሕልሟ የሚሳካ መስሎ ታይቶ ነበር፡፡ ሽንፈት መከናነብ ግን አልቀረላትም፡፡
የሶማሊያም ሽንፈት፣ የኢትዮጵያም ድል እንዲደጋገም ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ብሔራዊ ስሜት (nationalism) መገንባት ከመቻልና አለመቻል ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያብራራው “ሐበሻ በሶማሊያ እስር ቤቶች” መጽሐፍ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት ሥርዓት መከተል የጀመረችው ከዘመነ መሳፍንት ማክተም ወዲህ ቢሆንም እጅግ ጥንታዊ ሊባል የሚችል ብሔራዊ ስሜት በሕዝቡ ውስጥ መገንባቱ፤ ኢትዮጵያዊያን ለወረራቸው የማይመቹ ሕዝቦች ሊያደርጋቸው እንደቻለ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
በተቃራኒ መጽሐፉ ምንጭ ጠቅሶ “ሶማሊያ የሚለው ስም ራሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ተመዝግቦ የታየው በ15ኛው ምዕተ ዓመት በአንድ ኢትዮጵያዊ የግጥም ሥራ ውስጥ ነው፣ በኢትዮጵያ ወግ መሰረትም ዛሬ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ተብላ የምትታወቀው አገር የጥንታዊት ኢትዮጵያ አካልና ቤሳዋም (ገንዘቧም) በሶማሊያ ይሠራበት እንደነበር በሚገባ ይታወቃል” ይላል፡፡
በነፃና ሉአላዊ አገርነት የቆየ ታሪክ ያልነበራት ሶማሊያ “የአውሮፓ ኮሎኒያሊዝም ቀጥተኛ ውጤት ናት” የሚለው ፀሃፊው አገሪቱ በሕዝቧ ውስጥ ጊዜና ድካም የሚጠይቅ ብሔራዊ ስሜት ሳትፈጥር በፕሮፖጋንዳ ቅስቀሳ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለመፈፀም በመነሳቷ ምክንያት ሁለቱንም አገርና ሕዝብ ለብዙ ኪሳራና ጉዳት የዳረገ ስህተት እንድትሰራ ሰበብ መሆኑን በሰፊው ያመለክታል፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ወረራ ለመፈፀም ያነሳሳት ሌላው ምክንያት በቅኝ ግዛት ዘመን ጣሊያንና እንግሊዝ የሸረቡት ተንኮል ነው የሚለው መጽሐፉ፤ ታላቋን ሶማሊያ የመፍጠር ሐሳብ ያመጣችው እንግሊዝም ሆነች ለተመሳሳይ ዓላማ ነገሮችን ያወሳሰበችው ጣሊያን፤ ሁለቱም አገራት በታሪክ ተወቃሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ይላል፡፡
መፅሃፉ በመጀመሪያው ክፍል ስለ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በንጽጽር የሚያቀርብ ሲሆን፤ በሁለተኛው ክፍል ኢትዮጵያውያን በሶማሊያ እስር ቤቶች ስላሳለፉት እስርና እንግልት ሰፊ መረጃዎች በማቅረብ ያስነብባል፡፡ የንብረትና ሌሎች ጉዳቶችን ሳይጨምር ከሲቪልና ከወታደሩ ክፍል በድምሩ 150ሺህ ያህል ኢትዮጵያዊያንን ለሞት በዳረገው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት፤ 6ሺህ የሚሆኑት በምርኮ ወደ ሶማሊያ ተወስደው የነበረ ሲሆን ከ11 ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው መመለስ የቻሉት 3508 ብቻ የሆኑበት ዋናው ምክንያት በስቃይና እንግልት ለሞት በመዳረጋቸው ነው፡፡
በሶማሊያ እስር ቤቶች ስለነበረው እስር፣ እንግልትና ስቃይ ማስረጃ እያቀረቡ የሚያስነብቡት አቶ ጥላሁን አትሬሶ፤ አንዳንዶች በመፅሃፉ የተካተቱት ታሪኮች ተጋነዋል በሚል ጥርጣሬ ሊያድርባቸው እንደሚችል እገምታለሁ ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም የባሰ ዘግናኝ ሁኔታዎች እንደነበሩ ያወሳሉ፡፡ “እጅግ ዘግናኝና ብገልፃቸው በሕዝባችን ላይ የሚፈጥረውን ስነ ልቦናዊ ስብራትና ለቁጥጥር የሚያስቸግር የበቀል ስሜት በመፍራት ሕዝብ ለሕዝብ ሊኖረው ስለሚገባው መግባባትና መልካም ጉርብትና ስል፣ በጥንቃቄ የዘለልኳቸው ነገሮች አሉ”
መጽሐፉ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የታሳሪዎችን ታሪክ ማዕከል አድርጎ ይዘጋጅ እንጂ እግረ መንገዱን የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ የቅኝ አገዛዝ ጦስና የቀዝቃዛው ጦርነት ትግል አፍሪካን በምን መልኩ እንደጎዳት፤ ዛሬም በባሕር ላይ ውንብድናና ዘረፋ የሚታወቁት ሶማሊያዊያን፤ በ1970ዎቹም በዚሁ ተግባር መንግሥታቸውን አስቸግረው ለእስር ይዳረጉ እንደነበር፤ ዛሬም የመሰደድ ፍላጎታችን ያልተገታው ኢትዮጵያዊያን ከ30 ዓመት በፊትም በህዝቡ ላይ ከስደት ጋር በተያያዘ ብዙ እንግልት መድረሱን . . . ያመለክታል፡፡
በዘመኑ በኢህአፓ ውስጥ በተፈጠረ መከፋፈል ምክንያት ሕይወቴ አደጋ ላይ በመውደቁ፣ ከአዲስ አበባ ተነስቼ በጅቡቲ በኩል ፈረንሳይ ለመግባት ከጓደኞቼ ጋር የጀመርኩት ጉዞ ለሶማሊያ እስር ቤት ዳረገኝ የሚሉት ፀሃፊው፤ “የሶማሊያ ምርኮኞች በእኛ አገር በምን ሁኔታ ተይዘው እንደነበር” የሚያስነብብ መጽሐፍ ቢኖር ጥሩ ነበር ይላሉ፡፡ ፀሃፊው በሶማሊያ እስር ቤቶች ኢትዮጵያውያን ያሳለፉትን የ11 ዓመታት እስር ብቻ ሳይሆን እስረኛው ነፃ ሆኖ አገሩ ከገባ በኋላም የተከተለውን እንግልት በመጽሐፋቸው አቅርበዋል፡፡ በሶማሊያዊያን ማሳ ላይ እንዲሰራ ታዞ ለዘር ከተሰጠው በቆሎ 3 ፍሬ በአፉ ውስጥ በመገኘቱ ምክንያት በ3 ጥይት ተደብድቦ የተገደለው፤ የረሀብ አድማ በማድረጉ 30 ጥይት ተኩሰውበት አልሞት ያላቸውን በ31ኛው ጥይት አናቱን በርቅሰው የገደሉት ኢትዮጵያዊ እስረኛና መሰል የእንግልት፣ የስቃይና የሞት ታሪክ የሚያስነብበው መጽሐፉ፤ ታሪክን ከማስታወስ ባሻገር ለአህጉሪቱ መንግሥታት፣ ባለስልጣናትና ሕዝቦች ብዙ ትምህርት ይሰጣል፡በመጽሐፉ ከሚታዩ ጉልህ ስህተቶች አንዱ በሽፋን ገጹ ላይ “የኛ ሰው በሶማሊያ እስር ቤት” ሲል በውስጥ ገጽ “ሐበሻ በሶማሊያ እስር ቤቶች” የሚል ሁለት ተቀራራቢ ግን የተለያየ ርዕስ መሰጠቱ ነው፡፡ ፀሃፊው መፅሃፋቸውን ለማዘጋጀት ራሳቸው ያሳለፉትንና ያዩትን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎችንና ምንጮችን እንደተጠቀሙ ጠቅሰዋል፡፡ በሶማሊያ እስር ቤት ለ11 ዓመታት ታስረው ነፃ ከወጡ በኋላ ሕግ አጥንተው ለዲግሪ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በእስር ቆይታው ላይ የሰሩት የሻለቃ ገ/ሊባኖስ ወ/አረጋይ የጥናት ፅሁፍ፣ የከበደች ተክለአብ መጽሐፍና፣ በቃለ መጠይቅ የተሰበሰቡ መረጃዎች ይገኙበታል፡፡ የመፅሃፍ ዝግጅቱን በ1995 ዓ.ም እንደጀመሩ የሚናገሩት አቶ ጥላሁን አትሬሶ፤ ለንባብ እንዲበቃ በተለያየ መልኩ ያተጓቸውንና የተባበሯቸውን ሰዎች አመስግነዋል፡፡

 

Read 2234 times Last modified on Tuesday, 01 November 2011 14:14