Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 September 2011 11:38

|ሌባ እና ፖሊስ..

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንድ ኬንያዊ ህፃን ..ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?.. ብላችሁ ብትጠይቁት እንደ እኛ ሀገር ህፃን ..ዶክተር.. ወይም ..ኢንጂነር.. ይላል ብላችሁ  እንዳትጠብቁ፤ ካለምንም ማመንታት ፖሊስ ሊላችሁ እንደሚችል እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ናይሮቢ ሌላም ገድል አላት፡፡ ፖሊሶቹ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የማይወጥኑት ነገር የለም፡፡ አንድ ስደተኛ ገንዘብ አልከፍልም ካለ ድብደባ ይደርስበታል ብላችሁ እንዳትሰጉ፡፡ ወይም ደግሞ ሕገ ወጥ ስደተኛ ነው በሚል ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ አይታሰብም፤ ሌላ ዘዴ አለ፡፡

ሙሰኛ ፖሊስ
የብሪቲሽ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ አውሮፕላን ጉዞውን ከናይሮቢ ወደ ለንደን አድርጓል፡፡ የአውሮፕላኑ አስተናጋጆች ድግስ እንዳለባት የሀገሬ ባልቴት ጥድፊያ ላይ ናቸው፡፡ መንገደኞች በየግል ጉዳያቸው ተጠምደዋል፡፡አብዛኞቹ መጽሐፋቸውን ወይንም ላፕቶፓቸውን ከፍተው አንገታቸውን ቀብረዋል፡፡ ማንም ማንንም የመመልከት ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡
የአውሮፕላኑ የጸጥታ ድባብ ቤተ መጽሐፍት የገቡ ያህል ጎልቶ ይሰማል፡፡ የኔ ዐይን አንዳች ነገር የሚፈልግ ይመስል በየአቅጣጫው ይተራመሳል፡፡ ምናልባትም የተለየ ነገር አሳዶ ለመያዝ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከጎኔ የተቀመጠውን ሰው ልብ አላልኩትም ነበር፡፡ ብቻ አንድ አፍሪካዊ ወንድሜ እንደሆነ አስተውያለሁ፡፡ ወደ አርባዎቹ የሚገመተው ጐልማሳ ገና አውሮፕላኑ አፍንጫውን ወደ አየር ላይ እንደቀሰረ፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተደላድሎ እንቅልፉን መለጠጥ ጀምሯል፡፡ ..ይህ ሰው ኬንያዊ መሆን አለበት.. አልኩ ለራሴ፤ የአውሮፕላኑ አስተናጋጆች የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማርካት የሚያደርጉት ጥድፊያ የአውሮፕላን ላይ ጎረቤቴን ቀሰቀሰው፡፡ ኬንያን እና ኬንያውያንን ለማያውቅ ሰው የጉልበት ስራ ሲሰራ ውሎ የመጣ ያስመስለዋል፡፡ እንቅልፍ ለኬንያውያን ብርቃቸው ነው፡፡ በማንኛውም ቦታ ሸለብ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ..ደክሞሃል መሰለኝ?.. ብዬ ለመግባቢያ ያህል ወሬ ጣል አደረኩ፤ በፍጹም እንዳልደከመው አረጋገጠልኝ፡፡ ከዚያም ..ኢትዮጵያዊ ወይስ ኤርትራዊ ነህ?.. ሲል ጥያቄውን አስከተለ፤ ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ ስነግረው በርካታ ኢትዮጵያውያንN እንደሚያውቅና የኢትዮጵያን ምግብ አዘውትሮ እንደሚመገብ ነገረኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ቆንጆ መሆናቸውንም አከለበት፡፡
ነዋሪነቱ በናይሮቢ የሆነው ይህ ግለሰብ የፖሊስ ባልደረባ እንደሆነና ለትምህርት ወደ ለንደን እየተጓዘ መሆኑን አጫወተኝ፡፡ ..ኦው የፖሊስ ባልደረባ?.. አልኩ ሳይታወቀኝ፡፡ የናይሮቢ ፖሊሶች ምን ያህል ገንዘብ ወዳዶችና መጥፎ እንደሆኑ አሳምሬ አውቃለሁና ከጐኔ የተቀመጠው የኬንያ ፖሊስ የስንቱን ወገኔን ኪስ እንዳራገፈ ሳስብ ብሽቅ አልኩ፡፡ ..የኬንያ ፖሊሶች ሙሰኞች ናቸው.. አልኩት በስሜት ተነድቼ፤ ..የኬንያ ብቻ ነው ወይስ የአፍሪካ?.. ሲል ያልጠበቅኩትን ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡  
ስደተኞች እቅፍ አድርጋ የያዘችው ናይሮቢ ውስጧ ያለው ጉድ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ የናይሮቢ ክሲች፣ የናይሮቢ ነዋሪዎች ሁሉም ባለ ብዙ ታሪኮች ናቸው፡፡ የናይሮቢ ፖሊሶች ግን ከብዙም እልፍ የሆነ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከጎኔ የተቀመጠው ፖሊስ ተመልሶ ወደ እንቅልፍ አለሙ ጭልጥ ሲል እኔ ግን ስለ ናይሮቢ ዘራፊዎች እና ፖሊሶች ትዝታዬን መመንዘር ቀጠልኩ፡፡ በልጅነታችሁ ..ሌባና ፖሊስ.. የሚለውን ጨዋታ ያልተጫወታችሁ ሰዎች የምላችሁ ነገር ግር እንዳይላችሁ፡፡ ይህ የናይሮቢ ..ሌባና ፖሊስ.. ጨዋታ ከልጅነት ጨዋታችን ፍጹም የተለየ ነው፡፡ በጨዋታው ሕግ ሌባው ሌባ ፖሊሱም ፖሊስ ነው፤ የናይሮቢ ፖሊሶች ግን ሌባም ፖሊስም መሆን ይችሉበታል፡፡ ስደተኛ ሲያገኙ ኪስ ገብተው ከመፈተሽ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ፖሊሶቹ ስለ ሕጋዊ ወረቀት (መታወቂያ) ማሰብ አይፈልጉም፡፡ በፖሊስ የተያዘ ስደተኛ ያለው አማራጭ መደራደር ነው፡፡
ድርድሩ እቃ መሸመት እስኪመስል በ..ቀንስልኝ.. እና ..አልቀንስም.. ይታጀባል፡፡ አትገረሙ ይህ ኬንያ ነው፡፡ የናይሮቢ ፖሊሶች ባለፀጎች ናቸው፤ ይህንንን ስል ምን ያህል ከወንጀል ጋር እንደተቆራኙ መገመት አይከብድም፡፡ አንድ ኬንያዊ ህፃን ..ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?.. ብላችሁ ብትጠይቁት እንደ እኛ ሀገር ህፃን ..ዶክተር.. ወይም ..ኢንጂነር.. ይላል ብላችሁ                                እንዳትጠብቁ፤ ካለምንም ማመንታት ፖሊስ ሊላችሁ እንደሚችል እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ናይሮቢ ሌላም ገድል አላት፡፡ ፖሊሶቹ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የማይወጥኑት ነገር የለም፡፡ አንድ ስደተኛ ገንዘብ አልከፍልም ካለ ድብደባ ይደርስበታል ብላችሁ እንዳትሰጉ፡፡ ወይም ደግሞ ሕገ ወጥ ስደተኛ ነው በሚል ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ አይታሰብም፤ ሌላ ዘዴ አለ፡፡ በአደገኛ እፅ ክስ ይመሰረትበታል፡፡ ለአደጋ ጊዜ የሚያስቀምጧት ..ጋንጃ.. ወይም ..አጠፋሪስ.. ከፈረደበት ስደተኛ ላይ የተገኘች ሆና ፍርድ ቤት በማስረጃነት ትቀርባለች፡፡ YH እንዳይሆን ስደተኛው ተበድሮም ቢሆን ለፖሊስ ይገብራል፡፡ አንድ መገበር የሰለቸው የሶማሌ ስደተኛ ይህንን የፖሊስ ሽወዳ ተሳልቆበታል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፣ ሶማሌው በፖሊስ ተይዞ ገንዘብ ሲጠየቅ ..አንገቴ ይታረድ አልሰጥም.. አለ፡፡ ፖሊስ እንደለመደው ወደ ፍርድ ቤት ያቀርበዋል፡፡ የናይሮቢ ፍርድ ቤቶች ቀጠሮ የላቸውም፤ የዕለቱ እለት መቅረብ ይቻላል ፖሊስም ችሎት ፊት ቀርቦ ..ይኸው ኤግዚቢት የያዝኩት አደገኛ እጽ ይላል፡፡ ዳኛውም ሶማሌውን በአንክሮ እየተመለከቱ ..ይህን ይዘህ ተገኝተሃልን?.. ብለው ይጠይቁታል፤ ቆፍጣናው ሶማሌ ..አያ የኔ ነው ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም ከ20 ፓኬት በላይ ነው.. ሲል ለፍርድ ቤቱ ይናገራል፡፡ ይኼን ጊዜ የፖሊስ ዐይን ድንገት ይፈጣል፤ ፍርድ ቤቱም ..ሌሎቹ ፓኬቶች የታሉ?.. ሲል ይጠይቃል 20 ፓኬት እጽ ከየት ይምጣ፡፡ ፖሊሱ እና ሶማሌው ተያይዘው ወደ እስር ቤት፡፡
የናይሮቢ ዘራፊዎች
ድሮ የአራዳ ልጆች ..ውጋ.. እንባባል ነበር ፡፡..ውጋ.. ማለት በአራድኛ ያገኘኸውን አካፍለኝ ማለት ነው፡፡ በኬንያ ፖሊሶችና በሌቦች የተለመደ ነገር ላውጋችሁ፡፡ ነገሩ ..ውጋ.. መሆኑ ነው፡፡ ኬንያውያን ፖሊሶች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለዘራፊዎች መሳሪያ ይወጋሉ፤ ዘራፊዎችም ካገኙት ላይ ለፖሊስ ገንዘብ ይወጋሉ፡፡ ሂሳብ ያካፍላሉ፡፡ ይህ ስምምነት በናይሮቢ የተለመደ ነው፡፡ ይህንን ስራ አደገኛ የሚያደርገው፣ ሌቦቹ በዘረፋ ላይ እያሉ ሌሎች በስምምነቱ ውስጥ የሌሉ ፖሊሶች ከመጡ ወይም ዘራፊዎቹ የመያዝ አዝማሚያ ከታየባቸው ሸሪኮቹ ፖሊሶች ቀድመው ሌቦችን መግደላቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ እነዚህ ዘራፊዎች ከሃብታም ቤት ጀምሮ እስከ ባንክ ድረስ የመዝረፍ አቅም ያካበቱ ናቸው፡፡ ከፖሊስ ጋር በውጋ የተስማማ ዘራፊ ..እተኩሳለሁ.. ካለ ሳይሰስት ይተኩሳል፡፡ ተዘረፍኩ ብሎ ..ኡኡ.. ማለት ህይወቴንም ውሰዷት የማለት ያህል ነው፡፡
በናይሮቢ የተሰማሩ ዘራፊዎች አደገኞች ናቸው፡፡ በናይሮቢ በማንኛቸውም ሰአት ዝርፊያ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ዝርፊያዎች ሁሉ በመሳሪያ የታጀቡ ሊሆኑ ስለሚችሉ ህይወትን ለማትረፍ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የናይሮቢ ዘራፊዎች ቀልድ አያውቁም፡፡ አስፈራርቶ መዝረፍ የሚባል ጨዋታ በፍጹም አይታሰብም፡፡ ..እጅ ወደ ላይ.. ከተባለ ንቅንቅ ማለት የለም፡፡ አለበለዚያ የጥይት ሲሳይ መሆን ነው፡፡ እንኳን መነቃነቅ ዞሮ የዘራፊዎቹን መልክ መመልከት በራስ ላይ መፍረድ ነው፡፡ ይህንን ኬንያውያን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡መሳሪያ ሲያዩ ከመቅጽበት መሬት ላይ በደረታቸው ሲነጠፉ ቅልጥፍናቸው ያስደምማል፡፡ ቀረርቶ እና ፉከራ ለኬንያውያን አይመቻቸውም፡፡ አበሻ ያደገበትን ቀረርቶ እና ፉከራ በኬንያ ምድር ከደሙ ሙልጭ አድርጎ ማስወጣት ይገደዳል፡፡
የአበሻ ሰፈር
መቼም ናይሮቢ ሰፊ አይደለች... አበሻ ተበታትኖ በናይሮቢ ይኖራል፡፡ ..ኢስሊ.. እና ..ያያ.. የሚባሉት አካባቢዎች በአበሻ መኖሪያነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ..ጊዶራይ.. የሚባለው ቦታም እንዲሁ ለአበሻ ኑሮ የተመቸ አካባቢ ነው፡፡በነዚህ አካባቢዎች ብዙ አበሾች እንደመኖራቸው ወደ መሸታ ቤት ጎራ የሚሉ አይጠፉም፡፡ ከመሸታ ቤትም ደግሞ ሙዚቃ ያለበትና ሞቅ ደመቅ ያሉ ቤቶች ይመረጣሉ፡፡ አንዱ ወዳጃችን በኬንያ ሙዚቃ ልቡ ጥፍት ብሏል፡፡ ..በኩኩዩ.. ሙዚቃ ካልጨፈረ እንቅልፍ አይወስደውም፡፡ ..ለእንቅልፉ አንድ ቢራ በጭፈራ አወራርጄ ልመለስ.. ብሎ ወደ መሸታ ቤት ጐራ ይላል፡፡ መሸታ ቤቱ የደመቀ አልነበረም፡፡ ሁለት ሦስት እያለ ዞር  ሲል በመጨረሻ ቀውጢ ቤት ተገኘ ብሎ ዘው ማለት፤ መጠጥ ቤቷ በጭፈራ ትናጣለች ሙዚቃው ይደለቃል፡፡ ወዳጃችን ተንደርድሮ እንደገባ ሁለት ሽጉጥ ጐንና ጐኑ ላይ ይደቀንበታል፡፡ ምን ተአምር ተፈጠረ ብሎ ገልመጥ  ሲል፣ መጠጥ ቤቱ በሌቦች ቁጥጥር ስር መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ለእንቅልፍ ብሎ የወጣው ወዳጄ በሌቦች እጅ ወድቆ ገንዘቡን እና ሞባይሉን ያስረክባል፡፡ ወደ ባልኮኒው ስር ሲወረውሩት አይኑ የተመለከተውን ነገር ማመን ያቅተዋል፡፡ ከሰባት የማያንሱ የእርሱ ቢጤ ጎረምሶች ንብረታቸውን አስረክበው ባልኮኒ ስር ተከምረዋል፡፡ ለካስ የቤቷ ድምቀት በዘራፊዎቹ የተፈጠረ የማስመሰያ ድራማ ነበር፡፡ ደናሾቹም፤ ጠጪዎቹም፤ ዘራፊዎቹም ሌቦቹ ሆነው የዛች ቡና ቤት ተግባራቸውን ፈጽመው ውልቅ አሉ፡፡ ወዳጃችንም አመዱ ቡን ብሎ ካለ ምንም መጠጥና ዳንስ ሦስት ቀን እንደተኛ አስታውሳለሁ፡፡ገድለ ናይሮቢ መች ይሄ ብቻ፤ ሲዘርፍ የተያዘ ሌባ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሌባ ተይዞ ለፖሊስ ማስረከብ የሚባል ነገር መች ኬንያውያን ያውቁና ፤ሌባ ከተያዘ በተገኘው ነገር ውቃው ነው፡፡ሌባ የሚባል ሁሉ የሰው ፍጡር አይመስላቸውም፡፡ መንገደኛ ሁሉ ይወቅረዋል፡፡ በድብደባው አልሞት ካለ ቤንዚን ተርከፍክፎ ይቃጠላል፡፡ ይህ የመረረ እውነት ነው፡፡ l¤§ አንድ እውነት ልጨምርላችሁ፡፡ በናይሮቢ ኪስ የሚያወልቁ እና በሌሎች ዘረፋዎች ላይ የተሰማሩ የሃገሬ ልጆች እንዳሉ ስሰማ ውስጤ በድንጋጤ ተኮማተረ፡፡መሳሪያ ይዞ የዘረፈም ሆነ ኪስ ያወለቀ ሌባ  ነው፡፡ የሕዝቡ ቅጣትም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ያወቁ ኪስ አውላቂ የሃገሬ ልጆች ምንኛ ደፋር ቢሆኑ ነው ጃል፡፡ ኪስ ለማውለቅ መርካቶ አንሷቸው ይሆን ናይሮቢ የከተሙት? የመርካቶ ሕዝብ አራዳ ነው፣ ሌባ ሲያዝ ለፖሊስ አሳልፎ ይሰጣል እንጂ ደብድቦ አያቃጥልም፡፡ የመርካቶ ሌባም ..ነቄ.. ነው ሲነቃበት |FÊND ላሽ በይ.. ብሎ ይሮጣል እንጂ ሰው አይገልም፡፡ ናይሮቢ ግን ከዚህ የከፋውን ይዛለች፡፡ ሌባም የሚገደልበት ሌባም የሚገድልበት፤ ዝርፊያ ከሞት የተቆራኛት ውብ ከተማ ነች - ናይሮቢ፡፡
አብርሃም በጊዜው ነዋሪነቱን በአሜሪካ ሚኒሶታ ያደረገ የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ ነበር፡፡

 

Read 6712 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:44