Monday, 05 March 2012 14:42

ስብሃት ደህና ሁን!

Written by  ከማዕረጉ በዛብህ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ሰሞኑን ካጣቻቸው ጽኑ አገር ወዳድ ምሁር ልጆችዋ አንዱ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ነው፡፡ ስብሃት ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ በንባብ ብዙ ዕውቀት ያካበተ፣ ለዕውቀት የኖረ፣ በጽሑፎቹ አያሌ አዳዲስ ትምህርቶችንና ዕውነቶችን በሰላ ብዕር የሚገልጽ ሰው ነበር፡፡ በንባብ ያከበተው ዕውቀት ወጣቱን ብቻ ሳይሆን እንማር ካልን በርሱ ዘመን ያለነውን ትውልድ ጭምር ሊያስተምር የሚችል ሰው ነው፡፡ አገሩን ኢትዮጵያን በጣም የሚወደው ስብሃት፤ አካሉ ከሲታ ቢሆንም በህሊናዊ ጥንካሬው ግዙፍ ሰው ነበር፡፡ በልዩ ልዩ የዓለም ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ የመነጩትን መፃህፍት ያነበበ፣ ስለዘመናዊ እውቀትና ሕይወት በጥልቀት የተመራመረ፣ በሱ ዘመን ከተገኘነው የትውልዱ አባሎች የተለየ ሰው ነበር፡፡ እውቀትን ለንግድና የራስን ኑሮ ለማዳበር ሳይሆን በእውቀትነቱ ብቻ የሚያፈቅርና የሚመረምር ዘመን-አይሽሬ (ክላሲካል) ምሁር ነበር፡፡ ስለታላላቆቹ የዓለም ሃይማኖቶች፣ (ክርስትና፣ እስልምና፣ ጁዴይዝም፣ ቡዲዝምና ታዎይዝም ወዘተ) ያለአድልዎ በእኩልነት ዓይን በማየት ያጠናና በትክክል ሊያስረዳ የሚችል ልዩ ምሁር ነበር፡፡

ባገራችን ምሁር የሚለው ቃል ዩኒቨርስቲ ገብቶ በዲግሪ የተመረቀ የሚለውን ትርጉም እየያዘ መጥቷል፡፡ ያ ደግሞ ፈረንጆች ኢንተሊጀንሺያ (Intelligentsia) የሚሉት ይመስለኛል፡፡ ስብሃት ግን የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ከማግኘቱም በላይ እጅግ ብዙ ርቀቶች ተጉዞ የዓለምን እውቀቶችና ጥበቦች ተመራምሮ በፅሁፎቹ ብዙዎችን ያስተማረና፣ ለጥበብ የኖረ ነው፡፡ (ፈረንጆች Intellectual የሚሉት ሰው ነው) አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን እንዳለ በስማቸው እንጥራቸው፣ “አካፋን አካፋ እንበል” የሚለው የስብሃት ብሂልም ይህንን አዕምሮአዊ (ኢንተለክችዋል) ባህሪውን የሚያንፀባርቅ እውነታ ነው፡፡

ስለ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ይህችን አጭር ፅሁፍ የፃፍኩት የኢትዮጵያ ሕዝብ ስብሃትን ስለማያውቀው ላስተዋውቀው ለማለት አይደለም፡፡ ሕዝቡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ይወደዋል፣ ያከብረዋልም ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውለድ በጣም እንደሚወደውና እንደሚያከብረው በሰፊው ይታወቃል፡፡ እኛ የትውልዱ አባሎች አልተሳካልንም እንጂ ስብሃት በኛና በወጣቱ ትውልድ መካከል ድልድይ በመሆን ሊያገናኘን ሞክሯል፡፡

ስለ ስብሃት የፃፍኩት አብሮ-አደግ ተብሎ ሊጠቀስ ከሚችለው የረጅም ዘመን ትውውቃችንና ግንኙነታችን በላይ በሁለት አጋጣሚ አብረን ስለሠራን የርሱን ባህሪ የሚያሳዩ አንዳንድ ነጥቦችን ለመጠቃቀስ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ በኔ ላይ የተወው መልካም ትምህርታዊ ተፅእኖ አብሮኝ ስላለም ጭምር ነው፡፡ በየካቲት መፅሔትና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን አብረን ሰርተናል፡፡ አጋጣሚ ሆነና እኔ የመፅሄቱ ዋና አዘጋጅ እሱ ተራ አባል ሆነን ስንሰራ እኔና ሌሎቹ የስራ ጓደኞቹ ከስብሃት እውቀት፣ ከስብሃት የስነፅሁፍ ችሎታ፣ ከስብሃት ጨዋታ ብዙ እንማር ነበር፡፡ ቢሮክራሲ አይፈቅድም እንጂ፣ እሱ አለቃ እኛ የሱ የሥራ ባልደረቦች ሆነን መስራት እንደሚገባን አውጥተን ባንናገረውም በልባችን እናውቀው ነበር፡፡ የስብሃት ስራዎች እጥር፣ ምጥን፣ ጥርት ያሉ ናቸው፡፡ እንደዋና አዘጋጅ የስብሃትን በእጅ-ፅሁፉ የሚቀርቡ ፅሁፎች የፕሮቶኮል ችግር እንዳይኖራቸው ከማየት በስተቀር አንድም እርማት ለማድረግ ደፍሬ አላውቅም፡፡ ላርመው ብል ያ አንባቢ የሚወደው ስነፅሁፋዊ ጣእሙ ሊበላሽ ይችላል የሚል ስጋት ነበረብኝ፡፡ ስልጣንን በተመለከተ፣ ፕሮቶኮላዊ አቀማመጥ ሁልጊዜ የሰውን እውቀትና ችሎታ በትክክል የሚመዝን አይመስለኝም፡፡ አንድ ጊዜ ለመፅሄቱ ባዘጋጀው ፅሁፍ የአንድ ባለስልጣንን ስም ይጠቅሳል፡፡ ባለስልጣኑ በነበራቸው ፕሮቶኮል ‘ክቡር’ መባል ያለባቸው ስለነበሩ “ስብሃት እኝህ የጠቀስካቸው ሰው’ኮ በፕሮቶኮሉ መሰረት ‘ክቡር’ መባል ያለባቸው ናቸው” አልኩት፡፡ “እኔ ምን ቸገረኝ ክቡር እምክቡራንም በላቸው፡፡ ለኔ ቁምነገሩ ሰውየው በጉዳዩ አነስተኛ ተዋናይም ቢሆኑ ስማቸው መጠቀሱ ነው” ነበር የሰጠኝ መልስ (ቃላቱን በደምብ አስታውሻቸው ከሆነ)

ስብሃት ጋ እውነት እንጂ ማስመሰልም ውሸትም የሌሉ ነገሮች ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ የካቲት መፅሔት እያለን እቢሮዬ ይመጣና “ማዕረግ፤ እኪሴ ሳንቲም የለኝም፡፡ ሞዴል ስድስትንም ተጠቅሜባታለሁ፡፡ ስለዚህ ጐጃም ላከኝና “ስለ በላይ ዘለቀ አንድ ዘናጭ ፅሁፍ ይዤ ልምጣ” አለኝ በፈገግታ፡፡ ደስ የሚለው እውነተኛነቱ ብቻ ሳይሆን ለመፅሄቱ ያሰበው ተነባቢ ፅሁፍም ስለሆነ የመጓጓዣና የውሎ አበል እንዲዘጋጅ አደረግሁና ሄደ፡፡ ሲመለስ ስለ እኝያ የኢትዮጵያ ጀግና ያዘጋጀው ፅሁፍ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን አካባቢ የጥናትና ምርምር ግኝት እንደሚባለው ከዚያ በፊት ተገልፀው የማያውቁ አዳዲስ እውነቶችን የያዘ ከመሆኑም በላይ የስነፅሁፍ ጣእሙም “እጅ የሚያስቆረጥም” ነበር፡፡

የስብሃት ፅሁፎች ትክክለኛ፣ እውነቶች ሳይቀባቡ፣ ሳይደበቁ፣ በጥዑም የስነፅሁፍ ጥበብ የሚቀርቡባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም ይነበባሉ፣ ያስተምራሉ፣ ያዝናናሉም፡፡ ለምሳሌ ከመሞቱ በፊት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጥር 19 ቀን 2004 “አገርም እንደሰው” የሚለውን የመንግሥቱ ለማን ህያው ግጥማዊ ቃላት በመጥቀስ ባቀረበው ፅሁፍ Great Britain (ታላቁዋን ብሪታንያን) ሲገልፅ፣ “በመጀመሪያ ኢንግላንድ ብቻ ነበረች፡፡ በኋላ በጦር ኃይል (እና በዲፕሎማሲ) ተራ በተራ Scotland, Wales እና Southern Ireland ገበሩላትና The United Kingdom ሆነች” ሲል ነው የፃፈው፡፡ ይህ አገላለፅ ከቋንቁ ውበቱ ሌላ፣ ብዙ ሰው ምሁራን ጭምር የሚደበላለቅባቸውን የእንግሊዝንና የግሬት ብሪትንን ታሪካዊ ግንኙነትና የአሁኑንም እውነታ በሚገባ የሚያሳይ ነው፡፡ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር (ጆርጅ በርናርድ ሾውን) ለሚያውቁ የኢትዮጵያ በርናርድ ሾው ነበር፡፡

ቱሪዝም ኮሚሽን ውስጥ አሁንም እኔ የመምሪያ ኃላፊ ሆኜ ስብሃት ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዛውሮ አብረን እንሰራ ነበር፡፡

ስብሃት በዚህ ሰዓት ግባ፣ በዚህ ሰዓት ውጣ የሚለው የቢሮክራሲ ጣጣ አይመቸውም፡፡ ነፃነቱን ስለሚወድ ሲፈልግ ይገባል፣ ሲፈልግ ደግሞ ከስራ ይቀር ነበር፡፡ አለቆች ይጠሩኝና ይሄ ሰውዬ በስራው ላይ አይገኝም፡፡ አንድ ነገር አድርግ ይሉኛል፡፡ ጠራሁና በምክር መልክ በስራው ላይ በሰዓቱ እንዲገኝ ነገርኩት፡፡

“እናንተ ማለት አንተና አለቆችህ ከኔ የምትፈልጉት የስራ ውጤት ነው ወይስ ቢሮ ውስጥ መጐለቴን ነው?” አለኝ፡፡ “ሁለቱንም ነው” አልኩት፡፡

“የስራ ውጤቴን አሳምሬ እሰጣችኋለሁ፣ ሁለተኛውን ግን አታገኙም” አለኝ፡፡ እስቲ ላስፈራራው አልኩና ከደሞዙ የተወሰነ ገንዘብ እንዲቆረጥ የሚያዝ ደብዳቤ አዘጋጅቼ ጠረጴዛዬ ኪስ ውስጥ ቆልፌ ጠበቅሁት፡፡ አንድ ቀን ወደ ቢሮው ሲገባ ከሩቁ አይቼ ጠራሁትና የቅጣት ደብዳቤውን እንዲያነበው ሰጠሁት፡፡

አንብቦ ሲጨርስ እየሳቀ “ጐበዝ ቢሮክራት፣ ትክክል ነው የፃፍከው፣ እባክህ ላከው ወደ አስተዳደር” አለኝ ምንም አይነት ቅሬታ በፊቱ ላይ ሳይታይ፡፡ እኔም ደብዳቤውን ተቀበልኩና ከፊቱ ቀድጄ ጣልኩት፡፡ አሁንም ምንም አይነት የስሜት መግለጫ ምልክት በፊቱ ላይ ሳይታይ “እስቲ አንተን ጓደኛየን ላለማሳጣት ምክርህን በስራ ላይ ለማዋል እሞክራለሁ” ብሎኝ ወጣ፡፡ ታዲያ እውነትም የቢሮክራሲ ጣጣ ሆኖብን ነው እንጂ ከሰው የሚጠበቀው ጥሩ የስራ ውጤት ነው እንጂ ቢሮ ተጐልቶ መዋሉ አልነበረም፡፡ በተለይ ስብሃት ከተገኘ የሚሰጠውን ስራ እጥር፣ ምጥን፣ ጥርት አድርጐ በሰዓቱ ስለሚያቀርብ ከዓመት እስከ ዓመት ቢሮ ውስጥ ከሚጐለተው ሠራተኛ እሱ በጥቂት ቀናት አዘጋጅቶ የሚያቀርባቸው ስራዎች እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ነበሩ፡፡

አንድ ቀን ለምሳ ስንወጣ አገኘሁትና “ምሳ ልጋብዝህ” ብሎኝ አብረን ሄድን፡፡

ቦታው ሠንጋ ተራ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ ፊት ለፊት፣ ያኔ አውሮራ ከሚባለው የጣሊያን ቡና ቤት በስተጀርባ መደዳ ጠላ ቤቶች ባንደኛው ውስጥ ነበር፡፡ እዚያ እንደደረስን እጃችንን ታጥበን እንግባ አለኝና ስንታጠብ ሁለት ጭቃ ሲመርጉ የዋሉ ወዝአደሮች ሲታጠቡ አገኘን፡፡ ከስብሃት ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው እነርሱም አብረውን ገቡና ራቅ ብለው ተቀመጡ፡፡ እኛ ቁጭ ስንል ስብሃት “አንድ ምሳ” ብሎ አዘዘ፡፡ አንድ ወፍራም እንጀራ በትልቅ ትሪ ተዘርግቶ እመካከሉ ላይ ፍልጥ ፍልጥ የሚያካክሉ ክኮች የፈሰሱበት ቀይ ወጥ ተቆልሎ ቀረበልን፡፡

ምግብ አቅራቢዋ የሚጠጣስ ስትለው “የተለመደው ነዋ” ብሎ ሳቅ አለ፡፡

አንድ ጣሳ ጠላና ሁለት የቆርቆሮ ኩባያዎች ቀረቡልን፡፡ “እንዴ በስራ ሰዓት እንዴት ጠላ ጠጥተን እንገባለን?” አልኩት፡፡ “አለቆቻችን’ኮ ወይን ጠጅ፣ ዊስኪና ኩርቫዝየር ነው ጠጥተው የሚመጡት፤ እኛ እንኳን ጠላ ነው፡፡ ጠላ ደግሞ የኛን ሞተር የሚያንቀሳቅስ ቤንዚን ነው” አለኝ፡፡ እዚያ ቤት የሚመገቡት ሁሉ ጠላ አስቀርበው ይጠጡ ስለነበር ምንተ እፍረቴን ግማሽ ያህሉን ጠጥቼ ወጣን፡፡ ሜንታ ከረሜላ ገዛሁና የጠላውን ሽታ እንዲያጠፋለት ሰጠሁት፡፡ “ጠላ መጠጣቴ ሐቅ ነው፤ ያንን ሀቅ በከረሜላ አላጠፋውም፡፡ ለኔ አትጨነቅ” ብሎኝ ወደ ቢሯችን ገባን፡፡ እኔም ምግቡና መጠጡ ባይመቸኝም እዚያ የወሰደኝ አንድ ቁምነገር ሊያስተምረኝ ነው ብዬ ከራሴ ጋር ተወያየሁ፡፡

አንድ ቀን ጠዋት ስብሃትን አገኘሁትና ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ቀጠለና “ማኪያቶ ብንጠጣ “ዘናጭ ሃሳብ ነው… አይደለም?” አለኝ፡፡ “አዎ ጥሩ ሃሳብ ነው” አልኩት፡፡ ያን ጊዜ (የዛሬ ቡና ቤቶች እንዳይሰሙ እንጂ) ማኪያቶ 25 ሣንቲም ነበር፡፡ 15 ሳንቲምም ነበር፤ ቀደም ብሎ፡፡ እንዳጋጣሚ ቡና ቤት አጠገብ ነበርንና ከመግባታችን በፊት ወደኔ ዘወር አለና “ስማ ማዕረግ፤ እኔ ያለኝ 40 ሣንቲም ነው አንተ አስር ትጨምራለህ” አለኝ፡፡

ገባንና ሁለት ማኪያቶ አዘን ስንጫወት 40 ሣንቲም አውጥቶ እጠረጴዛው ላይ አስቀመጠ፡፡ እኔ ቀልዱን መስሎኝ አንዲት አሮጌ ብር አውጥቼ “እኔ እከፍላለሁ ግዴለም” አልኩና ሳንቲሞቹን ወደሱ ፊት ገፋ አደረግሁዋቸው፡፡

“አይደለም 40 ሳንቲምማ ጋብዣለሁ እኔ ነኝ የምከፍለው፣ አንተ አስር ብቻ ነው የምትከፍለው” አለኝ፡፡ እሱ ጋ መግደርደር ስለሌለ 10 ሳንቲም አውጥቼ ጠረጴዛው ላይ በማስቀመጥ ግብዣው ተከናወነ፡፡ ስንወጣ “በጥዋቱ በማኪያቶ ዘነጥን አይደለም?” አለና ተሳስቀን ሁለታችንም ወደየጉዳያችን ሄድን፡፡

እኔ ስብሃትን በጓደኝነትም ሆነ በስራ ባልደረባነት እንደማውቀው ሐቅን አክባሪ ብቻ ሳይሆን ሀቅን ወይም እውነትን ራሷን ሆኖ የኖረ ሰው ነው፡፡

ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ብዙ ብልህ ቀልዶች የሚያውቅ፣ ሰውን የሚወድና በሰዎች በቀላሉ የሚወደድ ሰው ነው፡፡ የሚፈልገውን ለማድረግ መግደርደር አያውቅም፡፡ የኖራትን ዘመን ሁሉ ዓለምን ለማወቅ ሲመራመርና ለህሊናው ብቻ ተገዢ ሆኖ፣ የራሱን የህልውና ነፃነት አስከብሮ፣ ሕይወቱን በሚያምንበት በራሱ ፍልስፍና የመራ ምሁር ሲሆን ከሕልውና እውነታውና ከእሳቤው አንፃር ፈረንጆች ኤግዚስትተንሺያሊስት (Existentialist) በሚሉት ዘርፍ ሊመደብ የሚችል ፈላስፋ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ቤተሰቡንና ልጆቹን ፅናት ይስጣቸው፡፡

 

 

Read 2141 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:45