Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Tuesday, 01 November 2011 14:14

ጋዜጣን በፀፀት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የጋዜጣ አንባቢና የውሃ-ሙላት አንድ ነው፡፡ ጋዜጠኛና ለውሃ-ሙላት የዘፈነው አዝማሪም እንደዚያው ተመሳሳይ፡፡ ኧረ እንደውም ተተካኪ ናቸው፡፡ ለጋዜጣ መፃፍ ለውሃ ሙላት እንደመዝፈን ነው፡፡ የሰማው ሲሄድ ያልሰማው ይመጣል፡፡ ቆሞ የሚያዳምጥ ጋዜጣ አንባቢና የውሃ ሙላት የለም፡፡ እየሄደ አዳምጦህ፣ እያዳመጠህ ይሄዳል…

…እያዳመጠ መጥቶ እያዳመጠ የሚሄድን ተደራሲ ለማርካት፤ እያዘመረ መጥቶ እየዘመረ የሚሄድ ተንቀሳቃሽ ዘፋኝ ግድ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ከ”ውሃ-ሙላት” ጋር የመንጦልጦል ኑሮ ገፍተዋል፡፡ ህይወታቸው “የወንዝ” አፍ የተከተለ፣ “የሙላት” ከንፈር ደርዝ የነበረ ብዙዎች አሉ፡፡ በር ከፋቻቸው ከንቲባ ደስታ ምትኬ ናቸው አሉ፡፡ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስ ደግሞ ይከተላሉ፡፡ ነጋሽ ገብረማሪያም፡ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ደምሴ ፅጌ… እየሮጡ የሚያዘምሩ፣ እያዘመሩ የሚሮጡ ነበሩ፡፡
እነዚህ ሰዎች አንድ ዘፈን ያስታውሱኛል፡፡ ግጥሙ በገደምዳሜ እንዲህ ይነበባል:-
የመኖሪያ ቤቱን አባይ ላይ የሰራ፣
ልቡን አስረክቦ በወዳጅ የኮራ፣
ሁለቱ አንድ ናቸው…
አባይም ሲሞላ ይወስደዋል ቤቱን፣
ወዳጅም ሲከዳ ያዞረዋል ፊቱን፡፡
ንፅፅሩ የጋዜጠኛ ህይወትና የጋዜጣ አንባቢ ነው፡፡ የጋዜጣ ሙላት ላይ እንደ ጀልባ ሲንሳፈፉ ኖረው ሲበቃ ወደ ዳር የተተፉ ብዙ ናቸው፡፡ እንደ ጀንበር ጠዋት ወጥቶ ማታ የሚጠልቅ የ12 ሰዓት እድሜ ላለው ጋዜጣ፤ ቅርስ አልባ ልፋታቸው የሚቆጭ ብዙዎች ናቸው፡፡ ትናንት ተወልዳ፣ ትናንት የሞተችውን ጀንበር ማን ይከልሳል? የጋዜጣ ፀሐፊውንም እንደዚያ፡፡ ደረጀ ደስታ፣ የሺጥላ ኰከብ፣ አብርሃም ረታ፣ ሰለሞን በርሔ፣ ተድባበ ጥላሁን፣ ቶማስ አርጋው፣ ክፍሌ ሙላት፣ ዘገየ ኃይሌ… እነማን ናቸው? የጋዜጣ ላይ የትናንት ጀንበሮች አይደሉምን? እንደ አቃቢት ህይወት ስማቸው ከመቃብር ፅሁፍ ጋር ስለምን ተዳበለ? መኩሪያ መካሻ፣ ዐረፈአይኔ ሐጐስ፣ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ አደባባይ አባይ፣ አብደላ እዝራ… “ለዕለት የጋዜጣ ጉርስ”፣ ከእጅ ወደ አፍ ለሆነ የጋዜጣ ጥበብ፣ እድሜያቸውን አልቀለቡምን? የማይጠረቃን ለማስባት አልተፍገመገሙምን? ጋዜጣ ይሉት ጉድ!
ጋዜጣ ይሉት ጉድ የተጀመረው ሮማ ውስጥ በዘመነ ጁሊየስ ቄሳር ነው አሉ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ59 ዓመተ ዓለም፡፡ ጋዜጣ የሚለውም ቃል የተገኘው “ጋዜታ” ከሚለው ጣሊያንኛ ነው፡፡ ያኔ ሮማ አደባባይ፣ በተከታታይ ለህዝብ በሰሌዳ ላይ ይሰፍር የነበረው “አክታ ዲዮረና” የተባው ጋዜጣ ብኩርናውን ወስዷል፡፡ በህትመት በኩል ግን ቅድሚያውን ቻይና ትወስዳለች፡በ700ኛው ክፍለ ዘመን በህትመት የተሰራጨ ጋዜጣ ነበራትና፡፡ ዘመናዊ የማተሚያ ማሽን ከተፈበረከ በኋላ አውሮፓ ለዘመናዊው ጋዜጠኝነትና ጋዜጣ ምንጭ ሆነች፡፡ 1609 ዓ.ም የተጀመረው የጀርመኑ “አቢሳ ሪሌሽን ኦደር ዙ ይዙንግ” ጋዜጣ ለዚህ ዋቢ ነው፡፡
ጋዜጣ ይሉትን ጉድ ከአገራችን አንፃር እንይ…
…ከንጉሥ አጤ ምኒሊክን፣ ከከተማ ምፅዋን ማንሳት አለብን ስለጋዜጣ ውልደት ለመነጋገር፡፡ ከዘመን ደግሞ 1890 ዓ.ም፡፡ ሙሴ እንድርያስ ካቫዲያስ “ኮከብ” ይሰኝ የነበረ ጋዜጣ ያዘጋጁ ነበር ይባላል፡፡ ይባላልን ትተን ወደ እርግጠኛው ስንመጣ አዲስ-አበባ ከተማ ላይ እንገኛለን፡፡ ወቅቱ 1897 ዓ.ም፡፡ ጋዜጣው ደግሞ “አእምሮ” ይሰኛል፡፡ በእጅ ፅሁፍ ተዘጋጅቶ በሃያ ቅጂ ለታላላቅ የቤተመንግሥት ሹማምንት ይታደል ነበር፡፡ ይሄንን የትጋት ጋዜጠኝነት የሚያከናውኑት ቅድሚያ ሙሴ ካቫዲያስ ሲሆኑ ከሳቸው በመቀጠል ከንቲባ ደስታ ምትኬ የኢትዮጵያዊነቱን ቅድሚያ ይወስዳሉ፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ-ቅዳሜ መንማኒቷ “አእምሮ” ጋዜጣ ትወጣለች፡፡ ኋላ ላይ አጤው የጋዜጣዋ መኮስመን አንጀታቸውን ስለበላው ማባዣ ማሽን ከውጭ አስመጥተው በአስር እጥፍ አሳደጓት፡፡ 200 ቅጂ ጉድ ተባለ፡፡ መቼ ሊያልቅ ነው? አንባቢ የለማ፡፡
የያኔው ጋዜጣ አንባቢ የውሃ ሙላት አልነበረም፤ ጋዜጠኛም ለውሃ-ሙላት አያዘምርም፡፡ ጭል-ጭል የሚለውን አንባቢ ለማጠራቀም “ዕቃውን” ደቅኖ ዘወር ነው፡፡ ለምሳሌ ከንቲባ ደስታ ከጋዜጠኝነቱ ሌላ የፖስታ ሚኒስቴር ሰራተኛ ነበሩ፡፡ በስልከኝነትም አገልግለዋል፡፡ “አእምሮ” ጋዜጣ እንደ ዶሮ ማርባት ተጨማሪ የጓሮ ሥራቸው ናት፡፡ ይሄን ሁሉ ሰርተው ደግሞ የወር ደሞዛቸው ሰባት ብር፡፡ ከዚህ በተረፈ “ደስታ ጋዜጠኛው” የሚባል የሙገሳ ስም ይመረቅላቸዋል፡፡
“ልጅ ደረሰ፣ ቤት ፈረሰ” አይደል? ግዴለም እንቀይረውና “ጋዜጣ ደረሰ - የጋዜጠኛ ህይወት ፈረሰ” እንበል፡፡ የአገር ውስጥ ጋዜጦች በቅርፅና በይዘት እየጐለበቱ የመጡት ከጠላት ወረራ በኋላ ነው፡፡ ከቋንቋም ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛን አዳረሱ፡፡ እንግዲህ “አዲስ-ዘመን” በየሳምንቱ ብቅ ማለት የጀመረው በ1943 መሆኑ ነው፡፡ “የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን” መመስረቱን አሳብቦ “አዲስ ዘመን” እለታዊ ሆነ፡፡ ልብ በሉ፣ የሚቀለበውም የጋዜጠኛ ጉልበት እለታዊ ሆነ ማለት ነው፡፡
ጋዜጣ የባሪያ ፈንጋይ ባህርይ አለው፡፡ ብዙዎች ቢማስኑለትም በግዢና ሽያጭ አካክሶ ድካምን ስለውለታ አይቆጥርም፡፡ በህትመት በተመጠነ እርምጃው ለሚደፈጠጡት ቁብ የለውም፡፡ በእለት ጉዳይ ተጠምዶ ለትናንት እና ለትናንቶች ማሰቢያ አልመደበም፡፡ ጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን አንባቢውም የተከላተፈ፣ ሲሮጥ የሚታጠቅ ነው፡፡ ትናንት፣ ያለፈው ሳምንት፣ ያለፈው ወር… ምን ተፃፈ? ምን ተነበበ? ምን ታተመ? የውለታ መዝገብ አልተዘጋጀም፡፡ ጋዜጣና አንባቢዎቹ ቀርቶ ጋዜጠኛውም ስለውለታው አይብከነከንም፡፡ እንደ ህልም ተጓዥ የደረሰበት እንጂ የመጣበት አይታወሰውም፡፡ በተጨማሪ ሥራ ስሙን ያልደጐመ ጋዜጠኛ ሲሞት መቃብሩ እንደሙሴ ያለመታወቅ እጣ ይወጣለታል፡፡ ተፈራ አስማረና ቶማስ አርጋውን ልብ ይሏል፡፡
እንደ ግማሽ ጨረቃ የስማቸው አካፋይ የጋዜጠኝነት አዘቀት ውስጥ ወድቆ በደራሲነታቸው የሚያበሩ ግለሰቦችም አሉ፡፡ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስ በአሥራ አራት መፅሐፍቶቻቸው ስማቸው ተደጉሞ ተቀብሮ ከመቅረት ተርፈዋል፡፡ ነጋሽ ገብረማሪያምም እድሜያቸውን ከገበሩለት ጋዜጠኝነት ይልቅ በብዕር ሥም በፃፏት መፅሐፋቸው ይታወሳሉ፡፡ “እናኑ አጐናፍር” ትሰኛለች መፅሐፏ፡፡ ለምን በብዕር ሥም እንደፃፏት ሰለሞን ተሰማ ሲጠይቃቸው እንዲህ ብለው ነበር:-
“ምናልባት በመፅሐፉ የዘባረቅሁት ነገር ቢኖር በሙያው ላይ ካሉት የበለጠ እኔን አዋቂ አስመስሎ እንዳያስገምተኝ ፈርቼ ነው” ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ስም ለበስ ነው፡፡ “በሙያው” የሚሉት ሴተኛ አዳሪነትን ነው፡፡ የመፅሐፏ ርዕሰ ጉዳይ እሱ በመሆኑ፡፡ ያም ሆነ ይህ ነጋሽ በኮሩበት ጋዜጠኝነት ሳይሆን ሐፍረት በተሰማቸው መፅሐፍ የሚታወሱ ሆነዋል፡፡
ጳውሎስ ኞኞ፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ስብሐት ገብረእግዜአብሔር፣ ማሞ ውድነህ፣ ተስፋዬ ገብረአብ፣ ደምሴ ፅጌ፣ የሺጥላ ኰከብ፣ አብርሃም ረታ አለሙ፣ ዘነበ ወላ… የሚታወሱት ግማሽ ልፋታቸው በጋዜጠኝነት ተቀምቶ በተቀረው ገፅታቸው ነው፡፡
አናፂ በወንበሩ፣ አንጥረኛው በጌጡ፣ ፋቂው በኮርቻው፣ ነጋዴው በመደብሩ… ይታወሱ የለምን? ጋዜጠኛን የየትኛው አማልክት ፍርጃ ተጠናወተው? ፈጭቶ ቋቱ እንዳይሞላ፣ ተንከባላይ የአቀበት ላይ ቋጥኝ እንዲገፋ የመቅኖቢስነት ብይን ማን ሰጠው?
ጋዜጠኝነት ላይ የዘየደው እንግሊዛዊው ደራሲ ቻርልስ ዲከንስ ነው፡፡ ሙያው የህልም እሩጫ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ የደረሱበት እንጂ የመጡበት የማይታወስ፡፡ ስለዚህ ይሄን ህልም ወደ ድርሰት ፕሮጀክትነት ለወጠው፡፡ ጋዜጠኝነትን ከደራሲነት ጋር ደባለቀው፡፡ “ቦዝ” (Boz) በሚል ብዕር ሥም “Morning Chronicle” ለተሰኘ ጋዜጣ ፅሁፎቹን ይልካል፡፡ ፅሁፎቹ ትረካዎች ናቸው፡፡ ጋዜጣው አገኘሁ መስሎት ያሻምዳል፡፡ በአመቱ ፅሁፉ ተጠራቅሞ ወደ መፅሐፍነት ይቀየራል፡በዚህ ዘዴ ጋዜጣን ወደማጠራቀሚያ እቃነት ቀይሮ ብዙ ልቦለዶቹን እውን አደረገ፡፡ “Hard Time”፣ “Little Dorrit”፣ “A tale of two cities” “Great expectation”፣ “David Copperfield”፣ “Pickwick papers”… ምናለፋችሁ ሁሉም የዲከንስ ሥራዎች እውን የሆኑት በጋዜጦች ማጠራቀሚያነት ነው፡እንደውም ዲከንስን “ጋዜጣ ካላጣደፈው የማይፅፍ ደራሲ ነው” ይሉታል፡፡ እንደ ዲከንስ አይሁን እንጂ ፊዮዶር ደስተየቭስኪና አንቶን ፓቭሎቪች ቼሆቭም ጋዜጣ ለራሱ ሲጋልብ ወደ መድረሻቸው ተሳፍረውበታል፡፡
እኛም አገር ጅማሬው ከጋዜጣ ወደ ሬዲዮ አፈገፈገ እንጂ “ዲከንሳዊ” ዝንባሌ ነበር፡፡ እጓለ ገብረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”ን በመፅሐፍ ያቀረቡት ከሬዲዮ አፍ ነጥቀው ነበር፡፡ እንዲሁ አምደፅዮን ተሰማም “ባህልና ሥልጣኔ” የሚል መፅሐፋቸውን ያሳተሙት ከ1956 ዓ.ም አንስቶ ለሬዲዮ የሰጡትን ነስተው ነው፡፡ “ሰጥቶ የነሳ…” አንላቸውም፡፡
ወደዚህ ዘመን ስንመጣ “ዲከንሳዊው” ባህሪ ተስፋፍቶ እናገኘዋለን፡፡ የስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሁለቱ “እግረመንገድ”ዎች፣ የኤፍሬም እንዳለ “እንጨዋወት”ዎች የነቢይ መኰንን “የእኛ ሰው በአሜሪካ” የበእውቀቱ ስዩም “በራሪ ቅጠሎች” እና “መግባትና መውጣት”፣ የእንዳለጌታ “ከጥቁር ሰማይ ስር” የኃይለጊዮርጊስ ማሞ (ጲላጦስ) “ጥበብ”ዎች፣ የሌሊሳ ግርማ “የንፋስ ህልም”፣ የኢዮብ ካሣ “ፖለቲካ በፈገግታ”፣ የብርሃኑ ሰሙ “ከእንጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ”፣ የመሐመድ ሰልማን “ፒያሳ”… ከጋዜጣ ገሃነማዊ መረሳት ውስጥ ብልጠት “ሺ-በክነፉ ሺህ በአክናፉ” መንጥቆ ያወጣቸው መፃህፍት ናቸው፡፡
“ዲከንሳዊውን” ዝንባሌ የፅድቅ ሥራ አድርገን የምናየው በጋዜጣ ግዴለሻዊ ባህርይ ሳቢያ ከመታወስ ጠለል በታች የተቀበሩ ጋዜጠኞችን ስናስብ ነው፡፡ አንዳንዶቹን ተስፋዬ ገብረአብ በ”እፍታ” (አምስት ቅፆች) ታድጓቸዋል፡፡ መኩሪያ መካሻ፣ ደረጀ ደስታ፣ እሸቱ ተፈራ፣ ቶማስ አርጋው፣ ብርሃነመስቀል ደጀኔ፣ ወሰን ይሔይስ፣ እቱ ገረመው፣ ጌጡ ተመስገን… ወደፊት ለሚያጠና ጥሩ አመላካች ፈለጋቸውን “እፍታ” ላይ ጥለዋልና “የትንሳኤ ወ ዝንጋኤ” ተስፋ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ አይመስላችሁም? እኔን መስሎኛል፡፡
ለማንኛውም ሀተታዬን ጨርሼ ከመለየቴ በፊት ይቺን የጋዜጣ ቁራኛነትን የምታጐላ ታሪክ ልንገራችሁ፡፡
ባለታሪኩ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ነው፡ተራኪያችን ደግሞ ዘነበ ወላ፤ “ማስታወሻ” መፅሐፍ ውስጥ፡፡ ስብሐት በጉልበቱ ተንበርክኮ ሆዱን ጭኑ ላይ አጣብቆ መሬት ላይ ወረቀት አስቀምጦ ይፅፋል፡፡ ይሄ ያልተለመደ ሁኔታ ግር ያሰኘው ዘነበ ይጠይቃል፡፡
“ጋሽ ስብሐት ምን ሆነሃል?”
“አሞኛል”
“ታዲያ…”
“የጋዜጣው ፅሁፍ ማስገቢያም ደርሶብኛል”
“እና ለምን በአሁኑ አትዘለውም?”
“ፅሁፍ አንባቢ መታመሜን የት ያውቅልኛል፡፡ በእንዝህላልነት ይመስለዋል” መፃፉን ቀጠለ…
እና ጋዜጣና ጋዜጣ አንባቢ የሚዘነጉት ይሄንን ውለታ ነው፡፡

 

Read 3512 times Last modified on Tuesday, 01 November 2011 14:20