Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 September 2011 10:05

ንግሥተ ሳባ እና እራስን የመውቀስ ጥበብ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ነባር የግዕዝ ቅኔ (በስማ በለው) ልጥቀስሽ፡-
..እመ ተናገርኩ ድቅ ሰብአዛቲ ዓለም ይፀልዑኒ
ወከመ ኢይ ንብብ ሐሰተ ኩነኔ ዘአከ ያፈርሃኒ፤..
በዚያው በስማበለው ሲተረጐም፣
..እውነትን እንዳልናገር የዚህ ዓለም ሰዎች ይጠሉኛል
ሐሰትንም እንዳልናገር ፍርድህ (የእግዚአብሔር) ያስፈራኛል..
የዚህ ቅኔ መድፊያ እኔን አይመለከተኝምና ነው የቆረጥኩት፡፡ እንዲህ ይላል ..ወእምኩሉስ አርምሞ ይኀኄይስ ወይሣኔ.. (ከሁሉ ግን ዝም ማለት ይሻለኛል) ይሄ ነባር ቅኔና አመለካከቱ ተጋግዘው ኢትዮጵያውያን በሌለን የታሪክ ቁመና ለመዘናከት እንድንሞክር አድርገውናል፡፡

ዝንካቴአችን በተመልካች ..ውበት.. ሳይሆን ..እብደት.. ተደርጐ ቢቆጠር አያስገርምም፡፡
..ከሁሉ ግን ዝም ማለት ይሻለኛል.. ከሚሉ አዋቂዎች በላይ ተላላ ..ታሪክ.. ፀሐፊዎች ለ..እብደታችን.. ከፍተኛ አስተዋኦ አላቸው፡፡ ያሞገሱ፣ ያሞካሹ፣ ከፍ-ከፍ ያደረጉ እየመሰላቸው በግብዝነት በተረት አቃቢትነታቸው ስለገፉበት እውነታችንን በሚጋፋ የህልም አለም ውስጥ ለመቆየት ተገደናል፡፡
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ተረት ከተረትነት ያለፈ ስፍራ ሲኖረው ህገወጥ ማህበራዊ ግንባታ ተካሂዷልና እንደ ..ጨረቃ ቤት.. በፍጥነት መፍረሱ ተገቢና የግድ ነው፡፡ እራቁቱን እየተኛ ..ሐፍረተ-አኗኗሩን.. የነተበ ተረት የሚጋርድ ማህበረሰብን የሚጠቅመው መናኛ ተረቱን ነጥቆ በማራቆት፣ ገላውን የሚመጥን ..የእውነታ ጥብቆ.. እንዲያፈላልግ መገፋፋት ነው፡፡
የተረት ..አቅም ግንባታዎች.. ፖሊሲያቸውን ከሚያስፈሙባቸው ሁነኛ ትርክቶች ውስጥ የንግሥተ ሳባ ተረት አንዱ ነው፡፡ የተረቱን ተዋረድ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ በ1941 ዓ.ም ..ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና.. በሚል መሐፋቸው ላይ እንዳቀረቡት አድርገን እንመልከተው፡፡
..የኢትዮጵያ የመዠመሪያ ንጉስና አምላክ ዘንዶ ነበር ይባላል፡፡ በዘመኑ የነበረች አንዲት ቆንዦ ልጃገረድ አንድ ሴት ልጅና አጋቦስ የተባለ ዘንዶ፤ ሴቷን ከሰው ዘንዶውን ከዘንዶ መንታ ወልዳ እንደነበር ይተርካል.. እናቲቱ ከሞተች በኋላ ከርሷ የተወለዱት መንትዮች ዘንዶውና ሴቷ ልጅ አብረው አደጉ፡፡ በኋላም ዘንዶው ቁመቱ ሰባ ክንድ ጥርሱም ሰባ ሆኖ ሰው እያሳደደ ይበላ ጀመር፡፡ በዚህ ነገር ህዝቡም ተቸገሩ፡፡ መውጋትም አልቻሉ፡፡ በኋላ ግን በእህቲቱ አማካኝነት ህዝቡ ለዘንዶው ለአጋቦስ በቀን 10 በሬ፣ 10 ላም፣ 50 ፍየል፣ 50 በግ፣ እንዲሁም ማር፣ ወተትና አንዲት ልጃገረድ ሊገብሩለት ውል ገቡና እርቅና ሰላም ሆነ፡፡ እሱም አገሪቱን 40 ዓመተ ገዛ (ከነዘሩ 400 ዓመት ገዛ የሚሉም አሉ)
..40ኛው ዓመት ሲፈፀም ከወደ ሐማሴን ገብገቦ የሚባል ሰው መጣ፡፡ እርሱም ለዘንዶው የሚሰጠውን ግብርና መስዋእት ባየ ጊዜ ተደነቀና ስለምንድነው ይኸን ያህል ግብር የምትገብሩለት፤ ብትገድሉት አይሻልም? አላቸው፡፡ እነሱም ቢያቅተን ነው ይኸን ሁለ ለመገበር የተገደድነው፡፡ አንተ ግን ብትገድለው ገዣችን ትሆናለህ ብለው ቃልኪዳን ገቡለት፡፡..
ትርክቱን እናሳጥረው፡፡ ገብገቦ በእሳትና በፍላፃ ዘንዶውን ገጥሞ ከገደለው በኋላ የዘንዶውን እህት አግብቶ ነገሰ፡፡ ንግሥተ ሳባ ወይም ንግሥተ ሐዜብ ወይም ማክዳ የዚህ ሰው አምስተኛ ትውልድ ናት፡፡ እሷም በተራዋ ከነገሠች በኋላ አገሬው አጉረመረመ፡፡ ሴት አይገዛንም - ልምድ የለንም አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንግሥተ ሳባ አምርራ ብታለቅስ በእንባዋ ዘንዶውን ዳግም አስነሳችው፡፡ ህዝቡ አማራጭ በማጣቱ ወንድ እስኪደርስባት ድረስ እንድትነግስ ፈቀዱላት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የሰሎሞንን ጥበብ በመስማቷ በእንቆቅልሽ ልትፈትነው ገፀ-በረከት አስጭና ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘችው፡፡
ለካ፤ ታሪካችን ብቻ ሳይሆን ዘራችንም ግማሽ ሰው ግማሽ ዘንዶ ኖሯል? ይሄን የሚነግረን የሳባ ሥረ-መሰረት ነው፡፡ ከሥነ-ኑባሬ የተፋታው ይሄ ተረት ዘንዶና ሰው በአንድ ተፀንሰው አንድ ሆድ ውስጥ ማደራቸው ሳያንስ፣ ከ40 አመት የንግሥና ዘመን በኋላም የዘንዶው መንትያ ከዘንዶው ገዳይ ጋር ተጋብታ ዘሯን ማስቀጠሏን ይተርካል፡፡ እንግዲህ ዘመናዊዎቹ የተረት ..አቅም ግንባታዎች.. ተልዕኮ አድርገው የያዙት ከተረቱ ውስጥ የማይታመነውን ዘምዝመውና ቀምቅመው የተጣራ አፈ-ታሪክ ማቅረብን ነው፡፡ በእንዲህ ያለ ሥራ ከተጠመዱት መካከል አንዱ እራሳቸው ተክለፃድቅ መኩሪያ ናቸው፡፡ በዚሁ ..ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና.. በተሰኘ መሐፋቸው ላይ .....የንግሥተ ሳባ መጣ የሚባልበት እውነትና ተረት የተደባለቀበት ታሪክ.. ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡
ተረት አሹትም በጠበጡትም ያው ተረት ነው፡፡ ቢያዝሉትም ቢያቅፉትም ያው ተሸከሙት ነው፡፡ ይሄ ሳይገባቸው በስህተት፣ እያወቁም በድፍረት ተረቱን በመዘምዘምና በመቀምቀም የታሪክ ፍጣሮት ለመስጠት የተጉ ፀሐፊያን ብዙ ናቸው፡፡ ..ግልገል - ግልገሎቹን.. ትተን አውራዎቹን ብንጠቃቅስ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴን እናገኛለን፡፡ ..የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ አድዋ ድል.. የተሰኘው መሐፋቸው ተጠናቅሮ ያለቀው በ1920ዎቹ ይሁን እንጂ የህትመት እድሜውን መቁጠር የጀመረው ከ1999 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ በዚህ መሐፍ ላይ ብላቴን ጌታ ህሩይ፤ ታሪክን ከተረት አሽክት ለቅመው ለማጥራት ብዙ ደክመዋል፡፡ ቃል በቃል እንዲህ ይላሉ፡፡
..እንደ ተረት የተፃፈውን ታሪክ ሳልፍላችሁ በመቅረቴ እንዳታዝኑ እለምናችኋለሁ፡፡ አለመፃፌም እውነትን ፈላጊዎች ከሆናችሁ የተረት ነገር አያስፈልጋችሁም ብዬ ነው.. (የኢትዮጵያ ታሪክ ገ 39)
ብላቴን ጌታ ህሩይ እንዲህ ይበሉ እንጂ ሳይፉልን የቀሩት ተረቱን ሳይሆን የተረት ማስገረሚያ ድንቃዩን ነው፡፡ ለምሳሌ ንግሥተ ሳባ ከዘንዶ መዛመዷን፣ እግሯ ሸኾና መሆኑንና የመሳሰሉትን ነቅሰው አመ-ተረቱን እንዳለ የታሪክ ተዋረድ ለመስጠት ያበጃጁታል፡፡ አንዳንድ የማገናዘቢያ ጥያቄዎችን በማንሳት ተረቱን እንደ ታሪክ ይሞግቱታል፡፡
..በአንዳንድ ታሪክ ሰለሞን ልጁን ሚኒሊክን በኢትዮጵያ አነገሰው ተብሎ ተፎ ይገኛል፡፡ እንዲህም ተብሎ መፃፉ ምናልባት ኢትዮጵያ ከብዙ ዘመን አስቀድሞ ስምዋ የታወቀ ገናና መንግሥት መሆንዋ ባይታወቅ ይሆናል.. እያሉ ኢትዮጵያ ከእስራኤል የምትበልጥበትን ብዙ ምክንያቶች ይደረድራሉ፡፡ ወደ ሙግት ከመግባት አስቀድሞ የመሟገቻ ርእሱን እውነትነት ማረጋገጥ አይቀድምም ነበር? ለመሆኑ በኢትዮጵያ ምድር ንግሥተ ሳባ የምትባል ሴት ነግሳ ነበር? መቼ? እንዴት?...
የንግሥተ ሳባ ግዛትና አስተዳደር ምንጭ ተደርጐ የሚወሰደው በጥንታዊዎቹ ግብፆች፣ ግሪኮችና ሮማውያን ዘንድ ተስፋፍቶ ይነገር የነበረው አፈታሪክ ነው፡፡ “Fabulous cities, of tombs filled with gold,” (በወርቅ የተሞሉ መቃብሮች ያሉባቸው ድንቃ ድንቅ ከተሞች) ይሏቸዋል፡፡ በዚህ አፈታሪክ ተማርኮ ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገው ሮማዊው አውጉስቶስ ቄሳር ነበር፡፡ ጄኔራሉን አይሊየስ ጋሉሰን ወታደሮች እንዲያደራጅ አዝዞ ወደ ደቡብ አረብ ላከው፡፡ አፈታሪኩን ለማረጋገጥ የተላኩት 10 ሺህ ወታደሮች በበረሃ በሽታና በአካባቢው ነዋሪዎች እየተመቱ ተመናምነው ወደ መነሻቸው ግብ ያለምናምኒት ተመለሱ፡፡
ከዚያ ወዲህም ቢሆን “The Spice Kingdoms” (የቅመማ ቅመም ግዛቶች) በመባል የሚታወቁት ሚኒያ (Mineas)# ካታባን (Kataban)# ሀድረሙት (Hadhramaut) እና ሳባ (Sheba) እንዲሁ የሰውን ቀልብ ከመሳብ አልቦዘኑም፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ90 ዓ.ም ዲዮኒሲየስ የተሰኘ ፀሐፊ “Fortunate Arabia” በሚል ባጠናቀረው መሐፉ ላይ፤ በወርቅ የተሞሉት መቃብሮች ምድራዊ ገነት መሆናቸውንም ጠቆመ፡፡ ..የጣፋጭ እንጨት ሽታ ዘወትር የሚያውዳቸው፣ በበግ መንጐች የተጣበቡ፣ በወፍ ጫጫታ የደነቆሩ አካባቢዎች.. አላቸው፡፡ ይሄንን አፈታሪክ ተገን ያደረገ ዘገባ ተመክተው ብዙ ሰዎች በደቡብ አረቢያ በረሃ ውስጥ ዋትተዋል፡፡ «B ያለ አልተገኘም፡፡ ይሁንና ጀርመናዊዎቹ ተመራማሪዎች ካርል ራትጄንስ እና ኤች.ቮን ዊስማን በ1928 ዓ.ም ላይ አንድ ግኝት ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ኒቡር የተሰኘ የደቡብ አረብ ነዋሪ ፍንጭ የሰጠበት ቦታ ሲመረመር ..አዋም.. የተሰኘ የጨረቃ አምላክ የሚመለክበት ጥንታዊ ቤተመቅደስ ተገኝቷል፡፡ ይሄ ቤተመቅደስ ከክርስቶስ ልደት በፊት የ2ሺህ ዓመት እድሜ ያለው እንደሆነ ከመታወቁም በላይ ምናልባትም የጥንታዊዎቹ ሳባውያን ሳይሆን እንደማይቀር ተጠርጥሯል፡፡
ወርነር ኬለር ያጠናቀረው “The Bible as History” መሐፍ ድምዳሜ ለመስጠት እንደሞከረው፤ ንግሥተ ሳባ (በህይወት ብትኖር እንኳን) ንጉስ ሰሎሞን የእስራኤልን መንበር ከመቆናጠጡ አንድ ሺህ አመት በፊት ከተማዋ በረሃብ ሙሉ በሙሉ ከገፀ ምድር ጠፍቶ ነበር፡፡ እንግዲህ ንግሥተ ሳባና ንጉስ ሰሎሞንን ተአምረኛው ተረት ካልሆነ በቀር ምንም ነገር የሚያገናኛቸው የለም ማለት ነው፡፡ ይሁንና ደቡብ አረቢያን አልፈው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተረት ቀጠሮ ይዘው፣ በመገናኘት ዘንድሮም የሌሉበትን ታሪክ ተፈናጠው አሉ፡፡ እንዴት?
ታደሰ ታምራት የተሰኙ የታሪክ ምሁር ..ተረትና ታሪክ በኢትዮጵያ.. በሚል ጥናታቸው የንግሥተ ሳባ አፈታሪክ በ850 ዓ.ም አካባቢ ግብ ተፈብርኮ እንደመጣ ይገልፃሉ፡፡ ወቅቱ የአክሱም መንግሥት የተዳከመበት ..የጨለማ ዘመን.. ተብሎ በሚጠራ የታሪክ ዳፍንት ውስጥ ስለነበርን ተጨባጭ መረጃ በማጣት፣ ተረቶችና አፈታሪኮች ለማበብ እድል ያገኛሉና ነው ንግስተ ሳባ ብቅ ያለችው፡፡ በኋላም ተረቱ በመሐፍ መልክ የቀረበበት ዘመንም የራሱ የታሪክ ግዴታ የታየበት ነበር፡፡ ከ1314-44 ዓ.ም የንግሥተ ሳባ ተረት በ..ክብረነገሥት.. ውስጥ የሰፈረው በአፄ አምደዮን ዘመን ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የአደፋ/ላሊበላ መንግሥትና በኋላ ሰሎሞናዊ ነኝ ብሎ በሚነሳው አዲስ ስርወ መንግሥት መካከል የሥልጣን ትግል ስለነበር አፈታሪኩ የጐላ አስተዋኦ ስለሚኖረው ይመስላል፡፡ ታደሰ ታምራት እንዲህ ይላሉ፣
..ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክን ከመሐፍ ቅዱስና ከእስራኤል ጋር የማያያዝ ነገር ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃ የለውም፡፡ እንዲያውም ያሉን አስተማማኝ የታሪክ ቅሪቶች በቀጥታ ይቃወሙታል፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክና ጓደኞቹ የእስራኤል ወጣቶች ከኢየሩሳሌም ታቦት ሰርቀው፣ አክሱም ከተማ ቤተ መቅደስ አኖሩት በሚባልበት ጊዜ አክሱም ገና አልተቆረቆረችም፡፡ የአክሱም ከተማና የታሪክ ዘመን የሚጀምረው የቀዳማዊ ሚኒልክ አባት ነው ከሚባለው ከንጉስ ሰሎሞን 800 አመታት ያህል ቆይቶ ነው፡፡..
የንግሥተ ሳባን ጉዳይ እንደ ጉራጅ ብርድልብስ ወደ ላይ ስንጐትት እግራችን ሲራቆት፤ ወደ ታች ስንስብ ደረታችንን ሲበርደን መካከል ላይ ቀርቷል፡፡ በደቡብ አረቢያዋ ሳባ ከሄድን ሰለሞን ሺህ አመት ይዘገይብናል፤ በአክሱምዋ ሳባ ከሄድን 800 ዓመት ይቀድምብናል፡፡ ታዲያ የዚች የንግሥተ ሳባ ጉዳይ እንዴት ታሪክ መሆን ይችል ይሆን? አለቃ አጥሜ (አለቃ ለመጊዮርጊስ) በ1900 ዓ.ም አካባቢ በፃፉት የታሪክ መሐፍ ይሄንን ነገር በገደምዳሜ አሽሟጥጠውታል፡፡
|_ንት በኢትዮጵያ የነበረ ህዝብ የኢትዮጲስ ልጆች ሳባ፣ ኖባ፣ ከለው... ናቸው፡፡ በትግሬ ያሉ ህዝብ የሳባ ወገኖች ናቸው፡፡ የከለው ልጆች በዳህና፣ ሐርጊጉ፣ ምጥዋ... ያሉት ናቸው፡፡ አለቃቸውም ..ናይብ.. ይባላል..... እያሉ ወደ ቀደምት ሳባ የንግስና ታሪክ ይገቡና መደምደሚያቸው ላይ .....ይህ ነገር፣ እንቅፋት፣ ጥፋት ነው፡፡ እውነቱ ከውሸቱ ስላልተለየ በዘንዶ መቅደስ ላተ-ሙሴ ገባችበት.. በማለት ይሸረድዳሉ፡፡
የንግሥተ ሳባንና የንጉስ ሰሎሞንን በተረት የመሞሸር ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ በጠንካራ ሂስ የሸነቆጡት ፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤል ናቸው፡፡ በ1936 ዓ.ም በፃፉት ..ስለ ኢትዮጵያ ደራሲያን.. በተሰኘ ጥናታቸው ጉዳዩን ለአደጋ በሚያጋልጣቸው ሁኔታ ያብጠለጥሉታል፡፡
..ይሄንን አፈታሪክ (የንግሥተ ሳባን) የሚነግሩን መፃህፍት በሐገራችን መፃፍ የጀመሩት ከሺህ 300 ዓ.ም (13ኛው ክፍለ ዘመን) ወዲህ ነው፡፡ ሺህ አመት ያህል ከዚያ በፊት ለህዝቡ ወንጌል ተሰብኮለት ነበር፡፡ በሺህ አመት ውስጥ የመሐፍ ቅዱስ አሳብ በአህዛብነት የነበረበትን ዘመን እንዲጠየፈው የህዝበ እሰራኤልን መፃህፍት አሳብ እንዲወድ አድርጐት ስለነበር፣ ጥቂት በጥቂት የገዛ ራሱን ታሪክ እየዘነጋ የእስራኤል ልጅ ነኝ ከማለትና የእስራኤል ህዝብ የፃፏቸውን መፃህፍት አያቶቼ የፃፏቸው ናቸው ከማለት ደርሰዋል... ይህም ከወገን ለጊዜው የበለጠ መስሎ የታየውን እየመረጡ ወገኔ ማለት የዛሬ ሳይሆን የጥንት፣ የእኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉ የደረሰና ታሪክ ተመርምሮ ወሬው ትክክለኛ አለመሆኑ ሲታይ የሚቀር ነው፡፡..
አለቃ አጥሜ እንዲህ ካሉን 67 አመታት አልፈዋል፡፡ ይሁንና ..ታሪክ ተመርምሮ ወሬው ትክክለኛ አለመሆኑ ሲታይ የሚቀር ነው.. በማለት ተስፋ የጣሉበት አልያዘላቸውም፡፡ ባለፈው አሮጌ አመት (በ2003 ዓ.ም) እንኳን ተረት ግርሻ ሆኖ በፍስሃ ያዜ መሐፍ ተፀናውቶናል፡፡ ..የኢትዮጵያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ - ከኖህ እስከ ኢህአዴግ.. በሚል የታተመው መሐፍ ላይ እነብላቴን ጌታ ህሩይ እንኳን የማይታመንላቸው ሆኖ የቆረጡትን አግበስብሶ ከትቷል፡፡ እንደውም ተረታዊ ተአምራቱን እንደምስጢር ክርታስ ቆጥሮ ሊፈተሽ ይገባዋል ይላል፡፡ እንዲህ፣
..ሳባ የመጣችው ከዘንዶ ነው... ወዘተ... የሚል ሐተታ ይገኛል፡፡ በብዙዎቹ የዛሬ ሊቃውንት እይታ ይሄ መሰሉ ሃተታ ተረት ተረት ተብሏል፡ ነገር ግን ሚስጥራዊ አገላለ ይመስላል.. (የኢትዮጵያ የ5ሺ... ገ 103) ሚስጥራዊ አገላለፁ ምንድነው? መሐፉ ምንም አይነት የገለፀው ምስጢር የለም፡፡ መሐፉ ይሄን የራሱ ጉዳይ ከማድረግ ይልቅ የኛ ጣጣ አድርጐ ያልፈዋል፡፡ የአብዛኞቹ ታሪክ መሰል የተረት መፃህፍት ችግር ይሄ ነው፡፡ ከመመርመር ይልቅ ሳይነካካ እንዳለ መገልበጥ ላይ ይመረኮዛሉ፡፡ ምርመራ የሌለው መሐፍ እንደጠጣር አካል ከማስተጋባትና የተረት ገደል-ማሚቶ ከመፍጠር ባሻገር ለሳይንሳዊ ታሪክና ለትክክለኛ ገታ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

 

Read 7953 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:09